ሰማይ ሲታረስ ባናይም፣ መንግስት  ሲከሰስና  ሲወቀስ ግን ተመልክተናል!

              

ኢትዮጵያ ብዘሃነትን ማስተናገድ የሚያስችል ህገመንግስት  ማጽደቅ በመቻሏ  አንድነቷ  በጠንካራ አለት ላይ  የተመሰረተ ሆኗል። ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት  በርካቶች  ኢትዮጵያ ፈረሰች፣ ተበታተነች፣ ህዝቦች ተጫረሱ፣ አበቃላት፣ ወዘተ  እያሉ ሲያሟርቱባት የነበረ ቢሆንም፤ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  እኛ  የፈለግነው ለዘመናትም የታገልነው ነጻነትና እኩልነትን ፍለጋ እንጂ ለመበታተን አይደለም በማለት ሁሉም አካል መክሮበትና ዘክሮበት የሁሉን ይሁንታ ያገኘ ህገመንግስት ጸደቀ። የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት የዜጎች ሰባዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች ተከብረው ዜጎች በነፃነት የሚኖሩባት አዲሲቷን ኢትዮጵያን እንድትፈጠር ምክንያት ሆኗል።

 

በኢፌዴሪ ህገመንግስት ሳቢያ አገራችን የብዙሃን ፓርቲ ስርዓትን ዘርግታለች። በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራችን በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ። ይህን ሰላማዊ የትግል መስመር አንፈልግም ያሉም አካላት መብታቸውን በሃይል እናስከብራለን በሚል የህዝብና አገርን ጥቅም ለሌሎች አሳልፈው በሚሰጥ መልኩ የወንጭፍ ፓለቲካቸውን ወደ አገራችን እየረጩ  ይገኛሉ። በወንጭፍ  የሚደረግ የፖለቲካ ሂደት ለአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት የሚበጅ አካሄድ አይደለም። በቅርቡ እነዚህ ጽንፈኛ ሃይሎች በአገራችን በረጩት መርዝ ከባድ ዋጋ ከፍለናል። ይህ መርዛማ ድርጊታቸው በቀጣይ እንዳይደገም  በቃችሁ ልንላቸው ይገባል።   

 

ህገመንግስታችን  ሃሳብን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማራመድ ለሚፈልግ ማንኛውም አካል የህግ ከለላ ሰጥቷል። ይሁንና አንዳንድ ሃይሎች ይህን ሰላማዊ የትግል መስመር አሻፈረኝ በማለት ለአገራችንና ለህዝባችን መልካም ከማይመኙ እንደኤርትራ መንግስት ካሉ  አካላት ጋር ሲያብሩ የእነሱን ተልኮ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ እየተመለከትን ነው። ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆኑት ግንቦት ሰባት፣ ኦነግና ኦብነግን  ማንሳት ይቻላል። እነዚህ አከላት በሽብር ድርጊት ተግባራት ውስጥ የገቡት  በሰላማዊ  የመታገያ መንገድ ዝግ  ሆኖባቸው ሳይሆን  ስልጣንን በአቋራጭ ለመያዝ ካደረባቸው  አባዜ የተነሳ ነው።   

 

የኢፌዴሪ ህገመንግስት በየትኛውም ዓለም ዓቀፍ  መስፈርት እጅግ ዘመናዊ የሚባል ህገመንግስት ነው። ህገመንግስቱ ማንኛውም ዜጋ  የሌሎችን መብት  እስካልተጋፋ ድረስ ሃሳቡን ሰላማዊ በሆነ መንገድ  የመግለፅ መብትን አጎናጽፏል።  ህገ-መንግስታችን ዜጎች በነጻነት መንግስትንም ሆነ የመንግስትን አሰራር መተቸት የሚችሉበት ስርዓት ተዘርግቷል። በዚህም የመንግስት ሃላፊዎች ለፈጸሙት ድርጊት ሽልማትም ሆነ ቅጣትን እየተቀበሉ ይገኛሉ። ይህን መልካም ጅምር አጠናክሮ መቀጠል ይኖርብናል።  

