ሀገራችን በምትከተለው የዲፕሎማሲ መርህ ተቀባይነቷ እየጎለበተ ነው። በዚህም በዲፕሎማሲው መስክ ከቀጣናው አልፋ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያገኘችና የሀገራትን ትኩረት እየሳበች ትገኛለች። ታዲያ ይህ ተቀባይነት እንዲሁ ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም—ኢትዮጵያ በውስጧ እያከናወነች ያለችው ስራዎች ነፀብራቅ ነውና። እናም በውጭ ዓለም ያለን ተቀባይነት መነሻው በሀገር ውስጥ የምናከናውናቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ተግባራት ውጤቶች መሆናቸው ሊዘነጉ አይገባም።
ኢትዮጵያ ለሰላም ባላት ቁርጠኛ አቋም የህዝቦችን የሰላም እጦት ለመታደግ ላለፉት 26 ዓመታት ሰርታለች። በዚህ ጥረቷም በአሁኑ ወቅት ከአስር ሺህ በላይ የሚገመት የሰላም አስከባሪ ሃይል ወደ ተለያዩ ሀገራት በማሰማራት ከአፍሪካ በአንደኛነት እንዲሁም ከዓለም በአራተኛነት ደረጃ ለመቀመጥ ችላለች። ይህም መንግስት በሀገር ቤት ሰላምን ለማስፈን እንደሚያደርገው ሁሉ በጎረቤት ሀገርም ይሁን በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ይህንኑ መርሁን በመከተል የፀና አቋሙን እያንፀባረቀ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
መንግስት ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚያሰማራው የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በሚከተለው ህዝባዊ ወገንተኝነትና ዲሲፕሊን አንቱታን ያተረፈ ነው። እዚህ ላይ ለዚህ ፅሁፍ ይሆን ዘንድ ሁለት አብነቶችን ብቻ ማንሳት እሻለሁ። ዛሬ ህዝባዊ መንግስት የመሰረተችውን ሶማሊያንና አጨቃጫቂውን አብዬ ግዛትን። እንደሚታወቀው ለሁለት አስርት ዓመታት መንግስት አልባ በነበረችው የያኔዋ ሶማሊያ ውስጥ መሽጐ በሀገራችን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ራሱን ሲያዘጋጅና ሲያደራጅ የነበረው “አል-ኢትሃድ አል-ኢስላሚያ” የተሰኘው አክራሪ ቡድን፤ ከሶማሊያ ወደ ሀገራችን ሰርጐ በመግባት የሽብር ጥቃት ለመሰንዘር ተዘጋጅቶ ነበር። ለዚህ እኩይ ሴራው እንደ መተላለፊያ በዋነኛነት ይጠቀምበት የነበረው የምስራቁን የሀገራችን ክፍል እንደነበርም አይዘነጋም። ሆኖም ይህ ተግባሩ የአካባቢው ህዝብ በህገ-መንግስቱ የተጐናፀፈውን መብትና ጥቅም የሚያሳጣ በመሆኑ ተቀባይነት አልነበረውም።
ህዝቡ ሠራዊታችን ከአብራኩ ክፋይ የወጣ የሰላም ሃይል መሆኑን ስለሚያምን ህዝባዊ ባህሪ ተላብሶ አክራሪውን ቡድን ለመመከት ለተንቀሳቀሰው መከላከያ ሃይላችን ፅኑ ድጋፉን ሰጥቷል። የአካባቢው ህዝብ “አል-ኢትሃድን“ ፊት ለፊት ከመዋጋት ባሻገር፤ የሰላም ሃይል ለሆነውና በህዝባዊ ወገንተኝነት ብሎም በዲሲፕሊን ተግባሩን ለሚወጣው ሰራዊታችን ጥቆማ በመስጠት ጉልህ ሚና እንደተጫወተ አይዘነጋም። በዚህ ቅንጅታዊ አሰራር ሰራዊታችን የህዝቡን ሰላም ሲያስጠብቅ፤ ህዝቡ ደግሞ ለሰላም ባለው ቀናዒነት የኋላ ደጀን በመሆን አክራሪው ቡድን ተደምስሶ የሰላም አየር በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ሊነፍስ ችሏል።
