ኢትዮጵያዊያን፤ የዘመኑ ትውልድ አንድነትና ታላቅነት መገለጫ የሆነውን በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን 6ኛ ዓመት እያከበሩ ይገኛሉ። የግድቡ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ አንዴም ሳይቋረጥ አሁን ከግማሽ በላይ የተከናወነበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የግድቡ ባለቤት የሆነው ህዝብም ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገው ድጋፍ አንዴም ሳይቋረጥ እዚህ ደርሷል። አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ የግድቡን ግንባታ እንደሚያስጨርስ እርግጠኛ ሆኗል።
ታዲያ ኢትዮጵያዊያን በዚህ የአሸናፊነት ስሜት ውስጥ ባሉበት በዚህ ሰሞን፣ በውጭ አገር የሚንቀሳቀሰው ዘሃበሻ የተሰኘውና በኤርትራ መንግሥት የሚመራው ማህበራዊ ሚዲያ በፌስ ቡክ ገጹ ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ የበላይነት እየያዘች ነው የሚል ወሬ ለጥፎ ነበር። የወሬው ዓላማ ኢትዮጵያዊያንን ማስፈራራት ነው። የዘሃበሻን ወሬ ጠለቅ ብዬ የማንበብ ትዕግሥት አልነበረኝም። የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ የሚሰጠው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ፈጥሮ ያቀበለው የቀቢፀ ተስፋ ወሬ መሆኑ ስለገባኝ የሰኮንድ ያህል እንኳን ጊዜ ልሰጠው አልወደድኩም። እውነቱን ለመናገር እጅግ ተፀየፍኩት። ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ይህን እኔ ላይ ያደረ የመፀየፍ ስሜት እንደሚጋሩ ምንም ጥርጥር የለኝም። ሆኖም፤ ይኼው ግብጽ በአባይ ላይ የበላይነት እየያዘች ነው የሚል የዘሃበሻ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የተለጠፈ ዐረፍተ ነገር አንድ ጥያቄ ጫረብኝ፤ ግብጽ በአባይ ውኃ ላይ የበላይነት ኖሯት ያውቃል ወይ? የሚል ጥያቄ። እስከሚታወቀው ድረስ ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ የበላይነት ኖሯት አያውቅም። የበላይነት እንዲኖራት ለማድረግ ግን ብዙ ጥረት አድርጋለች።
ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያን ጨምሮ የታችኞቹን ተፋሰስ አገራት ሳያካተቱ እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 ዓ.ም የተፈራረሙት የውኃ ድርሻ ክፍፍል ስምምነት በተለይ ከቅኝ ግዛት ነጻ በነበረችው ኢትዮጵያ አንዴም ተቀባይነት አግኝቶ አያውቅም። እናም ግብጽ እና /ወይም ሱዳን በአባይ ውኃ ላይ ከኢትዮጵያ የበለጠ የባለቤትነት ሥልጣን ኖሯቸው አያውቅም። እንዲኖራቸው ፈልገው ግን ያውቃሉ። ዘሃበሻ አሁን ይህ የዘመናት የግብጽ ፍላጎት ዘንድሮ ተሳካ እያለን ነው። ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከግማሽ በላይ አድርሳ መጠናቀቁ አይቀሬ መሆኑን ህዝቡ ባረጋገጠበት በዚህ ወቅት እንዴትና በምን አኳኋን የግብጽ የዘመናት የአባይ ወንዝ ላይ በበላይነት የማዘዝ ፍላጎት /ህልም እንደተሳካ የዘሃበሻ ባለቤቶችና ተልዕኮ የሚያቀብለው የኤርትራ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስቴር ብቻ ናቸው የሚያውቁት። ያም ሆነ ይህ ዘሃበሻ ራሱን አጋልጧል፤ ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪ መስሎ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር እንደሚሰራ መስክሯል፤ ታዝበነዋል።
እርግጥ ነው፤ ኢትዮጵያ በተለይ ከአሥር ዓመት በፊት የአባይን ውኃ ምንም ጥቅም ላይ አላዋለችም። አባይ ለዘመናት ከነገባር ወንዞቹና ጅረቶቹ በየአጥቢያው በእንስራ እየተቀዳ ለቤት ውስጥ ፍጆታ ከመዋል ያለፈ ጥቅም ላይ ውሏል ሊባል አይችልም። ከ25 ዓመት በፊት በፊንጫ ወንዝ ላይ የተከናወነው የሸንኮራ አገዳ ልማትም ቢሆን የአባይን ተፋሰስ ውኃ አንድ በመቶ እንኳን ስለማይጠቀም ከቁጥር የሚገባ አይደለም። እርግጥ ከአሥር ዓመታት ወዲህ 300 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው የተከዜ ግድብና 460 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ጣና በለስ ፕሮጀክት ሊጠቀሱ ይችሉ ይሆናል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ወንዞች ላይ ያላትን የመጠቀም መብት ያሳዩ ቢሆንም፣ ከአጠቃላይ አባይ ኃይል በማመንጨትና በመስኖ ሊያለማው ከሚችለው ጋር ሲነጻጸር ግን ይህም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
