በህዳሴው ግድብ ግንባታ ጉዳይ ላይ ግብፅ የዓለም ባንክ አደራዳሪነት እንዲኖር ያቀረበችውን ጥያቄ ኢትዮጵያ እንደተቃወመችው ይታወቃል። ይህም አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት አለባቸው ከሚል ጽኑ አቋም እና ትክክለኛ ውሳኔ የተነሳ ነው።
ይህ የኢትዮጵያ ተቃውሞ አገራችን አንድን ነገር ያለ ምክንያት የማትቃወም መሆኗን የሚያሳይ ነው። የአባይ ወንዝ ጉዳይ አስሩንም የተፋሰሱን አገራት የሚመለከት እንጂ በኢትዮጵያና በግብፅ ስምምነት ላይ ብቻ ያተኮረ አለመሆኑን እንዲሁም የህዳሴው ግድብ ግንባታ ጉዳይም የሦስትዮሽ አገራት ጉዳይ እንጂ አገራችን ከግብፅ ጋር በተናጠል የምታራምደው ግንኙነት እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ ነው።
ይህ እውነታ ትናንት ግብፆች ኢትዮጵያን ባገለለ መንገድ የቅኝ ግዛት ውሎችን ከሱዳን ጋር ሲዋዋሉ እንደነበሩ ሁሉ፤ ዛሬም አገራችን ያንን ከፋፋይ አስተሳሰብ ልትከተል የማትችል መሆኗን ያረጋግጣል።
እንደሚታወቀው ሁሉ ሀገራችን የናይል ወንዝ አጠቃቀምን አስመልክቶ በእንግሊዝና በግብጽ የተካሄደው የ1929ኙ ስምምነትንም ይሁን በግብጽና በሱዳን መካከል የተፈረመው የ1959ኙ ስምምነት ተቀባይነት እንደሌለው ስታሳውቅና አቋሟን ስታንጸባርቅ መቆየቷ ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይደለም፡፡ የስምምነቱን ኢ-ፍትሃዊነትንም እንዲሁ፡፡
ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መንግስታት ሁሉ በአባይ ውኃ አጠቃቀም ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል፡፡ እርግጥም “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” እንደማይታሰብ ሁሉ፤ ሁሉንም የተፋሰሱን ሀገራት ያላከተተውና በሁለቱ የታችኛው ተፋሰሱ ሀገራት መካከል የተካሄደ ስምምነት ተቀባይነት የሌለው መሆኑ አይካድም፡፡ ሆኖም የላይኛው ተፋፈስ ሀገራት አቋም ሰሚ ጆሮ ማግኘት አልቻለም፡፡
በተለይም በግብጾች በኩል ይህ “የቅኝ ገዥዎች” ስምምነት የማይጣስ መሆኑን ከመግለፅ ባለፈ፣ ከዛቻ አዘል ማስፈራሪያዎች ጋር ሲሰነዘር ቆይቶ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያን ዋነኛዋ የትኩረት አቅጣጫ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ዓለም ያወቀው ሃቅ ነው፡፡
ታዲያ እዚህ ላይ ግብጾች ሊያውቁት የሚገባው ነገር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ የምትሰጥበት ጊዜ ያከተመ መሆኑን እንዲሁም በእኩልነትና ምክንያታዊነት በጋራ የመጠቀም መርህ ጽኑ አቋሟ ሊቀለበስ እንደማይችል ነው፡፡
ለነገሩ “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንደሚባለው እነዚህ በሙባረክ ዘመን እሳቤ የሚዳክሩ አሮጌ ፍራሽ አዳሽ የግብፅ ሚዲያዎችና አንዳንድ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ አቋም በሚገባ ስለሚያውቁት እዚህ ላይ ብዙ ማለት አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡
በዘመነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮችን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ተግባብቶ መፍታት አንዱ የስልጣኔ መገለጫ ነው። ማናቸውም አለመግባባቶች ባህሪያዊና በሰው ልጅ መስተጋብሮች ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ክስተቶች በመሆናቸው መፍትሔያቸው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መሆን እንደሌለበትም ይታመናል።
