ንግግር የመመንዘር በሽታ

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ከተመረጡ በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ በፓርላማው ቀርበው ያደረጉት ንግግር ከምክርቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች የሰጡት መልስ ታሪካዊና አስደማሚም ነበር፡፡በተለያዩ ጥያቄዎች ላይ የሰጧቸው መልሶች አሳማኝ ምክንያታዊ ብዥታና መደናገሮችን ማጥራት የቻሉ ናቸው፡አሁን ችግር እየሆነ የመጣው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማም ሆነ በተለያዩ መድረኮች የሚናገሯቸውን ንግግሮች ከትክክለኛው መልእክት ውጪ በተዛባ ሁኔታ የሚመነዝሩ ክፍሎች መበራከት ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ሁሉም በተረዳው መልኩ ሊወስደው ይቻላል፡፡ችግሩ አዛብቶና ከመረዳት ጉድለት በራስ ፍላጎት መመንዘሩ ላይ ነው፡፡ያሻቸውን ትርጉም በመስጠት ሌላ ሁከት ሌላ ግጭት ሌላ ትርምስ ለመፍጠር ቀዳዳውን ማስፋት በመፈለግ አይነት በማሕበራዊ ሚዲያውና በሌሎችም የሚታየው መዛባት መታረምና መስተካከል ያለበት ነው፡፡

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግልጽና ቀና ተነሳሽነት ለማደናቀፍ መልካም ጅምሮችን ለማሰናከል መጠላላቱ እንዲሰፍን በጎሪጥ መተያየቱ እንዲሰፋ ሆን ተብሎ የሚደረግ ሩጫ እንጂ ለእሳቸው ያለንን ፍቅርና አጋርነት ማሳያና የመደመር መገለጫ መቼም አይሆንም፡፡አስፈላጊም አይደለም፡፡ቃላትን ነጥለው በማውጣት መመንዘር ልክ ለተወሰነ ክፍል እንደተባለ እንደተነገረ አይነት አድርጎ በመውሰድ ማሰራጨት ቅሬታና ጥላቻን የሚፈጥር የመደመር መንፈስን የሚያናጋ እየደከሙለት ያለውን ፍቅር ሰላም አብሮነት ምሕረትና ይቅርታ የሚንድ እኩይ ተግባር ነው፡፡

አንድን አባባል ወይንም ንግግር አንድ ሰው በተረዳበት መልኩ ሊወስደው ይችላል፡፡ በጅምላ ወስዶ ቡድን ወይንም ብሔረሰብ ላይ ሊጭነው ከቶውንም አይገባም፡፡ነውርና ወንጀልም ነው፡፡እንዲህ አይነት ታሪክም የለም፡፡ግለሰቦች እንጂ የሕዝብ ጥፋተኛ የለም፡፡ወንጀለኛ ሙሰኛ ኪራይ ሰብሳቢ ዘራፊና ቀማኛ ሌቦች የሆኑ ግለሰቦች በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውስጥ አሉ፡፡በአማራው በኦሮሞው በትግራዋይ በጉራጌው በሶማሌው በሲዳማው በስልጤው ወዘተ ውስጥ ሁሉም ቦታ አሉ፡፡በሌላውም አለም ይሀው ነው፡፡

ከሀገር ከሕዘብ የሚዘርፉ ሲዘርፉ የኖሩ ዘርፈውም አግበስብሰውም በቃኝን የማያውቁ  ዘርፈውም የከበሩ ሚሊዮነር ቢሊዮነር የሆኑ የቀን ጅቦች በሁሉም ዘር ውስጥ አሉ፡፡በህግ የሚጠየቁት በግለሰብነታቸው እከሌ ተብለው እንጂ በጎሳቸው ወይንም በዘራቸው አይደለም፡፡

ለዚህ ማሳያው በአምናው የኢሕአዴግ ጥልቅ ግምገማ የመጀመሪያው ምእራፍ ላይ በሁለም የሀገሪቱ 9 ክልሎች በሕዝብና መንግስት ሀብት ዘረፋ ላይ ተሰማርተው የነበሩ፤ስልጣናቸውን በመጠቀም ሲዘርፉ የኖሩ ከሕዝብ ጋር በተደረገው ቀጥተኛ ውይይት ሕዝቡ ራሱ ያጋለጣቸው በመሬት ቅርምትና ዘረፋ ላይ ተሰማርተው የነበሩ፤ከኪራይ ሰብሳቢዎችና ከደላሎች ጋር ተመሳጥረው ከፍተኛ የዘረፋ ኔት ወርክ(መረብ) ውስጥ በተገኙ ሰዎች ላይ በአማራ በትግራይ በኦሮሚያ በደቡብ  በድሬደዋ በጋምቤላ በሶማሊያ በአፋር ክልል ወዘተ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡

ከእርምጃዎቹ ውስጥ ከስራ ማገድ ማሰናበት ከኃላፊነት ማንሳት ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት መምራት ይገኙበታል፡፡በአጠቃላይ ኢሕአዴግ በራሱ የውስጥ ግምገማ ወደ 50 ሺህ አባላቱን ከሙስና ከመልካም አስተዳደር ከፍትሕ ችግር ከመሬት ቅርምት ከግንባታ ስራዎች፤ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ወዘተ ጋር በተያያዘ እርምጃ በመውሰድ አሰናብቶአል፡፡ በእርግጥ የሕዝብ መነጋገሪያ ሁኖ የቆየው ዛሬም የቀጠለው ከስር ያለው ሰራተኛም ሆነ አባል አለቆቹን ትልቅ መንግስታዊ ስልጣንና ቦታ ላይ ያሉትን ምግባረ ብልሹዎች አይቶ የገባበት ስለሆነ ኢሕአዴግ ዋናውን እርምጃ መውሰድ ያለበት በትላልቆቹ ሙሰኞች ዘራፊዎችና የቀን ጅቦች ላይ መሆን አለበት ሲል ነው የቆየው፡፡

ቀኑን ለሰራዊት ሌሊቱን ለአራዊት እንዲል መጽሀፉ ጅቦች በተፈጥሮ ስጦታቸው አይናቸው በሚገባ የሚያየው የሚጮሁት የሚንቀሳቀሱት ምግባቸውን የሚፈልጉት ለሊት ነው፡፡የቀን ጅብ ለሊቱ አልበቃ ብሎት ማየት ባይችልም በቀን በጠራራ ጸሀይ ያገኘውን ሁሉ ከመብላት የማይመለስ ነው፡፡የቀን ጅብ የመጨረሻው ሆዳምና አግበስባሽ በልቶ ጠገብኩ የማያውቅ ሆዳም ማለት ነው፡፡ዋና ስራውም ከብትና እንሰሳቱን እያሳደደ እየዘረፈ እየነጠቀ መብላት ነው፡፡አልፎ ተርፎም የሚበላ ካላገኘ ሰው ይበላል፡፡በባሕላችን እነዲህ አይነት ምግባር ያለው ሰው ሲታይ የቀን ጅብ ይባላል፡፡

የቀን ጅብ የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አገላለጽ በትክክልም የመንግስትና የሕዝብን ሀብትና ንብረት መሬት እንዳሻቸው ሲዘርፉ ሲሸጡ ሲለውጡ ድሀውን ገበሬ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ሲያፈናቅሉ የኖሩትን፤ከባንክ በኢንቨስትመንት ስም በሀሰት ማስረጃና ማስያዣ(ኮላተራል) በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ብድሮችን በመውሰድ ገንዘቡን ለሌላ ስራ ያዋሉ ብድሩንም ያልከፈሉትን፤በኢንቨስትመንት ስም ብዙ ሺህ ካሬሜትሮችን ወስደው ከተፈቀደለት አላማ ውጪ መሬቱን እንደ ግል ንብረታቸው ሲቸበችቡ የኖሩትን ይመለከታል፡፡

በመንግስታዊ ወንበራቸው ስልጣን ተጠቅመው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየገደሉ ስፋት ባለው ኮንትሮባንድ ስራ ተሰማርተው በማይፈተሹና ጥበቃ በሚደረግላቸው መኪኖች እንደልብ ሸቀጦችን ከድንበር እስከ መሀል ሀገር እያስገቡ ሕጋዊውን የመንግሰት ግብር ከፋይ ነጋዴ ከጨዋታ ውጪ ያደረጉትን፤በከተማና በክልሎች በልማትና ተነሺ ስም ዜጋውን ከይዞታው በመንግሰት ስም እያፈናቀሉ መሬቱን በመሸጥ በሚሊዮንና በቢሊዮን የከበሩትን  ወዘተ…በሁሉም ብሔርና ብሔረሰብ ውስጥ የሚገኙ አይን አውጣ ሀገርና ሕዝብ የዘረፉ ሌቦች የቀን ጅቦች ቢባሉ ምንም አይገርምም፡፡ትክክለኛ ስማቸውም ነው፡፡

እነዚህ በሁሉም ቦታ ያሉ ግለሰቦች ዘራቸውን ብሔራቸውን አይወክሉም፡፡ሊወክሉም አይችሉም፡፡የቀን ጅቦችም ናቸው፡፡በልተው ዘርፈው ነጥቀው አጭበርብረው በቃን የማይሉ አውሬዎች፡፡በሁሉም ዘር ውስጥ አሉ፡፡ለዚህ ነው የቀን ጅቦች የሚለውን አገላለጽ በተዛባ መልኩ ከመመንዘር መቆጠብ ያለብን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን ማብራሪያም ከግንዛቤ ማነስ ወይንም በትክክል ካለመረዳት የሚመነዝሩም አሉ፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢሕአዴግ አሸባሪ ነው ብለዋል በማለት ንግግሩን ከአውዱ ውጪ ሌላ ትርጉም ለመስጠት ሲታትሩ ታይተዋል፡፡ንግግራቸውን የጎንዮሽ ለመሰንጠቅ ለመመንዘር ከመሮጥ ይልቅ ዋነኛውን መልእክት መረዳት ይገባቸው ነበረ፡፡

