30ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ስብሰባ ዘንድሮ በአገራችን መካሄድ የቻለው አፍሪካውያን ወንድሞቻችን በአገራችን ዘላቂ ሰላም ላይ ባላቸው ፍጹም መተማመን ሳቢያ ነው። አፍሪካዊያን በህዝባችን አኩሪ የእንግዳ ተቀባይነት ባህልና እሴት የሚኮሩ እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን በሚሰጡት የላቀ አክብሮት ስብሰባው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲደረግ መወሰኑ ይታወቃል። በመሆኑም ይህ ሰላማችንን አስተማማኝ የማድረግ ስራችን፣ አኩሪ የሆነው እንግዳ አክባሪነታችንና ተቀባይነታችን ወደፊትም ሊጠናከሩ ይገባቸዋል።
ህብረቱ ጉባኤውን እዚህ አገራችን ውስጥ ሲያደርግ ለሰላም ወዳድነታችን እውቅና ሰጥቶ ነው። ለዚህ ደግሞ ሀገራችን ቀደም ሲል ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኋላም፣ ለአፍሪካ ህብረት ያደረገቻቸውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ከግምት ውስጥ ገብቶ ይመስለኛል። ታዲያ እዚህ ላይ ህብረቱ ለ26ኛ ጊዜ የሚያካሂደውን የመሪዎች ጉባኤን ስናስታውስ ሀገራችን ለአህጉሪቱ ያበረከተችውን አስተዋፅኦ በመጠኑም ቢሆን መዳሰስ ተገቢነቱ የሚያጠያይቅ አይመስለኝም—ህብረቱ ለኢትዮጵያ ያለው ቦታ የተለየ ነውና።
ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ ሰላም መርሁ በሆነው የኢፌዴሪ መንግስት አማካኝነት አፍሪካዊ አስተዋፅኦውንና ኃላፊነቱን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል። በዚህ መሰረትም በሩዋንዳ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ በተከሰተውና የዓለምን ሕዝብ ባስደነገጠው የዘር ማጥፋት እንቅስቃሴ ሰላም እንዲያስከብሩ ከተደረጉት ሀገሮች አንዷ ሀገራችን ተደርጓል። ያኔ ቡሩንዲ ውስጥ ሁቱና ቱትሲ የተባሉ ጎሳዎቿ ግጭት ላይ ነበሩ። ዘር ለይቶ የተፈጠረውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም በአፋጣኝ ሰላም አስከባሪ ኃይላቸውን እንዲልኩ ከተደረጉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። በዚህም ታሪካዊ አስተዋጽኦዋን አበርክታለች። በላይቤሪያም እንዲሁ። ላይቤሪያ በከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሀገሪቱን ወደ ሠላምና መረጋጋት ጎዳና ለመመለስ በተደረገው ሂደት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪነት ሚና የገዘፈ ነበር። በዚያች ሀገር ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በማድረግም ሀገራችን የተጫወተችው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በሱዳን ዳርፉር ግዛት ከሌሎች ሀገሮች ጋር በመሆን ባሰማራችው ሰላም አስከባሪ ሃይልም የእርስ በርስ ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ላይ መሆኗም ይታወቃል። ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በይገባኛል በሚከራከሩበት የአብዬ ግዛት ከዓለም በብቸኝነት ተልዕኮውን የሚወጣ ሰላም አስከባሪ ኃይል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ሥር በመሆን አሰማርታለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነቷን ያሳደገ ተግባርም እየከወነች ነው። ሀገራችን በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ሠላም፣ ጸጥታና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ባለችው ሚና በሶማሊያ የነበረውን መንግሥት አልባነትና አክራሪነት በመታገልም ውጤታማ መሆን ችላለች።
እርግጥ ሰላማቸው የተረጋገጠ፣ በኢኮኖሚያቸው የበለጸገና ዴሞክራሲ ያበበባቸው ጎረቤቶች የጋራ ጥቅም መሠረት መሆናቸው የማይታበይ ቢሆንም፤ ሀገራችን ከዚህ ባለፈ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች ሰላም ያለማሰለስ በመሥራት ላይ ትገኛለች። ለዚህም በአሁኑ ወቅት በአዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን ውስጥ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት የበኩሏን ጥረት በማድረግ የዚያች ሀገር ህዝብ የሰላም አየርን እንዲተነፍስ በማድረግ በገለልተኝነት የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ከዚህ በተጨማሪም ሀገራችን በኢኮኖሚው መስክ ያላት አህጉራዊ ትብብር ኮሜሳ በሚሰኘው በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ የጋራ ገበያ የተጠናከረ ውህደት ለመፍጠር ያላት ሚናም ከፍተኛ ነው። በመሠረተ-ልማት ግንባታ መስክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ጥረት እያደረገች ነው። የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግም በመሥራት ላይ ነች።