እናም በማናቸውም ቦታ የሚከሰቱ አለመግባባቶች ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ አካላት መካከል የሚከሰት በመሆኑ የመፍትሔ አማራጮች ሊሆኑ የሚችሉት ሁሉም ወገኖች አሸናፊ የሚሆኑበት መንገድ እንጂ፤ ባለፉት አሮጌ ዘመናት አሳፋሪ ማንነት እየቆዘሙና ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብን እያቀነቀኑ አንደኛው በሌላኛው ላይ ቀረርቶና ፉከራ በማሰማት የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም አሊያም እኩይ ሴራዎችን በመጎንጎን ተፈፃሚ የሚሆን አይደለም።
ይህን መሰሉ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ ምልከታም የትኛውንም ወገን ቢሆን አሸናፊ የማያደርግና የማይጠቅም ከመሆኑም በላይ፤ በዘመናዊው ዓለም ውስጥ በአላዋቂ ተጓዥነት መገለልን በማስከተል የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ አይቀሬ ነው። “በትናንት በሬ ያረሰ የለም” እንዲል የሀገራችን አርሶ አደር፤ የትናንቱ አሮጌ አስተሳሰብ እንዳለቀ ሸማ ወልቆ መጣል ያለበት ትናንት ነው—ዛሬ ላይ እንኳንስ ቦታ ሊኖረው ቀርቶ አዳማጭም የለውምና።
በተለይም ለዘመናት የአፍሪካንና የልጆችዋን ማንነት ሲያዋርድ፣ ልጆችዋን በባርነት ሲሸጥና ሲለውጥ እንዲሁም አንጡራ ሃብቶቿን ሲቦጠቡጥና ለራሱ ጥቅም ሲል መርዛማ ውሎችን ሲከትብ የኖረው የቅኝ አገዛዝ ኢ-ሰብዓዊ አስተሳሰብ በፀያፍነቱ ሳቢያ ዛሬ ላይ ከታሪክነት በዘለለ ሰሚ ጆሮ የለውም።
ይህን ፀረ-ሰውዓዊ እሳቤን ከላያቸው ላይ አሽቀንጥረው ለመጣልም አፍሪካውያን በተናጠልም ይሁን በቅንጅት ታግለዋል፤ ህይወታቸውንም ቤዛ አድርገዋል፤ ታስረዋል፤ ተሰቃይተዋል፤ ቤት ንብረታቸውንም አጥተዋል— “ሰውነታቸውን” ከሰው በታች አውርዶ በመፈጥፈጥ እንዳሻው ሲያደርጋቸው የነበረውን አስከፊ ተግባር ከነ ግሳንግስ አስተሳሰቦቹ ለማስወገድ።
እናም ይህ ዘረኛ ተግባር ዛሬ በአፍሪካ ልሳነ-ምድር እንኳንስ አስተሳሰቡ ገቢራዊ ሊሆን ቀርቶ የሚታሰብ አይደለም። ምንያቱም አርጅቶ የተቀበረው የቅኝ አገዛዝ እሳቤ በያኔው የአህጉሪቱ ድርጅትም ይሁን በአሁኑ ህብረት ውስጥ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ነው።
የዓባይ ጉዳይ የ10ሩ የተፋሰሱ ጉዳይ አገራት እንጂ የሌላ ወገን ሊሆን አይገባም። ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ዓለም አቀፋዊው የእኩልነትና የፍትሃዊነት መርህን መሰረት ላደረገው የኢንቴቤው የስምምነት ማዕቀፍ ተግባራዊነት በግንባር ቀደምትነት ተሰልፋለች፡፡
መላው ዜጎቿም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬታማነት ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን እያበረከቱ የሚገኙት ደግሞ ግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትን ሙሉ ለሙሉ የሚያረጋግጥ መሆኑን ጥንቅቀው ስለሚያውቁ መሆኑን ማንም አይክድም፡፡
የተፋሰሱ ሀገራት በዚህ ብቻ አልተወሰኑም። በተፈጥሯዊው የውሃ ሃብታቸው በእኩልነትና ፍትሃዊነት መርህ የመጠቀም መብታቸው የማይገደብ መሆኑን ሊገነቧቸው ያቀዷቸውን ፕሮጀክት ይፋ በማድረግ ቁርጠኝነታቸውንም አመላክተዋል፡፡ ይህ አቋማቸውም የግድቡን ሀገራዊና አህጉራዊ ጠቀሜታ በግልጽ ማመላከት የቻለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነት ጠንካራ አቋምንም እንዲሁ፡፡
እናም የአፍሪካዊያን ችግር በአፍሪካዊያን መፈታት አለበት የሚል አቋም የያዘችው አገራችን ትናንትም ይሁን ዛሬ ለአፍሪካዊያን ያላትን ከበሬታ ከማሳየት ባለፈ፤ ዓለም ባንክም ይሁን ሌላ ሶስተኛ ወገን የአፍሪካዊያንን የጋራ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ አይችልም ከሚል እውነታ የተነሳ ነው። ይህ የሀገራችን አቋም 21ኛውን ክፍለ ዘመን የሚወክልና ምክንያታዊ ተቃውሞ መሆኑን ማንም የሚክደው አይደለም። ግብፆች ትናንት ቅኝ ዥዎች ያሰመሩላቸውን መስመር ዛሬም መከተል እንደማይገባቸው ያስተማረ ትክክለኛ ምላሽ ነው ብዬ አስባለሁ።