ሰላም በአንድ ሃገር የፖለቲካ ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ወሳኝ ሚና በሚጫወተው ልክ ሃገራት በሂደት የሚገነቡትም ማናቸውም አይነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ በራሱ ለሃገራቱ ሰላማዊ የለት ተለት እንቅስቃሴዎች ሚናው የጎላ መሆኑ ይታወቃል። በየትኛውም አይነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ በአብዛኛው የግጭት መነሻ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ጉዳይ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይመሰክራሉ። ከዚሁ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ በሃገራችን የሽግግር መንግስት ዘመን እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች የነበሩ ቢሆንም በህዝቡ ባለቤትነት የሠላምና የደህንነት ተልዕኮዎችን በአግባቡ መወጣት በመቻሉ ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም ለፀደቀው ህገ-መንግስት እና በዚሁ ህገ-መንግስት መነሻነት እየተገነባ ለሚገኘው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጎታል፡፡ የኢፌዲራ ህገ-መንግስት የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በፖለቲካ መድረክ እኩል የመደመጥና የመሳተፍ መብት እንዲያገኙ ያስቻለ ከመሆኑም በላይ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ዋስትና የሰጠ በመሆኑም የግጭት ምክንያቶች ሁሉም እንኳ ባይሆን መሰረታዊ የነበሩት ቀዳዳዎች ተደፍነዋል፡፡
ህገ-መንግስቱ ለዘመናት ያልተመለሱ የዜጎቻችን የማንነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሃይማኖትና ራስን በራስ የማስተዳደር በአገሩ የመጠቀምና የማደግ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ያስቻለ ከመሆኑም በላይ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመገንባትም የጋራ ቃል ኪዳናቸውን ያስቀመጡበት ሰነድ በመሆኑ መሠረታዊ የሠላም ዋስትናችን ሆኗል።
ህገ-መንግስቱ አዲስቷን ኢትዮጵያ የፈጠረና እየገነባ የሚገኝ ሰነድ ነው የተባለት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ ዓለም አቀፍ ህጎችንና ድንጋጌዎችን ከአገራችን ተጨባጨ ሁኔታ ጋር አገናዝቦ ያስቀመጠና የተቀበለ ከመሆኑም በላይ ከሰው ልጆች ተፈጥሮዋዊ ድንጋጌዎች የሚመነጩ መብቶች ሙሉ በሙሉ ያካተተ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ያስከበረ ዜጎች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በዕድሜ፣ በፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ አድልዎና ልዩነት ሣይኖራቸው በህግ ፊት እኩል የሚሆኑበት ድንጋጌዎችንም ያካተተና በተግባርም የቀየረ በመሆኑ የአገራችን ህዝቦች የሠላምና ደህንነት ጥያቄዎች በመሠረታዊ መልኩ እንዲፈቱ አስችሏል፡፡
ህገ-መንግስቱ ባጐናፀፈው ድልና ስኬት የአገራችን የመንግስት አደረጃጀቱም ፌዴራላዊ የመንግስት ቅርፅ እንዲይዝ በመደረጉ ይህም በዋናነት የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች ማንነታቸውንና አሰፋፈራቸውን ማዕከል ያደረገ አስተዳደራዊ አደረጃጀት ተፈጥሮላቸው አካባቢያቸውን የሚያስተዳድሩበትና የሚያለሙበት ከልማቱም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት የተፈጠረ ከመሆኑም በላይ በፌዴራልና በየደረጃ ባሉ የፖለቲካ መድረኮችና የህዝብ ምክር ቤቶች በመርህ ላይ የተመሠረተ ውክልና እንዲኖራቸው በማደረጉና ይህም በተግባር ውጤት ያመጣ በመሆኑ የአገራችን ህዝቦች የሠላምና የደህንነት ጥያቄዎች ከስጋት ቀጠና ተላቀዋል።
ለዚህም ማሳያው ያለፉትን 25 አመታት በሙሉ እንደ አሊ-ኢትሃድና አብነግ የመሣሠሉ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች ከአገር አቀፍ አሸባሪ ቡድኖችና ጽንፈኛ አካላት ጋር በተናጠልና አንዳንዴ በጋራ የሽብር እና የትርምስ አደጋ ለመጣል በተደጋጋሚ የሞከሩ ቢሆንም በወሳኝ መልኩ የፀጥታ መዋቅሮቻችን በጋራና በቅንጅት በዋናነት ደግሞ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሠሩት ጠንካራ ሥራ የአገራችን ህዝቦች የሠላምና የደህንነት ሁኔታ አስተማማኝ እንዲሆን ማድረጉ ነው፡፡
