እውነት በምክንያት እንጂ በስሜት አይመረመርም

ከመስከረም 28 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ወራት በሥራ ላይ እንዲውል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሣኔ የተወሰነው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ በአራት ወራት እንዲራዘም ተወስኗል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአራት ወራት የተራዘመው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም ጥያቄ ያቀረበው በህገ መንግሥቱ መሠረት አዋጁን ለማስፈፀም የተሰየመው ኮማንድ ፖስት ነው። ከስድስት ወራት በፊት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ እንዲታወጅ ያደረገው ሁኔታ ምን እንደነበረ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሚያውቀው ወደ ኋላ ተመልሼ መመልከት አልፈልግም። ይሁን እንጂ አዋጁ ለአራት ወራት እንዲራዘም ሲደረግ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያትና የመከላከያ ሚኒስትር ሲራጅ ፈጌሣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቧቸውን ምክንያቶች መጥቀስ እወዳለሁ።

የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬተሪያትና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጀ ፈጌሣ አዋጁ እንዲራዘም ሲጠይቁ ያቀረቧቸው ምክንያቶች፤ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመጠቀም የሚፈልጉ ፀረ ሠላም ኃይሎች እየተንቀሳቀሱ ነው፣ በሁከትና ብጥብጡ ቀንደኛ መሪዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቢያዙም እስካሁንም ያልተያዙ አሉ፣ በወረቀት ፅሁፎችን በመበተን አሁንም ሠላምና መረጋጋትን ለማደፍረስ የሚጥሩ ወገኖች አልፎ አልፎ ይታያሉ የሚሉ ናቸው። በተጨማሪም የአገሪቱ ሠላምና መረጋጋቱ የተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኝም፣ የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉም የአዋጁን መራዘም አስፈላጊ እንደሚያደርገው አመልክተዋል። በመላ አገሪቱ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ህዝቡ የተሻለ ሠላም እንዲሰፍን አዋጁ ይራዘም የሚል አስተያየት እንዳለው መረጋገጡንም በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም ሲጠየቅ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ህገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ጥያቄው ሲቀርብ አስተያየት የመስጠት ኃላፊነት የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻፀም መርማሪ ቦርድ አስተያየት እንዲሰጥ ተደርጓል። ቦርዱ በሰጠው አስተያየት ያካሄደውን ቅኝት መነሻ በማድረግ አዋጁ ቢቀጥል መልካም ነው የሚል አሰተያየት ሰጥቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከላይ በተገለፀው ምክንያት ህገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ለአራት ወራት መታደሱን ተከትሎ፣ የተለያዩ ሚዲያዎች በጉዳዩ ላይ ይመለከታቸዋል ያሏቸውን ሰዎች አነጋግረዋል። በተለይ በውጭ አገራት የሚገኙ ጽንፈኛ ሚዲያዎች፣ የአሜሪካ ድምጽ ራድዮ የአማርኛ ፕሮግራምን (ቪኦኤ) ጨምሮ፣ ጉዳዩን ውዥንብር ለመንዛት ዓላማ ሊጠቀሙበት ሞክረዋል። እነዚህ ሚዲያዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መራዘም ሚዛናዊነት በጎደለው ሁኔታ ከአንድ ጠርዝ ሊያራግቡት ሞክረዋል። እርግጥ ማንኛውንም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወን ተግባር የሚቃወሙትና ህዝብን ውዥንብር ውስጥ በመክተት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በመራወጥ የሚታወቁት ሚዲያዎችና አጋሮቻቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም የተደረገበትን ምክንያት ከህዝብ ፍላጎትና ጥቅም አንጻር ለመመዘን ይሞክራሉ ተብሎ አይጠበቅም። ይህ ከእባብ እንቁላል እርግብ ይፈለፈላል ብሎ የመጠበቅ ያህል ነው።

ያም ሆነ ይህ፤ በተለየ ቪኦኤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መራዘም አስመልክቶ የማራዘሙን እርምጃ ምንም መመርመር ሳያስፈልጋቸው የሚቃወሙ ግለሰቦችን አነጋግሮ ካሰራጨው መካከል አንዱን ለመመልከት ወድጃለሁ። ለዚህ ጽሁፍ የመረጥኩት አሰተያየት ሰጪ የዌብ ሣይት አምደኛ እንደሆነ የተነገረለት ሥዩም ተሾመ የተባለ ግለሰብ ነው። ቪኦኤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መራዘም አስመልክቶ ለግለሰቡ ያቀረበው ጥያቄ፣ በተለይ የአስቸኳይ አዋጁ እንዲራዘም በዳሰሳ ጥናት ውስጥ ከተካተቱ ዜጎች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም ድጋፋቸውን ሰጥተዋል በሚል የቀረበው ላይ የሚያተኩር ነው። 

አቶ ሥዩም ተሾመ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት “ይህን ተአማኒነት አለው ብሎ መቀበል በጣም ይከብዳል። እንዲህ ዓይነት የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል የተባለው እንደተለመደው ለፖለቲካ ፍጆታነት ለመጠቀም ነው” ብለዋል።

