የሁለት መርማሪዎች ወግ

በወታደራዊው ደርግ ኢሰፓ ስርአት የመንግስት ስልጣን በህግ የተገደበ አልነበረም። ወታደራዊው ደርግ ከ1967 እስከ 1979 ዓ/ም ሃገሪቱን ለአስራ ሶስት ዓመታት የይስሙላ እንኳን ህገመንግስት ሳይኖረው ነበር ያስተዳደረው። የይስሙላም ቢሆን የህዝብ ውክልና  ያለው መንግስታዊ አካልም አልነበረውም። መቶ ገደማ የሚሆኑ ተመራርጠው ስልጣን ላይ የወጡ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንት እንደፈለጋቸው በሚያወጡት አዋጅ፣ መመሪያና በየግላቸው በዘፈቀደ በሚያስተላልፉት ትእዛዝ ነበር ሃገሪቱ የምትመራው። እስከ ቀበሌ መዋቅር ያሉ የስርአቱ ባለሟሎች በተለይ የአብዮት ጥበቃ የተሰኘው ተቋም ሃላፊዎችና አባላት ሰዎችን በራሳቸው ውሳኔ በቁጥጥር ስር የማዋል፣ ለፈለጉት ያህል ጊዜ የማሰር፣ የመደብደብ፣ የመግደል . . . ስልጣን ነበራቸው። ወታደራዊው ደርግ በ1980 ዓ/ም የኢህዲሪን ህገመንግስት ማጽደቁን ካወጀ በኋላ ባሉት ሶስት ዓመታትም ውስጥ ሁኔታዎች ምንም መሻሻል አላሳዩም። ለአስራ ሶስት ዓመታት በመጡበት ሁኔታ ነበር የቀጠሉት።

ታዲያ በእነዚህ ዓመታት በሃገሪቱ እጅግ ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል። ወታደራዊው ደርግ የዘውዳዊውን ስርአት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የጦር መኮንኖች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመግደል ነበር የሰብአዊ መብት ጥሰትን መፈጸምነ አንድ ብሎ የጀመረው። ከዚያ በኋላ የሰብአዊ መብት ጥሰት በአዋጅ የተፈቀደ ነበር የሚመስለው። ወታደራዊው ደርግ ከ1968 ዓ/ም ጀምሮ በገጠርና በከተሞች ህዝባዊው ተቃውሞ ሲያይልበት ደግሞ ተቃውሞውን ለማፈን የሰብአዊ መብቱን አጅግ አበረታው።

ሰዎች ያለምንም መረጃ በዘፈቀደ ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሚሰሩበት ቦታ፣ ከመንገድ ላይ ታፈነው ይወሰዳሉ። ታፍነው እንደተወሰዱ ይገደላሉ። በመላ ሃገሪቱ እስከቀበሌ ባለው የመንግስት መዋቅር የተቋቋሙ እስር ቤቶች ውስጥ ይታጎራሉ። ምንም አይነት የወንጀል ምርምራ እውቀት በሌላቸውና የፖሊስ ስነምግባር በራቃቸው ግለሰቦች አካላቸው እስኪጎድል፣ ህይወታቸው እስኪያልፍ ይደበደባሉ፣ ከእስር ቤት ወጥተው መንገድ ላይ በጠራራ ጸሃይ በጥይት ተደብድበው ይገደላሉ ወዘተ። የወንጀል ምርመራ ሞያ የሰለጠኑ ፖሊሶች የነበሩባቸው የደርግ ጽህፈት ቤትና የማዕከላዊ ምርመራ ጣቢያዎችም ቢሆኑ በፖሊስ የአሰራር ደንብና ስነምግባር መሰረት ሰብአዊ መብቶች አይከበሩባቸውም ነበር። እንዲያውም እጅግ የሰሉ የማሰቃያ ስልቶችን በመጠቀም ለመስማት የሚዘገንኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸሙባቸው ነበር።

