በ”ይቻላል” ተጀምሮ እየተቻለ፤ በአንድ ቋንቋም እያናገረን ያለ ፕሮጀክት

ሱዳን፣ በተለይም ግብፅ ህልውናቸው በዓባይ ወንዝ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ሲነገር ኖሯል፤ እውነትም ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት አገራት አብዛኛው የመሬት ክፍል በበረሃ የተሸፈነ ነው፡፡ 86 በመቶ ምንጩ ከኢትዮጵያ የሆነው ዓባይ ወንዝ ከአገሩ ሲወጣ/ድንበር ሲሻገር ‹‹ናይል/Nile›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ በተፋሰሱ አገሮች መካከል የፀብና የጥላቻ መንስዔ መሆን የጀመረው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ታሪክ ይናገራል።

ግብፅ የታላቁ የህዳሴ ግድብን ኢትዮጵያ እንዳትገነባ፣ ለጋሽ ድርጅቶች ዕርዳታ እንዳያደርጉ ከመወትወት፣ መለማመንና ማግባባት ባሻገር፤ ወታደራዊ ዕርምጃ ሁሉ ለመውሰድ ዝታ/አቅዳ እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ እኛም ምተናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ‹‹አፍሪካን ኢንተለጀንስ›› የተባለ ተቋም በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ እንዳመለከተው የግብፅ መንግሥትና ተቋማት ከእጅ አዙር ጥቃት ባሻገር የአፍሪካ አገሮችን በማስተባበር በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርጉ መንቀሳቀሳቸውን አረጋግጧል፡፡  ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መሠረት ከጣለችበት ቀን ጀምሮ የዓለም ባንክም ሆነ ሌሎች “ለጋሽ” የተባሉ ድርጅቶች ለግድቡ ድጋፍም ሆነ ዕርዳታ ላለመስጠት ያደረጉትን ጉትጎታና ውትወታ ማስታወታሱ ብቻ በቂ ነው። የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሠረት በተጣለበት እለት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ:-

ግድቡን ለመሥራት ብድርና ዕርዳታ እንዳናገኝ የተለያዩ ኃይሎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ምክንያት፣ የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን የሚተባበረን አገር ወይም ተቋም ማግኘት አልቻልንም፡፡ ስለሆነም ወጪውን ብቻችንን ለመሸፈን የምንገደድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዩሮ በላይ በመሆኑና ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች በራሳችን ወጪ ልንሸፍናቸው የሚገቡን በርካታ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው ወጪውን መሸፈን በእጅጉ እንደሚከብደን ጥርጥር የለውም፡፡ ሸክሙን ለማቃለል ያደረግነው ጥረት ስላልተሳካና ያለፉት 50 ዓመታት ታሪካችን እንደማይሳካ ያረጋገጡልን በመሆኑ የሚኖረን አማራጭ አንድም ግድቡን አለመሥራት፣ አለበለዚያ እንደምንም ወጪውን  በራሳችን መሸፈን ነው፡፡ ከእነዚህ ከባድ ሁለት አማራጮች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ የትኛው እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ በተለመደው ወኔው ምንም ያህል ደሃ ብንሆንም ድህነታችንን ለማስወገድ ማንኛውም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክቱ መሠራት አለበት እንደሚል ለአፍታም ያህል አልጠራጠርም።

ነበር ያሉት፡፡  

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ለመገንባት ሥራው ከተጀመረ እነሆ ድፍን ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ለአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ነው፡፡ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳይ፤ ከዚህ ውድድር ከተያዘበት የግሎባላይዜሽን ዘመን ጋር አብሮ አስተሳስሮ ለመሄድ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጅጉን ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ለዚህም የዓለም አገሮች እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማርካት ብዙ ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት ይህንን ክፍተት ለመሙላት በእንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህም ዋነኛው ማሳያ በአፍሪካ አንደኛ፣ በዓለም ደግሞ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል የሚባልለት የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው፡፡

ይህ በተፋሰሱ አገሮች መካከል ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳው ጉልህ የሆነው ወንዝ ኢትዮጵያንም ተጠቃሚ ያደርግ ዘንድ ሥራው ከተጀመረ እነሆ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. የግንባታው የመሠረት ድንጋይ የተጣለው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት የግንባታው 57 በመቶ ተጠናቋል፡፡

