እንደ አባይ ወንዝ በመደመር (ከመቅደላ እስከ ጉባ) (ክፍል አንድ)

አንድ ሰው ‹‹የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ›› ሲል፤ ምናልባት ከአፄ ቴዎድሮስ ወዲህ ከማለት ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ የሚመጡት የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪዎች፤ እንኳን የአፄ ቴዎድሮስ ዘመንን በ2010 ዓ.ም የተከሰተን ድርጊትም የዘመናዊ ታሪክ ክፍል አድርገው ሊቆጥሩት አይችሉም፡፡ እኛ ዛሬ እንደ ዘመናዊ የምንቆጥረውን እና የምንኖርበትን ዘመን፤ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ በ3010 ዓ.ም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፤ ዘንድሮ በ2010 ዓ.ም የተካሄደውን የስልጣን ሽግግርን ‹‹እጅግ ጥንታዊ ታሪክ›› በሚል የሚጠቅሱት ይሆናል -ለመጠቀስ የሚያበቃ ፋይዳ ይዞ ከታያቸው፡፡

ምናልባትም ራሱ ታሪክ የሚባል ፅንሰ ሐሳብም ሊጠፋ ይችላል፡፡ የታሪክ ፀሐፊ የሚል የሙያ ዘርፍ ሊከስም ይችላል፡፡ ዛሬ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ግስጋሴ የቦታን ገዳቢነት እንዳጠፋው ሁሉ፤ በተመሳሳይ የጊዜ ገዳቢነትም ሊጠፋ ይችላል፡፡ ምናልባትም፤ በ‹‹ቢጫ ታክሲዎች›› ተሳፍረን በጊዜ ጎዳና ወደፊት እና ወደ ኋላ ለመሄድ የምንችልበት ሁኔታ ይፈጠር ይሆናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የ3010 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ‹‹ለጉብኝት ወደ 2010 ዓ.ም እንሂድ›› ለማለት የሚችሉበት ዕድል ሊኖር ይችላል፡፡ ምናልባት፤ እንደ ሬሳ ማድረቂያ ባለ ነገር የደረቁ የታሪክ ክስተቶችን ማየት፤ ምናልባትም ‹‹ሃሎ ሲኦል ወይም ገነት›› ወይም ‹‹ሃሎ ሰማይ ቤት›› እያሉ መደወል ይችሉ ይሆናል፡፡ የሆነ ሆኖ ‹‹ዘመናዊ ታሪክ›› (Modern History) የሚል ስያሜ በጣም የተሳሳተ ሆኖ ሳለ ቃሉ ከአገልግሎት አልተሻረም፡፡

 ሆኖም፤ የነገሮች መሠረታዊ ይዘት ብዙ ሳይቀየር በአሁኑ መልክ እስከ 3010 ከቀጠለ፤ በ3010 ዓ.ም የሚኖር ጋዜጠኛ የዚህን ዘመን ኢትዮጵያውያን (ከኛ ከቀደሙት እና እኛን ተከትለው ከሚመጡ በርካታ ትውልዶች መካከከል ለይቶ የሚያስታውሰን ከሆነ) መታወሻችን ታላቁ የህዳሴው ግድብ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ፡፡  

ይህ ትውልድ የተስፋ ዘር ማየት የጀመረ ትውልድ ነው፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው፤ በ3010 ዓ.ም የሚኖረው ጋዜጠኛ  ደርግን ከስልጣን ያባረረው ኢህአዴግ ይሁን ቅንጅት አይለይም፡፡ ‹‹ለረጅም ዘመናት ቁልቁል ስንወርድ ከቆየን በኋላ፤ እንደገና መነሳት የጀመርነው፤ በሁለተኛው ምለኒየም መጀመሪያ አካባቢ ነው›› በሚል ጥቅል ነገር ያነሳ ይሆናል እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ በኃይለማርያም ደሳለኝ እና በመንግስቱ ኃይለ ማርያም መካከል ልዩነት አይመለከትም ብቻ ሣይሆን ልዩነት የማየት ፍላጎትም ጨርሶ አይኖረውም፡፡

