መንግስት ለወጣቶች የመደበውን ፈንድ እያንዳንዱ ክልል የየራሱን ድርሻ ወስዶአል፡፡ መመዘኛ መስፈርቱንና አስፈላጊውን ደምብ አሟልቶ ገንዘቡን ለስራ በመመደብ ወጣቱን ፈጥኖ ወደስራ ለማሰማራት በየክልሉ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን አንዳንዶቹ ፈጥነው እንቅስቃሴ የመጀመራቸውን ያህል በሌሎች አካባቢዎች ድግሞ የመዘግየትና የመጓተት ሁኔታዎችም ይስተዋላሉ፡፡
ይሄ በሂደት ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ከፌደራል መንግስቱ እቅድና አላማ ለወጣቱ ፈጥኖ ለመድረስ ከሚደረገው ርብርብ አንጻር የአንዳንዶቹ አካባቢዎች በስራው ያለመፍጠንና ማዝገም በመንግስትም በሕዝቡም የጎላ ተጠያቂነት እንደሚያስከትልባቸው ግልጽ ነው፡፡
የወጣቶች ፈንድ ከመነሻው በመንግስት የተመደበው ለወጣቶች በየክልሉ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር ነው፡፡ገንዘቡ ከዚህ ውጭ ለተለየ አላማ ወይንም ስራ የሚውል አይደለም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ክልሎች በተሰጣቸው ኮታ መሰረት የፈንዱ ድልድል ተደርጎ የተሰጣቸው ቀደም ሲል በተጠኑትና በተዘጋጁት የስራ መስኮች መስፈርቶችን አሟልተው የቀረቡ ወጣቶችን ስራ እንዲጀምሩ ለማድረግ ነው፡፡መፍጠንም ይገባቸዋል፡፡
የወጣቱን ፈንድ የተቀበሉ አካላት በተግባር ወደስራ የማስገባቱን ሂደት ቅድሚያ ስራቸው ሊያደርጉት ይገባል፡፡ይህ የወጣቶች ፈንድ ወጣቱ በመላው ሀገሪቱ አዲስ የስራ ባሕል የሚጀምርበት የፈጠራ ችሎታውን በመጠቀም አዳዲስ ስራዎችን የሚፈጥርበት ራሱን ጠቅሞ ሕብረተሰቡንም የሚጠቅሙ ውጤታማ ስራዎችን ይሰራል ተብሎ የሚጠበቅበት ነው፡፡
በማኒፋክቸሪንግ፤በግብርና፤በአሳ ሀብት፤በወተት ምርት፤በንብ ማነብ፤በከብት እርባታና ማድለብ፤በቱሪዝም፤በደን ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ፤አትክልቶችን በማልማት፤የግብርናና ሌሎች ምርቶችን ተቀባይና አከፋፋይ በመሆን፤በእንጨት ስራ፤በብረት ስራና ብየዳ፤ መዋእለ ሕጻናት በመክፈት፤ቤተመጻህፍት በመክፈት፤በትራንስፖርቱ ዘርፍ በመሰማራት፤ ታሪካዊ ቦታዎችን የማስጎብኘትና የሀገራችንን መልካም ገጽታ የማስተዋወቅ የመገንባት ስራ በመስራት፤መዝናኛ ፓርኮችን ከፍቶ ለሕዝብ አገልግሎት ማዋል፤መዋእለ ሕጻናት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤቶችን በተለይ ከዩኒቨርሲቲ አንደኛና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች ተደራጅተው ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት የሚያስችላቸው ተዘርዝረው የማያልቁ ሰፊ የስራ መሰኮች አሉ፡፡
እጅግ ያልተነኩ ብዙ ብዙ የስራ መስኮች የመኖራቸውን ያህል ወጣቱ ስራ ፈጣሪና አክባሪ ሆኖ የተለየ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡የመጀመሪያው ቁልፍ ነጥብ ማንኛውንም አይነት ስራ ማክበር ነው፡፡ስራን ያከበረ ሁሉ ሽልማቱ በአካባቢውም በሕብረተሰቡም መከበር ነው፡፡የቆየውና በሀገራችን የኖረው ስራን ትንሽ ነው ብሎ መናቅ፤ያለመስራት ከመስራት ይልቅ የመቀመጥ፤ ሌላ የተሻለ ስራን አገኛለሁ ብሎ የመጠበቁ ኃላቀር የሆነ አስተሳሰብና አመለካከት ከዚህ ትውልድ ውስጥ ተቀርፎ መውጣት አለበት፡፡