እዚህ ላይ ላነሳ የፈለኩት ዋና ጉዳይ ኢትዮጵያ እስካሁን የአባይ ተፋሰስ ወንዞቿን ያልተጠቀመች ቢሆንም ይህ የሆነው በአባይ ወንዝ ላይ ግብጽ በበላይነት የባለቤትነት መብት ስላላትና ኢትዮጵያም ለዚህ እውቅና ስለሰጠች አለመሆኑን ነው። ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ መጠቀም የሚያስችላትን ፕሮጀክት የመገንባት የሀብት አቅም ስላልነበራት ነው። እርግጥ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግሥታት የአባይ ተፋሰስ ወንዞችን ለማልማት የሚያስፈልግ ብድር ለኢትዮጵያ እንዳይሰጡ ግብጽ ተጽዕኖ አሳድራለች። ተጽዕኖው ግን ብድር ሰጪዎቹ መንግሥታትና የገንዘብ ተቋማቱ ለግብጽ የአባይ ብቸኛ ባለቤትነት እውቅና ስለሰጡ ሳይሆን ግብጽ ከፍተኛ የዓለም ንግድ የሚንቀሳቀስበትን የስዊዝ ቦይ ስለምትቆጣጠር በዚህ ልታደርስባቸው የምትችለውን ጫና በመፍራት ነው። እናም ኢትዮጵያ የሀብት አቅም ሲኖራት በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ሊገሰስ የማይችል የባለቤትነት መብት በተጨባጭ ታየ። ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠው 300 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው የተከዜ ግድብ ፕሮጀክት እንዲሁም 460 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው የጣና በለስ ሁለገብ ፕሮጀክት ግድብ ሲገነባ ነው። አሁን ደግሞ ግንባታው ሲጠናቀቅ ዓለም ላይ ከሚገኙ አሥር ግዙፍ ግድቦች አንዱ የሚሆነውንና 6450 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል። የዚህን ግድብ ግንባታ አንድም የተቃወመ አገር ወይም ዓለም አቀፍ ተቋም የለም። ግብጽ ጭምር ግድቡ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖ እንዲጠና ጠየቀች እንጂ የግድቡን ግንባታ በይፋ አልተቃወመችም። ይህ እውነታ ግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ በበላይነት የባለቤትነት መብት እንዳልነበራት ለወደፊትም እንደማይኖራት ያረጋግጣል። ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ወንዞቿ ሳትጠቀም የቆየችው የሀብት አቅም ስላልነበራት ብቻ ነው፤ በቃ። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ እንዳትጠቀም ያደረጋትን ሁኔታ አስመልክቶ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ በተጣለበት ዕለት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ ባደረጉት ንግግር ልብ በሚነካ ሁኔታ ገልፀውታል። መለስ ዜናዊ በዚህ ንግግራቸው ላይ ያነሱት ሃሳብ፤
"…ግድቡን ለመሥራት ብድርና ዕርዳታ እንዳናገኝ የተለያዩ ኃይሎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ምክንያት የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን የሚተባበረን አገር ወይም ተቋም ማግኘት አልቻልንም። ስለሆነም ወጪውን ብቻችንን ከመሸፈን አልፈን በራሳችን ቁጠባ ለመሸፈን የምንገደድበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዬን ዩሮ በላይ ወይም ከ78 ቢሊዬን ብር በላይ በመሆኑና ከዚህ ፕሮጀክትም ባሻገር ሌሎች በራሳችን ወጭ ልንሸፍናቸው የሚገቡን በርካታ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው፣ ወጪውን መሸፈን እጅጉን እንደሚከብደን ጥርጥር የለውም። ሸክሙን ለማቃለል ያደረግነው ጥረት ስላልተሳካና ያለፉት 50 ዓመታት ታሪካችን እንደማይሳካ ያረጋገጡልን በመሆኑ የሚኖረን አማራጭ አንድም ግድቡን አለመስራት ነው፣ አለበለዚያ እንደምንም በራሳችን መሸፈን ነው። ከእነዚህ ከባድ ሁለት አማራጮች መካከል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ የትኛው እንደሚሆን ግልፅ ነው። በተለመደው ወኔው ‘ምንም ያህል ደሃ ብንሆንም ድህነታችንን ለማስወገድ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን። ስለዚህ ፕሮጀክቱ መሰራት አለበት’ እንደሚል ለአፍታም ያህል አልጠራጠርም። እንዲህ ዓይነት ቁርጠኝነት ተኪ የሌለው ኃይላችን ቢሆንም፣ ብቻውን ግን በቂ አይደለም። ቁርጠኝነት ወደ ተጨባጭ የልማት ፋይናንስነት እንዲሸጋገር ከተፈለገ የቁጠባ ባህላችንን በማዳበር የፋይናንስ አቅማችንን ማጠናከር ይገባናል።