በ3010 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታሪክ ፀሐፊ የሚኖር ከሆነ፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ታሪክ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ማንሳቱ አይቀርም፡፡ ይህን ታሪክ ሲጽፍም፤ ‹‹አባቶቻችን ለበርካታ ዓመታት የአባይን ወንዝ ለማልማት የሚያስችሉ የተለያዩ ጥናቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ብዙዎቹ ጥረቶች ከሽፈዋል፡፡ የአባይን ወንዝ የማልማት ዕቅድ ሁሌም ከውጭ ዕርዳታ ጋር ተያይዞ የሚታሰብ በመሆኑ፤ ዕርዳታ ፍለጋ ሲወጡ፤ ዘወትር ሐሳባቸውን በእንጭጩ የሚቀጭ ምላሽ እየገጠማቸው፤ ከኛው ሐገር መንጭቶ በበራችን ከሚፈሰው የአባይ ወንዝ አንዲት ጠብታ ውሃ መንካት ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ ግብፅም፤ ‹ከአባይ ውሃ አንዲት ጠብታ ውሃ መንካት አትችሉም› በሚል እያስፈራራችን ረጀም ዘመን ቆይተናል፡፡ እንዲህ ዓይነት መራራ በደል ተሸክመን በመኖራችን ከፍተኛ የመንፈስ ስብራት ደርሶብን ነበር፡፡ ሰፊ ለም መሬት እና የውሃ ሐብት ይዘን፤ በተደጋጋሚ በረሃብ ማለቃችን እና በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች እየተራቡ በዓለም ህዝብ ፊት ለልመና መቆማችን የመንፈስ ስብራት ፈጥሮብን ነበር፡፡ ስለዚህ የ‹መቻል› ሳይሆን ‹ያለመቻል› መንፈስ ነግሶብን፤ ድህነት እንደ በሬ ቀንበር ጭኖ፣ እንደ ባሪያ ቋንጃችንን ሰብሮ ሲገዛን ኖሯል›› የሚል ታሪክ ሊፃፍ ይችላል፡፡

እንዲህ ያለ ታሪክ ላለው ህዝብ፤ እንደ ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት በራስ አቅም ለመስራት መነሳት የሚኖረው ትርጉም ትልቅ ነው፡፡ እኛ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ለመገንባት መነሳታችን፤ የበራ ሻማን እፍ ብሎ ማጥፋት ይሳነው የነበረ ሰው፤ ተራራን ገፍቶ ለመጣል ሲነሳ ከማየት ጋር ሊነፃፀር የሚችል ለውጥ ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት እንደ አውድማ በሬ በዝማም ሸብቦ ከያዘን ‹‹የአይቻልም መንፈስ›› መፈታት ነው፡፡ ስለዚህ፤ የህዳሴውን ግድብ ያለ ውጭ ዕርዳታ ሰርቶ ማጠናቀቅ ሳይሆን ‹‹ግድቡን ራሳችን እንገነባዋለን›› ብለን ከመነሳታችን የሚልቅ እና ተዓምራዊ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነገር የለም፡፡  ከሞት መነሳት እንጂ፤ ከተነሱ በኋላ መራመድ ተአምር አይሆንም፡፡ እንደኔ ሐሳብ፤ የህዳሴው ግድብ የፈጠረው የመንፈስ ብርሃን፤ ከኢትዮጵያ ድንበር እና ከዘመን አጥር ተሻግሮ፤ በተከታታይ ብዙ ትውልዶች ልብ ውስጥ ሊያበራ የሚችል፤ የአፍሪካ ህዳሴ ፋና ለመሆን የሚችል አህጉራዊ ክስተትም ነው፡፡ ከጠፈር ላይ ሆኖ ትልቁ የቻይና ግንብ ይታያል እንደሚባለው፤ 3007 ዓ.ም ሆነን ወደ ኋላ ስንመለከት ጎልተው ከሚታዩን የዛሬው ትውልድ ክንዋኔዎች አንዱ የህዳሴው ግድብ ሊሆን ይችላል፡፡

በዕቅድ ከተያዙት እና በአባይ ተፋሰስ ሊገነቡ ከሚችሉት ግድቦች ውስጥ ትልቁ የሆነው እና ለመጪዎቹ 400 ዓመታት ሊያገለግል የሚችለው ይህ ግድብ፤ ወደፊት የሚመጡ ተከታታይ ትውልዶች በልዩ አድናቆት የሚመለከቱት ሥራ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ሐገሪቱን ከአንድ ሺህ ለሚበለጥ ዓመታት ቁልቁል እያወረዳት፤ እንደ ሲዖል አዘቅት ያለ ማቋረጥ እየዋጣት፣ ከተስፋ መቁረጥ ጠርዝ የጣላት፣ የተሸናፊነት መንፈስ ያከናነባት የውርደት ጉዞ እንዲገታ ማድረግ የቻለ ትውልድ ነው፡፡ ሐገሪቱን፤ ከአይቻልም መንፈስ መንጥቆ ያወጣ ጀግና ትውልድ ነው፡፡

