ህገ ወጥ ስደትን በጋራ ለመከላከል

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደ አውሮፕያኑ አቆጣጠር በ2000 ዓ.ም ያወጣውና “የፓርሌሞ ስምምነት” እየተባለ የሚጠቀሰው ሰነድ ላይ በግልፅ እንደተበየነው፤ ሰዎችን ለብዝበዛ ዓላማ በኃይል፣ በዛቻ፣ በተንኮል፣ በማታለል፣ በመጥለፍ ወይም በተበዳይ ላይ ኃላፊነት ላለው ሰው ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም በመስጠት መመልመል፣ ማጓጓዝ፣ ማስተላለፍ፣ መደበቅ ወይም መቀበል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መሆኑን ያስረዳል።

የአገራችን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ህግም ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወርን በወንጀል ተግባር ይፈርጀዋል። ይኸውም ሰዎችን በኃይል ወይም በማታለል መመልመል፣ በሀገር ውስጥ ወይም ወደ ሌላ ሀገር ህገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር እና አዘዋዋሪዎች ተበዳዮችን የገንዘብ ጥቅም ማግኛ ማድረጋቸው ወይም ለብዝበዛ የተጠቀሙባቸው እንደሆነ በወንጀል ድርጊት እንደሚያስጠይቅ እንደሆነ ትርጓሜ ሰጥቷል።

እርግጥ የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኘና በተግባር እየተከናወነ ያለ ጉዳይ ነው። እናም እዚህ ላይ ዜጎች ለምን ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ እያልኩ አለመሆኑ ሊታወቅልኝ ይገባል። ይሁንና ሰዎች በሀገር ውስጥ ወይም ወደ ውጭ ሀገር ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወይም ስደት የተሻለ ስራ ፍለጋና ህይወት ወይም ልክ ወንድም እንደሆነው የኤርትራ ህዝብ ከጭቆና ለመሸሽ አሊያም የመኖሪያ ቦታን ለመቀየር ሊሆን ይችላል።

ዳሩ ግን የእንቅስቃሴው ዓላማ በሰዎች ለመነገድ ሲባል የሚከናወን ከሆነ ተግባሩ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚፈረጅ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል። እናም በዚህ ፅሑፍ ላይ የማነሳው ነገር ቢኖር የዜጎቻችንን ህይወት እየቀጠፈ ስላለው በህገ ወጥ ስደት አማካኝነት ቤተሰብንና ዘመድ አዝማድን ብሎም ዜጎችን እያስለቀሰ ስላለው የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጉዳይ ነው። ጉዳዩንም ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማስተሳሰር ይገባል፤ ትክክልም ነው።

ህገ ወጥ ስደት እስከ 100 ሺህ ብር ድረስ የሚዘልቅ ወጪን እንደሚጠይቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህን የሚያህል ገንዘብ እጅ ላይ እስካለ ድረስ እዚህ ሀገር ውስጥ ሰርቶ መቀየር የማይቻልበት ምክንያት አይታየኝም። ይህን ገንዘብ ሊሳካ አሊያም ላይሳካ ለሚችል ነገር እንዲያው አውጥቶ ከመስጠትና በህይወት ላይ በራስ ገንዘብ ሞትን ለመጋበዝ ከማሰብ ይልቅ እዚሁ ሀገር ውስጥ አዋጪ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ ማጤን ይገባል።

እርግጥ ድህነትና ስራ አጥነትን ለመቅረፍ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር በቀላሉ እንደማይገመት ይገባኛል። ይሁንና የችግሩ መንስዔ ሁሉንም ይወክላል ብሎ መፈረጅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በህጋዊ መንገድ መውጣት እየተቻሉና እዚሁ ሀገር ውስጥ ሰርተው መበልጸግ የሚያስችል ገንዘብ እያላቸው ለህገ-ወጥ ደላሎች ከፍለው ለችግሩ የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር የትየለሌ በመሆኑ ነው፡፡

በላቡና በወዙ ጥሮ…ግሮ ህይወቱን ለመለወጥና ሀገሩን ለመጥቀም የማይሻ ሰው አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ዜጎች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ድህነትን ለመቅረፍ የሚያደርጉት ተነሳሽነት ትክክል አይደለም ሊባል የማይችል ቢሆንም፤ በህገ ወጥ ደላሎችና አፈ ቅቤዎች ተታልለው የእነርሱ ሲሳይ መሆናቸው ግን እጅጉን የሚያስቆጭ ነው። ከዚህ ባሻገርም ሁሉም ነገር ህግን የተከተለ አካሄድ ተጠቅሞ ማደግና መለወጥ ሲቻል ህገ- ወጥ አካሄድን መርጦ ለአደጋ መጋለጡ አግባብነት ያለው ተግባር አይመስለኝም።

እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በትክክለኛ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች። ዕድገቱም ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፈጠሩ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ በተለይም ወጣቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ልማታዊ ሥራዎች ላይ በመሳተፋቸው የቤተሰብ እጅን ከመጠበቅ ለመዳን ችለዋል። እንዲያውም ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ቤተሰቦቻቸውንም እየረዱ ነው። ይህ እዚህ ሀገር ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሃቅ ነው።

