የመልማት መብትና ፌዴራሊዝም

ባለፉት ስርዓቶች ዜጎች በልማት አጀንዳ ተሳታፊ ስላልነበሩ ህይወታቸውን የሚለውጥ ሀብት የማፍራትና ከአገሪቱ ሀብት በፍትሃዊነት የመጠቀም መብት አልነበራቸውም፡፡ የሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ አንዱ መሠረታዊ እምነት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሀብት ምንጭ የሆነውን መሬት ባለቤቶች እንዲሆኑ ማድረግ፣ የጋራ አስተዳደር ማለትም ፌዴራል መንግሥት ከሚያከናውናቸው የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማቶችና ከሚሰበሰበው ሀብት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማስቻል ብሎም በተጎናፀፉት የራስ አስተዳደር አማካይነት አቅማቸውን አስተባብረው አካባቢያቸውን እንዲያለሙ ሥልጣንና ኃላፊነት መስጠት ነው፡፡   

ባለፉት መንግሥታት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ የተነሳበት ዋናው መሠረታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩበት፤ ለዴሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት የተጣለበት፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት፤ ውበትና ህብረት የታየበት ብሎም የሥልጣን ባለቤት የተረጋገጠበት፤ የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ የተጀመረበት መሠረቱ ይኸው ህገ መንግሥት ነው፡፡

የህገ መንግሥቱ ድሎችና ውጤቶች ከመቼውም በላይ ተስፋፍተው፤ የዜጎች ማንነትና ባህላዊ እሴቶች ጎልተው ወጥተው፤ መልካም ተሞክሮዎችም ይበልጡን ጎልብተው የአንድነታችንና የጥንካሬያችን መገለጫ ሆነው እንዲቀጥሉ ዜጎች እጅ ለእጅ ተያይዘው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት የክልሎችን እኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል በተለይም በልማትና ዕድገት አፈጻፀም ረገድ በጎ እርምጃዎች ተወስደው መልካም ውጤቶች ታይተዋል፡፡ በህገ መንግሥት በተደነገገው እኩል የመልማት መብት በመጠቀም በሁሉም ክልሎች በተነፃፃሪ ፈጣን የሚባል ልማትና ዕድገት ተመዝግቧል፡፡

ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ከአገሪቱ ተጨባጭ ታሪካዊ ሁኔታ በመነሳት በህገ መንግሥቱ ተደንግጎ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ ህብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ያለፉት አፋኝ መንግሥታት የቀበሩትን የማንነትና የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት ጥያቄን በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ችሏል፡፡ በመፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን ለማስቀጠልና ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሰሩበትን አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት ጉዳይ በህዳሴው እየተቀላጠፈ ይገኛል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አስችሏል፡፡

በዚህም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ተሳትፏቸውና በየደረጃው ተጠቃሚነታቸው ጎልብቷል፡፡ አካባቢያቸውንም በማልማት ለአገር ብልፅግናና እድገት ከፍተኛ ደርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ደግሞ የልማትና ዕድገት አፈጻፀም በክልሎች እኩል ተጠቃሚነት እየተፈፀመ መሆኑን የሚያረጋግጥ እውነታ ነው፡፡

የክልሎችን የእኩል ተጠቃሚነት በማረጋገጥ አንፃር ልማታዊው መንግሥት ግልፅ የሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ ህጎችን፣ የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ በየአካባቢው ተጨባጭ እቅድ እየተመነዘሩ የሚፈፀሙበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በአፈጻፀም ሂደት የተገኙ በጎ ልምዶችም እየተቀመሩ በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎችና ለምልዓተ ሕዝቡ የሚደርስበት ስልቶች ተቀይሰዋል፡፡

የልማት ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመተግበር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ማነቆዎች የሚለዩበትን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥያቄዎች ካለፉት ልምዶች በመነሳት እንዲፈተሹና እንዲስተካከሉ በማድረግ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ይገኛል፡፡ ክልሎች በገጠርና ከተማ የልማትና መልካም አስተዳደር ዕቅዶችን በመንደፍና ሕዝቦቻቸውን ዋናው ፈፃሚ አካል በማድረግ ባለፉት ስምንት ዓመታት በአማካይ ለተመዘገበው ከሁለት አኃዝ በላይ እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ አግዟል፡፡

የፌዴራል መንግሥትም ክልሎችን ከክልሎች ብሎም ከአዋሳኝ አገሮች ጋር የሚያገናኙ መንገዶችን በመስራትና ፈጣን የቴሌኮም አገልግሎቶችን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማፋጠን፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትንና የአገር ውስጥና የውጭ አገር የገበያ ትስስርን በመፍጠርና በማጎልበት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱ ግብ በአስተማማኝ ሁኔታ እየተተገበረ  ይገኛል፡፡

በአገሪቱ ያሉ ክልሎች እርስ በርስ በመደጋገፍና ልምዶችን በመለዋወጥ የሚያደርጉት የጎንዮሽ ይሁን የተዋረድ ግንኙነት ለእኩል ተጠቃሚነትና በተመጣጣኝ ልማትና እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይህም የልማትና የመልካም አስተዳደር ማነቆዎችን በመፍታትና በጎ ልምዶችን በማስፋፋት ሂደቱን ማስቀጠል ከተቻለ አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ አገሪቱ መካከለኛ ገቢዎች ካላቸው አገራት ተርታ የማትሰለፍበት አንዳች ምክንያት የሌለ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በአጠቃላይ ሀገሪቱ ከተዘፈቀችበት ድህነትና ኋላ ቀርነት በባሰ ደረጃ ስር ሰዶ የቆየባቸው አካባቢዎችም ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግሥት ላይ በግልፅ እንደተደነገገው እነዚህ ክልሎች በአሁኑ ወቅት ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን እንደተቀሩት የአገሪቱ ክልሎች አስከብረዋል፡፡ ይህ ሲባል ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደር ጀምሮ አካባቢያቸውን በማልማትና ሕዝቦቻቸውን የሠላም፣ የልማት የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚዎች ለማድረግ እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ዜጋ በግልጽ አይቶ መፍረድ እንደሚቻለው በእነዚህ ክልሎች ዛሬ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተቋማትና የመሠረተ ልማት አውታሮች በሚያስደንቅ ሁኔታ እየተገነቡ ነው፡፡