አሁን እኛ ስለራሳችን ያለን ግምት ብቻ ሣይሆን፤ ዓለም ስለኛ ያለው ግምትም ተለውጧል፡፡ ታላቁ የህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየተሰራ ያለው፤ የውርደትን መራራ ጽዋ ሲጨልጥ በቆየው፤ ረሃብን፣ ድህነትን፣ ስደትን እስኪያንገሸግሽ በተጋተው፤ በመጥፎ የታሪክ ሸክም ጎብጦ እና ቅስሙ ተሰብሮ በደቀቀው፤ በዚህ በእኛው ትውልድ መሆኑ ልዩ ትርጉም አለው፡፡ በልቶ በተረፈው ትውልድ ሳይሆን፤ ገና በልቶ መጥገብ ባልጀመረው በዚህ ትውልድ መገንባቱ ልዩ ትርጉም ይሰጣል፡፡

በዚህ ረገድ፤ ይህ የኛ ትውልድ አርበኛ ትውልድ ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ትውልድ፤ ከፊተኛው ትውልድ ድህነትን ተቀብሎ፤ ከእርሱ በኋላ ለሚመጡ ትውልዶች ብልፅግናን አውርሶ የሚያልፍ ልዩ ትውልድ ነው፡፡ ይህን ትውልድ ከቀዳሚው የተለየ እንዲሆን የሚደርግ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይህ ትውልድ ጠላቱን ለይቶ አውቋል፡፡ ‹‹ዋነኛ ጠላቴ ድህነት ነው፡፡ ዘረኝነት፣ ጥላቻ እና ቂም ዋነኛ ጠላቴን መዋጋት እንዳልችል አስሮ የያዘኝ ሰንሰለት ነው›› ብሏል፡፡ ድህነትን እና የድህነት ሚዜ የሆነውን ኋላ ቀርነትን ከማስወገድ በቀር፤ ሌላ የከበረ እና የላቀ ግብ የለኝም ብሏል፡፡ ይኸ ትውልድ ይገርማል፡፡ በፍቅር፣ በይቅርታ እና በመደመር መንፈስ አዲስ ታሪክ ለመስራት ቆርጦ ተነስቷል፡፡

እኔ ያለፉ አራት መቶ ዓመታት የኢትዮጵያ ታሪክን ተመልክተህ፤ ከቅኝትህ የተገነዘብከውን የታሪክ ሐቅ አስፍር ብባል፤ ኢትዮጵያን እጅ ከወርች አስረው ያሰቃይዋት፣ የግሪንግሪት ጥለው የረጋገጧት ሁለት ዋነኛ ችግሮችን ተናገር ቢሉኝ፤ ‹‹የሀገራችን ሁለት ሠይጣን ችግሮች፤ ሐይማኖትን ወይም ጠቅላይ ግዛትን ሰበብ አድረገው የሚለኮሱ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ወይም ግጭቶች፤ እንዲሁም የውጭ ወራሪ ኃይሎች ቀጥተኛ ጥቃት እና ዘወርዋራ ሸፍጥ ናቸው›› እላለሁ፡፡ እነዚህ ሁለት ችግሮች፤ ለድህነት እና ለኋላ ቀርነት አሳልፈው ሰጡን፤ ድህነት እና ኋላ ቀርነት መልሰው ለሁለቱ ችግሮች ያቀብሉናል፡፡ ቅብብሎሹ ያለ ማቋረጥ ይቀጥላል፡፡ እንዲህ ሆኖ እዚህ ደርሰናል፡፡

ይህ ትውልድ፤ ያለፉ ተከታታይ ትውልዶች፤ ‹‹የጠላቶቼ አካል›› የሚሉትን ነገር ሁሉ ‹‹ጥላቸው እንጂ አካላቸው አይደለም›› አለ፡፡ ‹‹የችግራችን ምንጭ ከውጭ ነው›› ብለው ወደ ውጭ ሲመለከቱ፤ እርሱ ‹‹ምንጩ ከውስጥ ነው›› ብሎ የቤቱን ወለል አደላደለ፡፡ እነርሱ፤ ‹‹ዕርዳታ የሚሰጠኝ ማነው›› ብለው፤ የውጭ ዕርዳታ ፍለጋ ዓይናቸውን ሲያንከራትቱ፤ እርሱ፤ ‹‹በራሴ ገንዘብ እሰራለሁ›› አለ፡፡