በወታደራዊው ደርግ ስርአት እነዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በስውር አልነበረም የሚፈጸሙት። በማንአለብኝነት በይፋ ነበር የሚፈጸሙት። የስርአቱ ባለሟሎችና የጸጥታ አካላት የተለየ አመለካከት የያዙና የሚያራምዱ፤ የተለየ አመለካከት አላቸው ተብለው የተገመቱ ዜጎች ላይ ጭምር የሰብአዊ መብት ጥሰት የመፈጸም ስልጣን እንዳላቸው ነበር የሚያስቡት። በወቅቱ ከወጣትነት እድሜ ጀምሮ ያሉ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በተለያየ አጋጣሚ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባዎች ሆነዋል። በዘፈቀደ ውሳኔ መታሰር፣ መደብደብ፣ በግዳጅ ለውትድርና መመልመል ወዘተ አብዛኞቻችን የዚያ ዘመን ወጣቶች ቀመሰነዋል።

በወታደራዊው ደርግ ዘመን የነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰት ሁሉም ዜጋ የሚያውቀው ይፋ የነበረ ቢሆንም፣ በስርአቱ ውድቀት ማግስት የጥሰቱ ሰለባዎችና ዘመዶቻቸው በመገናኛ ብዙሃን መጥተው የደረሰባቸውንና ያዩትን የሰብአዊ መብት ጥሰት ድርጊት ሲናገሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደአዲስ በእንባ ተራጭቷል። በደርግ ውድቀት ማግስት አሰቃቂ ድብደባ የሞቱ ሰዎች ታሪክ በይፋ ተነገረ። ለቋሚ የአካል ጉዳት የተዳረጉ፣ የአባለ ዘር አካላቸው ላይ በደረሰ ጉዳት የመከኑ፣ ለስነልቦና ችግር የተዳረጉ ወዘተ ዜጎች ታሪካቸው ተዘከዘከ። ይህን የፈጸሙ ግለሰቦች በቴሌቪዥን መስኮት ቀረበው ለህዝብ ታዩ። በኋላም ማስረጃ እየተሰባሰበ ክስ ተመሰረተባቸው። በጥፋታቸው ልክ ቅጣት ተወሰነባቸው። የወታደራዊው ደርግ የቀይ ሽብር የአፈና፣ የድብደባና የግድያ ዘመቻ ሰለባዎች መታሰቢያ ሙዚየምም ተቋቋመ። ይህ ሙዚየም በተወሰነ ደረጃ የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ያስታውሳል።

በወታደራዊው ደርግ የስልጣን ዘመን የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፋ የወጡት፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በነጻ የፍርድ ሂደት ተሟግተው ጥፋተኝነታቸው በማስረጃ ተረጋግጦ የተቀጡት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሰለባ የሆኑ ዜጎችን የሚዘክር ሙዚየም የተቋቋምው ለወደፊት የዚያን አይነት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይደገም ለማስተማርም ጭምር ነበር።

ይሁን እንጂ አሁንም ትምህርት ያለመወሰዱን የሚያመለክቱ እውነታዎች ይፋ እየወጡ ነው። ሰሞኑን በመገናኛ ብዙሃን የምንሰማው የሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚመለከት ጉዳይ እጅግ አስደንግጦናል። ከነጻ የፍርድ ሂደት ውጭ ሰዎች የሚገደሉበት፣ ለዓመታት የሚታሰሩበት ሁኔታ ላይ ለውጥ መኖሩ እርግጥ ነው። ቢኖር እንኳን የስርአቱ ዋና መገለጫ በሚሆነበት ደረጃ አይደለም፤ ግለሰቦች ስለጣናቸውን ተገን አድርገው ከህግ ተሸሽገው የሚያደርጉት ከመሆን ውጭ አይደለም። ይሁን እንጂ በወንጀል ምርመራ ሽፋን የሚፈጸሙት ለአካል ጉዳትና ለመካንነት የሚዳርጉ ድብደባዎች፣ ሰብአዊ ክብርን የሚያዋርዱ ድርጊቶች፣ ለስነልቦና ቀውስ የሚያጋልጡ አያያዞች፣ ወዘተ በወታደራዊው ደርግ ከነበረው ጋር በተቀራረበ ሁኔታ ሲፈጸሙ መቆየታቸውን ታዝበናል።