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተምሬ ከከተማ ወጥቼ ገጠር እንዴት እሰራለሁ፤ተምሬ በዚህ ደመወዝ እንዴት እቀጠራለሁ፤ማን ሩቅ ቦታ ሄዶ ይሰራል ሲባል የተኖረባት ሀገር ነች፡፡እውቀትን በሀገር ላይ የትም ሄደው ቢሰሩበት ለወገን ቢያካፍሉት አዳዲስ ስራ ቢፈጥሩ በሰፊው ልምድና እውቀትን ማካፈል ቢቻል የሀገር ልማትና እድገት የሚመጣው እያንዳንዱ በዚህ መልኩ ኃላፊነቱን መወጣት ሲችል ነው፡፡
የስራ አክባሪነት ባሕሉ የሚጀምረው ስራን ዝቅ ብሎ ታች ወርዶ በመስራት ነው፡፡ እያንዳንዱ በተሰማራበት የስራ መስክ የግልም ሆነ የመንግስት ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ ስራ ለመስራት በመቻል ነው፡፡የስራ ባሕላችን እጅግ ደካማ ሆኖ በመዝለቁ ነው ድሕነት በሀገር ደረጃ ሲፈነጭ የኖረው፡፡ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ስራን ሳይንቁ አክብሮ መስራት ለችግሮች ሁሉ መፍትሄ ያስገኛል፡፡ቁጭ ብሎ ስራን መጠበቅ ሳይሆን በተገኘው አጋጣሚ ያለውን የስራ እድል ተጠቅሞ መስራት ማስፋት ማሳደግ ይቻላል፡፡
ወጣቶች አደረጃጀታቸውን መሰረት በማድረግ ከመንግስት የተመደበላቸውን ፈንድ በአግባቡ በስራ ላይ በማዋል የበለጠ ስራ መፍጠር የሚችሉበት አጋጣሚ ነው የተፈጠረላቸው፡፡ሕብረተሰቡ ወጣቶች ለስራ ለሚያሳዩት ተነሳሽነት ከቤተሰብ ጀምሮ ቤተዘመድ አልፎም ሕብረተሰቡ ሰፊ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው በእርግጠኝት መናገር ይቻላል፡፡ሰርተው አግኝተው መለወጣቸውን ማደጋቸውን ነው የሚፈልገው፡፡
ፈንዱ በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ያሉ ወጣቶችን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን የተሳሳተ ውዥንብር የሚያሰራጩ ክፍሎች እንደሚነዙት ወሬ አባላት ለሆኑ ወጣቶች ብቻ እየተመረጡ የሚሰጣቸው አይደለም፡፡እንዲህ አይነት ሁኔታም አይኖርም፡፡
ፈንዱ የሚውለው በወጣቶቹ የሚቀርበው ፕሮጀክት አዋጪነቱ ታይቶና ተመዝኖ፤ አብዛኛውን ወጣት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተረጋግጦ፤ተመራቂ ተማሪዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩም ታይቶ ነው ስራ ላይ የሚውለው፡፡
ብድሩ የሚመቻቸው ወጣቶች በቢዝነስ እቅዱ መሰረት መሟላት ያለባቸውን ዋነኞቹም የስራ ቦታ፤የንግድ ፍቃድ፤መታወቂያና መሰል መስፈርቶች በሕጉ መሰረት አሟልተው መቅረብ ሲችሉ ነው፡፡ወጣቱ የእኔ የሚለው የራሱ ስራ እንዲኖረው በማቀድ መንግስት የመደበው 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ፈንድ ለተገቢው ስራ እንዲውል በመጠነኛ ወጪ በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ የስራ እቅድ የተዘጋጀለት መሆኑ ይታወቃል፡፡
