አጀንዳን የማሳከር አጀንዳ

መንግስት የአገራችንን ወቅታዊ ችግሮች ለመፍታት በአጀንዳነት የያዛቸው ዋነኛ ጉዳዩች አገራዊ መግባባትን መፍጠር፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋትና የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ወደ ተግባር መግባት ናቸው። እነዚህን ችግር ፈቺ ዋነኛ ጉዳዩችን ለመፈፀምም የተለያዩ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

እስረኞችን መፍታት የመንግስት ዋነኛ አጀንዳ አይደለም። ፅንፈኞች ግን እስረኞችን የመፍታት ጉዳይ የመንግስት ዋነኛ አጀንዳ አድርገው ይገልፃሉ። ይህ ፈፅሞ የተሳሳተ አመለካከት ነው። ምክንያቱም እስረኞችን የመፍታት ጉዳይ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ሥር ከተጠቃለሉ በርካታ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ብቻ ስለሆነ ነው።

የጽንፈኞቹ ሃሳብ ትክክል ያልሆነ ብቻ ሳይሆን አጀንዳን የማሳከር ዓላማ ያለው ነው። ጽንፈኛው ኃይል ሆን ብሎ እያደረገ ያለው የህዝቡን ትኩረት ለማሳትና ሙሉ ሃይሉን በእስረኞች መፈታት አሊያም በአንድ እስረኛ ጉዳይ ላይ ማተኮርን ነው። ይህ ግን ቅንጣት አስተሳሰብ ነው። በአንድ ቁንፅል ጉዳይ ላይ ተንተርሶ አጀንዳን ለማሳከር የህዝቡን የስራ ተነሳሽነት ለመግደልም የታለመ ነው።

መንግስት በአገራችን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት አገራዊ መግባባትን ለማጠናከር እየሰራ ነው። ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አገራዊ መግባባት ኖሮ አንድ የጋራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ እንዲኖር ይሻል። ሥርዓቱ በሂደት ራሱን በራሱ እያረመ ለዛሬው የህዝቦች መፈቃቀድና አንድነት መጠናከር ጉልህ ተጫውቷል። ይህ የአገራዊ አንድነት ሁኔታ ይበልጥ መጥበቅ አለበት። ታዲያ ለዚህ ጥንካሬያችን ህገ መንግስቱን ምርኩዝ ማድረግ ይኖርብናል።

በህገ መንግስቱ ላይ እንደተገለፀው የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመገንባት ቃል ገብተዋል። በዚህ ሰነድ መሰረት እየተመሩም ኢኮኖሚቸውን አሳድገዋል። በአንድነታቸው ጥላ ስር ሆነው የቀጠናው መሪነት ሚናቸውን እያጠናከሩ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከሀገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይወት ተገልለውና ተረስተው በባይተዋርነት ለመኖር የተገደዱበት አድሎአዊና ፍትህ አልባ ሁኔታ ውስጥ እንዲያልፉ ተደርገዋል። ዛሬ ግን ይህ ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሮ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ተደርጓል።

በአገሪቱ ተንሰራፍቶ የኖረውን የተዛባ ግንኙነት በመፋቅ አዲስ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለመገንባት የሚያስችሉ የማንነቶች እኩልነት ማረጋገጥ፣ ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ፣ በአካባቢ ጉዳዮቻቸው ላይ ወሳኝ የሚሆኑበትን የራስ አስተዳደር ማረጋገጥ በአጠቃላይ ከአገሪቱ ልማት ተመጣጣኝ ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግ ሕብረ ብሄራዊ ፌዴራል ሥርዓቱ የተነሳበት ዋናው መሠረታዊ አስተሳሰብ ነው።

ይህ አስተሳሰብ እየደረጀ ነው። አንድነታችን መጠናከር ከቻለ የማንሻገረው ተግዳሮት የለም። በአንድነት ውስጥ ዘላቂ ዴሞክራሲ ሊገነባ ይችላል። በመለያየት ውስጥ ግን እርስ በርስ ከመበጣበጥ በስተቀር የምናተርፈው ነገር የለም። እናም ሁሌም አንድነታችን ሊጠብቅና ፈር ባለው መንገድ መጓዝ እንዳለበት ልንዘነጋው አያስፈልግም። ይህን ሃቅ የተገነዘበው መንግስት አገራዊ መግባባትን ለማምጣት ቃል ገብቶ እየሰራ ነው። የእስረኞች መፈታት ጉዳይ የዚህ አስተሳሰብ የክፍልፋዩች ክፍልፋይ ነው፤ እጅግ አናሳው ክፍል።

