ሰላምና ልማት፤ ነብስና ስጋ

ሁከትና ግርግር የተለመደ ክስተት ሲሆን ስጋት ይነግሳል።  ስጋት ተስፋን ያደበዝዛል። ስጋት ባለበት ወላጆች የልጆቻቸው የወደፊት እጣ ፈንታ ያሳስባቸዋል። ምሉዕ ሰው ሆኖ የመኖር እድላቸው፤ ተስፋቸው ጨልሞ ይታያቸዋል። ጎልማሶች  እረፍት በሚፈልጉበት የእርጅና ዘመናቸው ሊገጥማቸው የሚችለው ያልተረጋጋ ህይወት ያሳስባቸዋል። ባለለሃብቶች ሃብታቸውን ስራ ላይ ከማዋል ይልቅ ሁኔታውን ማጤን ይመርጣሉ። ሁከትና ግርግር የበላይ ሆኖ ሰላም ሲጠፋ ደግሞ ሞት፣ ስደት፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ . . . ጓዛቸውን ጠቅለለው በየጎጆው ይገባሉ። አሁን በሶሪያ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ደቡብ ሱዳን የምንመለከተው ይህንን ነው። ማንም ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ይህ በሃገሩና በእርሱ ላይ እንዲደርስ አይፈልግም።

የሁከትና ግርግር ምንጭ ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የፍትህ መዛነፍ፣ የዴሞክራሲ እጦት የሚፈጥረው የህዝብ ቅሬታ ቢሆንም፣ ሁከትና ግርግር ሰላምን ያጠፋል እንጂ መፍትሄ አያመጣም። ስለዚህ ተቃውሞዎችን በሰላማዊ መንገድ በማሰማት፣ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ፣ ችግሮች በሰከነ አካሄድ መፍትሄ የሚያገኙበትን ጫና መፍጠር ይበልጥ ወደፊት ያዘልቃል።

በሶሪያ ሁከትና ግርግር የጀመረው እ ኤ አ በ2011 መንግስትን በሚቃወሙ የከተማ እንቅስቃሴዎች ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ተቃውሞ በአግባቡ ባለመያዙና የበሽር አል አሳድን መንግስት ማስወገድ ይፈልጉ የነበሩ ምዕራባውያንም የቀለም አብዮት የመንግስት ለውጥ ስልታቸውን አቀብለው ጣልቃ ስለገቡበት መስመሩን ሳተ። የበሽር አል አሳድ መንግስት ይህን የምዕራብዋይንም እጅ የተነከረበትን የከተሞች ተቃውሞ ለማፈን ከፍተኛ ሃይል ወደመጠቀም ተሸጋገረ። በዚህም ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ሄዱ። ከዚህ በኋላ ምዕራባውያኑ የቀለም አብዮት የከተማ ተቃውሞውን ወደ የትጥቅ ትግል አኘጋገሩት። ምዕራባውያኑ ለዘብተኛ የሚሏቸው፣ ሌሎች ግን ያው አክራሪ የዋሃቢ ሰለፊ አመለካካት አራማጅ ናቸው የሚሏቸው በርካታ ቡድኖች በምዕራባውያን ጠመንጃ እየተረዱ በየአቅጣጫው የትጥቅ ትግል ጀመሩ። ይህ ሁኔታ የፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ የሃገሪቱን መንግስት፣ ትናንሽ ታጣቂ ቡድኖችንም የማይደግፈው አይ ኤስ ተፈጠረ።

አሁን ሶሪያ የምዕራባውያንን ጠመንጃና ሮኬት የታጠቁ በርካታ ትናንሽ ቡድኖች ከመንግስትም ጋር እርስ በርስም የሚዋጉባት የጦርነት አውድማ ነች። የየራሳቸው ፍላጎት ያላቸው በርካታ ጉልበተኛ ሃገራትም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ቦምብ የሚያዘንቡባት የፈረሰች ሃገር ሃገር ለመሆን በቅታለች። በዚህ ግጭት ከሩብ ሚሊየን በላይ ዜጎቿ ህይወታቸውን አጥተዋል። በብዙ ሚሊየን የሚቀጠሩ ዜጎቿ ተሰደዋል። በሃገር ውስጥም የቀሩት ምንም የላቸውም። ሶሪያ ስራ የሚሰራባት፣ የእለት እንጀራ የሚሸመትባት፣ ቤተሰብ የሚመሰረትባት ሃገር አይደለችም። በዩኔስኮ ተመዝግበው የነበሩ ጥንታዊ ቅርሶቿ ሳይቀሩ ወድመዋል። ሰላም ሲያመልጥ እንደዚህ ነው። እርግጥ ነው የበሽር አል አሳድ መንግስት አምባገነን ነበር። የበሽር አል አሳድን መንግስት መቀየሪያው መንገድ ግን ይህ አልነበረም።