እነዚህ ሰዎች በትልቅ ቦታ ሆነውም ሆነ ከእዛ ውጪ በትክክል ሕገመንግስቱን አያውቁትም ማለት ነው፡፡የሀገሪቱ ሕገመንግስት ለዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲዊ መብት መከበር ከፍተኛ እውቅና ይሰጣል፡፡ባለስልጣናትም ሆኑ ሕግ አስፈጻሚዎች(ፖሊስ ወይንም የጸጥታ አካላት)በዜጎች ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት መፈጸም፤መግረፍ ፤መደብደብ አካላዊ ጉዳት ማድረስ፤ ማሰቃየት፤ብልት ማኮላሽት፤ ሰብአዊ ክብርን መድፈር አይችሉም፡፡ሕገ መንግስቱ በህግ የከለከለ ከመሆኑም በላይ ይህን የሰብአዊ መብት የፈጸሙ ኃላፊዎች በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡

ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሀን ታስረው የነበሩ ዜጎች የደረሰባቸውን ግፍና በደል ሲገልጹ ነበር፡፡ተፈጸመብን በሚል የሚገልጹዋቸው እጅግ ሰቅጣጭና ዘግናኝ ድርጊቶች በግልጽ ሰፍሮ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ሕገመንግስት የጣሱ የከፉ የወንጀል ድርጊቶች ናቸው፡፡ይህንን ተግባር አክራሪና አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ወንጀለኞች ናቸው ሲፈጽሙ በአለም የሚታወቀው፡፡ሕገመንግስቱ ለፖሊስ ሰብአዊ መብትን አክብር የዜጎችን ክብርና መብት ጠብቅ በሕግ ቁጥጥር ስር ከዋለም መብቱ የተከበረና የተጠበቀ ነው ምርመራና ማጣራቶች በፈቃደኝነት ይጠየቃሉ እንጂ ደብድብ ግረፍ አካል አጉድል አሰቃይ አይልም፡፡

አብዛኛው በእስርቤት የነበረው ዘግናኝ ሰቆቃና ግርፋት የሕዝብን ቁጣ ከቀሰቀሱት  ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ይህ የአሸባሪነት ስራና ድርጊት ነው፡፡ ይህንን  አይነቱን የሰብአዊ መብት ጥሰትና ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩትም ፖሊሶች ያው አሸባሪዎች ናቸው ማለት ነው፤፤በሕግ ከመጠየቅ ሊያመልጡ አይችሉም፡፡ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ባሉ ማረሚያ ቤቶች ስሕተቶች ተፈጽመዋል፡፡በርካቶችም  ባልሰሩት ጥፋት የአካልና የሞራል ውድቀት ደርሶባቸዋል፡፡በሚዲያም ቀርበው የደረሰባቸውን በይፋ ለሕዝቡ ተናግረዋል፡፡መካድ አይቻልም፡፡

ኢሕአዴግ ይህን አምኖ በተሐድሶው ወቅት ተሳስቻለሁ በማለት ሕዝብን በይፋ ይቅርታ ጠይቋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታራሚዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማሳየት የተጠቀሙበት አገላለጽ ነው አሸባሪነት፡፡ኢሕአዴግ በሚመራውና በሚያስተዳድረው መንግስት ውስጥ ይህ ሁሉ ኢሰብአዊ ድርጊትና ወንጀል በዜጎች ላይ መፈጸሙን ዜጎች በአደባባይ ወጥተው በሬድዮና በቴሌቪዥን እየተናገሩ አሸባሪነት አልተፈጸመም ብሎ መከራከር አይቻልም፡፡ኢሕአዴግ ስሕተቱን አምኖ ተቀብሎ አርማለሁ ብሎ ቃል በመግባት ነው ወደ ጥልቀታዊ ተሀድሶ እርምጃ የተሻገረው፡፡ዳግም እንዳይደገሙም  በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ ሕገ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጊት በእያንዳነዱ ቀበሌ፣ በእያንዳንዱ ወረዳ፣በእያንዳንዱ ዞን ሲፈጸም ቆይቷል፡፡በፌዴራል መንግስት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ቀጠናዎች፡፡የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያጠናውን ሪፖርት ታውቃላችሁ፡፡የወረዳው ፖሊስ ሲገርፍ ነበር፡፡ኢ-ህገ መንግስታዊ ነው፤ አሸባሪ ነው እሱ ፖሊስ፡፡›ለዚህ ደግሞ ኢሕአዴግ በግልጽ ይቅርታ ጠይቋል ሕዝቡን፡፡አጥፍቻለሁ፤ በድያለሁ ብሎ፡፡እኔንም እግዚአብሔር ይስጣችሁና ጠቅላይ ሚንስትር ስትሉኝ እዚህ ቆሜ ይቅርታ ጠይቄያለሁ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲሉ ነበር ለፓርላማው  የገለጹት፡፡ እውነቱን በድፍረት ተቀብሎ ለቀጣይ እርምት መስራት በሕዝብ ዘንድ ያስከብራል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትክክል ናቸው፡፡