ሀገራዊ ዲፕሎማሲያችን ተግቷል፤ እየሰላ ነው ማለትም ይቻላል፡፡ ግብጾች በሚደቅኑት የተለያየና ውስብስብ ሴራ ውስጥ መሰናክሉን እየዘለለ ማለፍ ችሎአል፡፡ ትግሉ አሁንም ገና በመሆኑ የኢትዮጵያ ምሁራን ከፖለቲካ ልዩነቶቻቸው ባሻገር፤ ለሀገርና ለወገናቸው ያላቸውን ተቆርቋሪነት ስለአባይ ወንዝና ግድብ በመጻፍ፣ ትንተና በመስጠት አለም እንዲያውቀው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፤ የውጭ ኃይሎችን ሴራ ማምከን የዜግነት ግዴታና ኃላፊነትም ነው፡፡
የግብጽ ምሁራን በዚህ ረገድ መንግስታቸውን ደገፉም አልደገፉ በአባይ ወንዝና ግድብ ዙሪያ ለሀገራቸው ቆመው ይፋለማሉ፤ ለብሔራዊ ጥቅማቸው ተግተው ይቆማሉ፡፡ የሀገራችን ምሁራን በሀገር ውስጥም ይሁኑ በዲያስፖራ ኢሕአዴግን ቢቃወሙም ኢህአዴግ የሰራውን ታላቅ ዘመን ተሻጋሪና ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ የታላቁን የሕዳሴ ግድብና ሌሎችንም ግዙፍ ስኬታማ ፕሮጀክቶች ሊያጣጥሉ ለውጭ ጠላቶችም መግቢያ በር ሊከፍቱ አይገባም፡፡
የጥንቱም ውድቀታችን ዋነኛ መነሻ እርስ በእርስ ተጠላለፎ መውደቅ በመሆኑ ከዚህ አዚም ለመውጣት አርቆ ማሰብን ግድ ይላል፡፡ ዘመንና ትውልድ ቢፈራረቅም ጸንታ ታፍራና ተከብራ መኖር ስላለባት ሀገር በጥልቀት ማሰብ ስለሀገራቸውና ስለሕዝባቸው ሲሉ ጸንተው መቆምና መከራከር ይገባቸዋል፡፡
እንደ ግብጾቹ ምሁራን ሁሉ የእኛዎቹም ከፖለቲካ ልዩነት ባሻገር ለሀገራቸው ጥብቅና የመቆም፣ የመከራከርና የማስረዳት የዜግነት ግዴታ አለባቸው፡፡ ሐምሌ 16 2014 (እኤአ) የግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ግጭትን ማስወገድና በጥቅሞችዋ ላይ ጉዳትን መቀነስ ትፈልጋለች ሲሉ መናገራቸውን አል አህራም ጋዜጣ ዘግቦአል፡፡ ግብጽ የግድቡን ግንባታ ማስቆም እንደማትችል ገልጸዋል፡፡ ይህን አባባል አስመልክቶ ግብጻዊው ጸሀፊ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በአጠቃላይም የመንግስት አቋም ይህ መሆን አለበት ወይ? ሲል ተችቷል፡፡
የኢትዮጵያው የመስኖ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ከካርቱምም ሆነ ከካይሮ ጋር ግድቡን በውሀ መሙላትን በተመለከተ ስምምነት ላይ አልደረሰችም፤ ግድቡን በውሀ የመሙላት ጉዳይ ከድርድሩ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፤ በተያዘለት የግዜ ሰሌዳ ይከናወናል። ሲሉ መናገራቸውን በአል አህራም የወጣው ጽኁፍ በቁጭት ገልጾአል፡፡
ግብጾች የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አላማ እድገትና ልማት ሳይሆን በአካባቢው ተጽእኖ ለመፍጠር ነው ይላሉ፡፡ በአብዛኛው ከግድቡ የሚገኘው ኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ውስጥ ፍጆታ አይውልም፤ የግድቡ ትክክለኛ አላማ ውኃን መልሶ ማከፋፈልና በአካባቢው ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪና ጫና አሳዳሪ የመሆን ፍላጎት ነው ይላሉ፡፡ ጥረትና ልፋቱ ከኢትዮጵያም ከናይል ሀገሮችም በላይ የገዘፈና ትልቅ ነው ሲሉ አል አህራም ላይ የጻፉት የቀድሞው የግብጽ የውኃ ኃብትና መስኖ ሚኒስትር የነበሩት ናቸው፡፡ (Wednesday, 15 March 2017)
