ራዕይን የሰነቀው ዘርፍ

የአገራችንን ልማት ቀጣይነት ያለውና ህዝባችንን በየደረጃው ተጠቃሚ ላይ የሚገኝ ነው። ይህም በዜጎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የቻለ ነው። በተለይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተገኘው እመርታ የለውጥ አብነት እየሆነ ነው ማለት ይቻላል። ዘርፉ ትናንት ከነበረበት ምንም ሊባል ከሚያስችል ሁኔታ ተነስቶ ዛሬ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህም በአገራችን ምጣኔ ሃብታዊ ለውጥ ላይ ጉልህ ለውጥ እያመጣ ነው።

የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደ ሌሎች የልማት ዘርፎች በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትኩረት የተሰጠው ነው። በዚህም ሊደርስበት የታሰበው ግብ የሀገሪቱን መዋቅራዊ ለውጥ ሊያሳካ የሚችል ይሆናል።

እንደሚታወቀው ሁሉ ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ኢንቨስትመንቶች ገበያው ላያስተናግዳቸው እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ፈጣን ዕድገቱን ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የዚህ ዓይነት የኢንቨስትመንት መስኮች በጥንቃቄ እየተጠኑና እየተመረጡ በቀጥታ በመንግሥት በራሱ ብቻ ወይም ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ እንዲካሄዱ እያደረገ ነው።

ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጡን ለማስጀመር የማምረቻ ኢንዱስትሪው በየዓመቱ ቢያንስ የ24 በመቶ ዓመታዊ አማካይ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርበታል። በዚህም በ2012 ዓ.ም የማምረቻ ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ያለውን ድርሻ ወደ ስምንት በመቶ ከፍ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል። ይህም የማምረቻ ኢንዱስትሪው ድርሻ አሁን ካለበት በአራት እጥፍ በማሳደግ በ2ዐ17 ዓ.ም ወደ 18 በመቶ እንዲደርስ ምቹ መደላድል ይፈጥራል።

የማምረቻ ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ሚና ከፍተኛ ነው። እንደሚታወቀው በአሁኑ ወቅት የዘርፉ ምርቶች ጠቅላላ የኤክስፖርት ገቢ ያላቸው ድርሻ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ ውስጥ ከ1ዐ በመቶ የማይበልጥ ነው። ሆኖም በዕቅዱ መሰረት በ2012 ላይ ወደ አምስት ቢልዮን ዶላር ገቢ እንዲያስገኝ ለማድረግ ታስቧል። ይህ ድርሻም ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግና በ2017 ዓ.ም 40 በመቶ ለማድረስ ግዙፍ ዕቅድ ተቀምጧል።

ሌላው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጡ አመላካች የሚሆነው በሚቀጥሉት ዓመታት ወደ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የሚደረገው የሰው ሃይል ሽግሽግ ነው። ይህም በአሁኑ ወቅት በመካከለኛና በከፍተኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የተሰማራውና ከ350 ሺህ የማይበልጠውን የሰው ሃይል በቀጣዩቹ አስር ዓመታት በአራት እጥፍ እንዲጨምር ለማድረግ ታስቧል። ይህም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዩን ዜጎች የስራ ዕድል እንዲያገኙ እድል የሚፈጥር ነው። እነዚህን የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ልማታዊ ፋይዳዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግስት ብርቱ ርብርብ እያደረገ ነው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ማንኛውም ሀገር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ መስኮች ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋል። ልማቱ እንደ ጨርቃጨርቅ በመሳሰሉ ቀላል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በርካታ የስራ ዕድል የሚፈጠር እና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትንም በስፋት መሳብ የሚችል ነው።

ይህም የህዝቦችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድም የራሱን ሚና ይጫወታል። ከዚህ ጎን ለጎንም የቀላል ማኑፋክቸሪንግ ልማቱን ያፋጥናል፤ ከተሞችን ወደ ላቀ የዕድገት ደረጃ የማሸጋገር ብሎም አዳዲስ ከተሞች እንዲፈጠሩና በዚያኑ ልክም የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ የራሱን አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።

