የኢትዮጵያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ገና ሁለት ተኩል አሥርት ዓመታት እድሜ ያስቆጠረ ነው። ከዓለም የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት እድሜ አኳያ ሲታይ የኢትዮጵያ ገና ዓይኑን የገለጸ ጨቅላ ነው። ይሁን እንጂ ይህ ጨቅላ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከጨለማ ወደብርሃን የመሸጋገር ያህል ብዙ አሳይቶናል። ከ25 ዓመታት በፊት በነበሩት የመንግሥት ሥርዓቶች ኢትዮጵያ የማንነትና የአመለካከት ብዝሃነት የሌላት ያህል፣ አንድ አመለካከትና የማንነት መገለጫ ብቻ የሚንፀባረቅባት አገር ነበረች። በመሠረቱ ኢትዮጵያ የተለያየ ብሄራዊ ማንነት (ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ወግ…) ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ ነች። ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ፍልስፍናና ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ዜጎች መኖሪያ አገር ነች። ኢትዮጵያ የብዝሃነት አገር ነች፤ የብዙዎች አንድነት የፈጠራት አገር። ይህ ብዙሃነት ነበር በህግ እውቅና የተነፈገው።
ብዝሃነት በህግ እውቅና ያጣበት ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ተሻረ። አገሪቱ በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ብዝሃነትን ማስተናገድ የቻለ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ጀመረች። እርግጥ ከ1983 ሐምሌ የሽግግር መንግሥቱ ሲመሠረት ብዝሃነት እውቅና አግኝቷል፤ በሽግግር መንግሥቱ ቻርተር።
ከዚህ በኋላ አገሪቱ ለብዝሃነት እውቅና ባልሰጠችባቸው ዓመታት በአመለካከትና በብሄራዊ ማንነት ተደራጅተው የትጥቅ ትግል ሲያካሄዱና በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች በይፋ መንቀሳቀስ ጀመሩ። በርካታ አዳዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተመሠረቱ። በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ ከ60 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ህጋዊ እውቅና ኖሯቸው በይፋ ይንቀሳቀሳሉ። የፖለቲካ ድርጅቶቹ አቋምና ፖሊሲዎቻቸውን በይፋ ያራምዳሉ፤ በማንኛውም ድርጅታዊ ወይም አገራዊ ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውንና አቋማቸውን ያለምንም ገደብ ይገልጻሉ፤ ለፖለቲካ ሥልጣን ይፎካከራሉ፤ ባገኙት የህዝብ ድምጽ ልክ የሥልጣን ውክልና ይረከባሉ። በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ የአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ገና ዓይኑን የገለፀ ጨቅላ ቢሆንም ለእኛ እትዮጵያዊያን ከጨለማ ወደብርሃን የመሸጋገር ያህል ብዙ አሳይቶናል ያልኩት ለዚህ ነው።
ምሉዕ ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በአዋጅና በዘመቻ በአንድ ጊዜ የሚሰፍን አይደለም። ዴሞክራሲ በሰዎች ውስጥ የሚሰርጽና በአመለካከት ለውጥ የኑሮ ዘይቤ ወይም ባህል ሆኖ የሚገለጽ ነው። ይህ ደግሞ ረጅም ጊዜ ይጠይቃል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት 25 ዓመታትን ቢያስቆጥርም አሁንም ገና እድገት የሚቀረው ጨቅላ የሚያደርገው ይህ ነው።
ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች በይፋ የተሳተፉባቸው አሥር ያህል አገር አቀፍ፣ ክልላዊና አካባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። እነዚህ ምርጫዎች ህዝብ በበቂ ሁኔታ የተሳተፈባቸው፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ነበሩ። ይሁን እንጂ በተለይ ከሦስተኛው ዙር ምርጫ በኋላ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በፌዴራልና በክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች መቀመጫ የሚያገኙበት እድል እየጠበበ መጥቷል።
ይህ የሆነው ምርጫው አሳታፊ፣ ፍትሃዊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ስላልነበረ አይደለም። ይህ እንዲሆን ያደረገው ቀዳሚው ምክንያት ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ልማታዊ የኢኮኖሚ መርህ የሚከተል መሆኑ ነው። ልማታዊ የኢኮኖሚ መርህ፣ መንግሥት ከሁሉም የልማት ኃይሎች ጋር ማለትም አርሶ አደር፣ የአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት አንቀሳቃሾች፣ ልማታዊ ባለሃብቶች ወዘተ…ጋር የቤተሰብ ያህል ተቀራርቦ በመሥራት ተግባራዊ የሚደረግ ነው። ይህ ሁኔታ የልማታዊ መርህ ተግባራዊ ሆኖ ውጤት ባስገኘበት ልክ የገዥውን ፓርቲ ደጋፊዎች ያበረክታቸዋል። ልማታዊ የኢኮኖሚ መርህ፣ ደጋፊዎች ከፓርቲው ጋር የደቀ መዝሙር ያህል የቀረበ ትስስር እንዲኖራቸው የማድረግ ባህሪ አለው። እናም ልማታዊው ኢሕአዴግ ከጊዜ ወደጊዜ የደቀ መዝሙር ያህል በቅርበት የሚያውቁትና የሚከተሉት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች አፈራ።
ይህ ሁኔታ በአንድ የምርጫ ክልል ከቀረቡ እጩዎች መካከል አሸናፊ ለመሆን ከሚያስፈልገው የ50 + 1 አብላጫ የድምጽ ሥርዓት ጋር ተዳምሮ ኢሕአዴግ በተወዳደረባቸው አካባቢዎች በሙሉ አሸናፊ በመሆን መቀመጫዎችን ጠቅልሎ እንዲይዝ አድርጎታል። ልብ በሉ፤ የቀላል አብላጫ የድምጽ ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ቢሆንም ሌሎች አናሳ ድምጽ ያገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውክልና የሚያገኙበትን እድል ሊያጠብ የሚችልበት ሁኔታ አለ። ይህ በመንግሥት ውስጥ የማይሰሙ የህዝብ ድምጾች እንዲኖሩ አድርጓል። ይህ ደግሞ ሥርዓቱ የአመለካከት ብዝሃነትን በአግባቡ ማስተናገድ ያልቻለበትን ሁኔታ አስከትሏል። የፖለቲካ ምህዳሩ ህዝቡን በሚመጥን ልክ ሰፊ እንዳይሆን አድርጓል። እናም ምህዳሩን የማስተካከሉ አጀንዳ ገንፍሎ ወጣ።
ያ አገሪቱን የአመለካከት ብዝሃነት በወጉ ማስተናገድ ያልቻለውን ሁኔታ የማስተካከል ጉዳይ በመንግሥት እውቅና ተሰጥቶት ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳው ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ነበር። ባለፈው ዓመት በመጋቢት ወር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ከሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ይህ ጉዳይ ተነስቶ ነበር። በዚህ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉንም የህዝብ ድምጾች የሚወክሉ አመለካከቶች በመንግሥት ውስጥ ውክልና እንዲኖራቸው የምርጫ ህጉ ይሻሻል የሚል ሀሳብ አንስተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉዳዩ ዋጋ ሰጥተውት እንደነበረ ይታወሳል።
በዚህ መነሻነት ይመስለኛል፤ የ5ኛው ዙር የመንግሥት የሥልጣን ዘመን 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሲጀመር ለህዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ የዓመቱን የመንግሥት የሥራ ክንውን አቅጣጫ የሚያመለክት ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጉዳዩን አንስተውት ነበር።
ፕሬዚዳንት ሙላቱ በንግግራቸው፤…የአገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ አንዱ ቀዳሚ ሥራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጋችንን የማሻሻል ጉዳይ ይሆናል። አገራችን የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ አገሮች እንዳለ የሚሰራበት ቢሆንም፣ ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱ ጋር የህግ ማሻሻያ ይደረጋል። ስለሆነም የምርጫ ህጋችን የአብላጫ ድምፅና የተመጣጣኝ ውክልና ሥርዓቶችን በትክክለኛ ሚዛን ያጣመረና የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድምፅ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች እንዲኖሩን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንዲስተካከል ይደረጋል። ይህም በፓርቲዎች መካከል በሚካሄድ የሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛና አገራዊ ጥቅማችንን ማዕከል ባደረገ ግልፅነትን የተላበሰ የድርድር ሂደት የሚፈፀም ይሆናል ነበር ያሉት።
በዚህ መሠረት ከአንድ ወር በፊት ኢሕአዴግን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚንቀሳቀሱ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የድርድር፣ ክርክርና ውይይት ሂደት ተጀምሯል። ፓርቲዎቹ እስካሁን በድርድር፣ ክርክርና ውይይት ሂደት ላይ ሲነጋገሩ የቆዩ ቢሆንም፣ በብዙ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ በሁለት ጉዳዮች ላይ ቁርጥ ያለ የጋራ አቋም ላይ መድረስ አልቻሉም። አንደኛው ገለልተኛ አደራዳሪ አካልን የሚመለከት ነው። ሌላኛው በተለይ የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንደነት መድረክ (መድረክ) የያዘው ሁሉንም ፓርቲዎች ወክዬ በአውራ ፓርቲነት ልደራደር፣ ይህ ካልሆነ ከኢሕአዴግ ጋር ለብቻዬ ልደራደር የሚል አቋም ነው። በዚህ ጽሁፍ አነዚህን ሁለት ጉዳዮቸ ከነባራዊ እውነታ አኳያ ምን አንደምታ እንዳላቸው ለመመልከት እሞክራለሁ።
ከኢሕአዴግ ውጭ ያሉት 21 የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለልተኛ አደራዳሪ ይኑር ባይ ናቸው። ከኢሕአዴግ በስተቀር ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ድርድሩ በገለልተኛና ነጻ አደራዳሪዎች ይመራ የሚል ሀሳብ አቅርበዋል። በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ፣ ድርድሩ በተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዙር ይመራ የሚል አቋም ይዟል። ኢሕአዴግ ከሦስተኛ ወገን የሚመጣ አደራዳሪ አያስፈልግም ባይ ነው። አደራዳሪው ለተናጋሪዎች እድል ከመስጠት ያለፈ ሚና ስለማይኖረው አስፈላጊነቱ አይታየኝም የሚል መከራከሪያ አቅርቧል።
ይህን የሁለቱን ወገን ሃሳብ እንመልከት። በቅድሚያ ገለልተኛ የሚለው ጉዳይ በራሱ ግልጽ አይደለም። ከምን ገለልተኛ የሆነ አካል ነው የሚፈለገው? ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ወይንስ የየትኛውም ፓርቲ ወይም ርዕዮተ ዓለም ደጋፊ ያልሆነ አካል? 22 የተለያየ አቋም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም አሁን ለድርድሩ የተሰባሰቡ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቡድኖች በተመሳሳይ ሁኔታ ገለልተኛ ነው ብለው ሊቀበሉት የሚችሉትን አካል ማግኘት አዳጋች ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ መስማማት ራሱ ወራትን የሚፈጅ ድርድርና ክርክር ሊጠይቅ ይችላል። ምናልባት ጭራሽ መስማማት የማይቻልበትም ሁኔታ አለ። በዚህ መካከል ድርድሩ ውኃ በልቶት ሊቀር ይችላል።
በሌላ በኩል ለጋራ ዓላማ የተሰባሰቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች በየተራ በመካከላቸው የሚካሄደውን ድርድርና ክርክር ቢመሩ፣ አካሄዱ ቀናና ቀላል ሊሆን ይቻላል። በዚህ አካሄድ የተገኘ የቅርብ ጊዜ ስኬታማ ተሞክሮም ይህን ያረጋግጣል። በ2001 ዓ.ም ማገባደጃ ላይ ተጀምሮ የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ ለማዘጋጀት ለወራት የተካሄደውን ድርድር አስታውሱ። ይህ ድርድር ገለልተኛ በተባለ የውጭ አካል የተመራ አልነበረም። ሆኖም ድርድሩ እጅግ ሠላማዊ በሆነ ሂደት በየትኛውም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ከዚህ ውጭ በሆነ አካል እንከን ያልወጣለትን የምርጫ ሥነ ምግባር ደንብ ማዘጋጀት አስችሏል። እናም አሁን ሊደረግ የታሰበው ድርድር፣ ክርክርና ውይይት ይህን ተሞክሮ ቢወስድ ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