አቶ ሥዩም ለድረ ገጽ ጽሁፍ  ሲያዘጋጁ  መረጃዎችን ያሰባሰባሉ ብዬ እገምታለሁ። ታዲያ እርሳቸው ለአንድ የግል አስተያየታቸውን ለሚገልጹበት ጽሁፍ መረጃ የሚያሰባስቡ ሆኖ ሳለ፣ መንግሥት አንድ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ላይ በዘፈቀደ ይወስናል ብለው ማሰባቸው ተገቢ አይደለም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተራዘመው፣ አቶ ሥዩም እንዳሉት ምንም በዳሰሳ ጥናት የተገኘ መረጃ ሳይኖር በዘፈቀደ አይደለም። አቶ ሥዩም የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደፈለጋቸው የመወሰንና አቋም የመያዝ መብት የሌላቸው፣ የታሪክ ተጠያቂነት ያለባቸው መሆኑንና ይህንንም እንደሚገነዘቡ ለምን ዘነጉ ወይም ይህን እውነታ ለምን የሌለ ያህል ቆጠሩ? ይህ አቶ ሥዩም በምክንያት ላይ የተመሠረተ እውነታን ሳይሆን ስሜታቸውን የሚናገሩ መሆኑን ያመለክታል። እንደመሰለኝ አቶ ሥዩም መንግሥት ላይ ወይም ሥርዓቱ ላይ መሠረተ ቢስ ጥላቻ (prejudice) አድሮባቸዋል። መሠረተ ቢስ ጥላቻ በስሜት ስለሚነዳ ግራ ቀኙን የመመርመር አቅም ያሳጣል።

ወደእውነታው ስንመለስ፣ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ላይ ይሁን ሌላ ማንኛውም ጉዳይ ላይ ውሣኔ ከማሳለፉና አቋም ከመያዙ በፊት ሁሌም በመላ አገሪቱ ናሙና ወስዶ የህዝብ አስተያየት ያሰባስባል። ይህን አጣዳፊ ችግር ሲገጥመው በድንገት የሚያደርገው ሳይሆን፣ መደበኛ ሥራው ነው። መንግሥት ለዚሁ ዓላማ የተደራጁ ተቋማት፣ ሙያዊ ብቃትና ልምድ ያላቸው ሠራተኞች አሉት። ለምሣሌ የፌዴራል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በማንኛውም መሠረታዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ወርሃዊ የህዝብ አስተያየት ማሰባሰቢያ በዋና ዳይሬክተር ሥር የተዋቀረ አደረጃጀትና የሰው ኃይል አለው። ከዚህ በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ወሣኝና ጠለቅ ያለ ጥናት የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ የህዝብ አስተያየትና አቋም ጥናት ያከናውናል። አሁን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም ሲጠየቅ በአስረጂነት የቀረበው የህዝብ አስተያየት የዳሰሳ  ጥናት በእነዚህ ተቋማት ነው የተከናወነው። አቶ ሥዩም ይህን ላያውቁ ይችሉ ይሆናል። አለማወቃቸው በራሱ ችግር አይደለም። ችግሩ ምንም የዳሰሳ ጥናት እንዳልተሰራ በድፍረት በመሳለቅ አፋቸውን ሞልተው መናገራቸው ላይ ነው ያለው።

አቶ ሥዩም አያይዘው “80 በመቶ የአገሪቱ ህዝብ እሥራቱን፣ መታፈኑን አምኖ ተቀብሎ አዋጁ እንዲራዘም ደግፏል ብሎ ማለት ተዓማኒነት የሌለውና ልቀበለው የማልችለው ነገር ነው። ምክንያቱም ማንም መታሰር አይፈልግም፣ ማንም ሃሳቡን እንዳይገልጽ መታገድ አይፈልግም” ብለዋል።

እርግጥ ነው አቶ ሥዩም ህዝቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለው ማወቅ አይችሉም፤ ይህን ማድረግ የሚያስችላቸው ምንም የዳሰሳ ጥናት ስላላካሄዱ። በዚህ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ እንዲታወጅ የግድ ያለውን አውዳሚ ሁከት፣ እርሳቸው እንደ ተገቢ እንቅስቃሴ ስለሚቆጥሩት ህዝቡ አዋጁ እንዲራዘም መጠየቁን መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል። እነዚህ ሁኔታዎች ከእውነታ ያርቋቸዋል።

