አባቶች አንዱና ትልቁ ጸሎታቸው ሀገር ሰላም ውላ ሰላም ትደር የሚለው ነበር፡፡ ከነቤቴ ከነጎረቤቴም ሰላም አውለኝ፤ ሰላም አሳድረኝ ይሉም ነበር፡፡ ጎረቤት ሰላም ከሌለ ሰላም መሆን አይቻልም፡፡ የመጀመሪያው ነገር የሀገር መረጋጋና ሰላም መሆን ነው፡፡ ሁሉም በየተሰማራበት የስራ ዘርፍ ሰላም ውሎ፤ በሰላም መመለስ መቻሉ ነው የሰላም መኖር መገለጫው፡፡
ገበሬው በእርሻው፤ ወዝአደሩ በፋብሪካው፤ ተማሪው በትምህርት ገበታው፤ ነጋዴው በንግድ ቦታው፤ ዳኛው በመንበሩ ወዘተ ሰላም ሰርቶ ውሎ መመለሱ በገንዘብ የማይሰላ መተኪያ የሌለው ትልቅ ሀብት ነው፡፡ የሰላምን ዋጋ በየትኛውም የአለማችን ውድ ሀብት፣ አልማዝም ሆነ ወርቅና እንቁ መተካት አይታሰብም፡፡ የሀገርና የወገን ሰላም መሆን ለአንድ ሀገር ትልቁ ጸጋዋ ነው፡፡ ልጅ፣ ቤተሰብ፣ ትዳር፣ ስራ ሁሉ እውን የሚሆነው ሀገር ሰላም ሲሆን ነው፡፡
በአጭሩ ሰላም ከሌለ ምንም የለም፡፡ ሰርቶ ተምሮ ነግዶም ሆነ አትርፎ ታሞም ሆነ ታክሞ አርሶም ሆነ አምርቶ መሸጥም ሆነ መገበያየት ወጥቶም መመለስ የሚታሰበው ሰለም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ያለሰላም ሁሉም አይሞከርም፡፡
በቅርብ እየተመለከትን እንዳለው፤ በአለማችን በቅርብ አመታት ውስጥ በርካታ ሀገራት በሰላምና በመረጋጋት እጦት እስከመፈራረስ ደርሰዋል፡፡ ሕዝባቸው ለእልቂትና ለስደት ተዳርጎአል፡፡ ሕጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን በረሀብና በሞት፣ በጥይት አረር ውድ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ቤተሰብ ዳግም ላይገናኝ የተለያየበትን አሰቃቂ፣ ዘግናኝና ሰቅጣጭ ውድመቶችንና እልቂቶችን እስኪዘገንነን ድረስ በየቀኑ በቴሌቪዥን መስኮት እየተመለከትን ነው።
በሀገራት ውስጥ ለተፈጠሩት የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ መተላለቆች፣ ውድመትና ጥፋቶች ዋነኛዎቹ መነሻዎች የውስጥና የውጭ ኃይሎች ናቸው፡፡ የአምባገነን መንግስታት መኖርና የሕዝቡን ችግርና ብሶት በአግባቡ ለመፍታተ አለመቻላቸው፤ ስልጣንን ለማቆየት የሚደረገው በኃይል የታጀበና የሕዝቡን ጥያቄ በጉልበት ለመደፍጠጥና እረጭ ለማድረግ የሚከተሉት መንገድ፤ በተቃዋሚነት የተሰለፉ ኃይሎች የሚከተሉት አክራሪና ጽንፈኛ በጥላቻ፣ በጀብደኝነትና በስሜታዊነት የታጀበ ሀገራዊ ጥፋትን የማቀጣጠልና የማስፋፋት ድርጊት ሲሆን በዚህ አጋጣሚ የራሳቸውን የዘረፋ አጀንዳ ለማሳካት፤ በግርግሩ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያልሙ የውጭ ኃይሎች ፈጣን ሩጫ አለ፡፡
በከፍተኛ ደረጃ ገንዘብ እየረጩ አክራሪውን ተቃዋሚ በጥቅም እየገዙና ከኋላ እየገፉ የገዛ ሀገሩን እንዲያወድም በዲሞክራሲና በነጻነት ስም እየቀሰቀሱ በነገ የተሻለ ተስፋ ሕልም የሚጫወቱት አስከፊና አውዳሚ ድርጊት በሶርያ፣ በሊቢያ፣ በየመን፣ በኢራቅ፣ በሶማሊያ ወዘተ በስፋት ታይቶአል፡፡
