እንደ አባይ ወንዝ በመደመር (ከመቅደላ እስከ ጉባ) (ክፍል ሁለት)

የታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት፤ ካሣ ኃይሉ በህይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ያየው፤ ደባኪ ላይ በተካሄደው ጦርነት ነበር፡፡ የቋራው ካሳ እንደ አንበሳ የሚያስፈሩ ጋሜዎቹን አሳልፎ፤ ከመሐመድ ዓሊ ጋር ደባኪ ጦርነት በገጠመ ጊዜ፤ ከዚያ ቀደም አይቶት የማያውቀው የመድፍ ቅምቡላ እያስገመገመ እና እየተምዘገዘገ መጥቶ መሬት – ሰማዩን ሲደበላልቀው ተመለከተ፡፡ ወደ ፊት የሚገጥመውን ጦርነት፤ በልበ ሙሉ ወታደሮቹ ጀግንነት ብቻ የሚዘልቀው አለመሆኑ ገባው፡፡ ደባኪ ላይ ጦርነት የገጠሙት፤ ጥበብ እና ድንቁርና ነበሩ፡፡

ሻምላቸውን አገንድረው፤ በጀግንነት ገድሎ መሞትን እንጂ፤ ንግድ የሚባል ነገር የማያውቀውት እኒያ የጃፓን የጦር አበጋዞች፤ ይህን የሻምላ ባህል እና ወግ አፍርሶ፤ ከጀርመኖች ጥበቡን ቀስሞ ቢራ ሲነግድ ያገኙትን አንድ ዘመዳቸውን ሲወቅሱ፤ ‹‹ልጄ የአባቶችህን ወግ ትተህ፤ ሻምላ አገንድሮ በጀግንነት መሰለፉን እንደ ከንቱ ነገር ወዲያ ጥለህ፤ ቢራ ጠማቂ ትሆን?›› በሚል ሲወቅሱት፤ ‹‹አጎቴ ተሳስተሃል፡፡ የዘንድሮ ሻምላ እንደ ድሮው፤ አየሩን ሲቀዝፍ ጆሮ የሚበጥሰውን የጃፓኖችን ሻምላ ይዞ መገኘት አይደለም፡፡ የዚህ ዘመን ጀግንነት፤ ዶላር ይዞ መገኘት ነው›› እንዳለው፤ ካሣ ኃይሉ በደባኪ (Dabaki) አውደ ግንባር፤  ዋናው ነገር ጥበብ እንጂ ባዶ ጀግንነት እንዳልሆነ ተረዳ፡፡ የደባኪ ትምህርት ዕድሜ ዘመኑን ሁሉ  እረፍት ነስታ ጥበብን ፍለጋ እንዲባዝን አደረገችው፡፡ በመጨረሻም ለሞት የሚያበቃ ስህተት አሰራችው፡፡

ያቺ ‹‹የአባቶቼ ሀገር›› እያለ ይጠራት የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ዘመናዊ ዕውቀትን ወይም የጦር መሣሪያን ካልታጠቀች፤ በዙሪያዋ ከሚያገሱት የተራቡ አውሬዎች አንዱ መጥቶ እንደሚሰለቅጣት፤ ያቺ የመሳሪያ ‹‹ሀሁ›› የተማረባት ዳባኪ ነግራዋለች፡፡ ስለዚህ የጦር ኃይሉን ለማዘመን፣ የመንግስትን አስተዳደር ለማፅናት፣ ወሳኝ አድርጎ የሚመለከተውን ጥበብ ለመቅሰም ተጋ፡፡ በዚሁ ሰበብ ከታላቋ ብሪታንያ ጋር ለመቀያየም በቃ፡፡ ‹‹የእጅ ሙያ የሚያሰለጥን ሰው ላኩልኝ›› እያለ በወዳጅነት ሲጠይቅ ቆይቶ፤ አልሆን ሲለው፤ ወዳጆቹ ሙያተኞች ከአውሮፓ እንዲያመጡለት በግል ሙከራ አድርጎ አልሳካ ሲለው፤ ለስብከት ከመጡት የመጡት አውሮፓውያ መካከል መርጦ፤ ጋፋት ላይ ጥበብን በኢትዮጵያ ሊያላምድ ሞከረ፡፡ በመንገድ እና በብረታ ብረት ወዘተ ሥራ የሚያግዙትን እያከበረ፤ ሰባኪ ነኝ ባዮቹን ሰሜን ‹‹ያና›› እንዲቀመጡ አድርጎ የቻለውን ሁሉ አደረገ፡፡ በመጨረሻም፤ የእየውሻከቱ፤ እንዳሰበው አልሆን ሲሉት እና እንግሊዝም ለላከው ደብዳቤ ምላሽ ስትነፍገው፤ ሰባኪ ነን ባዮቹን የውጭ ሐገር ሰዎች (ቆንስላዎቹን) ጠራርጎ እስር ቤት አስገባቸው፡፡