የሃገራችን ህዝቦች ዋንኛ ጠላት ድህነትና ኋላቀርነት እንደሆነ መንግስት አንጥሮ በመለየት ይህንን የሚፈታ በርካታ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ነድፎ እየተንቀሳቀሰና በተግባርም ውጤት ማስመዝገቡ የግጭት መንስኤዎች ሁሉ ባሉበት ጨንግፈዋል። በውጭና የደህንነት ፖሊሲያችን አግባብ የትኛውም ጉዳይ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማሸነፍ ከሚደረግ ሥራና እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ መፈጸሙ ለሠላማችን ዓይነተኛ ዋስትና ሰጥቶናል። ምክንያቱም ድህነትና ኋላ ቀርነት ሥር በሰደደው ህብረተሰብ ውስጥ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ሊኖር አይችልምና፡፡
ከየትኛውም አገር ጋር የሚኖረን ግንኙነትና ትስስር በሰላም አብሮ በመኖርና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ፤ አንዱ በሌላኛው የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብነት እንደማይኖር የሚያስረግጥ በመሆኑ ከጐሮቤቶቻችንም ሆነ ከሌሎች የዓለም አገሮች የውጭ ግንኙነታችን ሠላማዊ እንዲሆን በማስቻሉ የግጭት ቀዳዳዎች ሁሉ እንዲዘጉ ሆኗል።
በፖሊሲው ላይ የውጭ ዲኘሎማሲያችን ትኩረቱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡና በውስጥ የድህነትና ኋላቀርነት ተጋላጭነታችንን ለመቀየርና በሂደትም ለማስወገድ በምናደርገው የልማት ጉዞና የዲሞክራሲ ግንባታ ሥራዎች አጋዥና ገንቢ ሚና በሚጫወቱ ሥራዎች ላይ መሆን እንዳለበት አስምሯል፡፡በዚሁ መሰረት ልማታዊነትን ለማረጋገጥና ልማትን ለማፋጠን የንግድና የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችን ከመጨመርና ከማስፋፋት አንስቶ የተለያዩ አገሮች ባለሀብቶች ወደ አገራችን በመግባት መዋዕለንዋያቸውን የሚያፈሱበት ሁኔታዎች እንዲመቻቹ የሚያደርግ በርካታ ሥራዎች ከፖሊሲው መጽደቅ በኋላ መሰራቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (FDI) በመሳብ በአፍሪካ ተጠቃሽ አገር ለመሆን አብቅቶናል፡፡
ኢትዮጵያ የምትገኝበት የክፍለ-አህጉሩ ክፍል የአፍሪካ ቀንድ በመሆኑና ይህ አካባቢ ደግሞ በተለያየ ምክንያት የሠላምና መረጋጋት እጦት እየተጋረጠበት የሚገኝ አካባቢ ሲሆን ይህንን ጀግናው መከላከያ ሃይላችን ኃላፊነቱን ተረክቦ ግዳጅን በብቃት ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል፡፡ በተለይም በሶማሊያ በተፈጠረው ጠንካራ መንግስት አለመኖሩን ተከትሎ የሽብርተኛ ድረጅቶች እንቅስቃሴን ለመምታትና ለማክሸፍ የኢፌዲሪ መከላከያ ኃይል የከፈለው መስዋዕትነትና ያረጋገጠው ሠላም በሠላም ወዳድ ህዝቦች ዘንድ እየተወሳ የሚኖር የጀግንነት ተግባር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ጀግናው መከላከያ ሃይላችን፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሰሜን ሱዳንና በሌሎች የተባበሩት መንግስታት ፀጥታው ም/ቤትንና የአፍሪካ ህብረት ውሳኔን ተከትሎ በመግባት የተሰጠውን ግዳጅ እጅግ በሚያኮራ ውጤት በመፈፀም በአንድ በኩል ጀግንነቱንና ህዝባዊነቱን ሲያስመሰክር በሌላ በኩል ከራሳችን አልፈን ለሌላ የምንተርፍ መሆኑንም በማሳየት የግጭት ሃይሎችን ቅስም ሰብሯል።
በአገራችን ባለፉት ዓመታት ለሠላማችን እጅግ ጠንቅ ሆኖ የቆዩት አገር በቀል አሸባሪ ድርጅቶች እና ስርአቱ በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ላይ ተረማምደው ሊረማመዱብን የሚሹ ጽንፈኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸው በተለያዩ ተጨባጭ ማሳያዎች ተረጋግጧል። እነዚህ ሃይሎች የሻዓቢያ መንግስት ተላላኪዎች ሲሆኑ ዋንኛ ተልዕኮዋቸውም የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦች የተቀዳጁትን ህገ-መንግስታዊ ሥርዓት ማፍረስ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በፀጥታ ሃይሎችና በህዝቡ የተባበረ ትግል ከስመዋል፡፡ይህ ማለት ግን የአገራችንና የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች እነዚህ አሸባሪ፤ ፀረ-ሠላም ድርጀቶችና ቡድኖች የህዝባችንን ህይወት የሚቀጥፉ የሽብር እርምጃዎች ለመውሰድ ያደረጉት ሙከራ በሙሉ ከሽፏል ማለት አይደለም ።