አክራሪው ቡድን በዚህ መልኩ በህዝቡ ድጋፍ ሀገር ውስጥ ሲመታ በሼክ ዳሂር ሃዌይስ ይመራ የነበረውና ራሱን “እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት” እያለ የሚጠራው አክራሪ ቡድን ሶማሊያ ውስጥ ሆኖ በኤርትራ አይዞህ ባይነት በሀገራችን ላይ ጅሃድ አወጀ። ምናልባትም ከአስር ዓመታት ብዙም ያልዘለለ። መንግስት አሁንም ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በልመና ጭምር ለዚህ ቡድን ቢያሳውቅም በጎ ምላሽ አላገኘም። በወቅቱ በዚያች ሀገር በህዝብ የተመረጠ መንግስት ባይኖርም፤ ወንድምና እህት የሆኑትን የሶማሊያን ህዝቦች ማክበር ነበረበት። እናም ህዝቡን በማክበር የሶማሊያን ድንበር ጥሶ ለመግባት ባለመፈለጉ ቡድኑ ሃሳቡን እንዲስብ በተለያዩ ወገኖች ቢያስለምንም ለውጥ ሊገኝ አልቻለም። እናም ጉዳዩን ለፓርላማ በማቅረብ ካፀደቀ በኋላ በሀገራችን ላይ ያንዣበበውን ግልፅና ድርስ አደጋ በሰራዊቱ አማካኝነት መቀልበስ ችሏል። ይህ የሰራዊታችን አደጋን የመቀልበስ ግዳጅ በህዝባዊ ወገንተኝነትና በዲሲፕሊን የተመራ በመሆኑ ከሶማሊያ ህዝብ አክብሮት የተቸረው ነው።
“እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት” በሶማሊያ ህዝብ ትብብርና በሰራዊታችን ከብረት የጠነከረ ዲሲፕሊን ብሎም ጀግንነት ሲመታ ከአክራሪ ቡድኑ ፈርጥጠው ያመለጡ ርዝራዦቹ በምህፃረ ቃል “አልሸባብ” እየተባለ የሚጠራውን ፅንፈኛ ቡድንን መሰረቱ። ፅንፈኛው ቡድን ብዙም ሳይቆይ የምስራቅ አፍሪካ የአልቃዒዳ ክንፍ መሆኑን አወጀ። ዓለም አቀፍ ጀሃዲስቶችን ከያሉበት ሰበሰበ። በሀገራችን ላይም የጀሃድ ጦርነትን አወጀ። ሆኖም አሁንም በሀገራችን ላይ የተደቀነውን የስጋት አደጋ ለመቀልበስ መከላከያ ሰራዊታችን ወደዚያው አቀና። ከሶማሊያ ህዝብ ጋር በመሆን አልሸባብን ትርጉም በማይኖረው ደረጃ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ይህን ተግባሩን ሲወጣ በዲሲፕሊኑ ሳቢያ ከሶማሊያ ህዝብ የተለመደው ድጋፍ አልተለየውም። በወቅቱ የሶማሊያ የሽግግር መንግሰት ጠንካራ ያልነበረ ቢሆንም በዚያች ሀገር ግን ከበርካታ ዓመታት በኋላ መንግስት እንዲቋቋም መስዕዋትነትን ከፍሏል።
ያም ሆኖ አሸባሪው አልሸባብ ለሀገራችንና ለቀጣናው ስጋት መሆኑን በመቀጠሉ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል እንዲቋቋም ሲደረግ አካባቢውን በሚገባ የሚያውቀው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም ግብዣ ቀርቦለት “አሚሶም” (AMISOM) የተሰኘውን የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ተቀላቅሎ ሶማሊያ ዛሬ ህዝባዊ መንግስት እንድትመሰርትና ፕሬዚዳንቷን በሰላማዊ መንገድ እንድትመርጥ መሰረት ጥሏል። በእኔ እምነት ዛሬ በሶማሊያ የተገኘው አንፃራዊ ሰላም የኢትዮጵያ ሰራዊት ህዝባዊነትና ዲሲፕሊን የተሞላበትን ትግል በማድረጉ ነው። እናም የሶማሊያ ሰላም በኢትዮጵያ መንግስት ሰላም ወዳድነትና በሰራዊቱ ህዝባዊ ወገንተኝነት ብሎም ዲስፕሊን የተገኘ ነው ብል ከእውነታው መራቅ አይሆንብኝም።
ከሶማሊያ ወደ አብዬ ግዛት ስመለስ፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን የሚያጨቃጭቀው የአብዬ ግዛት የሰላም አስከባሪ ሃይል እንዲገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በወሰነው መሰረት የኢትዮጵያ ሰራዊት ብቸኛው ተመራጭ ሊሆን ችሏል። ሱዳንም ይሁን ደቡብ ሱዳን አብዬን በሰላም አስከባሪነት እንዲቆጣጠር አመኔታቸውን የጣሉት በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ ብቻ ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም የኢትዮጵያ ሰራዊት በብቸኝነት በሰላም አስከባሪነት በግዛቲቱ እንዲሰማራ ይሁንታ ሰጥቷል።
እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ምናልባትም እንዲህ ዓይነቱ በአንዴ በሶስት አካላት ተመራጭ የመሆን ሁኔታ በመንግስታቱ ድርጅት ታሪክ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። ብዙውን ጊዜ ሁለት ተቀናቃኞችና ሰላምን የማስጠበቅ ሃላፊነት ያለበት የመንግስታቱ ድርጅት በአንድነት የአንድን ሀገር ሰራዊት በአንድ ድምፅ መምረጣቸው ያልተለመደ ጉዳይ ነው። እናም ይህ በሁሉም አካላት ዘንድ ሰራዊታችን የተቸረው ይሁንታ መሰረቱ ሰራዊቱ ህዝባዊ ወገንተኛ መሆኑ፣ የገለልተኝነት መርህን መከተሉና በጠንካራ ዲሲፕሊን ግዳጁን እንደሚወጣ በሁሉም አካላት ስለታመነበት ነው። ያም በመሆኑ ዛሬም ድረስ ሰራዊታችን በሚያስደንቅ ዲሲፕሊንና ጀግንነት በአብዬ ግዛት ተግባሩን እየተወጣ ይገኛል። ታዲያ እነዚህና ሌሎች ተምሳሌታዊ የሰላም ዲፕሎማሲ ድሎቻችን ተጠናከረው ሊቀጥሉ ይገባል።
ከሰራዊታችን አብነታዊ ሰላምን የማስከበር ጥረቶችና ተቀባይነት ስንወጣ የምናገኘው ሌላኛው ጉዳይ የሀገራችን የአደራዳሪነት ሚና እየጨመረ መሄዱን ነው። ይህ የዲፕሎማሲ ድል በንጉሱ ዘመነ መንግስት ወቅት የነበረ ቢሆንም፤ ተቋማዊና በሰለጠነ መንገድ እየተመራ ይበልጥ ተቀባይነታችን እየጎላና እየደመቀ የመጣው በኢፌዴሪ መንግስት ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ድምፅ መሆን የጀመረችው በኢፌዴሪ መንግስት ነው። ኢትዮጵያ አፍሪካን ብሎም ዓለምን በሚያስጨንቀው የሙቀት መጠን መጨመር የአፍሪካዊያን ልሳን ሆና ብቅ ያለችው በዚሁ መንግስት ነው። የመፍትሔው አካል ሆናም በቅድሚያ በራሷ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫን በአርአያነት ያሳየችውም በኢፌዴሪ መንግስት ነው። ይህ ሁሉ ተግባሯም በየጊዜው ተቀባይነቷ እንዲጎለብት አድርጓል።
በእኔ እምነት የኢፌዴሪ መንግስት በአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ይሁን በአፍሪካ ህብረት ያበረከታቸው አስተዋፅኦዎች በአሁኑ ወቅት ለተጎናፀፈው የዲፕሎማሲ ድል መሰረት ናቸው። እዚህም ላይ ጥቂት ምሳሌዎችን ማንሳት ይገባል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም የሚሰፍንበት ሁኔታን ለመፍጠር ጥረት ማድረግ የጀመሩት በአፍሪካ ህብረት ወቅት ነው። እናም እ.ኤ.አ. በ1992 የሱዳንንና የወቅቱን የደቡብ ሱዳን አማፅያንን ችግር በኢጋድ በኩል ለመፍታትና ለቀውሱ እልባት ለመስጠት ኬንያ-ናይሮቢ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ውጤታማ የሆነበትን ድል አስመዝግቧል። ይህ የሀገራችን ጥረትና የተገኘው ውጤት የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ አድናቆት ሊያገኝ ችሏል።
እርግጥም ለዘመናት በእርስ በርስ ግጭት በዘለቁት የሱዳን መንግስትና የደቡብ ሱዳን የወቅቱ አማፂያን የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ መቻላቸውና ለዚህ ውጤት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ሚና የጐላ ነበር። ምክንያቱም ሁለቱ ወገኖች የሁሉም ነገር መሠረት የሆነው የሰላም ስምምነት ላይ መድረሳችው ቀጣዩን ሁኔታ አመላካች አድርጎት ስለነበር ነው።
በሁለቱ ተቀናቃኝ ወገኖች መካከል እ.ኤ.አ. በ1998 በመዲናችን አዲስ አበባ ለተካሄደው የሰላም ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንግስት የላቀ ድርሻ እንደነበረው የሚዘነጋ አይደለም። በመሆኑም ኢጋድና ሀገራችን ለዓመታት ያካሄዱት ጥረት በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት በማግኘቱ በመጨረሻ እ.ኤ.አ. በ2ዐዐ5 የተደረገው ስምምነት ለውጤት መብቃት ችሏል። ዳሩ ግን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ሀገሪቱ አንዱን ቀውስ ለመፍታት ያደረገችው ጥረት የተሳካ ቢሆንም፣ ሌላ ቀውስ መከተሉ አልቀረም። በዘር ግጭት ላይ የተመሰረተውና የተለያዩ ተዋናዬች የተካፈሉበት የዳርፋር ቀውስ ብቅ አለ። ቀውሱን ለማርገብ እና እልባት ለመስጠት ግን ጥረት መደረጉ አልቀረም። ከዚህ አኳያ በእነ ቻድ የተደረገው ቀጥሎም በአፍሪካ ህብረት የተካሄደው ጥረት እዚህ ላይ ሊጠቀስ ይገባል።
ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለው የዳርፋር ቀውስ በሱዳን መንግስትና በሁለቱ ታጣቂ ሃይሎች መካከል በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የማስማማት ጥረት በአዲስ አበባ ቢካሄድም ለውጤት ሳይበቃ ተበትኗል። ኢትዮጵያ መልካም ጉርብትናን የመፍጠር ፍላጐቷ ከውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲዋ የሚመነጭ በመሆኑ፤ ቀደም ሲል በሁለቱ ሀገሮች ይስተዋል ለነበረው ግንኙነት እንዲለወጥ አስችሏል። በተለይም ከሱዳን ጋር የነበረው ግኝኑነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ ተረርጓል።
እንደ እውነቱ ከሆነ መንግስት በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት የሚመነጨው ሌሎች ሃይሎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚተረጉሙት ሳይሆን የጐረቤቶቻችን ሰላም ለሀገራቸን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታችን መፋጠን ካለው ፋይዳ አኳያ እንደሆነ ሊጤን ይገባል። ለምን ቢሉ እኛ ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለመዋጋት የምናደርገው ትግል ሊሳካ የሚችለው ጐረቤቶቻችን ሰላም ሲሆኑ በመሆኑ ነው። እርግጥም እንኳንስ የድንበር አዋሳኞቻችን ቀርቶ የሩቅ ሀገራት ሰላም መሆንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለእኛ ሰላም መጐልበት ያለው ሚና የላቀ መሆኑ እሙን ነው። ይህም በአፍሪካ ደረጃ በጋራ ሰላም እጅ ለእጅ ለማደግና በዚህም አፍሪካዊ ህዳሴን ማጎልበቱ አይቀሬ ነው።
ያም ሆኖ ኢትዮጵያ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን አማፅያን መካከል የተካሄደው ዘግናኝ ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ ትልቁን ድርሻ ለተጫወተው የኢትዮጵያ መንግስት ያላቸውን ጠንካራ እምነት የገለፁበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህም ይህም ሀገራችን የተጎናፀፈችው ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው።
ደቡብ ሱዳን እንደ የራሷን ነፃ ሀገር ከመሰረተች ጀምሮም ኢትዮጵያ ከአዲሲቷ ሀገር ጋር ያላት ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ያተኮረ ነው። ይህም በንግድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በፀጥታ ጉዳዩች ላይ ያተኩራል። በአሁኑ ወቅትም ከአዲሲቷ ሀገር ጋር ሀገራችን ያላት መልካም ግንኙነት ቀጣናውን በልማት ለማስተሳሰር የምታደርገውን ጥረት እንደሚያጎለብት ተስፋ ተጥሎበታል። ይህም አንዱ የዲፕሎማሲ ድላችን ነው።
በአጠቃላይ ሀገራችን በሰላሙም ይሁን በፖለቲካው መስክ በአፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደማጭና ተፈላጊ እንድትሆን ያደረጋት በየዘርፉ እየተቀዳጀች የመጣችው የዲፕሎማሲ ድል ነው። እናም እነዚህን የዲፕሎማሲ ድሎች ይበልጥ ማጠናከር ተሰሚነታችንን የዚያኑ ያህል የሚያጎለብት በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።