‹‹የና›› እና ‹‹ጋፋት›› የቴዎድሮስን ሁለት ፈተናዎች መወከል የሚችሉ ናቸው፡፡ ጋፋት የጥበብ መንደር ነች፡፡ የና ደግሞ የውጭ ሐገር ሰባኪዎች ወረዳ ነች፡፡ ካሣ ሰባኪ ነን ባዮቹን የውጭ ሐገር ሰዎች ወደ የና የላከው፤ ለቤተእስራኤሉ ክርስትና እንዲሰብኩ ነበር፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ችግሩ በደንብ ገብቷቸው ነበር፡፡ ግን ችግሩን መፍታት ተሳናቸው፡፡ እንደ ዛሬው ዘመን በባህር ማዶ ያለውን ፖለቲካ ምን እንደሚዘውረው ፈጽሞ መረዳት አልቻሉም፡፡ ለምሣሌ፤ ‹‹ክርስቲያናዊ መንግስት›› ብለው የሚያስቡት የእንግሊዝ መንግስት፤ ከፖለቲካ ፍላጎቱ ተነስቶ አጤ ቴዎድሮስ ‹‹እስላማዊ መንግስት›› ብለው ከሚያስቡት ወገን ጎን ተሰልፎ ሊያጠቃቸው እንደሚችል ማሰብ የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ‹‹ክርስቲያናዊ መንግስት›› ሌላ ክርስቲያናዊ ነኝ የሚባልን መንግስት የሚወጋበት ሁኔታ መኖሩን የተረዱ አልነበሩም፡፡ እንዲህ ዓይነት የተሳሳቱ የፖለቲካ ስሌቶች ነበሯቸው፡፡ ስለዚህ ችግሩን ቢረዱትም፤ የችግሩን አፈታት የሚያግዝ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታውን ለመረዳት የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ተሳሳቱ፡፡ ሐገሪቱን አንድ ለማድረግ በዘመቻ እና በድንኳን ያለቀ ዘመን ገፍተው ወደ ፍጻሚያቸው አመሩ፡፡

የኛ ትውልድ ከዚያ ዘመን እየተንከባለለ የመጣ ችግር የመፍታት ዕዳ የወደቀበት ትውልድ ነው፡፡ ስለዚህ ራሱን መረመረ፡፡ ራሱን አልሸነገልም፡፡ ሀገራዊ ክብርን እየጠቀሰ ከመኩራራት መላቀቅን መረጠ፡፡ ‹‹የሥልጣኔያችን ምንጭ የሆነውን ሥራ ትተን ታሪኩን ብናወራ ጠብ የሚል ነገር የለም›› እንደ ሐገር በሚሊዮኖች ስንዴ ልመና እየወጣን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአረብ አገር ለግርድና እየተሰደዱ ባለበት ሁኔታ በአባቶቻችን ከታሪክ ብንኮራ ራስን ማታለል ነው፡፡ ያለ ውጭ ዕርዳታ፤ የማይንቀሳቀስ ኢኮኖሚ ይዘን፣ ዳገት የሚወጣ ነፃነት አለን ማለት አንችልም›› እያለ ከእውነቱ ጋር ተጋፈጠ፡፡

‹‹ፈጣን ዕድገት ካላረጋገጥን እንደ ሀገር ህልውናችን አደጋ ላይ ይወድቃል›› የሚል መነሻ ይዞ፤ ከድህነት ናዳ ለማምለጥ እንደሚሮጥ ሰው መስራት አለብን ብሎ ተረባረበ፡፡ የሀገሪቱን ልማት የሚያግዝ የኤሌክትሪክ ኃይል መፍጠር እንደሚገባ ተረድቶ፤ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ፈለገ፡፡ በታላቅ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ነገሮችን መልክ ካስያዘ በኋላ፤ የግድቡን ግንባታ ጀመረ፡፡ ይኸው ዛሬ ከ60 በመቶ በላይ የግድቡ ሥራ ተጠናቆ ሰባተኛ ዓመቱን ለማክበር በቅተናል፡፡ ህዝቡ ዛሬም እንደ አባይ በመደመር ኃይሉን አስተባብሮ እንደ ጀመርነው እንጨርሰዋለን እያለ ነው፡፡   

አፍሪካውያን ወንድሞቻችን፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ያለ ውጭ እርዳታ ምን መስራት እንደሚቻል አሳይተውናል›› እያሉ ነው፡፡ አሁንም የነፃነት አብነት አድርገው እየተመለከቱን ነው፡፡ የህዳሴው ትውልድ፤ ሐገራችን ለብዙ ዘመናት የማይፈታ እንቆቅልሽ ሆኖባት የተቸገረችበትን ነገር እየፈታ በመደመር መንፈስ በድል እየተረማመደ ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ፤ የጦርነት ቀጣና ለሆነው የአፍሪካ ቀንድ የኤሌትሪክ ኃይል ማማ እና የሰላም ካስማ በመሆን ስሟ የሚጠራበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር የነበሩት ዶ/ር ኒኮሳዛኒ ዲላሚኒ ዙማ፤ በአንድ ወቅት ከ‹‹ሚት ኢቴቪ›› ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የአፍሪካ ተስፋ ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ኮሚሽነሯ ከተፈራ ገዳሙ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በአፍሪካ አሳሳቢ ችግሮች መኖራቸውን አይክዱም፡፡ ግን ኢትዮጵያን እና ሩዋንዳን አብነት አድርገው፤ ዛሬ በአፍሪካ የሚታየው ተስፋ እንደሚበልጥ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ አፍሪካ የረጅም ጊዜ ራዕይ ነድፋ ጉዞ መጀመሯን ገልፀዋል፡፡

ዛሬ በአፍሪካ ምድር ችግር ስላለ፤ ወደፊት ሊፈጠር ስለሚታሰበው ነገር ማውራት አስፈላጊ አይደለም የሚሉ ወገኖች መኖራቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነሯ፤ ሆኖም እንዲህ ያለ ትችትን መቀበል እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡ አፍሪካውያን፤ ከ‹‹ዛሬ አስቀያሚ እስር ቤት›› አምልጠው በመውጣት፤ ዛሬ በአፍሪካ ምድር የሚታዩ አስቀያሚ የኑሮ ሐቆችን ተሻግረው በመሄድ፤ ነገ የሚጠብቀንን ውብ ህይወት በተስፋ ማለም የሚሰጠውን የለውጥ ኃይል መታጠቅ እንደሚሹ ገልፀዋል፡፡

ተፈራ ገዳሙ አልቀቃቸውም፡፡ እንዲህ በማለት ጥያቄ አነሳ፡፡ ‹‹የአፍሪካ ሀገራት ውህደት፤ ቅዠት እንጂ እውን ሊሆን የሚችል ህልም አይደለም›› በሚል የሚተቹ ወገኖች መኖራቸውን ጠቅሶ፤ ‹‹ራዕዩ ጥሩ ነው፡፡ ግን አሁን በአንዳንድ የአፍሪካ ሐገራት በተጨባጭ የሚታየው ሁኔታ፤ የዚህን ራዕይ እውን የመሆን ዕድል የሚያመለክት አይደለም፡፡ በአህጉሪቱ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር፤ በማዕከላዊ አፍሪካ፣ በማሊ፣ በናይጄሪያ፤ በቅርቡ ደግሞ በደቡብ ሱዳን የምንመለከተው ግጭት ወይም የእርስ በእርስ ጦርነት ይህን ራዕይ የሚፃረሩ ጉዳዮች አይመስለዎትም?›› የሚል ጥያቄ ሲያነሳ፤ የጠቀሰውን የተለመደ የአፍሪካ ትርክት (Narative) መደጋገም፤ ዛሬ የሚታየውን አስቀያሚው እውነት ለመለወጥ የሚያስችለንን ኃይል የሚሰልብ መጥፎ ደዌ መሆኑ የታያቸው ኮሚሽር ኒኮሳዛኒ ዲላሚኒ ዙማ፤ ‹‹የእኛ የአፍሪካውያን አንዱ ችግር ይኸ ነው›› በማለት ምላሽ መስጠታቸውን ቀጠሉ፡፡