በኢፌዴሪ የመንግስት ስርአት የተፈጸሙት እነዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ግን በዘግናኝነትና በመጠን ወደር ከማይገኝለት በወታደራዊው ደርግ ዘመን ከተፈጸመው በላይ የሚያሙ ናቸው። ይህ የሆነው በህገመንግስት የተገደበ ስልጣን ተሰጥቶት በህዝብ ውክልና ስልጣን የተረከበ መንግስት ባለበት፤ ስልጣኑን የገደበው ህገመንግስት ሁለት ሶስተኛ አንቀጾች የሰበአዊ መብት መከበርን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን በያዘበት ሁኔታ የተፈጸሙ በመሆናቸው ነው። አሁን ከቀደሙት ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥፋቶች ተምረን የሰብአዊ መብት ጥሰትን የሚጠየፍ ስነምግባር ገንብተናል ብለን የምናስብበትና ለመንግስት ስልጣን የህግ ገደብ ያበጀንበት ዘመን ላይ ነን። አሁን የተፈጸሙት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይበልጥ የሚያሙን ለዚህ ነው። ወታደራዊው ደርግ ምንም የስልጣን ገደብ አልነበረውም፤ በባለስልጣን ትእዛዝ መግደል፣ መገረፍ፣ የውትድርና ግዳጅ ላይ ማሰማራት፣ ማጋዝ ወዘተ  የህግ ጉዳይ አልነበሩም።

የኢፌዴሪ ህገመንግስት ምዕራፍ 3፣ በክፍል አንድ ሰብአዊ መብቶች በክፍል ሁለት ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚሉ ርዕሶች ስር ከአንቀጽ 13 እስከ 44 መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶችን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን አስፍሯል። በተለይ አሁን በምርመራ ማቆያ/ማረፊያ ቤቶችና በማረሚያ ቤቶች እንደተፈጸሙ የተነገረንን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አስመልክቶ በክፍል አንድ ሰብአዊ መብቶች በሚል ርዕስ ስር ከአንቀጽ 14 እስከ 28 መደረግ ያለበትንና ክልከላዎችን የያዙ ድንጋጌዎች ሰፍረዋል። ከእነዚህ መሃከል፤ የህይወት፣ የአካል ደህንነትና የነጻነት መብት፤ ኢሰብአዊ አያያዝ ስለመከልከሉ፤ የተያዙ ሰዎች መብት፤ የተከሰሱ ሰዎች መብት፤ በጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት፤ በስብዕና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚሉት ድንጋጌዎች ተጠቃሾች ናቸው። ሰሞኑን ይፋ የሆኑ ጉዳዮች የእነዚህን ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎች መጣስ የሚያመለክቱ ናቸው።

የህገመንግስቱ አንቀጽ 13 ቁጥር 1፤ በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌደራል መንግስትና የክልል ህግ አውጭ፣ ህግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሎች በዚህ ምዕራፍ (ምዕራፍ 3) የተካተቱትን ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ግዴታ አለባቸው ይላል። ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቶች እስረኞች በምርመራ ሂደትና በማረሚያ ቤት የተፈጸመባቸውን የመብት ጥሰት አካላቸውን ለአስረጂነት እያሳዩ አቤቱታ ሲያቀርቡ ጉዳዩን በችልታ ማለፋቸውን ተረድተናል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በእስር ቤቶች ያለውን ሁኔታ መርምሮ የደረሰበትን የሰብአዊ መብት ጥሰት የተመለከተ ሪፖርት ለፌደራልና ለክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ለሌሎች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አስፈጻሚዎች ቢያቀርብም ጉዳዩን ችላ ማለታቸውን ተረድተናል። እነዚህ የመንግስት አካላት በሙሉ በህገመንግስት የተጣለባቸውን ሃላፊነትና ግዴታ አላከበሩም።

የወታደራዊው ደርግ “ወንጀል መርማሪዎች” ኢሰብአዊ ድርጊት መፈጸማቸው በይፋ ተነግሮ እነዚህ ጥሰቶች እንዳይደገሙ ቃል በተግባባንበት ሁኔታ፣ በህገመንግስታዊ ድንጋጌ ጥበቃ ባተቀመጠበት ሁኔታ ሌሎች መርማሪዎች የሰብአዊ መብት ጥሰቱን ደግመውታል። እነዚህና የቀደሙቱ “ወንጀል መርማሪዎች” በጊዜ የሚለያዩ ቢሆኑም በምግባርና በድርጊት ግን ተመሳሳይ ናቸው።