በሀገራችን የተተለመው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፕሮግራም መሬትን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለልማት ስራ ብቻ እንዲውል የሚያደርግና የኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚዘጋ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ይመስለኛል። እርግጥም ልማቱ ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሚወጣውን ወጪ በተቀናጀ መልኩ መጠቀም የሚያስችልና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ኢንዱስትሪዎችን በእሴት ሰንሰለት እርስ በርስ ስለሚያስተሳስር ብክነትን የሚቀንስና የኪራይ ሰብሳቢነትን በመዋጋት ረገድ ሚናው የጎላ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚከናወኑ ስራዎችን በሂደት በሀገር ውስጥ የሙያው ባለቤቶችና በሀገር በቀል ተቋማት አማካኝነት እንዲከናወኑ መሰረት ይጥላል። ይህም የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ ሰፊ ዕድልን ይፈጥራል። ይህ የቴክኖሎጂ ሽግግርም ለአገር ውስጥ ባለሃብት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው።

እርግጥ በማደግ ላይ የሚገኘው የሀገራችን ባለሃብት የለውጡ ተሳታፊ እንዲሆን እንዲሁም በተመረጡ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ተግባሩ እንዲከናወን ማድረግ ያስፈልጋል። እናም ከሀገር ውስጡ ባለሃብት በተጨማሪ የውጭ ባለሃብቶች በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚኖራቸው የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ተሳታፊነት የማይናቅ ቦታ ይኖረዋል። ይህም የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን ጉልህ ሚና አለው።

ይህን መሰረታዊ ዕውነታ በመመርኮዝም በዕቅድ ዘመኑ በሁሉም ዘርፎች ጥንቃቄ በተሞላው ሁኔታ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብርቱ ጥረት ይደረጋል። በተለይም  ከፍተኛ አቅምና ፍላጎት እንዲሁም በአፈፃፀማቸው ጥሩ ስምና ዝና ያላቸውን የውጭ ኩባንያዎች በመመልመልና የማግባባት ስራ በማከናወን የዘርፉን ዕድገት እንዲያሳድጉት ማድረግ እንዲገባ ተጠቅሷል። ባለሃብቶቹን ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች ላይ በማሰማራት ሀገራችን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ ውጥን ተይዟል።

እርግጥ ሀገራችን የውጭ ባለሃብቶች ኤክስፖርት ተኮር በሆኑ ዘርፎች ውስጥ እንዲካተቱ ስታደርግ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ምንም ዓይነት ቦታ ሳትሰጥ ነው ማለት አይደለም። የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም መዋዕለ ንዋያቸውን በዘርፉ እንዲያፈሱ ይደረጋል።

በተለይም በማደግ ላይ የሚገኙት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ተመልምለው በቂ ድጋፍ እንደሚሰጣቸውና በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ገቢ ምርቶችን በሚተኩ ዘርፎች ጭምር እንዲሳተፉ ስለሚደረግ አቅማችንን ከፍ ያደርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንጂ ለብቻው ተፈፃሚ እንዲሆን ብቻ አይደለም። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ኢንቨስትመንትን ዕውን ከማድረግ አኳያ መቆራኘት ይኖርበታል። ይህን ዕውን ለማድረግም በአሁኑ ወቅት ያሉትም ይሁኑ በቀጣይ ወደ ስራ የሚገቡት ኢንዱስትሪዎች፤ የቴክኖሎጂ አቅማቸውን፣ ምርታማነታቸውን፣ የጥራት አመራር አቅማቸውን ብሎም ተወዳዳሪነታቸውን በቀጣይነት መገንባት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋል። 

ከዚህ ጎን ለጎንም የሳይንስ፣ የቴክኖሎጅና የኢኖቬሽን አቅምን ለማሳደግ ከሀገሪቱ የዕድገት ፍላጐት ጋር የተጣጣመ የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማድረግ በዕቅዱ ላይ ተቀምጧል። ይህን ለማከናወንም በተለይ ለሀገር ውስጥ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። ስለሆነም በዘርፉ እስካሁን ድረስ የተደራጁ የኢንዱስትሪ ልማት ደጋፊ ተቋማትና ዩኒቨርስቲዎች አቅማቸው ይበልጥ እንዲጎለብትና ጥራት ባለው የትምህርት ማሳለጫዎች እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። ከውጭ መሰል ተቋማት ጋር የሚኖራቸው ቁርኝትና እንዲጠናከር አሰራራቸውም እንዲዘምንም ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል። ይህ ትልቅ አገራዊ ራዕይ ነው። ራዕዩን ለማሳካት ዜጎች የየድርሻቸውን ሚና ሊወጡ የግድ ይላል።