‹‹በተለይ የጋዜጠኞቻችን ችግር ይኸ ነው፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት፤ የቅኝ አገዛዝ መወገድ አለበት፤ አፓርታይድ ከሥሩ መነቀል አለበት፤ ይህን ትግል የሚያስተባብር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት አለበት የሚል ራዕይ ይዘው ሲነሱ፤ እኒያ ባለራዕይ የአፍሪካ መሪዎች  ህልማቸውን በይፋ ሲያውጁ፤ ጨለምተኛ አመለካከት የያዙ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች፤ ራዕያቸውን ‹ሊሳካ የማይችል ከንቱ ቅዠት› በሚል ሲያካኪሱት ነበር፡፡ እኒያ ባለራዕይ  የአፍሪካ ልጆች ወይም መስራች አባቶች፤ የራዕያቸውን ፋና መከተል ትተው፤ የጨለምተኞቹን ድምፅ በመስማት፤ ‹አዎ፤ እውነት ነው፡፡ የማይቻል ነው›› ብለው፤ መስራች አባቶች ራዕያቸውን እውን ለማድረግ ያደርጉትን እንቅስቃሴ እርግፍ አድርገው ተቀምጠው ቢሆን ኖሮ፤ ዛሬ የምናያት ከቅኝ አገዛዝ እና ከአፓርታይድ የመድሎ አስተዳደር ነፃ የወጣች አፍሪካን ለማየት ባልታደልን ነበር›› በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹ወደፊት ተመልካች መሆን አስፈላጊ ነው፡፡ ለምናባችን ወይም ለራዕያችን ሰፊ ሜዳ መስጠት ይኖርብናል፡፡ ወደፊት ተመልካች የመሆን የአዕምሮ አዝማሚያ መያዝ፤ ለራዕያችን ተፈፃሚነት ሊያግዘን የሚችል አዲስ ጎዳና ይከፍትልናል፡፡ ራዕይህን መንከላወሻ ሜዳ አትንፈገው፡፡ አስቀድመህ፤ ‹የትም አልደርስም› ብለህ አትነሳ፡፡ ‹የትም አልደርስም› የሚል ሐሳብ ሲገዛህ፤ ይኸው ሐሳብህ ተጨባጭ እና እውን ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ ሐሳብህ፤ ራሱን ለማስፈፀም የሚችል ትንቢት (self- fulfilling prophecy) ይሆናል፡፡

‹‹በአፍሪካ፤ የጠቀስካቸው ችግሮች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ዋናው ነገር እነዚህን ችግሮች እንዴት ልናስወግዳቸው እንችላለን ብሎ፤ አቅጣጫ ተልሞ መንቀሳቀስ ነው፡፡ ከዚያም አልፈህ፤ የዛሬ ሃያ፣ ሠላሣ ወይም ሃምሳ ዓመት የት መድረስ እንደምትፈልግ ማሰብ ይኖርብሃል፡፡ አዕምሮህ ዛሬ በተዘፈቅህበት ችግር ተወስኖ ሲቀር፤ ትኩረትህ እሱ ብቻ ሲሆን፤ ለችግርህ ራሱን መላልሶ የሚወልድበትን ዕድል ትሰጠዋለህ፡፡ በጠላኸው ነገር ትወረሳለህ፡፡ የለውጥ የመጀመሪያ ምዕራፍ፤ ‹ይኸ ነገር እንዲህ መሆን የለበትም፡፡ የኔ ህይወት ከዚህ የተለየ መሆን አለበት› የሚል ቁርጠኛ ሐሳብ መያዝ ነው፡፡ ይህን ቁርጠኝነት ይዘህ ነገን ማለም አለብህ፡፡ ትኩረትህ ዛሬ በምትገኝበት መጥፎ ሁኔታ ብቻ መቀንበብ እና መወሰን የለበትም፡፡ ይኸ ነገር መቀየር አለበት ብለን፤ ነገ ሆኖ ማየት የምንፈልገውን ጉዳይ ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ወደፊት ተመልካች ሆነን፤ ዛሬ ያለውን ችግር ለመፍታት መጣጣር ይገባናል›› ብለዋል፡፡