እንደሚታወቀው ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን የተንሰራፋውን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማስወገድ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ሲጀምር፤ ስራ አጥነት መቅረፍ አንደኛው ተግባሩ በማድረግ ነበር፡፡ በዚህም በከተሞች የሚታየውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራትን በማደራጀት እንዲሁም የብድር አገልግሎት በመስጠት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ዜጎችም በየሙያቸው በመሰማራት ለሀገራዊ ልማት ከፍተኛ ጉልበትና አቅም መሆን መቻላቸውን አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከመንግስት እንዲሁም ከቁጠባና ብድር ተቋማት ባገኙት ገንዘብ ተጠቅመው ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ባለቤትነት የተሸጋገሩ ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ዜጎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር የመንግስትን ጥረት በመደገፍና የሀገሪቱን ልማት በማፋጠን ላይ እንደሚገኙ እማኝ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም። በዚህ የኢኮኖሚ ስራ ውስጥ ገብቶ እንደሌሎቹ ወገኖች ራስን መቀየር እየታቻለ ስደትን እንደ አማራጭ መውሰድ ተገቢ አይደለም።

ይህ የህገ ወጥ ስደት ጉዳይ የእያንዳንዳችንን በር እስኪያንኳኳ ድረስ መጠበቅ የለብንም። እናም ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጉዳዩችን ማወቅ ይገባል። እነዚህ የችግሩ ተዋናዮች ግብ አንድና አንድ ነው። ሆኖም ገንዘብን አገኛለሁ ብሎ በወጡበት መቅረት መኖሩን ማስታወስ ይገባል። የህገ ወጥ ስደቱን መንገድ ለመቀነስ ብሎም ለመዝጋት መንግስት ፈርጀ ብዙ ጥረት እያደረገ ነው።

በአሁኑ ወትት መንግስት ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር መንግስትነት ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋን ለመከላከልም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ደረጃም ደርሷል። እንደሚታወቀው በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል፡፡ በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀው ግብረ ሃይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በህጋዊ ተንቀሳቅሰው መስራት የሚፈልጉ ዜጎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የስራ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት እንዲሁም ከሥልጠናው በኋላ በሰለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት ለሚፈልጉ ዜጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ለስልጠና እና መሰል ስራዎች ድጋፍ የሚውል ሐብት ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀትና ሃብት የማፈላለግ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል። ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከናወኑትን ተግባራት እንደ ምሳሌ ብንወስድ እንኳን፣ ከአረብ አገር ተመላሾችን በጊዜያዊነት በመንከባከብ እንዲረጋጉ ከማድረግም አልፎ  ለ2 ሺህ 797 ከስደት ተመላሾች የስነ ልቦና፣ የአመለካከትና የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙና ወደ ተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ተደርጓል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በዚህ ትውልድን ለአደጋ በሚዳርግ ተግባር የተሰማሩ ደላሎች ላይ የህግ ማስከበር ስራዎችም ተከናውነዋል። በዚህም የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ቦታዎችን መለየት ችግራቸውን መሰረት አድርጎ በተመረጡ እንዲሁም ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች የመቆጣጠር ስራ ገቢራዊ ሆኗል።

በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግም ህግን መሰረት አድርጎ ነው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ተችሏል። የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችን የሚመለምሉና የሚያዘዋውሩ ደላላዎችን፣ ተባባሪና ቤት አከራዮችን እንዲሁም አጓጓዦችን መረጃ ማሰባሰብና በመለየት በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር የመፍጠር ርምጃዎችም ሲወሰድ ቆይቷል።

ይሁንና በመንግስት በኩል ችግሩን ለመቅረፍ ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም፣ ችግሩ ግን አሁንም በበቂ ሁኔታ ተፈትቷል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የህገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎቹ ብዛትና ዓይነት፣ የመረቡ ውስብስብነት፣ የቤተሰብ ገፋፊነትን ጨምሮ ሁሉም ለችግሩ መስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ነው።

ስለሆነም ይህን የህገ ወጥ ስደት መረብ ለመበጣጠስ ሁሉም እንደ አንድ ሰው በመሆን የበኩሉን ሚና ሊያበረክት የግድ ነው። ይህን ማድረግ ካልቻልን ግን ነገም የአገራችን ዜጎች በኮንቴይነር ሲጓጓዙ ተያዙ ወይም በባህር ላይ ሲጓጓዙ “እንዲህ ሆኑ” የሚል ዜናን መስማታችን የሚቀጥል ይሆናል። እናም ሳያውቅ በህገ ወጥ ስደት ማዕበል ላይ ለመንገላታት ለሚሻው ዜጋ ሁላችንም ዋስና ጠበቃ እንዲሁም መካሪ ልንሆን ይገባል።