ዜጎች የአደጋ ተጽዕኖን የመከላከል የሞራል ላፊነት አለባቸው

የአንድ አገር የኢኮኖሚ አቅም በዜጎች እጅ ባለው ሃብት ልክ ነው የሚለካው። የአገር ሃብት በዜጎች እጅ ያለ ሃብት ነው። የደሃ አገር ዜጎች ድሆች ናቸው። በድሃ አገራት ሃብታም ሊባሉ የሚችሉ ቢኖሩም በንጽጽር እንጂ ከፍተኛ ሃብት ያላቸው አይደሉም። በሌላ በኩል የባለፀጋ አገራት ዜጎች ሃብታሞች ናቸው። እርግጥ በተዛባ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት 1 በመቶ ዜጎች 99 በመቶ የአገር ሃብትን የያዙበትና የአገር ሃብት የዜጎችን ሃብታምነት የማያሳይበት ሁኔታ አለ። ያም ሆነ ይህ፣ የዚህ ጸሁፍ ዓላማ የአገራትን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ መተንተን ባለመሆኑ ወደዋናው ጉዳይ ልግባ። የዚህ ጽሁፍ ትኩረት፣ ኢትዮጵያ ባለፉ አምስት ዓመታት የተከሰቱ የድርቅ ተጽዕኖዎችን በአመዛኙ በራስ አቅም መከላከል የምትችልበት የኢኮኖሚ አቅም ላይ መድረሷን መነሻ በማድረግ፣ ይህ አቅም በዜጎቿም ላይ መንፀባረቁን ማሳየት ነው።

ከሁለት ተኩል አሥርት ዓመታት በፊት አገሪቱ በተደጋጋሚ ቢያንስ በየአሥር ዓመት ልዩነት በድርቅ ስትመታ መኖሯ ይታወቃል። ይህ ሁኔታ ከ25 ዓመታትም ወዲህ እንደቀጠለ ነው። ልዩነቱ ቀደም ሲል የነበረው ድርቅ ወደቸነፈርነት ተቀይሮ ለሰው ህይወት መጥፋትና ከመኖሪያ ቀዬ ለመፈናቀል ምክንያት ይሆናል። ከሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ ቀደም ሲል ከነበረው በባሰ ድግግሞሽ በአማካይ በየአምስት ዓመት ልዩነት ድርቅ ቢከሰትም ይህ ድርቅ ወደቸነፈርነት አልተለወጠም፤ የሰው ህይወት አልጠፋም፣ ሰዎች ለስደት አልተዳረጉም። የድርቁ ተጽዕኖ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት መንግሥት ሁኔታውን ይፋ በማውጣት ለጋሾች እርዳታ እንዲያቀርቡ የተቀናጀ ተግባር አከናውኗል። መንግሥት በድርቅ ተጽዕኖ ሥር ለወደቁ ዜጎች በራሱ አቅም እርዳታ ማቅረብ የጀመረው በተለይ በ2003 ዓ.ም የተከሰተውን የድርቅ ተጽዕኖ በመከላከል ነው።

በዚህ ወቅት የተከሰተውና የአገሪቱን ደቡባዊ ምሥራቅና ምሥራቃዊ ቆላማ አካባቢዎችን የመታው ድርቅ አስከፊ ነበር። መንግሥት ይህን አስከፊ ድርቅ ለመከላከል ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የእርዳታ ጥያቄ አቅርቦ፣ እርዳታው እስኪደርስ ከራስ የመጠባበቂያ የእህል ክምችት እርዳታ የቀረበበት ሁኔታ ነበር።

በ2007 ዓ.ም የበልግና ክረምት ዝናብ እጥረት ምክንያት የተከሰተውና ከ10 ሚሊዬን በላይ ዜጎችን ለምግብ እጥረት ችግር ያጋለጠውን አስከፊ ድርቅ በመከላከል ረገድ  የመንግሥት ሚና ከዚያ ቀደም ከነበሩት ሁሉ የላቀ ነበር። ድርቁ የምግብ እጥረት ተጽዕኖ ማሳደር በጀመረበት ወቅት አገሪቱ ከ450 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጠባበቂያ የምግብ ሰብል ክምችት ነበራት። ድርቁ እንደተከሰተ መንግሥት የተጽዕኖውን መጠን ከተባበሩት መንግሥታትና ሌሎች ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመሆን የመለየት ሥራ አከናወነ። የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ከተለዩ በኋላ፣ የለጋሾች እርዳታ ሳይጠበቅ ከአገር ውስጥ ክምችት እርዳታ ማቅረብ የጀመረበት ሁኔታ ነበር። በኋላም መንግሥት ከ16 ቢሊዬን ብር በላይ በጀት በመመደብና ከውጭ አገር እህል በመግዛት ጭምር እርዳታ አቅርቧል። በአጠቃላይ በ2007/2008 የድርቅን ተጽዕኖ በመከላከል ረገድ መንግሥት ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ ነበር።

