እብሪትና መዘዙ

ባለፈው አመት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራን መንግስት በሰው ልጅ ላይ እየፈፀመ ባለው የከፋ ወንጀል ምክንያት ከከሰሰ ወዲህ ኤርትራ ሰፊ አለም አቀፋዊ ተቃውሞ እየገጠማት ይገኛል። የአቶ ኢሳያስ መንግስትም በአለም የተገለለ ብቸኛው መንግስት ተብሎ እንዲጠራም ግድ ብሏል። ከሰሞኑ በኤረትራ የተጣለውን ማእቀብ የሚመረምረው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ዳግም በኤርትራ ላይ የተጣለውን እቀባ እንደሚያጸና የሚጠበቅ ሲሆን፤ የአሜሪካ መንግስትም በኤርትራ ላይ አዲስ እቀባ መጣሉ ይታወሳል። የእብሪት መዘዙ ብዙ ነው፡፡

የኤርትራ መንግስት በሀገር ውስጥ በዜጎቹ  የሚፈጽመው ዘግናኝና የከፋ ድርጊት የቀጠለ ሲሆን የአፍሪካን ቀንድ የሁከትና የብጥብጥ ማእከል ለማድረግ ከሚንቀሳቀሱ አሸባሪ ኃይሎች ጋር ከፍተኛ ቁርኝትና ትስስር እንዳለው በተደረገው ማጣራት የመንግስታቱ ድርጅት በተጨባጭ ማስረጃዎች ደርሶበታል፡፡

ኤርትራውያን በመንግስታቸው በመማረር በየእለቱ ባገኙት አጋጣሚ ማንኛውንም ፈተናና መከራ የሕይወት መስዋእትነትም እየከፈሉ ሀገሪቱን ለቀው ይወጣሉ፡፡ እስከአሁን ባለው መረጃ 5000 ኤርትራውያን በየወሩ ሀገራቸውን ለቀው በመውጣት ወደ ኢትዮጵያና ወደ ሱዳን ይገባሉ፡፡ ይሰደዳሉ፡፡

ከዚህ ውጭ በሀገሪቱ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ረገጣና አፋኝነት በአለማችን ከየትኛውም ሀገር በከፋ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የግል ፕሬስ፤ ተቃዋሚ ፓርቲ ሲቪክ ማሕበራት የሚባል በኤርትራ ውስጥ የለም፡፡ የዜጎች እንቅስቃሴ በከፍተኛ የጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥርና እይታ ስር መሆኑን ሀገሪትዋን ለቀው የወጡት ሰዎች በስፋት አጋልጠዋል፡፡

የኤርትራ መንግስት እንደ መንግሰት የሚያቆመው ቁመና የለውም፡፡ ከአንዳንድ የአረብ ሀገራት ጋር በፈጠረው ወዳጅነት በሚያገኘው ገንዘብ እየተውተረተረ የሚገኝ መሆኑን መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡ የአሰብን ወደብ ለአረብ መንግስታት በሊዝ በመሸጥ የተውጣጣ  ወታደራዊ ኃይል እንዲሰፍርበት አድርጎአል፡፡ በዚህም ብዙ እንዳገኘበት ይታወቃል፡፡ በየመን የውስጥ ጉዳይ ቀጥተኛ ጣልቃ በመግባት የጦርነቱ ተሳታፊ ሆኖአል፡፡

ከኢትዮጵያ ከየመን ከጀቡቲ ጋር በተለያየ ግዜ ጦርነት ከፍቶ በውርደት ተመልሶአል፡፡ ከአቅሙ በላይ የሚንጠራራ አሸባሪዎችን በማሰማራትና ወዳጅነት ፈጥሮ ከኃላ በመሆን የተለያዩ ጥቃቶችን በጎረቤት ሀገራት ላይ እንዲፈጸም የሚያደርግ ወንጀለኞችን የሚየሰማራ ለቀጠናው ሰላም አደገኛ መንግስት መሆኑን የመንግስታቱ ድርጅትና የአሜሪካን መንግስት በማስረጃ ያረጋገጡት እውነት ነው፡፡አምና የተጣለበት እቀባ ዘንድሮም ሙሉ በሙሉ እንደሚቀጥል ግልጽ  ነው፡፡