ሰኔ 1 2016 የወጣው አል አህራም ሳምንታዊ ጋዜጣ የኢትዮጵያን ግድብ አለመቀበል ትርጉም የለውም ሲሉ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ከግብጹ ኢል ሀያት ቴሌቪዝን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መግለጻቸውንም አስፍሮአል፡፡ ግብጽ ግድቡን በተመለከተ ጥርጣሬንና የተጋነነ አደጋን መሰረት አድርጋ አትሰራም፤ ይህንን ከኢትዮጵያና ከሱዳን አቻዎቻችን ጋር እንዴት ማድረግ እንዳለብን እየተነጋገርንበት ነው ማለታቸውን ጋዜጣው ይገልጻል፡፡
በሰኔ 2013 የቀድሞው የግብጽ ፕሬዚደንት የነበሩት ሞሀመድ ሙርሲ ግድቡን አስመልክተው ንግግር ሲያደርጉ ቀውሱን ለመፍታት ምርጥ አማራጭ የሆነው ውይይት ነው፤ ቢሆንም ግብጽ ከማንኛውም አይነት ምናልባታዊ አደጋ የራስዋን ደህንነት ለመከላከል ኮሚቴ ሰይማለች በማለት ገልጸው ነበር፡፡
ባለፈው አመት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ከአል ሻራክ አል አውሳት ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ግድቡ እውን ሆኖአል፤ ምንም ሆነ ምን የሚለወጥ ነገር የለም ካሉ በኋላ 50 በመቶ የሆነው የግድቡ ስራ መጠናቀቁን፤ አብዛኛው የግድቡ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ስራ ማለቁን፤ ተርባይኖቹ ሲተከሉ 70 በመቶ የሚሆነው ፕሮጀክት እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ እንዴት ይሄንን ያህል ርቀት ተራመደች በሚል ግብጾችን ትልቅ ብስጭት ውስጥ ከቶአቸው ነበር፡፡
መጋቢት 15 2017 የወጣው ሌላው የአል አህራም ጋዜጣ እትም አውዳሚው የኢትዮጵያ ግድብ በሚል ርእስ ናደር ኑረዲን የተባለን ጸሀፊ ጽሁፍ ይዞ ወጥቶአል፡፡ ግድቡ በግብጽና በሱዳን ላይ ከባድ አደጋ ያስከትላል በሚል አስፈሪና አስደንጋጭ በሙያተኞች የተደገፈ ነው የሚል ሐተታን አስነብቦአል፡፡ ግድቡ ቢፈነዳ የሱዳንና የግብጽን ከተሞችና ልማቶች ጠራርጎ ያጠፋቸዋል፤ ግድቡ ሆን ተብሎ ከሱዳን ጠረፍ ቅርብ በሆነ ቦታ እንዲሰራ የተደረገውም ታላቅ ፖለቲካዊ ሴራ ነው በማለትም ፀሀፊው ሀሳቡን ያብራራል፡፡ ጋዜጣው በናይል ወንዝ ዳርቻ ዙሪያ የሚኖረው የግብጽ ሕዝብ አደጋ ላይ ወድቆአል ሲልም ያብራራል፡፡ ግብጽ በአመት የምታገኘው የዝናብ መጠን 15 ሚሊ ሜትር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ የምንጠቀመው ከዝናብ ነው፡፡ ከመሬት ስር የምናገኘው 6 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ ከምንፈልገው ኮታ አንፃር ትንሽ ነው፡፡ ግዙፉ የግብጽ የውሀ ፍላጎት የሚገኘው ከናይል ሲሆን በየአመቱ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ እናገኛለን በማለትም ፀሀፊው ቁጭቱን አስፍሯል፡፡ ሆኖም ይላል ፀሀፊው፣ ሆኖም ግን ኢትዮጵያ የያዘቸውን ፕሮጀክት ገፍታበት ትልቅ ግድብ ወይንም የተለያዩ ግድቦችን በሱዳን ጠረፍ አካባቢ ከገነባች ይህ ሁኔታ ከስረ መሰረቱ ይለወጣል ሲል ይገልጻል፡፡
የአል አህራም ፀሀፊ በመቀጠልም ግብጽ የምትተማመንበት የናይል ውሀ ከሁለት ምንጭ ነው የሚገኘው ካለ በኋላ አንደኛውና በጣም ጠቃሚው ከኢትዮጵያ አምባ (ተረተር፤ ከፍተኛ መሬት) የሚፈሰው የአባይ ወንዝ ሲሆን ይህም ለግብጽ 85 በመቶ የውሀ ፍላጎትዋን ያሟላል፤ ሌላውና 65 በመቶ የሚሆነው ከብሉ ናይል የሚመጣ ሲሆን 20 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከአትባራ ወንዝ የሚገኝ ነው፡፡ ሁለተኛው የአፍሪካ ታላላቆቹ ሀይቆች አካባቢ ሲሆን እነዚህም 15 በመቶ የሚሆነውን የግብጽ የውሀ ፍላጎት ይሸፍናሉ ሲል አስተያየቱን አስፍሮአል፡፡