ወደኢትዮጵያ ለመልሳችሁ። በተለይ ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አቅጣጫዎች ሁከትና ግርግሮች፣ የእርስ በርስ ግጭቶች አጋጥመዋል። ይህ ብዙዎችን አሳስቧል። ሁኔታው በአግባቡ ካልተያዘ የሃገሪቱ ሰላም ጠፍቶ ሃገር መሆኗ ሊያከትም የሚችልበት እድል መኖሩ ነው ያሳሰባቸው። እናም ሁከትና ግርግሩ፣ የእርስ በርስ ግጭቱ የበላይ ሆኖ የሃገሪቱን ሰላም ጨርሶ ከማጥፋቱ በፊት ወደሰገባው እንዲገባ ተመኝተዋል።

ይህ ማለት ግን በመንግስት በኩል ህዝቡ ላይ የመረረ ቅሬታ ያስከተለ ችግር አልነበረም ማለት አይደለም። ህዝብ ችግሩን ተቋቁሞ በዝምታ መኖር ነበረበት፣ ተቃውሞ ማሰማት የለበትም ማለትም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተቃውሞው በሌሎች አካላት ተጠልፎ እያደረ የሃገሪቱን ሰላም ለያጠፋ ወደሚችል አስከፊ ግጭት እንዳያመራ ከስሜታዊነት በጸዳና ምላሽ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ላይ ባተኮረ መንገድ መቅረብ ነበረበት።

የኢፌዴሪ መንግስትና ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እያደረ ወደ ሁከትና ግርግር እንዲሁም ወደየእርስ በርስ ግጭት እየተቀየረ የመጣውን ህዝባዊ ተቃውሞ የቀሰቀሰ ተገቢ ምክንያት መኖሩን አምነው ተቀብለዋል። ተቃውሞውን የቀሰቀሰው በመንግስት በኩል የነበረ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የዜጎችን ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት ያዛባ ኪራይ ሰብሳቢነትና ጥገኝነት፣ የፍትህ እጦት፣ የከፋ የከተሞች ስራ አጥነት መሆኑን መንግስት ተገንዝቧል። ለዚህም ተጠያቂ መሆኑን በይፋ አሳውቆ ችግሮቹን ለማስተካከል ቃል ገብቷል። በ2008 ግንቦት ወር ላይ በመንግስትና በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ውስጥ ለህዝብ ቅሬታና ተቃውሞ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በጥልቀት በመታደስ እርምጃ ለማስተካከል ይፋ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል። የፌደራል መንግስት ካቢኔውን እንደአዲስ ነበር ያዋቀረው። የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የደቡብ ኢትዮጵያና የትግራይ ክልሎችም ካቢኔያቸውን በአዲስ መልክ አዋቅረዋል። ይህ የአስፈፃሚው አካል የአወቃቀር ማሻሻያ እስከቀበሌ የዘለቀ ነበር። በፌደራልና በክልሎች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች አባላት የምርጫ ስርአት ሁሉም ድምጾች መወከል የሚችሉበትን እድል የሚያጠበ ሆኖ በመገኘቱ፣ ይህን በማስተካካል የሃገሪቱን የዴሞክራሲ ምህዳር ለማስፋት ተወስኗል። በዚህ መሰረት በምርጫ ህጎችና ሌሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ገድበዋል በተባሉ አዋጆች ላይ በገዢው ፓርቲና በሃገር አቀፍ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል ድርድር ማካሄድ ተጀመሯል። በዚህ ድርድር የእስካሁን ሂደት የቀላል አብላጫ ድምጽ (simple majority) የምርጫ ስርአቱ በአብላጫና በተመጣጣኝ ቅይጥ ውክልና ስርአት እንዲቀየር የሚል ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ከዚህ በተጨማሪ በተለይ የተቃውሞው ዋና ተሳታፊ የነበሩት ወጣቶች ላይ የነበረውን አስከፊ የስራ አጥነት ችግር ማቃለል የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደዋል። ከ1998 ዓ/ም ጀምሮ ስራ ላይ የዋለው የወጣቶች የልማት ተሳትፎ ፓኬጅ፣ የወጣቶች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ፓኬጅ በሚል ወቅታዊ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልክ እንዲሻሻል ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል ለስራ ፈጠራ ይውል ከነበረው በጀት በተጨማሪ የ10 ቢሊየን ብር የስራ እድል ፈጠራ ተንቀሳቃሽ ፈንድ እንዲመደብ ተደርጓል። ከዚህ ፈንድ ግማሽ ያህሉ ባለፈው ዓመት ተለቆ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ከዚህ ባሻገር ክልሎች የየራሳቸውን እርምጃ ወስደዋል።