"መንግሥት ገቢውን በማሻሻልና ወጪውን በመቆጠብ ፕሮጀክቱን ለማስፈፀም የበኩሉን ድርሻ ይጫወታል። የአገራችን ባንኮች የህዝቡን ቁጠባ በማሰባሰብ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ይጠበቃል። ከዚህም ባሻገር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ታሪካዊ ግድብ ለመሥራት የበኩሉን ቀጥተኛ ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል። መንግሥት ለዚህ የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅቷል። አምስት በመቶ ዓመታዊ ወለድ የሚከፈልበት የህዳሴ ግድብ ቦንድ አዘጋጅቶ ለመሸጥ አቅዷል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቦንዱን እንደየአቅሙ በመግዛት፣ በአንድ በኩል ገቢውን ለማሻሻልና ከወለዱ ተጠቃሚ ለመሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ታላቅ ግድብ ከዳር ለማድረስ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል። በመሆኑም የዘመናት የልማት ህልማችንን እውን ለማድረግ፣ መላው የአገራችን አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ ባለሀብቶችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በቦንድ ግዥው ዘመቻ እንደሚሳተፉ እምነቴ የፀና ነው። "ነበር ያሉት።
ይህን ተከተሎ ኢትዮጵያዊያን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስገንብተው በአባይ ወንዝ የልማት ተጠቃሚ ለመሆን፣ እግረ መንገዳቸውንም በአባይ ተፋሰስ ወንዞቻቸው ላይ ሊገሰስ የማይችል ፍትሃዊ በሆነ አኳኋን የመጠቀም መብት ያላቸው መሆኑን ለማሳየት በቦንድ ግዥ ርብርብ ማድረግ ጀመሩ። እስካሁን ለግድቡ ግንባታ የሚውል 9 ነጥብ 6 ቢሊዬን ብር የቦንድ ግዥ አከናውነዋል። በኅብረተሰብ ተሳትፎ ለግድቡ ድጋፍ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 47 በመቶ የሚሆነው በመንግሥት ሠራተኛው የተከናወነ ነው። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮያውያን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እስካሁን 39 ሚሊዬን ዶላር ወይም 877 ሚሊዮን ብር አስተዋጽኦ አድርገዋል። የቦንድ ግዥው አሁንም ቀደም ሲል ከነበረው በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል።
አርሶ አደሩ የህዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የታሰበለትን አገልግሎት በአግባቡ መስጠትን ታሳቢ በማድረግ በልዩ ተነሳሽነት ግድቡን ከደለል ለመከላከል የተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ ርብርብ አድርጓል። ይህ የአርሶ አደሩ ተሳትፎ በገንዘብ ሲተመን 45 ቢሊዬን ብር እንደሚሆን የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
የታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ከሆኑት ሱዳንና ግብጽ ፍትሃዊና ሚዛናዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲኖር የውይይትና መግባባት አማራጭን እየተከተሉ ነው። በተለይ ሱዳን የህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ምንም ቅሬታ እንደሌላት ከመግለጽ ባሻገር ድጋፍም አድርጋለች። የህዳሴው ግድብ ለራሷም ጥቅም እንዳለው ተገንዝባለች። የግብጽ መንግሥትም ቢሆን እንደ ዘሃበሻ ባሉ ቅጥረኞች አማካይነት ውስጥ ውስጡን የሚያደርገውን ባናውቅም በይፋ ግን የግድቡን ግንባታ አልተቃወመም። እርግጥ የግድቡ ግንባታ በግብጽ ላይ ተገቢ ያልሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ማድረግ የሚስችል ሁኔታ ለመፍጠር ሱዳንን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጋር የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል። እውነታው ይኼው ነው።
አባይ የአንድ አገር ወንዝ አይደለም። የአገራት የጋራ ወንዝ ነው። ከላይኞቹም ይሁን ከታችኞቹ የተፋሰስ አገራት አንድ አገር በወንዙ ላይ የማዘዝና በብቸኝነት የባለቤትነት መብት ኖሮት አያውቅም፣ አሁንም የለውም፤ ለወደፊትም ሊኖረው አይችልም። ይህን ግብጽም ተረድታለች። በአባይ ውኃ ላይ በመተባበር በጋራ ከመጠቀም የተሻለ አማራጭ የለም። እናም ዘሃበሻ የግብፅ መንግሥት እንኳን ሊሆን እንደማይችል የተረዳውን በአባይ ወንዝ ላይ የበላይ የመሆን ጉዳይን አንስቶ ወዲያ ወዲህ ሲል ይታያል፤ አሳፋሪም ነው።