ጸሀፊው ሀሳቡን በማስፋት በ2009 የላይኛው የአባይ ተፋሰስ ሀገራት እኩል የውሀ ክፍፍል እንዲኖር መጠየቅ መጀመራቸውን፤ ይህም በቀጥታ ለመናገር ግብጽን ከአባይ ውሀ 5 በመቶ ብቻ እንድታገኝ የሚያደርጋት ነው ይላል፡፡
ግብጽ የውሀን ፍትሀዊ ክፍፍል በተመለከተ የምታቀርበው መከራከሪያና ታሪካዊ መብቶችዋ ቦታ አልተሰጣቸውም፡፡ ይህ በላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ውስጥ የታየው ድንገተኛ የሆነ የልብ (የአስተሳሰብ) ለውጥ በግብጽ ውስጥ ጥያቄና ጥርጣሬዎችን አስነሳ፡፡ እስራኤል፣ አሜሪካ፣ ቻይና ወይንም ሕንድ ከዚህ አዲስ ከተነሳው ጥያቄ ጀርባ ይኖራሉ የሚሉ ግምቶች በስፋት መነሳታቸውንም ይገልጻል፡፡
ይህ በአል አህራም ላይ የተነበበ ጽሁፍ ባለቤቶቹ የሀሳቡ አፍላቂዎች የስራውም መሪና መሀንዲሶች ግምበኛና አናጢዎች የግድቡ ግንባታ የገንዘብ ምንጮችም ኢትዮጵያና ልጆችዋ መሆናቸውን አምነው ለመቀበል መቸገራቸውን ያሳያል፡፡
ጋዜጣው የኢንቴቤው ስምምነት አለም አቀፍ ሕጉ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ አምባገነናዊ ውሳኔ እንዳይወስኑ የሚከላከለውን የጣሰ ነው ካለ በኋላ ስምምነቱ የአባይን ውሀ ውሳኔ ሰጪነት በተመለከተ የጨዋታውን ሕግ ቀየረው በማለትም የሁኔታዎችን በመሰረታዊነት መለዋወጥን ይገልፃል፡፡
የግብጹ አልአህራም ከአሁን በኋላ የውሀ ፕሮጀክቶች የሚጸድቁት በሚመለከታቸው አብዛኞቹ ሀገራት ድምጽ ብቻ ነው፡፡ እንደ ቀድሞው በሙሉ ድምጽ አይደለም፡፡ የኢንቴቤው ስምምነት ከተፈረመ ከጥቂት ወራት በኋላ የጥር 25 አብዮት በግብጽ ፈነዳ፡፡ ይህም ኢትዮጵያ የግብጽን ተቃውሞ ሳትፈራ በአባይ ወንዝ ውሀ ላይ ትልቅ ፕሮጀክት እንድትጀምር እድል ሰጣት ይላል፡፡
ኢትዮጵያ የራስዋ በሆነው መብት ማንንም አትፈራም፡፡ የማንንም ፈቃድ አትጠይቅም፡፡ ይልቁንም ግብጾች የአስዋንንና የናስር ግድብን ሲሰሩ ለኢትዮጵያ ማሳወቅ ይገባቸው ነበር፡፡
አል አህራም ጋዜጣ የኢትዮጵያው ሕዳሴ ግድብ ሲታቀድ 14 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ የሚይዝ ሐይቅ ለመፍጠር ነበር ይላል፡፡ በኋላም ሐይቁ የሚይዘው የውኃ መጠን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መሆኑን ይገልጻል፡፡ መጠኑን የመወሰን፣ የማስፋት፣ ሲያሻንም የመለጠጥ መብት የኢትዮጵያ እንጂ መቼም የግብጽ መሆን አይችልም፡፡
በአንድ ሉአላዊ ሀገር ልማትና የእድገት አጀንዳ ውስጥ ምን አስገባቸው? ለሚለው ጥያቄ ምንም አይነት መልስ አይኖራቸውም፡፡ መልሳቸው የአባይ ውሀ ይቀንስብናል ነው፡፡ የእነሱ ያረጀና ዘመን ተሻግሮት ያለፈው እምነት እኛ ብቻ በአባይ ውሀ እንጠቀም፤ ኢትዮጵያ በድህነትና በችግር ትኑር ብሎ የመፍረድ ያህል እጅግ ኋላቀርና የራስ ወዳድነት አመለካከት ያመጣው ችግር ነው፡፡ ግዜው ያለፈበት ኋላቀር አመለካከትም ነው፡፡
የግድቡን መጠን ደረጃ ስፋቱን ቁመቱን የመወሰን መብት የኢትዮጵያ እንጂ የግብጽ እንዳልሆነ፤ ሊሆንም እንደማይችል የተረዱም አይመስሉም፡፡ የአል አህራም ዝርዝሮች ብዙ ናቸው፡፡ ለሁሉም ግብጾች ከቆየና ጥንታዊ ቅዠታቸው ሊወጡ፣ የትም የማያደርስ ሴራቸውንም ሊያቆሙት ይገባል፡፡ መጠቀም የሚችሉት በሰላምና በመግባባት ብቻ ነው፡፡ ግድቡ በታቀደለት ግዜ የሚጠናቀቅ መሆኑንም ሊገነዘቡት የግድ ይላል፡፡