የማይገታው ማእበላዊ ኃይል

ሀገራችን ታላቅ በሆነ ከዚህ በፊትም ባልነበረና ባልታየ የለውጥ ጉዞ ላይ ትገኛለች፡፡ ከተመረጡ ወደሶስት ወራት አካባቢ የሚጠጋ ግዜ በማስቆጠር ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በግዜ ቀመር አጭር በሚባሉ ግዜያት በእጅጉ አስደናቂ የሆኑ የሕዝብን የልብ ትርታና ድምጽ ብሶቱን ያዳመጡ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡

በሀገር ደረጃ ተፈጥሮ የነበረውን የመከፋፈልና የመበታተን ስጋትና አደጋ እንዲቀረፍ ሕዝቡም በከፍተኛ ብሔራዊ ተነሳሽነት ከዳር እስከዳር በአንድ መንፈስ ሀገሬ ብሎ እንዲቆም ማድረግ ችለዋል፡፡በሕዝብ ከልብ የተወደደና የተደገፈ የተሳካ ስራ ተሰርቶአል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ላይ ከወጡ ሶስት ወር ባልሞላ ግዜ ውስጥ በመላ ሀገራችን ቢመባል መልኩ በሁሉም ክልሎች በመዘዋወር  ከሕዝቡ ጋር በቀጥታ ተወያይተዋል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ተወካዮችን፤የአለም አቀፍ ተቋማት መሪዎችን፤ከፍተኛ ዲፕሎማቶችን በመቀበል አነጋግረዋል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንዳንዷን ቀንና ሰአት ሳያባክኑ ተጠቅመውበታል፡፡

የጎረቤት ሀገራትን በመጎብኘት የነበረንን ዘመናት ያስቆጠረ ወዳጅነትና ወንድማማችነት  የበለጠ እንዲጎለብት አድርገው ለሀገራቸው የሚበጀውንም በጋራ አብሮ የመስራት ስምምነት ተፈራርመው ተመልሰዋል፡፡ጅቡቲ፤ ኬንያ፤ ሱዳን፤ ኡጋንዳ፤ ሶማሊያ፤ሳኡዲአረቢያ፤አረብ ኢምሬት፤ግብጽ ተጠቃሽ ናቸው፡፡በየሄዱበትም ሀገር ታስረው የነበሩ ዜጎቻችንን አስፈትተው ተመልሰዋል፡፡ይህም በሕዝብ  ዘንድ ታላቅ ፍቅርና ከበሬታ አስገኝቶአል፡፡

በነዚህ አችር ግዜያት አዲስ ካቢኔአቸውን አዋቅረዋል፡፡የተለያዩ ከፍተኛ መንግስታዊ ሹመቶችን ሰጥተዋል፡፡ ከሲቪል ማሕበረሰቡ፤ከከፍተኛ መንግስታዊ ሹሞች፤ ከተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች፤ከሠራዊቱ አመራሮች፤ከኪነት ባለሙያዎችጋር በመገናኘት የተነጋገሩ ሲሆን ሰሞኑን አፋር በመሄድ ከሕዝቡ ጋር ተወያይተዋል፡፡በዚያው እለት ቤንሻንጉል በመሄድ የተፈጠረውን ሁኔታ ለማረጋጋት  ከሕዝቡ ጋር ተነጋግረው ተመልሰዋል፡፡ 

በሀገርቤት ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ መነሻነት ቀደም ሲልም በፖለቲካ ታስረው የነበሩ እስረኞች በመላው ሀገሪቱ ተፈተዋል፡፡በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎችና ሚዲያዎች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ባደረጉት ጥሪ መሰረት የገቡ እንደሚገቡ የሚጠበቁም አሉ፡፡ከኤርትራ ጋር ያለውን ችግር በሰላም ለመፍታት ባደረጉት ጥሪ መሰረት የኤርትራ መንግስት ጥሪውን ተቀብሎ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተነጋግረው ጉብኝትም አድርገው ተመልሰዋል፡፡በቀጣይ በመሪዎች ደረጃ ጉብኝት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከተረከቡ ሶስት ወር በማይሞላው ግዜ ውስጥ ታላላቅ ሀገራዊና አለም አቀፍ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡እነዚህኑ ስራዎቻቸውን በማድነቅና በመደገፍ ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ያዘጋጀው ታላቅ የድጋፍ ትእይንት ባለፈው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ ተካሂዶአል፡፡በመደመር ቀን ልዩ ሕዝባዊ ድጋፍ ብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ለምስጋናና ለድጋፍ ሰልፍ በራሱ ተነሳሽነት ቲሸርት ገዝቶ ከርቀት ሳይቀር በእግሩ ተጉዞ  ሰልፉ ላይ መታደሙ የተአምር ያህል የሚቆጠር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይህን የመሰለ ለመሪ የተሰጠ ማእበላዊ የሆነ ሕዝባዊ ንቅናቄና ሰልፍ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡በራሱ ገንዘብ ያለማንም ጎትጓችና ቀስቃሽ ከየቤቱ ፈንቅሎ የወጣው የአዲስ አበባ ሕዝብ እንዲሁም ከቅርብና ሩቅ ከተሞች ለመሳተፍ የተገኘው ተደምሮ ሲታይ ቁጥሩ አራት ሚሊዮን ይደርሳል ከዚያም ያልፋል የሚሉም አሉ፡፡

