በእርግጥም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የብሔራዊ ኩራት ምንጭ፤ የኢትዮጵያዊ ማንነት መገለጫ አርማ መሆኑን እያየን ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ የተጀመረበትን 6ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እየተካሄዱ የሚገኙ ዝግጅቶችም እያረጋገጡ የሚገኙት ይህንኑ ነው። በሚሊኔም አዳራሽ በተካሄደው የችቦ መለኮስ ስነ- ስርዓት ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባሰሙት ንግግር ግድቡ በግዙፍነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ከመሆኑም ባሻገር የኢትዮጵያውያን ብሄራዊ ኩራት ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ በ6ኛው ዓመት የግንባታ ሂደት በዐል አከባበር ስነስርአቶች ላይ እየታየ የሚገኘው ንቅናቄ ለሕዝባዊ ተሳትፎው አዲስ መሰረት የጣለና በአኩሪነቱ ወደር የማይገኝለት ሲሆን፤ ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን የበለጠ እያጠናከረ መሆኑም ሌላኛው መገለጫ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብሄር፣ ኃይማኖት፣ ጾታ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ሳይገድቡት ለፕሮጀክቱ መጠናቀቅ እያደረገ ያለው ጥረት አለምን እያስደመመ ነው።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለችግር የማይንበረከክ፤ የጠላትን አንገት የሚያስደፋ፤ ኢትዮጵያዊ ጀግንነትንና ማንነትንም የተላበሰ ለሀገሪቱ ህዝቦች የህልውናቸው ጉዳይ ሆኗል፡፡ የግድቡ ግንባታ መበሰር አንድነትን ለማብሰር ከመርዳቱም በላይ የኢትዮጵያዊያንን ልብና አዕምሮ በመግዛት ከአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት እያጠናከረልን ነው።
በእርግጥም ግድቡ ከዓድዋ ድል ጀግንነት ምንጭ የተቀዳ የኢትዮጵያንን ታላቅነት የሚያውጅ ፕሮጀክት ነው፡፡ በአድዋ በዓል ላይ ይፋ የተደረገው ችቦ ፕሮጀክቱ እስኪያልቅ ቀድሞ ከሚዘዋወረው የህዳሴ ዋንጫ ጎን ለጎን በመላው አገሪቱ እየዞረ መሆኑም የዚሁ ማረጋገጫ ነው፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ችቦ በሁሉም ክልሎች ለአንድ ዓመት የሚዞር ሲሆን አቶ ድሪባ ኩማ በመዲናዋ ለአንድ ወር የሚቆየውን ችቦ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ በሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዶ በነበረው ስነስርአት ላይ ተቀብለዋል፡፡ ይህም የህዳሴው ችቦ ለህዳሴው ትውልድ የአሸናፊነት ምልክት የመሆኑ ማረጋገጫ ነው፡፡
በክልል ከተሞችም እየተካሄደ ያለው በተመሳሳይ ነው። ለበዓሉ ከተዘጋጁት ፕሮግራሞች መካከል በባህርዳር ከተማ የተካሄደው “የአባይ ዘመን አገር አቀፍ ታላቅ ሙዚቃዊ ድራማ” ይጠቀሳል፡፡ በተጨማሪም ከመጋቢት 20-23/2009 ዓ.ም. በብሔራዊ ሙዚየም የስዕልና ፎቶግራፍ አውደ ርዕይ የሚካሄድ ሲሆን፤ መጋቢት 15 የሚደረገው “የሊቀ ናይል” የጥያቄና መልስ ውድድርም ከዝግጅቶቹ አንዱ ነው፡፡
ዝግጅቶቹ ተጨማሪ የገቢ ማሰባሰቢያ ዕድሎችን ከመፍጠር ባሻገር ብሔራዊ መግባባትን ይበልጥ ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው። ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደው የህዳሴው ግድብ ዋንጫ የእግርኳስ ጨዋታ በተለይ ሰፊ መነቃቃትን ፈጥሮ አልፏል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአማራ ክልል ብቻ 1 ቢሊዮን 25 ሚሊዮን 885 ሺህ 224 ብር ቦንድ ግዥ ተፈጽሟል። የመንግስት ሰራተኛው 462 ነጥብ 9 ሚሊዮን፣ ባለሃብቱና የንግዱ ማህበረሰብ 85 ነጥብ 1 ሚሊዮን፣የክልሉ አርሶ አደር 211 ነጥብ 9 ሚሊዮን እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ 258 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ማካሄዳቸዉን የክልሉ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል፡፡
መረጃው አያይዞ እንደገለጸውም በልገሳ መልክ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተገኘ ሲሆን፤የክልሉ አርሶ አደርም ታላቁን የህዳሴ ግድብ ከደለል ለመከላከል የሚያስችልና 18 ቢሊዮን ብር የሚገመት የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራ አከናውኗል፡፡ በዚህ ዓመት በዓሉን ለማክብር ከየካቲት 20 እስከ 29/2009 ዓ.ም በተካሄደው የቦንድ ግዥ ሳምንት 16 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ እንደተፈጸመ የሚገልጸው ይሄው መረጃ በዓሉን መጋቢት 24/2009 በልዩ ልዩ ሁነቶች በድምቀት ለማከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ያመለክታል፡፡
በደቡብ ህዝቦች ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 6ኛ አመት በተለያዩ መርሀ ግብሮች ሲሆን፤ ግድቡ ከፍተኛ የሆነ ብሔራዊ መግባባት የፈጠረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወጣቱ ነገ ሀገር ለመረከብ ዛሬ ሀገር መገንባት ግድ ይለዋልና የወጣቱን ምክንያታዊ ስብዕና ለመገንባት በማሰብ በአሉ በፖናል ውይይት፣ በጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር፣ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የጥያቄና መልስ ውድድር በመከበር ላይ ነው፡፡
በደቡብ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ሲጣል 1.2 ቢሊየን ብር በአምስት ዓመት ዉስጥ ለመሰብሰብ ባስቀመጠው ዕቅድ መሠረት እስካሁን ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ አሰባስቧል፡፡ የዘንድሮው በዓል ቀደም ሲል ለመሳተፍ ዕድል ያላገኙትን ሁሉ ተሳታፊ ያደረገ ስለመሆኑም በመረጃዎቹ ተመልክቷል፡፡ ዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2ዐዐ9 ከ85ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀዋሣ ዓለም አቀፍ ስቴዲየም በመገኘት በዓሉን በድምቀት አክብረዋል፤ ከነዚህ ውስጥም ከ6ዐሺ በላይ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው፡፡
መጋቢት 24 ቀን 2ዐዐ9 በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ ስድስተኛው ዓመት ክልል አቀፍ በዓል ይከበራል፡፡ ባለሃብቶችም የተለመደውን ተሳትፏቸውን እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል። ሰሞኑን እንኳ ከ450ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፤ በተጨማሪም፣ ከ579ሺህ 500 ብር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ቁሳቁሶች (ማቀዝቀዣዎች፣ የቡና ማፍያዎች፣ የአቧራ ማጽጃ ቁሳቁሶች፣ የልብስ ማጠቢያዎችና ምድጃዎች)ን ለማበርከትም ቃል ገብተዋል፡፡ ይህ የቁሳቁስ ድጋፍ በቅርቡ ለሚጀምረው የቶምቦላ ሎቶሪ ሽልማት የሚውል ነው፡፡
ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የተገኘውን ገቢ ስንመልለት፤ ቀደም ሲል 10 ሚሊየን ብር ከሚያስገኘው የሎቶሪ ሽያጭ ከ64 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ፣ ከ8100ኤ፣ የህዳሴ ሎተሪ፣ ከዳያስፖራው የገንዘብ ድጋፍ እና ከቦንድ ሽያጭ ሳምንት 9 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ተገኝቷል፡፡ ከላይ በተመለከተው አግባብ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ባለሃብቶች ቀደም ሲል የቦንድ ግዢና የገንዘብ ስጦታ በማበርከት የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ የቆዩ ቢሆንም ከአርሷደሩና የመንግስት ሰራተኛው አንጻር ሲሰላ ግን ግና እታች ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ በየክልሉ መነቃቃት መፍጠሩ እየተነገረለት የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ነው።
በየዓመቱ በተለያዩ ክልሎች የሚዞረው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ገቢ ከማሰባሰብ በተጓዳኝ መነቃቃትን በመፍጠር የህዝቡን ልማታዊ ተሳትፎ እያሳደገ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ እንደ አንድ የልማት ሞተር እየተቆጠረ ይገኛል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖችና ከተሞች በመዘዋወር ገቢ ሲያስገኝ የነበረውን ዋንጫ ዛሬ በሀረሪ ክልል በተከበረው 11ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ዋንጫው በኦሮሚያ ክልል በነበረው የአንድ ዓመት ቆይታ የክልሉ ህዝብና መንግስት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ እንደ ትልቅ መሳሪያ በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ ገቢ ማሰባሰብ ተችሏል፡፡ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ከተማዎች በማዘዋወር ለግንባታው ድጋፍ ለማሰባሰብ በተደረገው ጥረት ብቻ 607 ሚሊዮን 347ሺ 813 ብር ተገኝቷል። የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዥና በስጦታ በአጠቃላይ 1 ቢሊዮን 671 ሚሊዮን 188ሺ 241 ብር ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስም የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም የክልሉ ህዝብ ለ6ኛ ጊዜ ቃሉን አድሷል፡፡
ዋንጫውን የተረከበው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የክልሉን ህዝብ በማስተባበር የተሻለ ገቢ ለማሰባሰብ እንደሚንቀሳቀስ አመልክቷል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ ዋንጫው ወደ ክልሉ መምጣቱ ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ማስገንዘባቸውም ከ6ኛው አመት ዝክረ በአል ጋር ተያይዘው ከወጡት ዜናዎች መካከል ሰፊ ሽፋን ያገኘ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን ያለምንም ብድርና እርዳታ በይቻላል መንፈስ ለዘመናት በአይደፈሬነት የቆየውን የአባይን ወንዝ በፍትሃዊነት ለመጠቀም የበኩላቸውን ያልተቋረጠ ድጋፍ በማድረግ አንድነታቸውን በተግባር ማረጋገጣቸውን የሚያሳይ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በራስ አቅም እየተገነባ ለሚገኘው ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአቅሙን ያህል ድጋፍ በማድረግ ግንባታው በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እንዲጠናቀቅ ያለውን ጉጉትና ቁጭት የሚያሳይ እንቅስቃሴና ተሳትፎ ነው።
በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አገሪቱ የተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ቢገጥሟትም ህዝቡ ችግሮቹን በመቋቋምና በመከላከል ለግድቡ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ አለሟቋረጡ ይህንኑ ቁጭት እና የተጠናከረ ተሳትፎ ያሳያል፡፡
ከላይ በተመለከተው አግባብ በክልሎች የታየው ርብርብ ግድቡ የፈጠረው የህዝብ የዲሞክራሲያዊ አንድነት ተጨባጭ መገለጫ ሲሆን ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ በመያያዝ ግዙፍ ልማቶችን ዕውን ለማድረግ ትግላቸውን ማጠናከራቸውን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ይህ ልማታዊ ርብርብ ህዝቦች በድህትና ኋላቀርነት ላይ አንፀባራቂ ድሎችን በመጎናፀፍ የምግብ ዋስትናን እንዲያረጋግጡ የሚያስችል ነው፡፡ ህገ መንግስታዊ የፌዴራል ሥርዓቱ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለአገራቸው ልማትና ዕድገት በንቃት የሚሳተፉበትን ዕድል መፍጠሩም በተመሳሳይ ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት 6ኛ ዓመት በመጪው መጋቢት 24፣ 2009 ዓ.ም “ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን የሀገራችን ሕብረ-ዜማ፤ የሕዳሴያችን ማማ” በሚል መሪ ቃል የመከበር መሆኑ ታውቋል ፡፡