ከሰሞኑ ኤኤፍፒ ባሰራጨው ዘገባ መሰረት ኤርትራ የተጣለባትን ማእቀብ በስውር በመጣስ ከሰሜንኮርያ መንግስት ጋር ምስጢራዊ ውል በማድረግ ወታደራዊ የመገናኛ መሳሪያዎችን በአውሮፕላን ከሰሜን ኮርያ በመነሳት ቻይናን በማቋረጥ ልታስገባ ስትል የደረሰበት የአሜሪካን መንግስት በባሕር ኃይልዋ ላይ ከሰሞኑ እቀባ ጥሎአል፡፡ ኤርትራ በተሳሳተ መረጃ ማእቀብ ተጥሎብኛል ስትል ነቀፌታ ሰንዝራለች፡፡ የሚሰማት አልተገኘም፡፡

ኤርትራ ከሰሜን ኮርያ ወታደራዊ መሳሪያዎች ለመግዛት ጥረት የማድረግዋ ምስጢር የተደረሰበት መሆኑ ነው እንድትጮህ ያደረጋት፡፡ ክህደቱ የተለመደ ክህደት ነው፡፡ አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ከኤርትራ ባሕር ኃይል ጋር ያላትን ግንኙነት በነን ፕሮሊፈሬሽን ሕግ መሰረት ነው የሰረዘችው፡፡ ሕጉ ከሰሜን ኮርያ ሶርያና ኢራን ጋር ወታደራዊ መሳሪያዎችን መገበያየት ይከለክላል፡፡

ዝርዝሮች ባይገለጹም እርምጃው የተወሰደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የተጣሉ እቀባዎችን ተፈጻሚነት የሚከታተለው አካል,በየካቲት ወር በአውሮፕላን የተጫነ ወታደራዊ ደረጃ ያላቸው የመገናኛ መሳሪያዎች ከሰሜን ኮርያ ተነስቶ በቻይና በኩል አድርጎ በማቋረጥ ወደ ኤርትራ ሲያመራ ደርሶበታል፡፡

የኤርትራው ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ያወጣውን መግለጫ ኤኤፍፒ እንዳየው ማእቀቡ ሊገለጽ የማይችልና አግባብነት የሌለው፤ አገላለጹ በአሳዛኝ ሁኔታ ተመሳሳይ የሆኑ የሀሰት ሪፖርቶች በመጀመሪያ እንዲሰራጩ ተደርጎ ቀጥሎም በራሳቸው በመሀንዲሶቹ የተከለከሉ እርምጃዎች ተወስደዋል ሲል ገልጾአል፡፡

የኤርትራው ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ራሳቸውን ፖሊስ አቃቤሕግና ዳኛ አድርገው በሚቆጥሩት ክፍሎች ነው እርምጃው የተወሰደው ሲል አሜሪካንን አውግዞአል፡፡ኤርትራ ከ2009 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማእቀብ ስር ስትሆን የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎችዋ ወደውጭ እንዳይጓዙ፤ ንብረቶቻቸው እንዳይንቀሳቀሱ፤ የጦርመሳሪያ ሽያጭ ድጋፍ  በጎረቤት ሶማሊያ ለሚገኘው አሸባሪው አልሻባብ እንዳያደርጉ ታግደዋል፡፡ እነዚህ ክልከላዎችና እቀባዎች በዚህ ወር መጨረሻ እንደገና ይታያሉ፡፡

ኤርትራ አዲሱ የአሜሪካ እርምጃ ማለት እቀባው ወይም ክልከላው እንዲታደስ የሚያበረታታ የሚያደፋፍር ነው ብላለች፡፡ የአሜሪካ መንግስትና ጥቂት የግል ውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ላኪዎች ከኤርትራ መንግስት ባሕር ኃይል ጋር ምንም አይነት የንግድ ግንኙነት ለ2አመት እንዳያደርጉ የተጣለውን ማእቀብ በተመለከተ ዝርዝሩ በዋሽንግተን በፌደራል ሬጅስትራር ታትሞ ወጥቶአል፡፡