 

“ሰማይ አይታረስ መንግስት አይከሰስ” የሚለው ብሂል በርግጥ ሰማይ ሲታረስ ባናይም መንግስት ግን አሁን ላይ ለእያንዳንዷ ጥፋቱ ሲከሰስ፣ ሲወቀስ፣ ሲብጠለጠል፣ ወዘተ ተመልክተናል። ለዚህ ጥሩ ማሳያው ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ የኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት እያንዳንዱ አካል የፈጸማትን ጥፋት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ሪፖርት አውጥቷል። በዚህም ተጠያቂ አካሎች ወደ ህግ ፊት እንደሚቀርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው በአንደበታቸው መስክረዋል። ይህ ነው የህግ የበላይነት!

 

በአገራችን በፖለቲካዊ አስተሳሰብ መደራጀትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የተለመደ ተግባር  በመሆኑ ማንም ሃሳቡን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ስለገለጸ ጫና ሊደርስበት አይችልም። ይሁንና ይህን መብት በመፈጸምና በማስፈጸም ረገድ ጉድለቶች አይኖርም ብዬ አላስብም። ይህን ታግሎ ማስተካከል የሁላችንም ሀላፊነት መሆን መቻል ይኖርበታል። የአገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት  ጅምር ነሆኑን መዘንጋት የለበትም። እያንዳንዷን ድርጊት ለስርዓቱ ማሳያ እያደረጉ ማቅረብ ለማንም የሚበጅ አካሄድ አይመስለኝም።  

 

አገራችን የተከተለችው ፌዴራላዊ የአስተዳደር ዘይቤ  የህገ-መንግስታችን ውጤት ነው። የፌዴራል ስርዓታችን በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል እንዲሰፍን አድርጓል። ሕገ-መንግሥቱ በፌዴራሉ ሥርዓቱ ውስጥ በሕዝቦች መካከል እንዲዳብር ስለሚፈለገው አንድ የጋራ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ቀድሞ አስቀምጧል። በህዝቦች መካከል ምን አይነት  ግንኙነትና አንድነት  መዳበር እንደለበት መሠረታዊ መርሆዎችን ያስቀምጣል። የፌዴራል ስርዓቱ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ፣ ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ እንዲሁም  ዜጎች በቋንቋቸው እንዲዳኙ፣ ወዘተ መብቶችን አስገኝቷል።   የፌዴራሉ ሥርዓት በክልሎችና  በመዓከላዊ መንግስት መካከል ስለሚኖረው ሚዛናዊ የሥልጣን ክፍፍልም  ቁልፍ መርሆዎችንም ያስቀምጣል።

 

አገራችን የፌዴራል ስርዓት መተግበር በመቻሏ ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው  ማልማት እንዲችሉ እንዲሁም የፌዴራል መንግስቱ በሁሉም አካባቢ ተመጣጣኝ ዕድገት እንዲኖር  በማድረጉ ፍተሃዊ የሃብት ክፍፍል በአገሪቱ ተፈጥሯል። እያንዳንዱ ክልል ለውድቀቱም ሆነ ለዕድገቱ የመጀመሪያዎቹ ተጠያቂዎች በቅርበት የሚገኙ የአካባቢ አስተዳደሪወዎች መሆናቸውን ማወቅ መቻል አለበት።

 

ባልተማከለ የአስተዳዳር ስርዓት እንኳን የፌዴራል መንግስት ይቅርና ክልሎችና ዞኖች በእያንዳንዷ  ጉዳይ በወረዳዎችና በአካባቢ አስተዳደሮች የውስ ጉዳይ እንደፈለጉ የሚገቡበት ሁኔታ አይኖርም። ይህ ማለት  የአካባቢ የህዝብ ተወካዮች ትልቁን ሃላፊነት ይወስዳሉ ማለት እንጂ  የፌዴራል መንግስቱም  ቢሆን  የራሱ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል።  በፌዴራል ስርዓት ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ መብትን ብቻ ሳይሆን ግዴታንም ጭምር ያስቀምጣል። በዚህ የአስተዳደር ዘይቤ የአገራች በርካታ ለውጦችን  አገኝታለች። በማግኘትም ላይ ነች። 