በአንዳንዶቹ እርምጃዎቻቸው ንፁሃን ዜጎች የጥቃቱ ሠለባ ሆነዋል፤ ቀላል የማይባል ንብረትም ወድሟል፡፡ ሆኖም ግን ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር ማለትም መከላከያ፣ ደህንነት፣ የፌዴራልና የክልል ፖሊስ ጥቃትን ከማይቀበለው ህዝብ ጋር በመሆን የአሸባሪዎችንና የፀረ-ሠላም ሃይሎችን ፍላጐትና አላማዎች ስራስር በመበጠስ የህዝቡን የሠላምና ደህንነት ፍላጐት በበቂ መጠን ማርካትም ተችሏል፡፡
በመሆኑም የአገራችን ህዝቦችና የፀጥታ ሃይሎች በሰጡት ትኩረትና በከፈሉት መስዋዕትነት ሃገራችን ላለፉት 25 ዓመት የተረጋጋ የሠላም ባለቤት ለመሆን ችላለች፡፡ ስለሆነም የአገራችን ህዝቦች ሙሉ ቀልብ ወደዋንኛው ጠላታችን ድህነት ላይ ሆኗል፡፡አገራችን የምትገኝበት ቀጠና በአብዛኛው ሠላም የታጣበት ሆኖ እያለ ብቸኛዋ የቀጠናው ሠላም ምንጭ መሆን በመቻሏ የራሷን ሠለም ከማረጋገጥ አልፋ ለቀጠናው የሠላም ተስፋ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ የዚህ ሰላምና መረጋጋት ዋነኛው ባለቤት ህዝቡ እንደሆነም በተግባር ታይቷል።
ያም ሆኖ ግን አሁንም ሙሉ በሙሉ ከስጋት ነጻ ነን ማለት አይቻልም። መቀመጫቸውን በውጭ ያደረጉ አንዳንድ ጽንፈኛ ሚዲያዎች በግልጽ እየተናገሩ ያሉት በአመጽና ሁከት መንግሥትን ለመጣል ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካላቸው መቅረቱንና በዚህም ፊታቸውን ወደትጥቅ ትግል ለማዞር መሞከራቸውን መሆኑ አንዱ ነጻ ላለመሆናችን ሊጠቀስ የሚችል ምክንያት ነው። በእርግጥ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች አሁን በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ለሰላማዊ ትግል አመች በመሆኑ ወደትጥቅ ትግል የሚያመራ ምክንያት የለም፤ የሚያዋጣም አይደለም። በሌላ በኩል ትጥቅ ትግል እንጀምር ቢባልም ለዚህ የሚያመች ሁኔታ በአገሪቱ ላይ የለም።
የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በሁሉም ክልሎች እየተደረገ ያለው ተሃድሶ እና የስራ ፈጠራ ከወዲሁ ስኬታማ መሆኑ እየታየ ነው። ሌላውና ለግጭት በምክንያትነት የሚቀርበው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ጉዳይ በውይይትና በድርድር አደብ የሚገዛበትን መንገድ ይዟል። በእርግጥ እዚህም ላይ ጽንፈኛ ሃይሎች ውይይቱ እና ድርድሩ ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አላካተተም በሚል የተደፈነውን የግጭት ቀዳዳ እንደገና ለመበርቀስ እየሞከሩ ነው። ሰላም ወዳዱና የሰላሙ ባለቤት የሆነው ህዝብ ግን መገንዘብ ያለበት በውይይቱና ድርድሩ ያልተካተቱት በውጭ አገር የሚኖሩ ህጋዊነት የሌላቸው ጽንፈኛ ቡድኖች ብቻ መሆናቸውን ነው። ይህ ብቻ አይደለም ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው እውነት። ገዢው ፓርቲ እውስጥ ካሉ ከሰላማዊ ፓርቲዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ካሁን ቀደም የትጥቅ ትግልን ከመረጡ ሃይሎች ጋር ጭምር ሲደራደር መቆየቱን ጭምር ስለሰላማችን ማስታወስ ያስፈልጋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የሚያካሄዷቸውን ውይይቶችና ድርድሮች ሚዲያዎች መከታተልና መዘገብ እንደሚችሉ ከስምምነት ላይ በመድረሳቸውም ከህዝብ የሚደበቅ አንዳች ነገር አይኖርም። ውይይቱና ድርድሩ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወይም በአገራችን የዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አካል ይልቁንም የዘላቂ ሰላማችን ዋስትና ነው።
ይህን የተገነዘበ ህዝብ ባለበት ሃገር ላይ የህዝብን ባህልና ጥቅም በማወክ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት የማይቻል ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያም ሰላማዊ ሃገር ለቀጣናዋም የሰላም አምባሳደር ሆና መቀጠል ያስችላታል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ህዝቡ በተረጋገጠው ሰላም የሚገኙ የልማት ውጤቶች ተጠቃሚ እኩል ተጠቃሚ የሚሆንባቸው እድሎችን ማስፋት ያስችለናልና ጉርምሩምታዎችን ሁሉ በአይነ ቁራኛ መመልከት ያስፈልጋል።