ከጅቡቲ፣ ከሱዳንና ከኬንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከታንዛኒያ ጋር የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ለጋራ ተጠቃሚነት በመትጋት ላይ ትገኛለች። በዚህም ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኝ የባቡር መስመር ግንባታው ተጠናቅቋል። ከኬንያ ጋር የሚያገናኘው መስመርም ወደ ስራ እንዲገባ ጥረት እየተደረገ ነው።
ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ከማድረጓም በላይ፤ ኬንያንን እንዲሁም ታንዛኒያን በተመሳሳይ ሁኔታ በኤሌክትሪክ ኃይል ለማስተሳሰር ጥረት እያደረገች ነው። ይህ ሁኔታም ወደፊት ለአፍሪካ ህብረት አንድ መሆን ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን ዕገዛ ሊያደርግ እንደሚችል ህብረቱ የሚገነዘበው ይመስለኛል።
በተለይም 6ሺህ 450 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ጎረቤት ሀገሮችንም ለመጥቀም እያደረገች ያለችው ጥረት በህብረቱ የሚታወቅ ነው። በአህጉሪቱ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን ለማስፈን የተያዘውን ጥረትም በአፍሪካ እርስ በርስ መገማገሚያ ስልትንም “በኔፓድ”አማካኝነት እንዲተገበር ፋና ወጊ ተግባራትን አከናውናለች።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የተገነባበትን 2ሺህ ስኩዬር ሜትር መሬት በነፃ ከመስጠቷም በላይ፤ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት ግንባታ ዕውን እንዲሆን ከህብረቱ መሪዎች ጋር በመሆን የቻይናን መንግስት በማግባባት ያደረገችው አስተዋጽኦ በህብረቱ የታሪክ ድርሳን ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ሃቅ ነው።
አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መናኸሪያ እንድትሆን በማድረግም የአፍሪካን ገፅታ እየገነባች ነው። በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ውስጥ የሚካሄዱት ጉባዔዎች፣ ስብሰባዎችና ዐውደ ጥናቶች…ወዘተ. ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር አንድ የአፍሪካ ከተማ በዚህ ረገድ ተመራጭ እንድትሆን ያደረገ ስለሆነ ለህብረቱ ሀገራትም በኩራት የሚመዘገብ ነው። አፍሪካዊ እሴትን በመጨመር ረገድም ዋጋው ከፍ ብሎ የሚታይ ይመስለኛል።
እነዚህ ጥቅል ዕውነታዎችም የአፍሪካ ህብረት ሀገራችንና ህዝቦቿ በሰላም ውስጥ ለአህጉሪቱ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ የሚገባና ህብረቱ ሁሌም ሀገራችን በምትሰጠው መረጃ ላይ እንዲመሰረት ያደረገው ነው ማለት ይቻላል። የአፍሪካ ህብረት የኢፌዴሪ መንግስትና ህዝቡ ለሰላም ያላቸውን ፍፁም የማያወላውል አቋም በሚገባ ይገነዘባል።
ላለፉት 25 ዓመታት ሀገራችን የራሷን ሰላም ዕውን ከማድረግ አልፋ የአፍሪካውያንን ሰላም ስትጠብቅ እንደነበረች ከህብረቱ መሪዎች የሚሰወር ዕውነታ አይመስለኝም። ህብረቱ የኢፌዴሪ መንግስት በሀገር ውስጥ የሚያከናውነው ሰላምን አስተማማኝ የማድረግ ስራዎችን ይረዳል። ቀደም ባሉት ዓመታትም የህብረቱን ጉባኤዎች ፍፁም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ሀገራችን ማስተናገዷንም ያውቃል። ለዚህም መንግስትና ህዝቡ የሚያካሂዱትን ማህበረሰብ አቀፍ የፀጥታ አጠባበቅ ሁኔታ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ይገነዘባል። በዚህም ሳቢያ ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ አድርጓል።
በሌላ በኩልም ህብረቱ የኢትዮጵያን ህዝብ እንግዳ ተቀባይነት በሚገባ ያውቃል። እንድጋ አክባሪነት፣ ለአፍሪካዊያን ቅድሚያ መስጠት፣ የትኛውንም አፍሪካዊ እንደ ራስ አድርጎ መመልከት የኢትዮጵያዊያን እሴቶች መሆናቸውን ይገነዘባል። እነዚህ ለዘመናት ሲገነቡ የመጡ እሴቶቻችን ሁሉንም አፍሪካዊ የሚያኮሩ እንደሆኑ ያውቃል። እናም አዲስ አበባ ውስጥ ጉባኤው እንዲካሄድ የተወሰነው በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶችና አኩሪ እሴቶቻችን በመሆኑ ተግባሮቹ ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል።