ባለሃብቶቻችን ከተኙበት ሊነሱ ይገባል

ሕንዱ Allana Group የቄራ ድርጅት በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል፣ አዳሜ ቱሉ ያስገነባውና 20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገበት ዘመናዊ የእርድ ፋብሪካ በቀጣይ ወር ሥራ የሚጀምር መሆኑ ታውቋል። በተመሳሳይም ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የአሜሪካ መንግሥት ያስገነባው ብሔራዊ የኅብረተሰብ ጤና ማሰልጠኛ ማዕከል መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም ላይ በይፋ ተመርቆ ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም መተላለፉን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ዋና ጉዳይ ፈጻሚ ፒተር ብሩማን ማስታወቃቸውን የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሰሞኑን የዘገቡ መሆናቸውም ይታወቃል። ይህ ብቻ አይደለም፤ የኖርዌይ የታዳጊ አገራት ኢንቨስትመንት ፈንድ (Norfund) ቨርድ ቢፍ ኘሮሰሲንግ በተሰኘው ኢትዮጵያዊ የሥጋ ላኪ ኩባንያ ላይ የ7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት በማድረግ ዘመናዊ የእርድ ፋብሪካ እና የሥጋ ማቀነባበሪያ እንደሚያካሂድ ይፋ ያደረገው ሰሞኑን ነው። በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኘው ሀሬዶ ታጠቅ ኢንዱስትሪ ዞን በአውሮፓ፣ አሜሪካ ባለሀብቶች እና በኢትዮጵያዊው ሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ አማካይነት አዲስ ከጤፍ የሚዘጋጅ የቸኮሌት ምርት ማምረቻ ፋብሪካ ለማቋቋም መታቀዱም ሰሞንኛ የነበረ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን የተመለከተ ዜና ነበር።

እኒህ እንደማሣያነት የቀረቡ ወሬዎችን ያነሳነው አገራችን ከተያያዘችው ልማትና የሥራ እድል ፈጠራ አኳያ ያላቸውን ፋይዳና የአገር ውስጥ ባለሃብቶቻችንን ቀርነት ለማሄስ ነው። በሌላ በኩልም መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰበት ከሚገኘው የወጣቶች ተጠቃሚነት ጋር የውጭ ኢንቨስትመንታችን ያለውን ፋይዳ ለመቃኘት እንዲቻለን ነው

በዚህች አገር ስለባለሃብቶቻችን ደካማ የሆኑ እንቅስቃሴዎች በተነሳ ቁጥር የምንሰማው መንግሥት በሁሉም ጉዳዮች ውስጥ እጁን እየነከረ ነው የሚለው ጎልቶ የሚሰማ ወቀሳ ነው። ያም ሆኖ ግን የመንግሥት ሚና በብዙ አገሮች ዘንድ ትልቅ ነው፡፡ የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ተምሣሌት ነች የምንላት አሜሪካን ያየን እንደሆነ ኩባንያዎቿ እንደ ቀድሞው ነፃ ኢኮኖሚ መሆናቸው ቀርቶ ከለላ የሚሰጡ ወይም ‹ፕሮቴክሽኒስቶች› ሆነዋል፡፡ ይኼን ትተን በልማታዊ መንግሥትነት የሚጠቀሱ መንግሥታት ሚና ምን እንደሆነ ለማየት ብንሞክር ‹ከኒዮ ክላሲካል› ጀምሮ እስከ ‹ዋሽንግተን ኮንሰንሰስ› የተንሸራሸሩ ሃሳቦችን ብናይ የመንግሥት ሚና አነስተኛ መሆን አለበት በሚለው ሲስማሙ እናያለን፡፡ ክርክሩ ግን የመንግሥት ሚና ምን ያህል ነው መሆን ያለበት? የሚለው ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የግሉ ዘርፍ ምን ያህል ጠንካራ ነው? የሚለው ጥያቄ ሳይመለስ የመንግሥትን ሚና መገደብ አመክንዮአዊ ስለማይሆን፡፡

የግሉ ዘርፍ እየጠነከረ ሲሄድ የመንግሥት ሚና እየቀነሰ መሄድ አለበት የሚለው በእርግጥም የሚያስማማና ምክንያታዊ ነው፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ኢንቨስትመንቱንና ሌላውንም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ስናየው የግሉ ዘርፍ የድርሻውን ይዞ እየተጓዘ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት መንገድ እየገነባ የሚጠቀምበት የግል ዘርፍ ከሌለ ትርጉም አይኖረውም፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን በስፋት እየሰራ ተጠቃሚ ከሌለ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ስለሆነም መንግሥት በማምረቻ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ እጁን ቢያስገባ እኒህና መሰል አሣማኝ ምክንያቶች ስላሉት ነው፡፡  

