ሰላም ለአንድ ሀገርና ሕዝብ ወሳኝ ነው፡፡ ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት የተጀመረውን እድገትና ልማት ለማስቀጠል ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ ለሀገራዊው ኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት ለተጠናቀቁትም ሆነ ለተጀመሩት ሀገራዊ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ከዳር መድረስና የበለጠም እድገት ለማስመዝገብ የሚቻለው ከምንም ነገር በላይ ወሳኙ ሰላምና ሰላም ብቻ ነው፡፡
በሀገር ውስጥ በሕዝቡ በኩል የሚቀርቡና የሚነሱ ማንኛቸውንም አይነት ጥያቄዎች ለመመለስ በተሀድሶ ንቅናቄው መሰረት ከፌደራል መንግስቱ ጀምሮ በሁሉም ክልሎች፣ አስተዳደርና አመራር ደረጃዎች በስፋት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በሰላማዊ መንገድ በመወያያትና በመነጋገር መታረም ያለበት እንዲታረም መስተካከል፤ ያለበት እንዲስተካክል በከፍተኛ ሙስናና ምዝበራ ውስጥ የተገኙትን በተጨባጭ ማስረጃዎች ከኃላፊነታቸው ተነስተው በሕግ እንዲጠየቁ፣ ከደረጃም ዝቅ ማለት ያለባቸው ዝቅ ብለው እንዲሰሩ፣ መሰናበት ያለባቸውም እንዲሰናበቱ የማድረጉ ሁኔታ የተሀድሶው ንቅናቄ አካል ሲሁን እርምጃውም ገና ጅምር ነው፡፡ ጅምር ይሁን እንጂ በሂደቱ አበረታች ለውጦች በመታየት ላይ ናቸው፡፡
ችግሮች በስፋት መፈጠራቸውን ገዢው ፓርቲ በጥልቀት አይቶና መርምሮ ወደ ተጨባጭ እርምጃዎች ከገባ ሰንብቶአል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ደረጃ በደረጃ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ተሀድሶ ማለት መለወጥ፤ ወደቀጣዩ ምእራፍና ደረጃ ለመሸጋገር እርካቡን መጨበጥ ማለት ነው፡፡ አሮጌውን አስተሳሰብ፣ አካሄድና አመለካካት በመተው፤ ዘመኑ በሚፈቅደውና ሕብረተሰቡ በሚፈልገው ደረጃ፣ መጠንና ልክ በመስራትና ለውጥ ለማምጣት በቁርጠኝነት መትጋት መቻል ነው፡፡
የተሀድሶው አላማ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥና ልማት በተሻለ ብቃትና ሕዝባዊ አገልጋይነት በበለጠ ውጤት ማስቀጠል ነው፡፡ ይህንን እውነትና የለውጥ ሂደት ሕብረተሰቡ በውል ሊረዳውና ሊገነዘበው ይገባል፡፡
በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱትን ጥያቄዎች አግባብ ባለው መልኩ የመፍታቱ አቅምና ብቃት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሀገራዊ ሁከት፣ ብጥብጥና ትርምስ በመፍጠር የውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን በተለይም በግብጽ ጉዳይ አስፈጻሚነት ተሰልፎ የትርምስ አጀንዳን ማራመድ የሚጠቅመው ለኢትዮጵያ ጠላቶች እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የተጀመሩት ሀገራዊ ልማቶችና እድገቶች እንዲገቱ ለማድረግ ግብጽ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መድባ የእኛኑ ማፈሪያ ዜጎች በመሳሪያነት በመጠቀም በተለያየ አቅጣጫ ዛሬም እየተንቀሳቀሰች መሆንዋን መንግስትም ሕዝብም ያውቃል፡፡ በሀገር ውስጥ በወኪሎቻቸው አማካኝነት ኢኮኖሚውን፣ ትራንስፖርቱን ግብይቱን ለማሽመድመድ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ፤ ስርአተ አልበኝነት እንዲሰፍን ለማድረግ (አልተሳካላቸውም እንጂ) ብዙ ሞክረዋል፡፡
የተጀመሩት ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በተለይ ስራው እንዲቆም ለማድረግ በሰርጎ ገቦቻቸው አማካኝነት የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደትላንቱ ሁሉ ዛሬም ሙከራቸውም አለባራም፡፡ አንድ ያልተረዱት ምስጢር ቢኖር፣ በየትኛውም አቅጣጫ ለሚሞክሩት ድርጊት ፈጣንና የማያዳግም ምላሹን የሚሰጠው ሕዝቡ መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህም እያበላሹ ያሉት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ነው፡፡ የመጡት በኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅምና በሀገራዊ ሉአላዊነቱ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፍፁም ይቅርታ የሌለው ድርጊት ነው፡፡