የሰው ኃይል ልማት በራሳቸውና በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እየጨመረ በሚሄድ ቁጥር በየዓመቱ እየገቡና እየተመረቁ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎችን የማስፈፀም አቅም በመገንባት ላይ ናቸው፡፡ አካባቢዎቹ ዛሬ ከየትኛውም ወቅት በላይ ሠላማዊ ሆነዋል፡፡ የመሠረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታውም እየተፋጠነ ሄዷል፡፡

ለክልሎቹ ምርታማነትና የገበያ ትስስር ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩላቸው ነው፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ አካባቢዎቹ በልማትና እድገት ጎዳና እየተራመዱ ይገኛሉ፡፡ ይህም በአካባቢዎቹ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር፣ የሥራ እድል እንዲፈጠርና ነዋሪዎቹም ተጨማሪ የገቢ እድል የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው፡፡

የክልሎቹ መንግሥታትና ሕዝቡ ከሚያደርጋቸው ልማታዊ ርብርብ ጎን ለጎን በፌዴራል መንግሥት በኩል የተለያዩ ተገቢነት ያላቸው ሚኒስትሮች የሚገኙበት የልዩ እገዛ ቦርድ ተቋቁሟል፡፡ የአጎራባች ክልሎች የልማት ትብብር ፕሮግራም በመንደፍና የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች የሚያሳኩ የበጀት አመዳደብና ድጋፍ ሥርዓቶችን የመዘርጋት ዘላቂ አቅም የመገንባት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡

እስካሁን የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸው እንደተጠበቁ ሆነው ለቀጣዩም መሠረት ስለሚጥሉ የፌዴራልና የክልሎች መንግሥታት የጋራ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በተለይ በእነዚህ ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ውስጥ እየተካሄደ ስላለው በመንደር የማሰባሰብ ፕሮግራም ጥቂት ማለት ተገቢነት የሚኖረው ይሆናል፡፡

በቅድሚያ መታወቅ ያለበት በመንደር የማሰባሰብ ፕሮግራም ዓላማው ዜጎች ከአገራቸው ልማትና እድገት በላቀ ደረጃ የሚጠቀሙበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አካል እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፕሮግራሙ በአገሪቱ የመልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲና የልማት መብቶችን ለማስጠበቅ የሚከናወን ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መብት ረገድ ዜጎች ተበታትነው በሚኖሩበት ሁኔታ የተደራጀ ትግል ሊያካሂዱ ይሁን ድምፃቸውን ሊያሰሙ አዳጋች እንደሚሆንባቸው እሙን ነው፡፡

በመሆኑም ዜጎች ተበታትነው ከሚኖሩበት ሁኔታ ወጥተው በመንደር መሰባሰብ ወደሚችሉበት ሁኔታ የሚያመጣቸው ነው — በመንደር የማሰባሰቡ ፕሮግራም፡፡ ዜጎች በመብቶቻቸውና ጥቅሞቻቸው ዙሪያ እንደ ሕዝብ ድርሻቸውን ሊወጡም ይሁን ከመንግሥት መዋቅር ጋር በቅርበት ለመወያየትና መፍትሄ ለማፈላለግም ያስችላቸዋል፡፡

ይህ ፕሮግራም ከአገሪቱ አቅም ተነስተን ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማቅረብ ያስቻለ ነው፡፡ በውጤቱም የዜጎችን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ከወዲሁ ከፍተኛ ለውጥ መታየት ጀምሯል፡፡ ይህ ፕሮግራም በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ከሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥና ከሚያስከትለው አደጋ ዜጎችን የመታደግ ዓላማም አለው፡፡

ህዝቡ በሚሰባሰብበት ወቅት ከሁሉም በላይ ከዴሞክራሲያዊ መርሆች በመነሳት በሙሉ ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ የሚፈፀም ፕሮግራም ነው፡፡ በቅድሚያም በየአካባቢዎቹ በቂ የጓሮ፣ የእርሻ፣ የግጦሽ መሬትና የውኃ አቅርቦት መኖሩን በማረጋገጥ ጭምር፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ሕዝቡ የተረጂነትና የጠባቂነት አስተሳሰብ ሳይሸከም ወደ ምርት ተግባር እንዲሸጋገር የሚያስችሉ የአመለካከት፣ የክህሎትና የግብዓት አቅርቦት ሥራዎች ጎን ለጎን ተከናውነዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ማህበራዊ የመሠረተ ልማት ተቋማት እየተገነቡ በአገልግሎት ላይ የዋሉበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡ ይህ በመንደር የማሰባሰብ ፕሮግራም በሌላ በኩል በልዩ ድጋፍ ክልሎች ያሉ ሕዝቦች በሠላም፣ በልማት፣ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ እንግዲህ ከእነዚህ እውነታዎች ማንኛውም ሰው ፌዴራሊዝም ለሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የመልማት መብት ምን ያህል ገንቢ ሚና እንደተጫወተ ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ። ስለሆነም ፌዴራሊዝም ሁሉም ክልሎች በአንፃራዊነት እኩል መንገድ እንዲለሙ ያደረገ ነው ማለት ይቻላል።