‹‹ዛሬ የምናየው ግጭት፣ ድህነት፣ ስደት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር መለወጥ ያለበት ነው፡፡ ዛሬ እንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ ስለሆንን ትልቅ ራዕይ መንደፍ የለብንም ካልክ፤ ራስህን ተስፋ በሚያሳጣው የዛሬ ማንነትህ እንዲወሰን ታደርገዋለህ፡፡ እኔ እንዲህ ዓይነት የማልረባ ሰው ነኝ ትላለህ፡፡ የተሸናፊነት ስሜት ውስጥ ትቀረቀራለህ፡፡ ለዝንተ ዓለም በዚያው ችግርህ እንደተዘፈቅህ ህይወትህን ስታማርር ትኖራለህ፡፡ ይኸ ነገር ከኔ አቅም በላይ ነው ብለህ ትረታለህ›› ያሉት ዶ/ር ዙማ፤ ‹‹ዛሬ አፍሪካ በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ውስጥ ገብታለች›› በማለት፤ ኢትዮጵያን እና ሩዋንዳን በምሣሌ በመጥቀስ፤ ከራሳቸው የህይወት ተመክሮ ጋር አስተሳስረው የለውጡን ሁኔታ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

ዶ/ር ዙማ፤ ከሐገራቸው የአፓርታይድ አገዛዝ ሳይወገድ በፊት፤ በ1968 ዓ.ም በስደት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አስታውሰው፤ ‹‹በስዌቶ ከተካሄደው አመጽ በኋላ፤ በስደት ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ነበር›› በማለት ታሪክ ማውሳት የጀመሩት ዶ/ር ዙማ፤ በወቅቱ የነበረውን የአዲስ አበባ ወይም የኢትዮጵያ ሁኔታ በማስታወስ እና ዛሬ ሀገሪቱ ከምትገኝበት ሁኔታ ጋር በማነፃፀር፤ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ለውጥ እውን ሊሆን የቻለው፤ ‹‹አይቻልም›› የሚል ጨለምተኛ አመለካከት በሌላቸው የሐገሪቱ ልጆች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኃላፊነታቸውን ለአሁኑ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ መሀመት ከማስረከባቸው በፊት ባደረጉት በዚህ ቃለ ምልልስ፤ ‹‹በአሁኑ ጊዜ መኖሪያ ሐገሬ ወይም ቤቴ በሆነችው ኢትዮጵያ የሚታየውን ለውጥ፤ በ1968 ዓ.ም ከነበረው ሁኔታ ጋር ሳነፃፅረው፤ በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ለማየት እችላለሁ›› ያሉት ዶ/ር ዙማ፤ በ1966 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ረሃብ በማውሳት፤ ያ ረሃብ በመላው ዓለም በሰፊው የታወቀበት ሁኔታ በመፈጠሩ፤ ‹‹ሌላው ቀርቶ ለዓለም ዜና ደንታ ያልነበራት የእኔ እናት እንኳን ስለ ረሃቡ ታውቅ ነበር፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ ደማቅ ምስል ሆኖ በብዙዎች ህሊና ተቀርፆ የቆየው የዚያ ዘመን ረሃብ ነበር›› ብለዋል፡፡

አያይዘውም፤ ‹‹ዛሬ ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚጠቀሱ 10 የዓለም ሐገራት ውስጥ አንዷ ሆናለች፡፡ ከእነዚህ 10 ሐገራት ውስጥ 3ቱ የአፍሪካ ሀገራት ሲሆኑ፤ ከእነዚህ 3 የአፍሪካ ሐገራት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነችው ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው አስገራሚ የኢኮኖሚ ዕድገት ግን፤ አዲሱ የኢትዮጵያ መልክ ከመሆን ደረጃ አልደረሰም›› ብለዋል፡፡