የግብፅ አቋም ሀገሬንና ወገኔን እወዳለሁ የሚል ዜጋ ሁሉ በሕብረትና በአንድነት ጸንቶ ሊፋለመው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ግብጾች አባይ የሕይወታችንና የሕልውናችን ጉዳይ ነው እንደሚሉት ሁሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ለእኛም የሞትና የሽረት፤ የሕልውናችን ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደ መንግስት የሰራቸውን ለሀገርና ለትውልድ የሚበጁ ታላላቅ ስራዎን የትም ይዟቸው አይሄድም፡፡ ስራዎቹ ከማንም በላይ የሚጠቅሙት ቢኖር ተተኪውን ትውልድ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል፡፡
እነዚህን የሀገር ሀብቶች መጠበቅና መንከባከብ ሲገባ ጭራሹንም ሀገሪቱን ለመበታተንና ለማውድም ያለ የሌለ ስልትና ስትራቴጂ ቀይሰው ብዙ መቶ ሚሊዮኖች ገንዘብ በቓሚነት መድበው ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማተራመስ ከሚሰሩ ኃይሎች ጎን ተሰልፎ መገኘት በታሪክም፣ በትውልድም ተጠያቂ የሚያደርግ ታላቅ የአገር ክህደት ወንጀል ነው፡፡
የውስጥ ችግርን በውስጥና በራስ አቅም መፍታት ይቻላል፡፡ በጥላቻ በመሞላት በስሜታዊነት እብደት ውስጥ ተዘፍቆ የፈለገው መአት ይውረድ በሚል የጅል እሳቤ የሚናውዘው ጽንፈኛው አክራሪ የፖለቲካ ኃይል ዙሪያዋን በተለያዩ ጠላቶች የአደጋ ቀለበት ውስጥ ኢላማ ሁና ያለችን ሀገር የእነሱ መሳሪያና ቅጥረኛ በመሆን ለመበታተንና ለማውደም መስራት የለየለት፣ መለኪያና መስፈርት የሌለው ጸረ ሕዝብነት፤ ሀገርን የመበታተን የማውደም ሴራ ነው፡፡
ሁሉም ዜጋ መቆም ያለበት የውስጥ ፖለቲካ ልዩነቶችን በማቻቻል፣ ችግሮችንም በውይይትና በድርድር በመፍታት፣ ሰላማዊ የምርጫ ውድድርም በማድረግ ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ኃይሎች ሴራና ደባ አደጋ ውስጥ እንዳትወድቅ ነቅቶ መጠበቅ ነው የሚገባው፡፡
የሀገር ሕልውና፣ ብሔራዊ ጥቅም፣ የተረጋጋ ሰላምና አንድነት ከምንም በላይ መቅደም አለበት፡፡ ከሶርያ በአለም ታሪክ ከዚህ ቀደም ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ጉድ ያሰኘ ሀገራዊ መፈረካከስና የሕዝብ እልቂት፤ ከሊቢያ ውድመትና ጥፋት፤ ከየመን ትርምስና እልቂት ብዙ መማር ይገባል፡፡ ዛሬ እነዚህ ሀገራት ቢኖሩም እንዳሉ አይቆጠሩም፡፡ የየሀገራቸው አስተዋይነት የጎደለው ስግብግብና ደንቆሮ አክራሪ ፖለቲከኛ በውጭ ኃይሎች ገንዘብና መሳሪያ እየተረዳ የገዛ ሀገሩን ምድረበዳ አድርጎ አወደማት፡፡ ሴራው የውጭ ሀይሎች ነው፡፡ በተለይም የምእራባውያን፡፡ ዛሬ ሶርያውያን ሀገር የላቸውም፡፡ ቤት የላቸውም፡፡ ስደተኞች፣ አለምን ያጨናነቁ፣ መድረሻ ጥግ ያጡ ተንከራታች ሕዝብ ሆነዋል፡፡
በ21ኛው ክፍል ዘመን እንደነዚህ አይነት ጨካኝ፣ አረመኔ፣ ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት የጎደላቸው፣ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ትንሽም እንኳን የማይጨነቁ፣ የሕጻናት የቤተሰብ መበተንና መሞት፣ የአረጋውያን እልቂት፣ የጥንታዊ ከተሞች መወድም ወዘተ ሁሉ ለነዚህ ወገኖች ምናቸውም አይደለም።
ይህ አለምን በእጅጉ ያስደነገጠና ከልብ ያሳዘነ ድርጊት የተፈጸመው በየሀገራቱ ተቃዋሚ ነን፣ ዲሞክራሲና ነጻነት፣ ነጻ ኢኮኖሚ ወዘተ እናሰፍናለን፣ እኛ ብንመራ የተሻለ ሀገር እንፈጥራለን ብለው ነገር ግን ከጀርባ በውጭ ሀይሎች በመደገፍና በመመራት በእራሳቸው ሀገርና ሕዝብ ላይ በዘመቱ ለውድመትና ለእልቂት ለስደት ባበቁዋቸው ዜጎቻቸው አማካኝነት ነው፡፡