 

በህገ-መንግስታችን የሃይማኖት ነጻነትንም  አጎናጽፎናል። ዛሬ በአገራችን መንግስታዊ ሃይማኖትም ሆነ ሃይማኖታዊ መንግስት የለም። በሃይማኖት ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሱ ተፅዕኖዎች ተወግደው የሁሉም ሃይማኖት ተከታዮች በእኩልነት የሚስተናገዱባት  አዲሲቷ ኢትዮጵያ ተፈጥራለች። ሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮታቸውን በነጻነት የሌሎችን መብቶች አክብረው ማስተማር የሚችሉበት ሁኔታ በአገራችን ተፈጥሯል። ይሁንና አንዳንድ ጽንፈኛ ሃይሎች የራሳቸውን ሃይማኖት የተሻለና ትክክለኛ አድርገው በማሰብ በሌሎች ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። ይህን ተግባር ሁሉም በቃችሁ ሊላቸው ይገባል።

በአገራችን የታየው ልማትና እድገትም ቢሆን የህገ-መንግስታችን ውጤት ነው። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት አገራችን በታሪኳ አከናውናው የማታውቃቸውን እጅግ ግዙፍ የሆኑ ባለ ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን መገንባት ችላለች። ለአብነት ያህል ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግንባታ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ፣ ዘጠኝ ግዙፍ የስኳር ፋብሪዎችና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታዎች እንዲሁም ሰፋፊ የመንገድ ግንባታ፣ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ዝርጋታ ወዘተ አገልግሎት በመስፋፋት ላይ ናቸው።  እነዚህ ትላልቅ  መሰረተ ለማቶ የአገራችንን ዕድገት ወደ ፊት በማራመድ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው እሙን ነው።ህገመንግስታችን በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማድረጉ ልማታችን ሊፋጠን ችሏል።

 

ከላይ እንደጠቀስኩት የኢፌዴሪ ህገመንግስት ዘመናዊነት ከሚያሳዩ ነገሮች  መካከል ህዝቦች አብረው መኖርን የሚያጎለብቱ አንቀጾችን ከማካተቱ ባሻገር ከፌዴራል ስርዓቱም መውጣት ለሚፈልግ አካል በሰላማዊ መንገድ  የሚፈጸምበትን ሁኔታዎች  አካቷል።  ከፌዴራል ሥርዓቱ ለመውጣት የሚሹ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የሚከተሉትን ሕጋዊ ሥርዓትም ሕገ-መንግሥቱ  በግልፅ አስቀምጧል። ይህን ህጋዊ መስመር የሚከተል ማንኛውም አካል ከፌዴራል ስርዓቱ መገንጠል የሚፈልግ አካል በህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት በአግባብ የሚስተናገድበት ሁኔታ ተቀምጧል።

ህገመንግስታችን ይህን ያህል የዜጎችን ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያስጠበቀ እጅግ ዘመናዊ አስተሳሰብን የያዘ ሰነድ ነው። የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ገና ከመግቢያው ጀምሮ ሕዝቦች አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያ ማኅበረሰብ እንዲፈጥሩ፣ በህዝቦች መካከል መከባበርና መቻቻል እንዲሰፍን  የሚያደርጉ አንቀጾችን ያሰፈረ ሰነድ ነው። ከዚህም ባሻገር ሕገ-መንግሥቱ ሁሉም ዜጎች የሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በእኩልነት መከበር እንዳለባቸው በግልጽ የሚደነግጉ አንቀጾችን አካቷል። ይህ ሰነድ የአገራችን የህልውና መሰረት በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበርም ግዴታ አለበት።