በ1999 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የሐገራቸው የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ያገለግሉ እንደነበር የጠቀሱት ዶ/ር ዙማ፤ ‹‹በወቅቱ ለሥራ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ስመለስ፤ በኢትዮጵያ የሚላስ – የሚቀመስ ነገር ማግኘት የማይቻል የመሰላት እናቴ፤ ‹ለመሆኑ ልጄ የሚበላ ነገር አገኘሽ?› ብላኝ ነበር፡፡ በአጋጣሚ፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ቆንጆ የኢትዮጵያ ማር ሰጥተውኝ ስለ ነበር ለእናቴ ሰጠኋት፡፡ እናቴ የሰጠኋትን ማር ከቀመሰች በኋላ ‹ለመሆኑ እንዲህ ያለ ቆንጆ ማር ከየት አገኘሽ?› ብላ ጠየቀችኝ፡፡ ከኢትዮጵያ ያመጣሁት መሆኑን ስነግራት፤ ‹አይ፤ እንዲህ ዓይነት ማር ከሰጡሽ፤ እውነትም በኢትዮጵያ ረሃብ የለም ማለት ነው› አለችኝ›› ካሉ በኋላ፤ ዛሬ በዚህች ሐገር የሚታየው ለውጥ ሊመጣ የቻለው፤ ‹‹ይኽ አስቀያሚ ህይወታችን ሊቀየር ይገባል ብለው በተነሱ የሐገሪቱ ልጆች ጥረት ነው›› ብለው ነበር፡፡

በተመሳሳይ፤ በሌሎች የአፍሪካ ሐገራትም አበረታች ሁኔታዎች እንደሚታዩ አመልክተው፤ ‹‹በ1990ዎቹ በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ፣ በድህነት ስትቀጣ፣ በረሃብ አለንጋ ስትገረፍ በነበረችው ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ዓይነት ለውጥ ማየት እና ከዘግናኝ የዘር ማጥፋት እልቂት ወጥታ የልማት ጉዞ የጀመረችው ሩዋንዳ ያስመዘገበችውን የኢኮኖሚ ዕድገት መመልከት፤ አፍሪካ በእውነት እየተለወጠች መሆኑን ያረጋግጣል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አሁን የሚታየው አስገራሚ ለውጥ ሊፈጠር የቻለው፤ ‹‹ይህ አስቀያሚ ህይወት መቀየር አለበት›› በሚል ቁርጠኝነት ለሥራ በተሰለፉ ወገኖች›› መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ዙማ፤ በተወሰኑ የአፍሪካ ሐገራት የሚታየው አሳፋሪ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ግጭት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና የሙስና ችግሮችን፤ ትኩረት ሰጥተን ከሰራን በፍጥነት ልናስወግዳቸው እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ዛሬ በአፍሪካ ምድር የሚሰማው የጠብመንጃ ጩኸት እንዲጠፋ እና የህዝቡ ህይወት በፍጥነት እንዲለወጥ ለማድረግ፣ በርትተን የመልካም አስተዳደር ችግሮቻችንን ለማስወደግ መረባረብ ይኖርብናል፡፡ በርግጥ ከፊታችን የተደቀኑት ችግሮች፤ ከባድ፣ እልህ አስጨራሽ እና ውስብስብ ናቸው፡፡ ሆኖም፤ ለችግሮቹ ትኩረት ሰጥተን፣ በመንፈሰ – ፅኑነት ተሰልፈን፣ በማይዝል እና በማይበገር ቁርጠኝነት ከተጋፈጥናቸው እናሸንፋቸዋለን›› ብለዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያያን በፍቅር፣ በይቅታ እና በመደመር መንፈስ ከተጓዝን ለውጥ እናመጣለን፡፡ ከመቅደላ እስከ ጉባ ያደረግነው ጉዞ ጥንካሬአችንን ሳያያል፡፡ የጥንካሬአችን ምንጭም መደመር ነው፡፡