እንደነዚህ አይነት ኃይሎች ለሀገርም ለሕዝብም ከጥፋትና ከውድመት በስተቀር የተሻለ ለውጥ የማምጣት አቅም የላቸውም፡፡ ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ እንዲሉ ከነበረው የተሻለ ማምጣት ቀርቶ ቀድሞ ሀገራቱ ወደነበሩበት ሁኔታ መመለስ አልቻሉም፡፡ በሀገራችንም የዚህ አይነቱን ተመሳሳይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ብዙ ተሞክሮአል፤ ግን አንዱም አልሆነም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ፈተናና መከራን አስቀድሞ ያየ፣ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን በቅጡ ለይቶ የሚያውቅ፣ በስሜታዊነትና በጀብደኝነት ተነሳስቶ የገዛ ሀገሩን የሚያጠፋ የሚያወድም አይደለም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ደግሞ አምና የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ በማረጋጋት ረገድ ቁልፉን ሚና የተጫወተው፤ ሀገሩንም ከማንኛውም አደጋ የጠበቀው፤ ሰላማዊና የተረጋጋች ሀገር ሁና እንድትቀጥል ከጥንት ጀምሮ በታላቅ መስዋእትነት የጠበቃት፤ ያስከበራት፤ አሁንም ሆነ ወደፊት ጠብቆአት የኖረው ሕዝቡ መሆኑ ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ሴራ የመጨረሻው ደረጃ እንደተጠቀሱት ሀገሮች አይነት አስፈሪና አርማጌዶናዊ ጥፋትና እልቂት ውስጥ ከመግባት ባሻገር የሚፈይደው አንዳችም ነገር የለም፡፡ ለኢትዮጵያ ይህንን የሚመኙ ደግሞ የሀገርና የሕዝብ ጠላቶች እንጂ ወዳጆች ከቶውንም ሊሆኑ አይችሉም፡፡
እስካሁን ባለው የጥልቅ ተሀድሶ ሂደት፣ የተከሰቱትን የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህ፣ ሙስና፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመሬት ቅርምት ችግሮችን ለመፍታት በሁሉም ክልሎች ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል፤ በርካታ የእርምት እርምጃዎችም ተወስደዋል፤ ኢህአዴግ በአጠቃላይ በ50ሺህ አባላቱ ላይ እርምጃ ወስዶአል፡፡
ለችግሩም መንስኤ በመሆን ድርጅቱንና ሕዝቡን መንግስትንና ሕዝቡን ጥላቻና አለመተማመን ውስጥ እንዲገባ ያደረጉት በየደረጃው ስልጣን ጨብጠው፤ ነገር ግን ለግላቸው ክብረት ሲሰሩ የነበሩ የራሱ አባላት መሆናቸውን አረጋግጦ ነው እርምጃ የወሰደው፡፡ ለአንድ ፖለቲካ ድርጅት፣ የድርጅቱ አባላት ታማኝነት፣ የመስመር ጥራት፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነት፤ ከሙስናና ከኪራይ ሰብሳቢነት መንጻት ከአድርባይነት መላቀቅ ወሳኝ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በሁሉም መስክ የተጀመረው የተሀድሶ ንቅናቄ መሰረታዊ ለውጥ ከማምጣትም ባሻገር ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋቱን የበለጠ ያስጠብቃል፡፡
በፖለቲካ ፓርቲዎችና በገዢው ፓርቲ በኩል እየተካሄደ ያለው ውይይትና ድርድር የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነው ልዩነትን ጠብቆ በሚያግባቡ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን በመፍጠር ለመስራት የሚያስችላቸው ደረጃ ላይ እንደሚደርሱ እምነት አለ፡፡ ውይይቱና ድርድሩ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጅ ውጤትን የሚያስጨብጥ የተጀመረው ዲሞክራሲዊ የውይይትና የድርድር ባህል እንዲያድግ እንዲጎለብት ለማድረግ ያስችላል፡፡
የሲቪል ማሕበራት በሀገራዊ ጉዳዮች ውስጥ ሰፊ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ በንቃት ሊሳተፉ ይገባል፡፡ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በሚያደርጉት ውይይት በታዛቢነት ወይንም በሙሉ ተሳትፎ ቢያደርጉ ሀሳብ በማፍለቅና በማመንጨት በማወያየትም ረገድ የተሻለ ለውጥና ውጤት ለማስመዝገብ ያግዛሉ፡፡ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ውስጥ የላቀ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ይሄንን በአግባቡ ወደስራ መለወጥ በፍጥነት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማስቻል ተገቢም ትክክልም ነው፡፡ ይህ ሲሆን ነው ፈርጀ ብዙው ሰላምና መረጋጋት በተሟላ መልኩ እውን የሚሆነው።