የአምናውን የድርቅ ተጽዕኖ ለመከላከል ከፌዴራል መንግሥት ባሻገር ድርቁ ያጋጠማቸው ክልላዊ መንግሥታትም ተጽዕኖውን ለመከላከል በጀት መድበው ነበር። የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት 684 ሚሊዬን ብር፣ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት 200 ሚሊዬን ብር፣ የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት 130 ሚሊዬን ብር፣ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት 78 ነጥብ 2 ሚሊዬን ብር፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት 52 ሚሊዬን ብር፣ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት 26 ሚሊዬን ብር በጀት ነበር የመደቡት።

ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት በተጨማሪ የህዝብ ለህዝብ ድጋፍም ሲደረግ እንደነበር ይታወሳል። በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ከኅብረተሰቡ 34 ነጥብ 1 ሚሊዬን ብር እንዲሁም ከክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ሠራተኞች ከደመወዛቸው በማዋጣት 96 ሺህ ብር ድጋፍ  ቀርቧል። በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) 30 ሚሊዬን ብር እርዳታ ሰጥቷል። በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ከኅብረተሰብ ለኅብረተሰብ እርዳታ 3 ነጥብ 2 ሚሊዬን ብር ድጋፍ ተገኝቷል። የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት 17 ነጥብ 6 ሚሊዬን ብር ከህዝብ ድጋፍ አሰባሰቧል። በኢትዮጵያ ሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ነጋዴዎች 20 ሚሊዬን፣ የክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ከደመወዛቸው 11 ሚሊዬን፣ የክልሉ ልዩ የፖሊስ ኃይል 2 ነጥብ 5 ሚሊዬን ብር እንዲሁም ከኅብረተሰቡ የተውጣጡ 30 ሺህ ከብቶች ለእርዳታ ተሰባስቦ ነበር። በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ባለሃብቶች የውኃና የእንስሳት መኖ ድጋፍ አድርገዋል።

የዘንድሮውን ድርቅ በመከላከል ረገድም መንግሥት የአንበሣውን ድርሻ እንደሚይዝ ይጠበቃል። ባለፈውም ዓመት ድርቅ ካጋጠማቸው አንዳንድ ኪስ አካባቢዎች በስተቀር የዘንድሮውን የድርቅ ተጽዕኖ ለመከላከል እየተደረገ ባለው ድጋፍ ላይ መንግሥት ቀዳሚውን ድርሻ ይዟል። መንግሥት ለዚሁ የእርዳታ አቅርቦት እስካሁን አንድ ቢሊዬን ዶላር መድቧል። ድርቁ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ክልሎች መንግሥታትም እንዲሁ በጀት መድበው እርዳታ እያቀረቡ ይገኛሉ።

እንግዲህ ቀደም ሲል ከነበሩት ድርቆች በተለየ መንግሥት (የፌደራል መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት) በጀት መድበው የድርቁን ተጽዕኖ በመከላከል እንቅስቃሴ ውስጥ የአንበሣውን ድርሻ መያዝ የቻሉት ባለፉት አንድ ተኩል አሥርት ዓመታት በአገሪቱ በተመዘገበው ተከታታይ እድገት ምክንያት ነው። ይህ የኢኮኖሚ እድገት በህዝቡ የገቢ አቅም ማደግ የተገለፀ ቢሆንም፣ የመንግሥት ገቢም የዚያኑ ያህል አድጓል። በዚህ ምክንያት መንግሥት የድርቅ ተጽዕኖ ለመከላከል በጀት መመደብ ችሏል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ድርቅና የውጭ እርዳታ የማይነጣጠሉ ነበሩ። አሁን ግን ድርቅና የውጭ እርዳታ እየተነጣጠሉ ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ድርቅ የምግብ እጥረት ተጽዕኖ የማያስከትልበት ደረጃ ላይ ሊደረስ መቻሉ ሳይዘነጋ የውጭ እርዳታ የሚባለው ነገር ሙሉ በሙሉ ሊቆም እንደሚችል አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያመለከታል።