አገራዊ መግባባት ማለት በሁሉም ጉዳዩች ዙሪያ ሁሉም ዜጋ ሙሉ ለሙሉ ይግባባል ማለት አይደለም። የተለያዩ እሳቤዎችን በሚያስተናግደው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም።

እናም አገራዊ መግባባት ማለት ዜጎች እንደ ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ በመሳሰሉ በዋና ዋና አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ይፈጥራሉ ማለት ነው። ለምሳሌ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የልማት ስራ ላይ ለአገሩ ልማት የሚያስብ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ከአብዛኛው ህዝብ ጋር መግባባት ላይ ይደርሳል ማለት ነው። ይህን መሰሉ ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ያለው አገራዊ መግባባትን ይበልጥ ለማጎልበት መንገስት እየሰራ ነው።

የፖለቲካ ምህዳርን ማስፋት ሌላኛው መንግስት ቃል የገባበት ጉዳይ ነው። መንግስት በአገሪቱ ዴሞክራሲን የሚያጠናክሩ ፖርቲዎች መኖር እንዳለባቸው የሚያምን ይመስለኛል፡፡ ተደጋግሞ እንደሚነገረውም የመንግስት ፍላጐት የሀገራችን የመድብለ ፖርቲ ስርዓት ዳብሮ እና ጐልብቶ ማየት የዘወትር ፍላጐቱ መሆኑ ነው፡፡ ሁሉንም የሀገራችንን ህዝቦች የሚወክሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፃቸው እንዲሰማ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

የሀገራችን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ ጤናማነቱ ተጠብቆ ሊጓዝ የሚችለው ጤናማ እና ገንቢ ሚና የሚጫወቱ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተሳትፎ እየጐለበተ ሲመጣ ነው፡፡ በመሆኑም በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን በማብቃትና ከጅምላዊ አካሄድ በመታቀብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማበብ ሀገራዊ ግዴታ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝቡ እንዲያስተዳድሩት የሚፈልጋቸውን ይመርጣል እንጂ፣ እንዳለፉት ስርዓቶች የሚያስተዳድሩት ራሳቸውን መርጠው አሊያም በገዥ ፓርቲ ተመርጠው የሚሄዱበት አሰራር ዶሴው ተዘግቷል፡፡ ዳግም አይመለስም፡፡

እናም በአሁኑ ወቅት ዴሞክራሲን መገንባት የውዴታ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱ የሚጠይቀው ግዴታም ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ይህን ለማከናወንም መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመወያየት ዴሞክራሲያዊ አሳታፊነት እንዲጎለብት በማድረግ ላይ ይገኛል። ምናልባትም ቅሬታን ለመፍታት በሰሩት ወንጀል ሳቢያ በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞችን መፍታቱ የዚህ ተግባር እጅግ አናሳው ክፍል አሊያም ቅንጣት ሊሆን ይችላል።

ታዲያ የአገራችንን ችግር ለመፍታት መንግስት እነዚህን ተግባራት በማከናወን የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እየሰራ ነው። ቃልም ገብቷል። ይህ ቃሉ የሚታጠፍ አይመስለኝም። መንግስት የገባውን ቃል የማያጥፈው ተግባራቶቹ ሁሉ በህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው ነው። ይህ በህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ፍላጎቱ ከሚመራበት ህዝባዊነት መንፈሰ የመነጨ ነው። ሃላፊነትም የሚሰማው ነው። ይህ ማንነቱ ገና ከመነሻው ጀምሮ በህዝብ የሚመራና ለህዝብ የታገለ ስለሆነ ነው። በመሆኑም መንግስት በየትኛውም ቦታና ጊዜ ህዝብን ያማከለ ተግባራት እየፈፀመ ላለፉት 26 ዓመታት ተጉዞ ዛሬ ላይ ደርሷል። በአገሩ ጉዳይና በህዝብ ፍላጎቶቹ ላይ ተደራድሮ አያውቅም።

እንደሚታወቀው ሁሉ በሀገራችን ረጅም የፖለቲካ ሂደት ወስጥ የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ፍትሐዊ የዘመናት ጥያቄዎችን አንግቦና ከአምባገነኖች ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ እንዲሁም የህይወትና የአካል መስዕዋትነትን ከፍሎ በአሸናፊነት የድል ፅዋን ያነሳው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ታሪክ በተሃድሶ ውስጥ ያለፈ ነው። ዛሬም እያካሄደ ባለው ተሃድሶ የህዝቡን ጥያቄ በመመለስ ላይ ይገኛል። ሆኖም ዋነኛ የሚመልሳቸው ጉዳዩች አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስቸሉና የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የሚያሰፉ እንጂ ፅንፈኞቸ አጀንዳን ለማሳከር በእስረኞች ጉዳይ ላይ ማተኮር አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።