የግንባታው የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ዕለት ምክንያት በማድረግም በየዓመቱ መጋቢት 24 ቀን ግድቡ በሚገኝበት ሥፍራ ክብረ በዓል ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዓመቱ የተለያዩ መሪ ቃላት የሚወጡለት ይህ ክብረ-በዓል ዘንድሮም ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የአገራችን ኅብረ ዜማ፣ የህዳሴያችን ማማ›› በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 26 እስከ መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በተለያዩ ዝግጀቶች ሲከበር ቆይቷል፡፡

በተለይም የበአሉ ማጠናቀቂያ በሆነበት እለት ግድቡ ያለምንም እንቅፋት ተሠርቶ እስኪያልቅ ድረስና ካለቀ በኋላም ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን፣ ከውስጥ እስከ ውጭ በሦስት አደረጃጀቶች እየተጠበቀ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡

ይህ ግድብ አንዱ ሌላውን በማይጠልፍበትና በማይጎዳበት መርህ ላይ ተመሥርቶ እየተገነባ  ያለ ፕሮጀክት መሆኑም በተመሳሳይ፡፡ ወደፊትም በተፋሰስ ሃገራቱ መካከል የጂኦ-ፖለቲካዊ ትስስርን በመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ሌሎች አገሮች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ቢኖሩዋቸውም ይህ ግን በተምሳሌትነቱ ጎልቶ የሚታይ ግድብ መሆኑም በተለያዩ አስረጂዎች ተመልክቷል፡፡

ብዙዎች ይህ ግድብ ይቻላልመንፈስ የፈጠረ ነው ሲሉም ተደምመውበታል። በእርግጥም ግድቡ እንችላለን በማለት የምንችል መሆናችንን ለዓለም የምናሳይበት አንዱ መሣሪያ ነው፡፡ የህዳሴ ግድቡን ለመሥራት የሕዝቡ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውም ስለዚህ ነው፡፡

ተደጋግሞ እንደተገለፀው፤ ይህ ፕሮጀክት ትልቁ የኢትዮጵያ የልማት አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡ ሥጋት ያለባቸው አገሮች ከሥጋታቸው ነፃ እንዲሆኑ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ከማድረግ ባሻገር፣ ባሉን የመረጃ መረቦች እየተጠቀምን ግድቡ ፍትሀዊ መሆኑን ለዓለም እየገለጽን  የምንገኘውም ስለዚህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ወንድ፣ ሴት፣ ልጅ፣ አዋቂ፣ ተቃዋሚና ደጋፊ ሳይባል በሁሉም ተሳትፎ እየተገነባ ያለ ግድብ ነው፡፡   ይህ ግድብ የመላው ሕዝብ ግድብ ነው፡፡ ስለሆነም ነው ሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች “ግድብ የማንነታችን ትልቁ ማኅተም በመሆኑ ዕውን እስኪሆን ጥረታችን ይቀጥላል” በማለት ጉባ ላይ ተገኝተው የተናገሩት፡፡

ፕሬዚዳንት ሙላቱም ተሾመም፣

ግድቡ እዚህ ደረጃ የደረሰው ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው ድጋፍ በማድረጋቸው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለልማት ጉዞ የጀመርነው አቅጣጫ ነፀብራቅ በመሆኑ፣ ዛሬ በማገባደድ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ ፕሮጀክት በጋራ ተጠቃሚነትና በፍትሐዊነት መርህ ላይ ተመሥርቶ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት በመሆኑ የሁሉም የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጎለብትና የሚያዳብር፤ የሰላም ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል እምነታችን ነው

ማለታቸውም የዚሁ ነፀብራቅ ነው።

የህዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሲያጠናክሩም፣

ፕሮጀክቱ ከግብ እንዲደርስና ኢትዮጵያን የመገንባት፣ የማዘመን፣ የማልማትና ሕዝቡም ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማብቃትና ወደ ላቀ ከፍታ እንዲደርስ የቀየስነው የህዳሴ ጉዞ በመላው የአገራችን ሕዝቦች ልብ ውስጥ በቅቡልነት መጓዝ አለበት።

በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የህዳሴውን ትውልድ ቁርጠኝነት ያስተጋባ፤ በይቻላል መንፈስ በአንድ ቋንቋ ያነጋገረና ያግባባ፤ ለወዳጅና ለጎረቤት አገሮች አርቆ አስተዋይነታችንን ያስመሰከረ ነው፡፡ ይህ ብርቅዬና ድንቅዬ ፕሮጀክታችን በአራቱም ማዕዘናት የፈጠረው ሕዝባዊ ማዕበልና ርብርብ ከራሱ አልፎ ሌሎች በርካታ ሥራዎችንም መሥራት እንደሚቻል ያስመሰከረ ነው፡፡  

በአሁኑ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችና ኢንዱስትሪዎች እየተገነቡ ነው፡፡ በዚህም የኤሌክትሪክ ኃይሉ ፍላጎት እያደገ የመጣ ሲሆን፣ ይህን ፍላጎት ለማሟላት ይህ ግድብ ከፍተኛ ዋጋ አለው፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ዘመን በኤሌክትሪክ ኃይል አቅማችን መጀመሪያ ላይ ከነበረበት 4ሺ 250 ሜጋ ዋት ወደ 17ሺ ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዷል፡፡ አሁን ያለው የማመንጨት አቅምና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ጨምሮ በመገንባት ላይ ካሉት ፕሮጀክቶች ባሻገር በዕቅድ ዘመኑ ከ7ሺ ሜጋ ዋት በላይ ሊሰጡ የሚችሉ የኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ይጠበቅብናል፡፡ ስለሆነም የህዳስው ግድብ ወሳኝነት የትየለሌ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ በተጓዘባቸው ስድስት የግንባታ ዓመታት የግድቡ ሮለር ኮምፓክት ኮንክሪት (አርሲሲ) ግንባታው 70 በመቶ፣ የሳድል ግንባታ 57 በመቶ ተጠናቋል፡፡ በተጨማሪም፤ የኃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታ፣ የ500 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ፣ የ125 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መዳረሻ መንገዶችና ከግድቡ በታች 240 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይና የአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳ ግንባታዎች ተከናውነዋል፡፡

በተመሳሳይ የኤሌክትሮ-መካኒካልና የኃይድሮ-መካኒካል፣ የዲዛይን፣ የአቅርቦት፣ የተከላና የፍተሻ ሥራዎች በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካይነት በተፋጠነ ሁኔታ እየከናወነ መሆኑም ታይቷል፡፡ በተለይም ቀድመው ኃይል የሚያመነጩ ሁለት ዩኒቶች የተከላ ሥራቸው እየተገባደደ መሆኑም ተገልፃል፤ ይህ ፀሀፊም በቦታው ተገኝቶ በአይን-በብረቱ ተመልክቷል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገነባው የአባ ሳሙኤል ግድብ የተጀመረውን ስድስት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም፣ ከአንድ ማመንጫ ጣቢያ ብቻ 6ሺ 450 ሜጋ ዋት ያሳደገ ታላቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ግድብ ሲጠናቀቅም ከ6ሺ 450 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይልና በአማካይ 15ሺ 759 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በዓመት በማመንጨት ለአገር/አህገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በጥናቶች ተረጋግጧል፡፡

በሌላ በኩል፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ 1ሺ 874 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋትና 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያለው ሰው-ሠራሽ ሐይቅ ስለሚፈጥር፣ በአካባቢው በታንኳና በጀልባ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም ተጨማሪ የዓሳ ሀብት ልማት ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ የውኃ ኃይል ማመንጫውም ከካርቦንዳይ ኦክሳይድ ልቀት ነፃ በመሆኑ የአካባቢ ሥነ-ምኅዳርን በመጠበቅ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው፡፡ በግድቡ ግንባታ ሒደትም እስካሁን 10ሺ 958 ያህል ሠራተኞች የተሰማሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 353 (ሦስት በመቶ) ያህሉ የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ የዕውቀት፣ የአሠራር ልምድና ክሂሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስገኘት ረገድም ሚናው ጉልህ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