የአሜሪካን ስቴት ዲፓርትመንት ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑ ግለሰብ ከሪፖርተሮች ጋር በተደረገው ቴሌኮንፈረንስ  ለምን ኤርትራ ብቻ ተነጥላ እቀባ ተጣለባት ለሚለው ጥያቄ መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ኤርትራ በአለማችን በጣም የተገለለች ሀገር ነች፡፡

ኤርትራን በተመለከተ አምና የወጣው የመንግስታቱ ድርጅት ሪፖርት የኤርትራን መንግስት በሰው ልጅ ላይ በሚፈጸም ወንጀል ከከሰሰና ካጋለጠ ወዲህ ከፍተኛ አለም አቀፍ ውግዘትና ወቀሳ ገጥሞታል፡፡

በብዙ አስርሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት እንዲገቡ ስለሚያስገድዳቸው ስርአቱን በመሸሽ ተሰደዋል፡፡ይህንኑ ድርጊት የሚኮንነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ባርነት ሲል ይጠራዋል፡፡

ከነጻነት በኃላ ምንም አይነት ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም፡፡ ባለስልጣናቱ ተቃዋሚዎችን በሙሉ እንዲጠፉ አድርገዋል ሲል የኤኤፍፒ ዘገባ ያስረዳል፡፡ የኤርትራ መንግስት ዛሬም የጠብአጫሪነት የትንኮሳ ተግባሩን በጎረቤት ሀገሮች ላይ ቀጥሎአል፡፡ ከአለምአቀፍ አሸባሪዎች ጋር ትስስርና ቁርኝት የፈጠረ መንግስትም ነው፡፡ አክራሪዎቹና አሸባሪዎቹ የወሀቢ አክራሪ እስላማዊ ቀንደኛ ክፍሎች በኤርትራ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

ቀጠናውን በጅሀድ ጦርነት ስር ለማዋል የሚሰራው የአልሻባብ አክራሪ እስላማዊ ጽንፈኛ ኃይል ከመነሻው ጀምሮ አስከዛሬ የሚደገፈው በኤርትራ መንግስት መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባደረገው ማጣራት ደርሶበታል፡፡ በየመን ላይ ጦርነት ያወጁት የወሀቢ አክራሪ እስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑት ሀገራት ከኤርትራ ጋር ተሳስረውና ተቆራኝተው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ወታደራዊ ጦር ሰፈራቸውን በአሰብ ላይ መስርተዋል፡፡

የኤርትራ መንግስትና አክራሪ ጽንፈኛ ኃይሎች የተጽእኖ አድማሳቸውን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ለማስፋፉት ቀጠናው የሽብር የሁከትና የትርምስ ማእከል እንዲሆን በዋናነት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

የአልቃይዳና የአይሲስ አጋርና አባል የሆነው አልሻባብ በአለም ጥቁር መዝገብ የሰፈረ አሸባሪ መሆኑን የሚያውቀው የኤርትራ መንግስት ከአልሻባብና ከአክራሪ የወሀቢ ኃይሎች ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያን የበቀል ኢላማ በማድረግ በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የኤርትራው መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭትና ትርምስ እንዲፈጠር ያለማሰለስ ሰርቶአል፡፡ እየሰራም ይገኛል፡፡ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ የተገነው አስደናቂና አለምን ያስደመመ ልማትና እድገት እንዲስተጓጎል፤ የተጀመሩት ታላላቅ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ፤ ከድሕነት ለመውጣት የሚደረገው ሀገራዊና ሕዝባዊ ትግል እንዲገታ ለማድረግ ትላንትም ዛሬም ተቃዋሚ የሚላቸውን ኃይሎች ከግብጽ የሚያገኘውን ገንዘብ በስፋት እየረጨ በመግዛት ይህ ቀረው የማይባል መንፈራገጥ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ አይሳካለትም፡፡