ደም እና አጥነቱን ገብሮ ያስከበረውን ነፃነት፤ ድህነቱ እያስነጠቀው በውርደት ቆየ፡፡ ድሃ እና ኋላ ቀር ብትሆንም፤ ነፃነቷ የተከበረ ሐገር አውርሶን አለፈ፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ፋና፣ የፀረ – ቅኝ አገዛዝ ትግል ቀንዲል የሆነች፤ ለጥቁር ህዝቦች ትግል የመንፈስ ኃይል በመሆን ታላቅ ከበሬታ የሚሰጣት ሀገር አስረከቡን፡፡

ኢትዮጵያ፤ ኋላ ቀርነት የተጫናት፣ ድህነት ያደቀቃት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት ያደከማት፣ የተረጋጋ የመንግስት አስተዳደር መመስረት የተሳናት ሐገር ሆና፤ የቅኝ አገዛዝ ኃይሎች  እንደ ተራበ አውሬ በዙሪያዋ ሲያንዣብቡ፤ እንደ ተኩላ መንጋ ዘለው ሊሰፍሩባት ሲያደቡ ቢቆዩም ነፃነቷን አስከብራ ኖረች፡፡

ሐገሪቱን ለጠላት ተጋላጭ የሚያደርጋት፤ ኋላ ቀርነት መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘቡት፤ አፄ ቴዎድሮስ ነበሩ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ጉዳይ አደጋ እንደተጋረጠበት ገብቷቸዋል፡፡ ስለዚህ በየአካባቢው ሥልጣን በያዙ እና እርስ በእርስ በሚቀናቀኑ መሳፍንት የተከፋፈለችውን ሐገር በጦርነት አንድ ለማድረግ ሞከሩ፡፡

ቋራ በሚገኝ አንድ ገዳም ውስጥ ትምህርቱን ሲከታተል የነበረው ህጻኑ ካሣ ኃይሉ፤ ኋላ አፄ ቴዎድሮስ ተብሎ ሊነግስ፤ ጥቂት ተከታዮችን ይዞ፤ የጎበዝ አለቃ ሆኖ የታሪክ ጉዞውን ጀመረ፡፡ ከሌሎች አቻ የአካባቢው መሳፍንት በተለየ  አስተሳሰብ እየተመራ፤ ለተጠቁ አለኝታ የመሆን እና ለፍትህ የመቆም ዝንባሌን እያሳየ፤ እያደርም ተከታዮቹን እያበዛ  የመጣው ካሣ ኃይሉ፤ የኢትዮጵያን ድንበር ገፍቶ፤ ሱዳንን በኃይል በመያዝ በሐገሪቱ አገዛዙን ከመሠረተው የግብፁ ገዢ መሐመድ ዓሊ ጋር ‹‹ደባኪ›› በተባለች ሥፍራ ጦርነት ገጠመ፡፡ ‹‹ደባኪ›› ላይ አስቦት እና ገምቶት የማያውቅ ሽንፈት ደረሰበት፡፡ አንዳንድ የታሪክ ፀሐፊዎች፤ ‹‹በአፄ ቴዎድሮስ ህሊና ለሥልጣኔ የመጓጓት ልዩ ስሜት እንዲፈጠር ያደረገው የደባኪ ጦርነት ነው›› ይላሉ፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ልዩ የመሪነት ሰብዕና እና ብቃት የተገለጠው በዚሁ የጦርነት መሆኑንም ይመሰክራሉ፡፡ ካሣ ኃይሉ፤ ‹‹ድባኪ››  ላይ ከግብፁ መሐመድ ዓሊ ጋር ጦርነት ገጥሞ  ክፉ ሽንፈት ሲገጥመው፤ ሽንፈቱን ሳያቅማማ ተቀብሎ፤ የሽንፈቱ ምንጭ ምን እንደሆነ ለመረዳት መቻሉን በማድነቅ፤ የመሪነት ብቃቱ የተገለጠበት የመጀመሪያው አጋጣሚም ይኸው መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ የታላቅ መሪነት መገለጫ ጠባዩ፤ ሽንፈቱን መቀበሉ እና የሽንፈቱ ምንጭ ለይቶ ችግሩን ለማስወገድ ጥረት ማድረጉ ነው፡፡