የተዘዋዋሪ በጀት መመሪያው ከ18 አመት በላይ የሆነን ወጣት ያለ ዋስትናና ቅድመ ክፍያ በፍጥነት ወደ ስራ ማስገባት የሚያስችል ሲሆን አዋጪ የተለያዩ የስራ አይነቶችም የመምረጡ ስራ ተከነውኖአል፡፡
የኢኮኖሚው ሥርአት በነጻ ገበያ መርህ የሚመራ በመሆኑ ከመንግስት ብቻ የሚጠበቅ ስራ የለም፡፡እያንዳንዱ መነሻ አቅም ካለው ወይንም ከፈጠረ በመረጠው የስራ መስክ ውስጥ ገብቶ የመስራት የመወዳደር በተናጠልም ሆነ በቡድን ተደራጅቶ የመግባት ስራውን የማሳደግ ሰፊ እድል አለው፡፡ወጣቶች ከአነስተኛ ወደ ከፍተኛ ደረጃ የኢኮኖሚ አቅማቸው እያደገ ሲሄድ በሂደት መካከለኛና የገንዘብ አቅማቸው ሲደረጅ ደግሞ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞችን ፋብሪካዎችን የተለያዩ ድርጅቶችን የመክፈት እድሉን ያገኛሉ፡፡
የነጻው ገበያ ፉክክር የተሞላበት በመሆኑ የኢኮኖሚ ውድድሩ የበረታ ነው፡፡ወጣቱ ባገኘው እድል ተጠቅሞ የፈጠራ ችሎታውን በማዳበር ሰፊ ስራዎችን በመክፈት ራሱን ጠቅሞ በአንጻሩም ለዜጎች የተለያዩ የስራ እድሎችን እንደሚከፍት ይጠበቃል፡፡
አዲስ የወጣው መመሪያ ወጣቱ አዋጪ ነው ብሎ የሚያቀርበው የስራና የቢዝነስ እቅድ ታይቶ ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ከስራው ስምሪት በፊት የሚቀርቡት የስራ ትልሞች በብሔራዊ ኮሚቴው እየተመዘነ ጠቃሚ መሆኑ ሲታመንበት ወደክልሎቸም ተልኮ ወደስራ እንዲተረጎም የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ይታመናል፡፡
የተንቀሳቃሽ ፈንዱ ስጋቶችን በተመለከተ የሚወሰደው ገንዘብ ብድር ወለዱ 6 በመቶ ብቻ ነው፡፡5 አመት ድረስ የብድር መመለሻ ጊዜ አለው፡፡ለተወሰኑ የስራ አይነቶችም የእፎይታ ጊዜ አበጅቶአል፡፡ተዘዋዋሪ በጀቱና መመሪያው በስራ ሂደት የሚገጥሙትን ችግሮች በመፍታት ተጨባጭና ሁኔታውን ያገናዘቡ ምላሾችን ይሰጣል፡፡
ወጣቱ ንግድ ፍቃድ በሚያወጣበት ወቅት በየተቋማቱ የሚኖር የአፈጻጸም መጓተት፣ስለ ስራው በቂ እውቀት ያለመኖርና መሰል ነጥቦች በተጨባጭ ስራው ወቅት ጎልተው የሚወጡ ችግሮች ቢሆኑም በየደረጃው በሚገኙ ተቋማት በልዩ ሁኔታ ማስተናገድ የሚያስችል አሰራር እንደሚከተሉ ይጠበቃል፡፡
ወጣቶችን በተለያዩ አዳዲስ የሥራ ዘርፎች እንዲሠማሩ ለማድረግ 107 የሥራ አይነቶች ተለይተው የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ተቀርጸው ወደ ስራ ተገብቶአል፡፡ዘንድሮ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ በገጠርና በከተማ የሚገኙ ወጣቶች ተደራጅተውም ሆነ በተናጠል በልዩ ልዩ መስኮች ተሰማርተው እንዲሰሩ ለማድረግ ቀደም ሲል የተለያዩ ሥልጠናዎች መሰጠታቸው ይታወቃል፡፡
ማጠቃለያ
መንግስት ለወጣቶች የመደበውን ፈንድ በተግባር ስራ ላይ በማዋል የወጣቶችን የስራ ችግር አቅም በፈቀደ መጠን ለመፍታት በቀጥታ ወደስራ እንዲሰማሩ ማድረግ ከሁሉም ክልሎችና መስተዳድሮች ይጠበቃል፡፡ፈጥነውም ወደስራ መግባት አለባቸው፡፡ነገ ሳይሆን ዛሬ፡፡