ወደእውነታው እንመለስ። ከአንድ ዓመት በፊት በተለይ በኦሮሚያ፣ በተወሰኑ የአማራና የደቡብ ክልሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረው ሁከት ለህዝቡ የፈለገውን አቋም የመያዝና ሃሳቡን በይፋ የመግለጽ ነጻነት ያስከበረና ያረጋገጠ አልነበረም። ህዝቡ ያለምንም ሥጋት በነጻነት ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮቹን ማከናወን የሚያስችለውን ሠላም ያረጋገጠ አልነበረም። ህዝብ ዘላቂ ህይወቱ ሠላማዊና የተረጋጋ ስለመሆኑ ዋስትና የሰጠ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ፤ ሁከቱን በማህበራዊ ሚዲያ ይመሩ የነበሩትን እነጃዋርና የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂ አስፈፃሚ ቡድኖችን ትዕዛዝና በትዕዛዙ መሠረት ይወሰዱ የነበሩ እርምጃዎችን የሚቃወሙ ዜጎች ይደበደቡ፣ ይገደሉ፣ ቤታቸው ይቃጠል የነበረበትን ሁኔታ የፈጠረ ነበር። በሁከቱ ወቅት ቤታቸው ውስጥ ተቆልፎባቸው እሣት ተለኩሶባቸው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ እንደነበሩ አስታውሱ። በምሽት ከቤታቸው ተጠርተው ወጥተው ወደልጆቻቸው ሳይመለሱ ለዘለዓለሙ የቀሩትን ቤት ይቁጠራቸው። በአቋማቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ይሰነዘርባቸው የነበሩ በርካቶች ናቸው። ጃዋር መሐመድና የኤርትራ ተላላኪዎች ሱቃችሁን ዝጉ የሚል ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ፣ ይህን ትዕዛዝ ባለማከበራቸው ብቻ ቤታቸው የተቃጠለባቸውና የተደበደቡ ዜጎች አሉ። ገበያ እንዳይቆም በአዋኪዎች በመከልከሉ አርሶ አደሩ ለገበያ ያወጣውን ምርት ተሸክሞ ወደ ቤት የተመለሰበት ሁኔታም እንደነበር ይታወሳል። ለቅሶ መድረስ፣ የአደባባይ ኃይማኖታዊ ሁነቶች ላይ መሳተፍ፣ ወዘተ…ለአደጋ የሚያጋልጥ ሆኖ ነበር። በእለት ሥራ የሚተዳደሩ ዜጎች ከቤት እንዳትወጡ በሚል በተላለፈ ትዕዛዝ ምክንያት ከነልጆቻቸው የሚበሉት አጥተው ለቀናት ተርበዋል። ወላጆች ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ልጆቻቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደቤት እንዲመለሱ ያደረጉበት ሁኔታ ነበር። በአጠቃለይ ባለሃብቶች ሰርተው ያፈሩት ንብረታቸው ላይ ዋስትና ያጡበት፣ ዜጎች ሰርተው መኖራቸው ለአደጋ የተጋለጠበት ሁኔታ ሰፍኖ ነበር።

የአስቸካይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ያደረጉት እነዚህ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር ያደረጉ ሁኔታዎች ናቸው። የአዋጁ ዓላማም ሁከቱን ቀልበሶ ሠላምና መረጋጋት ማስፈን ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህዝቡን በጅምላ እንዲታሰር፣ ሃሳቡን እንዳይገልጽ፣ እንዳይንቀሳቀስ አላደረገም። አዋጁ ከታወጀ በኋላ የነበረው ሁኔታ፣ አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ መኖሯን እንኳን ማወቅ በማይቻልበት ሁኔታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ሲከናወኑ ነበር። እናም ህዝቡ የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም ሲጠይቅ ሁከቱ አስከትሎት የነበረው የመብት ጥሰትና ሥጋት ዳግም ሊመለስ በማይችልበት ሁኔታ እንዲረጋገጥ ካለው ፍላጎት ነው።

እርግጥ ሃያ አምስት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ባለማወቅ በሁከቱ ውስጥ የተሳተፉ ዜጎች ነበሩ። የሚያስከተለውን ውጤትም እያወቁ የተሳተፉ ዜጎችም ነበሩ። እነዚህ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በሁከቱ ላይ የተሳተፉ ዜጎቸ በቁጥጥር ሥር ውለዋል። ባለማወቅ ሁከቱ ውስጥ የገቡትና ሊታረሙ ይችላሉ ተብለው የታሰቡ ሃያ ሺህ ገደማ የሚሆኑ ዜጎች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ወደተለመደው ሠላማዊ ህይወታቸው ተመልሰዋል። አራት ሺህ ገደማ የሚሆኑት ደግሞ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ሁከት ተቀስቅሶ የነበረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች፣ ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት የመኖር ዋስትናቸው ለአደጋ ተጋልጦ ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይህን አደጋ አቃሎላቸዋል። አሁን አዋጁ እንዲራዘም ያላቸው ፍላጎት በህዝብ አስተያየት ጥናት ተረጋግጧል። ህዝቡ አዋጁ እንዲራዘም የፈለገው ከሥጋት ነጻ የሆነው ሠላምና መረጋጋት ዘላቂነቱ የተረጋገጠበት ደረጃ ላይ እንዲደርሰ ነው። እናም አቶ ሥዩም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መራዘም አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ጥናትን መሠረት ያላደረገና ሥርዓቱ ላይ ባላቸው መሠረተ ቢስ የጥላቻ ስሜት (prejudice) የተቃኘ ነው። ስሜት ደግሞ የእውነታ መመርመሪያ ሊሆን አይችልም። ስሜትና እውነት ለየቅል ናቸውና። እውነት በምክንያት እንጂ በስሜት አይመረመርም።