የሰው ልጅ እዚህ ምድር ላይ ሲኖር ለገሃዳዊው ዓለም ውድቀትም ይሁን ትንሣዔ አንዳች ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ምክንያት እንዲሆነው በየአዕምሯችን ጓዳ ውስጥ ከምናብሰለስለው የአስተሳሰብ ቅኝት እንደሚቀዳ እሙን ነው። በዚህ የአመለካከት እሣቤ የብዙዎች ምርጫ መሠረት የሚሆነን የየራሳችንን የህይወት ዘመን ለቀጣዩ ኢትዮጵያዊ ትውልድ የምትበጅ በተስፋ የበለፀገችና ሊኖርባት የሚመኟት አገር በመፍጠር የህዳሴ ተግባር ላይ መሰማራት ነው።
በአንጻሩ ይህ አስተሳሰብ የሚጎረብጠው አይጠፋም። ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ ጉዞውን ቀልብሰው ወደ ትናንቱ የድህነት ማጥ፣ የረሀብና ስደት ህይወት፣ የሰቆቃና ችጋር ኑሮ፤ ወደ ድቅድቁ ጨለማ ሊመልሱን የሚዳዱ ኃይሎች አይጠፉም ብዬ እገምታለሁ። የሚያሟርቱትን፣ የሚያሴሩትን፣ የሚዶልቱትን የጥላቻ ፖለቲካ እያውጠነጠኑ እነሱ በገዛ እጃቸው ተቆርፍደው መልሰው እኛኑ ሊጠምዱን ታች ላይ ቢሉ አይገርምም – ተፈጥሯዊ ዑደት ነውና።
የዛሬው ጽሁፌ በእነዚህ የጎሪጥ በሚተያዩና ጀርባ በተሰጣጡ መሠረተ ሃሳቦች ላይ በማውጠንጠን ይህች የጋራችን የምንላት የዛሬዋ ኢትዮጵያ በየትኛው ቁመናዋ ላይ ትገኝ ዘንድ ምርጫችን ምን ይሁን? በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ይሆናል።
በዚህም በአንድ ጎራ ይህች አገር ለእኔ ምን አደረገችልኝ ከሚለው ጥግ ከያዘ ቆዛሚ አስተሳሰብ ከወዲያ እኔስ ምን አደረገኩላት ከሚለው ነባራዊ እውነታ በመነሳት የዜጎች ተግባራዊ ምላሽ የቱ ላይ ይደፋል አሊያም ከወዴቱ ላይ ያዘነብላል – ምላሽ ይሰጣል ብዬ እገምታለሁ።
ኧረ ለመሆኑ! ከዚህ የአስተሳሰብ አለመገጣጠም ባሻገር ልንግባባ በአንድ አገራዊ አጀንዳ ጥላ ሥር ልናርፍ የሚያስችሉን ስንትና ስንት ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች እያሉን ስለምን እነዚያን ላመስማት ጆሯችንን ያዝን? ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ያወረሱን ባህላዊ፣ ሞራላዊና ኃይማኖታዊ እሴቶች ሞልተውን ሳለ ስለምን እኒያን ዞር ብሎ ላለመመልከት ዓይናችን ታወረ? ላለማሰብስ አዕምሯችን ደነዘዘ? ስለምንስ ከእነዚህና ከእነዚያ ካልጠቃቀስኳቸው መሠረተ ሃሳቦች አኳያ የጋራ መግባባት የሚሹ ስንትና ስንት ቁልፍ ታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች እያሉን ተያይዘን ላለመጓዝ እጃችንን ሰብስበን ለመጠላለፍ ተሽቀዳደምን? ምነውሳ! ለመጠላለፍ፣ ለመደነቃቀፍና ረግጦ ለማለፍ ከረድፉ ላይ ቆምን? ኧረ ለመሆኑ! የዛሬዋ ኢትዮጵያ አዲስ መለያ አጥልቃ፣ የትናንቱን መጥፎ መጠሪያዋን ለውጣ ከቀዳሚዎቹ ጎራ ለመቆም ስትታትር መንገዷ ላይ መቆም ምን ይሉት ፈሊጥ ነው? – እሷ ግና የህዳሴ ጉዞ ላይ ናት።
ይህቺ የቀድሞ ታላቅ ሥልጡን አገርና ኩሩ ባህልና ታሪክ ያለው ህዝብ የመንግሥታትን ደጅ እየጠና ምፅዋት ይጥሉለት ዘንዳ እጆቹን ለልመና ዘርግቶ፣ በሐፍረት አንገቱን ደፍቶ፣ ሞራሉን ለሌሎች አሳልፎ ሰጥቶ በአሳፋሪው የድህነት ታሪክ ዓለም እየተጠቃቀሰበት ይኖር ዘንዳ የሚፈቅድ ኢትዮጵያዊ ከየትም አቅጣጫ ይኖራል ብሎ ማሰብ የጤንነት አይደለም። አሸማቃቂው የድህነት ታሪክ ዛሬ ላይ ይቀጥል ዘንድ ምርጫዬ ይሁነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ካለም የጤንነት አይሆንም። ይህን ለማለት የሞራል ብቃቱም ስለሚያንሰው ሰው የመሆኑ ጉዳይ የሚያጠራጥር ይሆናል።
መቀመጫቸውን ባህር ማዶ ያደረጉና አገር ቤትም ያሉ፣ ሠላማዊውንና የእሱ ተቃራኒ የሆነውን እንዳሻቸው እየደበላለቁ ሲፈልጉም እየነጣጠሉ በተቃውሞ ጎራ የቆሙ፣ የነጠረ ያልተበረዘ የፖለቲካ ፕሮግራም ሳይጨብጡ ዛሬ አንዱን ጥለው ሌላውን ለማንሳት ማንም የማይቀድማቸው በጭፍን ጥላቻ የተሞሉ የአገሬ ተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች ከስሜታዊ የፖለቲካ አራማጅነት ፀድተው መሬት ላይ ያለውን እውነታ በንጹህ አዕምሮ መቀበል ቢችሉ እንዴት ሸጋ በሆነ ነበር። እስቲ እውነት እውነቱን እንነጋገር። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተከወነ፣ ምን እየተሰራ፣ ምን ለውጥ እየተመዘገበ ይገኛል?