በዚህም የተነሳ በአመጹና በግርግሩ ወቅት ሲያስተጋቡት የነበረው የ”ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ” ባዶ ቅዠት መክኖ የተባለው ነጻ ዲሞክራሲ፣ ነጻ ምርጫ የሕዝቡ ኑሮ መሻሻል ወዘተ ጭርሱን አስታዋሽ አጥቶ የቀደመውን እስኪናፍቁ ድረስ እልቂትና መአት በየሀገራቱ ላይ ወርዷል፡፡
ቀድሞ የነበረው ሰላም እንዳልነበረ ሆኖ ጨልሞ፣ የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ በእርስ በእርስ ጦርነትና መገዳደል የሀገራቸውን የቀደመ ስልጣኔ፣ ኃብት፣ ንብረት፣ ቤታቸውንና ተቋሞቻቸውን አፈራርሰው የጦርነት አውድማ አድርገው አልፈዋል፡፡ የፈሰሰ ውሀ አይታፈስ እንዲሉ፤ ዛሬ በቀደመው ድርጊታቸው ቢቆጩና ቢንገበገቡም ምንም መመለስ አልቻሉም፡፡
ጽንፈኛና አክራሪ ተቃዋሚዎች ሕዝብ እንዲያልቅ እንዲሰደድ ሀገራቸውም እንድትጠፋ መሰረታዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ዛሬ ወደኋላ ተመልሰው ሲያስቡት በአያሌው ቢጸጸቱም ቀድሞ የነበራቸውን ሰላምና መረጋጋት በፍጹም ሊያገኙት አልበቁም፡፡ የሕልም አለም ቅዥት ሆኖባቸው ቀርቷል፡፡ ይሀ አይነቱ ስህተት ሳይሆን፤ ሳይፈጸም ነበር ቀድመው በስፋትና በጥልቀት ማሰብ የነበረባቸው፡፡
ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ ይላል የሀገሬ ሰው፡፡ ሳይሆን ነው መጀን ይላሉ የወሎ ሼሆችም፡፡ ሳይሆን ነው አስቀድሞ ማሰብ፣ ቀዳዳውን መድፈን፣ ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም መቆም የሚገባው፡፡ ከደፈረሰ፣ ቋጠሮው ከተበጠሰ በኋላ መልሶ ለመቀጠል እንደገና የትውልድ መስዋእትነት ሊጠይቅ ይችላል፡፡
ማንኛውንም ችግር በሰለጠነ መንገድ፣ በእርጋታና በወይይት መፍታት፣ ልዩነትን አጥብቦ ለጋራ ቤትና ለጋራ ሀገር ሰላምና ደሕንነት፣ ልማትና እድገት መቆም፣ ሰላምን መጠበቅና ማስከበር የሁሉም ዜጋ ሀላፊነትና ተግባር ነው፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ የሚያዋጣውም ይሀው ብቻ ነው፡፡
በሀገር መታመስ በሰላም መጥፋት እርስ በእርስ መናቆርና ግጭት ተጠቃሚም አትራፊም ወገን የለም፡፡ ከውጭ ሁነው የሚቆሰቁሱት የራሳቸው የተለየ አጀንዳ ያላቸው ግብጽን የመሰሉ መንግስታት እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ቢፈጠር ለእነሱ ፈንጠዝያ ሰርግና ምላሽ ነው የሚሆነው፡፡ መጠንቀቅ የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው፡፡
የሀገራችን ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥ ከጥንት ጀምሮ ዙሪያ ገባዋን ታሪካዊ በሚባሉ፣ የመኖር ሕልውናዋን በሚፈታተኑ፣ ተለይተው በሚታወቁ የየራሳቸው ፍላጎት ባላቸው ተቀናቃኞች ተከባ የምትኖር ሀገር ነች፡፡ ረዥሙ የማንነት ታሪኳ ከጦርነት ጋር የተቆራኘ የሆነበትም ምስጢር ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡
ለድሕነትና ኃላቀርነታችን አቢይ አስተዋጽኦ ያደረገው ለረዥም ዘመናት የውጭ ኃይሎች የውስጥ ጀሌዎቻቸውን በመጠቀም ሀገራችን የተረጋጋ ሰላምና ደህንነት እንዳይኖራት ሲሰሩ የነበረው ሴራና ደባ ነው፡፡ ከትላንት ታሪኮቻችን አክራሪና ጽንፈኛ የሆኑት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የተማሩ አይመስሉም፡፡ ሌላ ዙር የትውልድ የሀገር ጥፋትና ውድመት ባጅተው የሚናፍቁ ይመስላሉ፡፡ ባሕር ማዶ በተንደላቀቀ ሕይወት እየኖሩ በሀገር ቤት እልቂትና መጠፋፋት እንዲፈጠር መራወጥ ትረጉም አልባ ብቻ ሳይሆን ከንቱነት ነው፡፡
ዛሬ ሀገሪቱ የደረሰችበት የኢኮኖሚ ልማትና እድገት የተገኘው ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩ ሕዝቡ ከጦርነት ተላቆ ከድሕነት ጋር ሰፊ ትግል በማድረጉ ነው፡፡ ጦርነት የሀገርን ኢኮኖሚና የሰው ሀብት አሟጦ ቀርጥፎ ይበላል፡፡ ዳግም ወደኋላ፣ ወደ ድህነት፣ ወደ ተረጂነትኛ ተመጽዋችነት ይመልሳል፡፡ በንጹህ ሕሊና ከስሜታዊነትና ከጥላቻ ወጥቶ የሚያስብ ሰው እንዲህ አይነቱን ጥፋት ለሀገሩና ለሕዝቡ ከቶውንም አይመኝም፡፡
መንግስት የሰራውን ያህል ሰርቶአል፡፡ የዛኑም ያህል ይሰራሉ ሕዝብና ሀገር ይመራሉ ብሎ ታምኖባቸው በስልጣን ወንበር ላይ ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች በፈጠሩት ብልሹ አሰራር፤ ሙስናና ኪራይሰብሳቢነት፤ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ መዛባት ችግር ሕዝቡ መማረሩ፣ መንገፍገፉ፣ ለተቃውሞም መነሳቱ ገዢው ፓርቲ ራሱን በጥልቀት እንዲፈትሽ፣ እንዲመረምር፣ ወደውስጡም እንዲመለከት አድርጎታል፡፡ ጥልቅ ተሀድሶ እንዲደረግ ገፊና መነሻ ምክንያትም ሆኖአል፡፡
ኢህአዴግ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ አባላቱ ላይ ከፌደራል አንስቶ እሰከ ክልሎች ድረስ የተለያየ ደረጃ ያላቸውን እርምጃዎች ወስዶአል፡፡ ተሀድሶው ገና መጀመሩ ነው፡፡ የተዘጋ ፋይል አይደለም፡፡ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ግዜው ረዘመም አጠረ ይጠየቃሉ፡፡ ለሕግና ለፍትሕም ይቀርባሉ፡፡ ሕዝብን በግለሰቦች መለወጥ አይቻልም፡፡ ግለሰቦቹ የወጡትም የተገኙት ከሕዝብ ነውና፡፡ ሕዝብና የሕዝብ ጥያቄ ይቀድማል፡፡ የሕዝቡንም ጥያቄ በየደረጃው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በአንዴ ሁሉንም ጥያቄ ለመመለስ አይቻልም፡፡ ግዜ ይጠይቃል፤ በግዜ ሂደትም እየተፈታ ይሄዳል፡፡ ለዚህም ነው የጽንፈኛው የማይበጅ አታሞም ሆነ ትርጉም የለሽ ድቤ ዋጋቢስ መሆኑን ደግመን ደጋግመን የምንናገረው።