የመንግሥት ድርጅቶች ጫና ያደርጋሉ፣ የግሉን ዘርፍ ያስወጣሉ የሚለው ምልከታ ምክንያታዊነት ይጎድለዋል፡፡ ኢንዱስትሪ ልገነባ ተዘጋጅቻለሁ የሚል አካል መንግሥትን የኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፋት ሥራዎች ስለምን ትገባለህ ቢለው በምንም መመዘኛ ትክክል አይሆንም፡፡ መንግሥት በመሠረተ ልማት መስክ ሚናውን ይዞ መገንባት ካልቻለ ሁሉ ነገር ዋጋ አይኖረውም፡፡ መንግሥት የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር መሆን አለበት ሲል ዘወትር ቢደመጥም በጥሪው ልክ ምላሽ የሚሰጠው አካል አላገኘም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያዊው የግል ባለሀብት የኢኮኖሚው መዘውር መሆን አለበት የሚለው አያከራክርም፡፡  

አሁን ባለው ሁኔታ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው ሞተር በመሆን መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደማይገመት በርካታ ማሣያዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ እንደ ንግድ ባንክ ያሉት ብቻም ሳይሆኑ ትልልቅ የሚባሉት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሳይቀሩ የሚጠየቁት ብድር በአብዛኛው ከማኑፋክቸሪንግ ውጪ እንደሆነ መግለጻቸው አንዱ ማሣያ ነው፡፡ በማኑፋክቸሪንግ መስክ ብድር ተጠይቆበት ውድቅ ያደረጉት ፕሮጀክት የሌለ መሆኑም በተመሳሳይ፡፡ በማኑፋክቸሪንግ መስክ የግሉ ዘርፍ ለመግባት ትልቅ ክፍተት እያሳየ ነው፡፡ መሠረተ ልማት ዝቅተኛ በሆነበት፣ የግሉ ዘርፍ ሚና አነስተኛና ደካማ በሆነበት የኢኮኖሚው ክፍል ሁሉ መንግሥት መግባቱና የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰቱን ማበረታታቱ ምክንያታዊና ሣይንሳዊ ነው፡፡ ይህ በሌሎችም አገሮች ዘንድ የሚደረግ እና እየተደረገም ያለ ነው፡፡ በመሆኑም የመንግሥት ሚና ትክክል ነው፡፡ መንግሥት አቅርቦት እየፈጠረ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ ሊሰራው ይችል ነበር? የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት የደከመ በመሆኑ የግዴታ መንግሥት በመግባት መሥራት ይኖርበታል፡፡  

በማኑፋክቸሪንግ መስክ አብዛኞቹ እየመጡ ያሉት ኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡ በመሆኑም የግሉ ዘርፋችን አቅም ትንሽ ነው እናሳድገው ካልን ከዚህ ውጪ አማራጭ አይኖርም፡፡ በመሆኑም መንግሥት የግሉን ዘርፍ እያስወጣ ነው የሚለው ብዙም የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ደካማ የግል ዘርፍ ይዘን መኩራራት የትም ስለማያደርሰን፡፡

አብዛኛው የግሉ ዘርፍ በአገልግሎት መስክ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ብድር የሚጠየቀው ለሆቴል ግንባታ ነው፡፡ መኪና ለማስመጣት ነው፡፡ ውስን ሀብት ባለበት እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን እስከ ወዲያኛው ማስተናገድ ከባድ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ በሌሎች ትልልቅ የማኑፋክቸሪንግ መስኮች ላይ ለመሳተፍ ፋይናንስ እየጠየቀ እንዳልሆነ እየታየ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባሉት መስኮች ላይ መሳተፍ የሚችል፣ ኢንቨስት የሚያደርግ የግል ዘርፍ በሌለበት አግባብ ከውጭ የገቡትን እና በመግባት ላይ ያሉትን ጨምሮ መንግሥትን መውቀስ ተገቢ አይሆንም፡፡     

በወጣቶች ላይ ለመሥራት  አንዱ መፍትሄ የግሉን ዘርፍ ቢሆንም ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች አማራጭ ሊሆነን አልቻለም፡፡ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር በጣም ወሣኝ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ሰልጥነው ወደ ውጭ ሄደው የሚሰሩ፣ በሁለተኛ ደረጃ ራሳቸውን በራሳቸው ቀጥረው መሥራት የሚችሉ ወጣቶችን መፍጠር፣ በሦስተኛ ደረጃ በመንግሥት ቀጣሪነት የሥራ ዕድል መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ አንዳንዱ የራሱን ሥራ መስራት ይፈልጋል፣ አንዱንዱ ተቀጥሮ መሥራት ይፈልጋል፡፡ አንዳንዱ የመንግሥት ሥራ ላይ ያተኩራል፡፡ ከእነዚህ በተለየ ደግሞ መሥራት እየቻለ ሥራ ፈት የሚሆንም አለ፡፡ ዘመድ ገንዘብ ይልክልኛል ብሎ የሚጠብቅ ወይም ወደ ውጪ እሄዳለሁ ብሎ በተስፋ የሚቀመጥ አለ፡፡ ከዚህ ውጭ ግን አሳሳቢ የሥራ አጥነት አለ፡፡ ሥራ እየፈለገው ማግኘት ያልቻለ ብዙ ነው፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢ ያለው የሥራ አጥነትነት ላይ አልተሰራም፡፡  

ስለሆነም ከላይ ከተመለከቱት ሚናዎቹ ባሻገር መንግሥት ከራሱ በጀት ቀንሶ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያስተዳድረው ተዘዋዋሪ ፈንድ ለወጣቶች መመደቡ ተገቢና ምክንታዊ ነው፡፡ አሁንም ግን ባለሃብቶቻችን ሊያጤኑት የሚገባው በወጣቶች ሥራ ማጣት ላይ ሥራ የመስጠትና የመፍጠር ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ እንዳልሆነ ነው፡፡ ዘላቂነት ያለው የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችለው የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ ወላጆችም ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ወልደው አሳድገው ያስተማሩትን ልጅ መንግሥት ሥራ ይስጥህ ማለት ምክንያታዊ አያደርግም፡፡ የግሉ ዘርፍ የቅጥር ምንጭ መሆን መቻል አለበት፡፡ መንግሥት የሚሰራቸው ፕሮጀክቶች እንዳሉ ሆነው የግሉ ዘርፍ ግን ትልቁ የሥራ መስክ ነው፡፡ ባለሀብቶቻችን የችግሩ መፍትሔ አካል መሆን አለባቸው፡፡ መንግሥት የግሉ ዘርፍ ለሚፈጥራቸው የሥራ ዕድሎች ማበረታቻ የመስጠት ግዴታ ግን አለበት፡፡  

አሁን ለወጣቶች ሥራ ተብሎ የተመደበው በጀት ከሌላ የመንግሥት ፕሮጀክት ተቀንሶ የመጣ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ አንዱን ለማጥፋት የወሰድከው ርምጃ በሌላ ጎኑ የኢኮኖሚው መረጋጋት ላይ ችግር ሊያመጣ ይችላል፡፡ መንግሥት የበጀት ጉድለት ሊመጣበት ይችላል፡፡ ይህንን ለመሙላት ገንዘብ ሊያትም ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበትን በማስከተል ኢኮኖሚውን ያናጋል፡፡ በመሆኑም ባለሃብቶቻችን ከተኙበት ሊነሱ ይገባል፡፡

ያም ተባለ ይህ በረዥም ጊዜ ሒደት ለውጥ ማምጣት የሚችለውና የኢኮኖሚ ዕድገት ሞተር የሚሆነው የግሉ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ በምንም ሁኔታ የምንደራደርበት ሊሆን አይገባም፡፡ ምክንያቱም ለለውጥ ይኸው ነው መንገዱ፡፡ በወሣኝነት ለውጥ ለማምጣት የግሉ ዘርፍ በማይገባበት መስክ መንግሥት እየገባ እንዲከተሉት ማድረግ ጤናማ ነው፡፡ መንግሥት በአንድ በኩል ‹ፕራይቬታይዝ› እያደረገ እንደሚገኝም ማየት ያስፈልጋል፡፡ የነበሩትን እየሸጠ እየወጣ ነው፡፡ እንደ አዲስ እየገባ ነው ካልንም የግሉ ዘርፍ መግባት ባልቻለባቸው ቦታዎች እየገባ መንግሥት ከሰራ የሚደገፍ እንጂ ሊያስወቅስ አይገባም፡፡

ይልቁን ባለሀብቱ በአግባቡ ታክስ መክፈል አለበት፡፡ መንግሥትም ተቋማትን ማፅዳት አለበት፡፡ ሙስናውን፣ የቢሮክራሲ አሠራሩን መፈተሽና ማስተካከል አለበት፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ በቀላሉ ገንዘብ ለማግኘት ምቹ ከሆነ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም ልክ እንደዚያው እንዲሆን ለማድረግ መንግሥት አጥብቆ ሊሰራ ይገባዋል፡፡ መንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ባለሀብቶችን ለማፍራት፣ ተገቢውን ማበረታቻ ብቻ ሳይሆን ስለጥቅሙም በአግባቡ ማስተማር ይጠበቅበታል፡፡