መድረክ ወደያዘው አውራ ተደራዳሪ ልሁን ወደሚል አቋም እንመለስ። መድረክ ለዚህ አቋሙ ያቀረበው መከራከሪያ፣ በ22 የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ድርድር አካሂዶ አንድ የሚያግባባ ሃሳብ ላይ መድረስ አይቻልም ወይም አስቸጋሪ ነው የሚል ነው።
እርግጥ ነው ለድርድር የሚቀርቡ አቋሞች ሲበዙ መዝረክረክ ስለሚያጋጥም ወደመግባባት መድረስ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ድርድር፤ ግልጽ፣ ቀልጣፋና ወደመግባባት ሊያደርስ በሚያስችል ሁኔታ እንዲካሄድ የተደራዳሪዎቹ ቁጥርና የሚነሳው ጉዳይ ስብጥር የተቆጠበ ቢሆን ይመረጣል። ይህን መነሻ በማድረግ በድርድሩ ላይ የሚሳተፉት ፓርቲዎች ተመሳሳይ የጋራ አቋም ይዘው ለመቅረብ ተቧድነዋል። አንደኛው ቡድን ኢሕአዴግን ሳይጨምር የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ 11 ፓርቲዎችን የያዘ ሲሆን ሌላኛው መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ ስድስት ፓርቲዎችን የያዘ ቡድን ነው። መድረክና ኢሕአዴግም ራሳቸውን ችለው ይቀርባሉ። ከዚህ አንጻር ስናየው ተደራዳሪዎቹ አካላት 22 ሳይሆኑ ኢሕአዴግን ጨምሮ አራት ናቸው። ይህ ደግሞ ድርድር ለማካሄድ የሚያስችል የተመጠነ የተደራዳሪዎች ቁጥር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በዚህ ላይ ሁሉም በድርድሩ ላይ ለመሳተፍ የተዘጋጁ ፓርቲዎች የመድረክን የአውራ ተደራዳሪነት አቋም አልተቀበሉትም።
መድረክ አውራ ተደራዳሪነቱ ካልሆነ ለብቻዬ ልደራደር የሚል አማራጭ አቅርቧል። ልብ በሉ፤ ኢሕአዴግ በጋራ ጉዳዮች ላይ ከተደራደረ በኋላ የተለየ አጀንዳ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር በተናጥል ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል። መድረክ በዚህ እድል መጠቀም ይችላል። እስካሁን ግን ይህን የመቀበል ፍላጎት አላሳየም።
በዚህ የመድረክ አካሄድ ላይ ያለውን ችግር እንመልከት። የአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ጉዳይ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ የሚመለከት ነው። በመሆኑም በዚህ ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የአገሪቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመሠረታዊነት የተለያየ አቋም ይኖራቸዋል ብሎ መገመት ስህተትነቱ ያይላል። ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ነው የሚሆነው። እናም ኢሕአዴግ ከመድረክ ውጭ ከሆኑት ፓርቲዎች ጋር ድርድር ሲያደርግ፣ መድረክንም የሚመለከቱት መሠረታዊ ጉዳዮች ተነስተው መፍትሄ ማግኘታቸው የማይቀር ነው። ይህ ከሆነ በኋላ ኢሕአዴግ ከመድረክ ጋር መፍትሄ ባገኘ ጉዳይ ላይ መደራደሩ ትርጉም የሌለው ነው የሚሆነው። ይህ ደግሞ መድረክን ለብቻው የሚደራደርበት አጀንዳ አሳጥቶ አየር ላይ ሊያስቀረው ይችላል። እናም የመድረከ አካሄድ ለራሱ ለመድረክ አይጠቅመውም።
በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሊካሄድ የታሰበው ድርድር፣ ውይይትና ክርክር መድረሻው ህዝብና አገር ነው። የድርድሩ መድረሻ ፓርቲዎቹ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። በመሆኑም ለድርድር ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከራሳቸው ቀፎ ወጥተው በአገሪቱ ያሉ ሁሉም አመለካከቶች የሚወከሉበትና የሚደመጡበትን ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠርን መድረሻቸው አድርገው ሊንቀሳቀሱ ይገባል። ሰበብ እየፈጠሩ ድርድሩን ማጓተትና ህዝብን ማደናገር ውጭ አገር ላሉ የጽንፈኛ ተቃዋሚ ሚዲያዎች የወሬ ቀለብ ከመሆን ያለፈ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ፓርቲዎቹም ህዝቡም ሊገነዘቡ ይገባል። እናም ከቀፏችሁ ውጡ።