እንዲህ አይነት እጅግ ግዙፍ የሆነ አዲስ አበባን ከዳር እስከዳር ያጥለቀለቀ በፈቃደኝነት በራስ ተነሳሽነት የተካሄደ ሕዝባዊ ሰልፍ በቅርብ አመታት ተከስቶ አልታየም፡፡ሕዝብ በሙሉ ልብ በፍቅር ወጥቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከጎንህ ነን ብሎ ሲደግፍ የበለጠ ለሀገራቸው ለመስራት ጉልበት ብርታት ጥንካሬ እንዲያገኙ ያደረገም ነው፡፡

በመስቀል አደባባይ ንግግር አድርገው ከጨረሱ በኃላ አሳዛኙ ነገር ለውጡን ለማደናቀፍ በማቀድ እሳቸውም እንደገለጹት በተጠናና በታቀደ መልኩ የቦምብ ፍንዳታ በማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ላይ የተቃጣው, የግድያ ሙከራ ነው፡፡ዜጎች መስዋእት ሆነዋል፡፡በርካቶችም ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ጠ/ሚኒስትሩ ወዲያውኑ መግለጫ በመስጠት ሕዝቡን ባያረጋጉት ኖሮ ሊከተል የሚችለውን አደጋና ጥፋት መገመት አይቻልም ነበር፡፡የዛኑ ምሽት ተጎጂዎቹ በተኙበት ሆስፒታል ሄደው ጎብኝተዋል፡፡

መንግስት ሁኔታውን እያጣራ ሲሆን ጥበቃው የሚመለከታቸው ኮሚሽነሩን ጨምሮ  የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ወዲያው በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡ይህን በጭካኔ የተሞላ  አረመኔያዊ ድርጊት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጣ ቀስቅሶአል፡፡በሀገር ውስጥም በውጭም እየተወገዘ ይገኛል፡፡የተለያዩ ሀገራት መሪዎች ድርጊቱን ኮንነውታል፡፡መግለጫም አውጥተዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚደረጉት የድጋፍ ሰልፎች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ ቀጥለዋል፡፡በጅግጅጋ፤ በጎንደር፤ በደብረ ማርቆስ፤በደሴ፤ በኮምቦልቻ የለውጥ አደናቃፊውን ኃይል አንገት ያስደፉ የሕዝብ ደማቅ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ባሕርዳር፤ ደብረብርሀን የሌሎችም ከተሞች ሕዝቦች ድጋፋቸውን በሰልፍ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

በአጭሩ ባልተለመደ ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ አመራር የመጣውና የታየው ለውጥ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው  የሕብረተሰብ ክፍሎች በአንድነት ጸንተው እንዲቆሙ ማድረግ ያስቻለ የላቀ ስኬታማ ውጤት አስመዝግቦአል፡፡

ትልቁ ቁልፍ ነጥብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አግዝፈው ማሳየት መቻላቸው፤ዘረኝነትንና ጎጠኝነትን ማውገዛቸው፤ፍቅርን አብሮነትን መቻቻልን ይቅርታና ምሕረትን ማወጃቸው ነው በሕዝብ ልብ ውስጥ እንዲገቡ እንዲኖሩ ያደረጋቸው፡፡

በርካታ ንግግሮቻቸው ከትላንት እሳቤ ከጥላቻ በክፉ ከመተያየት ለመጠፋፋትና ለመገዳደል ከመፈላለግ ተላቀን በአንድ ላይ እንደመር፤ለሀገራችን ለሕዝባችን በፍቅር እንስራ፤በጉልበትና በጠመንጃ ሳይሆን በኃሳብ የበላይነት በውይይትና በመነጋገር ችግሮችን ተቀራርበን በመፍታት እንመን፤የዜጎች ስደት እንግልትና ሞት ያብቃ በሚሉት ላይ ማተኮራቸው የሕዝብን ቀልብና መንፈስ  ማሸነፍ ችሎአል፡፡

ሰርተን ሀገራችንን እንለውጥ፤ኢትዮጵያ ለኢትየጵያውያን ትበቃለች፤በአንድ ላይ ተደምረን ስንቆም እንከበራለን፤በመጠፋፋት ለሀገርና ሕዝብ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚሉት እሳቤዎቻቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ በሕዝቡ ውስጥ የአስተሳሰብ ለውጥ  እያመጣ  ይገኛል፡፡

የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የለውጥ አደናቃፊ ኃይሎቹ ሴራና የጥፋት ሙከራ ሊቀጥል እንደሚችል አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን ገልጾ ሕብረተሰቡ በሁሉም ቦታ ነቅቶ እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፎአል፡፡ ለውጡን ለማስተጓጎል መልከ ብዙ ሴራዎች ሊሸረቡ እንደሚችሉ ቢገመትም ይህንን የሕዝብ ውቅያኖሳዊና ማእበላዊ  ኃይል ሊገታው ሊመክተው የሚችል ምንም ኃይል አይኖርም፡፡የለውጡ ትንታግ ሂደት ለአፍታም  አይቆምም፡፡