የሩቅ ሆነ የቅርብ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ናቸው የምንላቸው እንኳን ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን የህዳሴ ጉዞ አምኖ በመቀበል አብሮ ለመሥራትና የአጋርነት መንፈስን ለማጠናከር ዴፕሎማሲያዊ ሥልቶችን ቀይሰው ሲሯሯጡ፤ የእኛዎቹ ይህን ሂደት ማገዝ እንኳን ቢጠፋቸው ለማደናቀፍ እንቅልፍ አጥተው ሲባዝኑ ሳይ በእውነትም አዘንኩ፣ አፈርኩም።
በዚህች የጋራ በምንላት አገር ዛሬ ታሪካዊ የህዳሴ ጉዞ ተጀምሯል፤ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ በባቡር መስመር ዝርጋታ፣ በመንገድ ግንባታ፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ሥራ የጋራ በምንላት አገር – ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እየተከወነ ይገኛል? ነባራዊውን ሁኔታ ላለመቀበል አሊያም እውነታውን ላለማየት ካልሆነ በስተቀር በእርግጥም ይህች የጋራ የምንላት አገር ለውጥ ላይ ናት። እነዚህን ሁሉ ላለመቀበል የሚዳዳቸው የአገሬ ልጆች ካሉ ሊያስደምሙኝ፣ ሊያስደንቁኝና ሊያስገርሙኝ ካልሆነ በቀር በእርግጥም አሳዘኑኝ።
እምብዛም ደግሞ አልገረምም – "ተቃዋሚ" ሲባሉ በጥላቻ ፖለቲካ ተወልደው በክፋትና በምቀኝነት ያደጉ ናቸውና አይደንቀኝም። ብርሃንን ጨለማ፣ ወተትን ጥቁር፣ እውነትን ሐሰት ብለው የሚምሉ ናቸውና አልደመምም።
ኧረ ለመሆኑ! ተቃዋሚ የአገሬ ተቃዋሚዎች በሠላማዊ መንገድ አማራጮቻቸውን ማቅረብ የሚችሉበት እድል እያላቸው ለዚህም ህገ መንግሥቱ ዋስትና ሰጥቷቸው ሳለ ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት በኃይል ለመናድ ካለመ የአመጻ መንገድ ጋር መጣበቃቸውስ ምን ይሉት ፖለቲካ ነው።
በሰለጠነና በዘመናዊ አካሄድ ከምርጫ ሣጥን ከሕዝብ በሚገኝ ድምጽ የመንግሥትን በትረ ሥልጣን መጨበጥ እያለ ዘወትር በጥላቻ መንፈስ ታውረው፣ በመናናቅ ስሜት ውስጥ ጠልቀው፣ በበጎው ተግባር ላይ አሸዋ በትነው፣ ሁከትና ብጥብጥ በትራቸው ሆኖ እስከ መቼ እስከ የት እንደሚጓዙ ፈጣሪ ይወቀው።
ራሳቸውን የችግሮችና የመፍትሄዎች አካል አድርገው፣ በጎደለው ላይ ሞልተው በጎ በጎውን አዳንቀው፣ ስህተቶችን ጠቋቁመው በጋራ ለዚህች የጋራ ለምንላት አገራችን ልቦናችሁ መቼ ይከፈት፣ ህሊናችሁ መልካም መልካሙን ሊያስብ እንደሚችል እሱ ይወቀው።
ጤናማና በጎ ተግባር ለመፈፀም፣ ቁም ነገር ያለው ሥራ ከውኖ ለማለፍ፣ ከጉድፍ ጉድፉ ውጪ ሌላ የማይታየው ተቃዋሚ ፓርቲ በዚህች አገር ተመሥርቶ ማየት ሕልሜ ነው።
ከጥላቻ ፖለቲካ ተላቅቆ፣ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የራስን ድርሻ አበርክቶ፣ አገራዊ መግባባት ተፈጥሮ ብሎም ዓለም በሚደመምባቸው ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የራስን አሻራ አኑሮ ማለፍ ከእድልም በላይ እድል ነውና ዛሬም አልመሸም።