ችግሮቹ የተከማቹና ከአመለካካት ጋር የተያያዙ በመሆናቸው እንዲህ በአጭር ጊዜ የሚፈቱ ባይሆኑም ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ግን ታይቷል። በተለይ ህዝብ የመንግስት አዛዥ መሆኑን፤ መንግስትም የህዝብ አገልጋይ መሆኑን ዕውን ያደረገ ሁኔታ ሰፍኗል። ይህም ሆኖ ግን ህዝብ መንግስት ላይ ካለው ቅሬታ ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው ሁኔታ የእርስ በርስ ግጭቶችንም የቀላቀለ ሁከትና ግርግር በተለያዩ አካባቢዎች አጋጥሟል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ወር፣ ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎችና ተቃውሞዎች ምላሽ ለመስጠት የተጀመረውን በጥልቀት የመታደስ እርምጃ  መርምሮ ተጨማሪ የመፍትሄ ውሳኔዎችን አስቀምጧል። እነዚህ የመፍትሄ ውሳኔዎች በኢህአዴግ ድርጅቶች ውስጥ እስከታችኛው እርከን በማወረድ ወደተግባር የመግባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ይህ በሆነበትም ሰሞን በጥቂት ቦታዎች ላይ ግጭቶች አጋጥመዋል። ወጣቶች ማንነትን መሰረት ወዳደረገ ግጭት እንዲገቡ በስሜት ያዘጋጃቸው ሁኔታ መንግስት ላይ የነበራቸው ቀሬታ ሊሆን ቢችልም፣ ከምክንያታዊነት ይልቅ በስሜት የመነዳት ነገር ይታይበታል። ይህ መንግስት ለቅሬታዎቹ ምላሽ ለመስጠት እስካሁን ባለው አካሄድ ቁርጠኝነቱን በሚያረጋግጥ አኳሆን እየተነቀሳቀሰ ሳለ ያጋጠመ ግጭት፣ በመንግስት ላይ ካለ ቅሬታ የተቀሰቀሰ ከመሆኑ ይልቅ፣ ሃገሪቱን ለማተራመስ በሚፈልጉ ቡድኖች የኤርትራ መንግስትን ጨምሮ ያቀናበሩት ሊሆን ይችላል። መደረሻውም የህዝቡ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ምላሽ እንዲያገኙና እንዲሟሉ ማድረግ ሳይሆን በእርስ በርስ ግጭት ኢትዮጵያን ዳግማዊ ሶሪያ ማድረግ ነው።

ኢትዮጵያውያን ጥንቃቄ ማደረግ ያለባቸው እዚህ ላይ ነው። በቅድሚያ መንግስት ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በይፋ ቃል ገብቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። በዚህ ሁኔታ የሚቀሰቀስ ሁከትና ግርግር መንግስት ከስራው እንዲደናቀፍና የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ተንጠልጥሎ እንዲቀር ከማደረግ ያለፈ ውጤት የለውም። በሌላ በኩል ጥያቄዎችን በሁከትና ግርግር በግጭት መልክ ማቅረብ የሃገሪቱን ሰላም አጥፍቶ ልማትም ኑሮም ከንቱ እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል።

ሰላም ከሌለ ልማት የለም። ሁከትና ግርግር፣ ግጭት የሰላም መጥፋት ስጋት ይፈጥራል። በዚህ ውስጥ ሃብቱን ስራ ላይ የሚያውል ባለሃብት አይኖርም። ስጋት ሲኖር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይቋረጣል። ስጋት ባለበት በስራ ላይ የነበሩ ተቋማትም ስራቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ። ግጭቶች እየተባባሱ ሲሄዱ አርሶ አደሩም ማምረት አይችልም። ስጋት በለበት ገበያ የለም። ስጋት ባለበት ቱሪስት የለም። ስጋት ባለበት . . .። ሰላምና ልማት የማይነጣጠል ትስስር አላቸው። ሰላምና ልማት፣ ነብስና ስጋ ናቸው። ሰላም ሲጠፋ ልማት ሞቶ ይበክታል። የበከተ ልማት መገለጫ ድህነት፣ ረሃብ፣ ስደት፣ ትምህርት ማጣት . . . ነው። እናም ሁኔታዎችን ከስሜታዊነት ጸድተን በሰከነ አእምሮ በመመልከት ሰላማችንን መጠበቅ አለብን።