የዘንድሮውን ድርቅ ተጽዕኖ ለመከላከል በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ከሚደረገው ድጋፍ ጎን ለጎን የህዝብ የእርስ በርስ እርዳታም እየተከናወነ ይገኛል። ከሁለት ሣምንት ወዲህ የተደረጉትን የእርስ በርስ እርዳታ እንኳን ብንመለከት፤ የአማራ ክልል በኦሮሚያ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች አምስት ሺህ ኩንታል እህልና የድርቁ ተጽዕኖ እስኪያበቃ የሚያገለግሉ ሁለት የውኃ ማመላለሻ መኪናዎች ሰጥቷል። በተመሳሳይ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በኦሮሚያ በድርቅ ለተጠቁ አርብቶ አደሮች 15 የጭነት መኪና የእንስሳት መኖ ሰጥቷል። ከዚያው ከኦሮሚያ  የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ህዝበ ሁለት ሺህ ኩንታል እህል ሲረዳ፣ የአዳማ ከተማ ባለሃብቶች 11 ሚሊዬን ብር ድጋፍ አድርገዋል። የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሠራተኞች ደግሞ የ1 ነብ 2 ሚሊዬን ብር ድጋፍ አድርገዋል። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነጋዴዎች እርዳታ ለመስጠት በዝግጅት ላይ የገኛሉ።

ከዚህ ቀደም በደረሱ ድርቆች የህዝብ ለህዝብ እርዳታ የነበረ መሆኑ ባይካድም እጅግ ውስንና በአሮጌ ልብስና የቤት ቁሳቁሰ እርዳታ የተገደበ ነበር። የባለሃብቶች ቁጥርና የሃብት አቅምም ውስን ነበር። አሁን ግን የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ያደረጉ በተለያየ ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች (አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች) ሃብት ማፍራት ስለቻሉ የእርዳታ እጃቸው ሰፍቷል። በጽሁፌ መግቢያ ላይ የአንድ አገር ሃብት በዜጎቿ እጅ ያለ ሃብት ነው የሚለውን ያነሳሁት ይህን ለማመልከት ነው።

የኢትዮጵያ ባለሃብቶቸ በድርቅ ተጽዕኖ ሥር ለወደቁ ዜጎች ማድረግ የጀመሩት እርዳታ የሚበረታታ ቢሆንም፣ አሁንም ካሉት የባለሃብቶች ቁጥር አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በየትኛውም አገር በተለይ በበለፀጉ አገራት በመደበኛ ኑሮ ራሳቸውን ያልቻሉ ዜጎችን መርዳት እንዲሁም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚሻ አደጋ ሲከሰት በእርዳታ አሰጣጥ ላይ ትልቅ ድርሻ የሚኖራቸው በባለሃብቶች የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ናቸው። የአውሮፓና የአሜሪካ ባለሃብቶችን የሂሳብ መዝገብ ብትመለከቱ ለበጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ የማያደርግ አታገኙም። ባለሃብቶችና ትላልቅ ኩባንያዎች ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ፣ በህግ ከተጣለባቸው የግብር ግዴታ ለይተው አያዩትም። በበለፀጉት አገራት ባለሃብቶች ዘንድ፣ በግብርና በልገሣ መካከል ያለው ልዩነት ግብር በህግ የተጣለ ግዴታ ሲሆን ልገሳ ደግሞ የሞራል ግዴታ መሆኑ ነው።

ይህ በኢትዮጵያም መለመድ ይኖርበታል። በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚያስፈልግበት አደጋ ሲያጋጥም፣ ዜጎች በተለይ ባለሃብቶች አሁን እያደረጉት ያለውን ድጋፍ የበለጠ በተጠናከረና በተደራጀ መልክ ማከናወን የሚችሉበት ሥርዓት ሊኖር ይገባል። የኢትዮጵያ ባለሃብቶች አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን በመለገስ እርዳታ የማቅረብ አቅማቸውን በማጎልበት በአደጋ ጊዜ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው የአደጋ ተጽዕኖን የሚከላከሉ አገር በቀል የእርዳታ ተቋማት እንዲኖሩ የማድረግ የሞራል ኃላፊነት አለባቸው። የአደጋ ተጽዕኖን መከላከል የዜጎች የሞራል ኃላፊነት ነውና።