“በአንድ ጠማማ ዛፍ የተነሳ ደኑ አይለቅ”

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ጓድ ዶ/ር አቢይ አህመድ ስለ ፍቅር፣ አንድነትና መደመር አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ያነሱ ሲሆን በአንፃሩ ዘረኝነትን፣ ሙስናንና ጥላቻን መኮነናቸውን ቀጥለዋል። ላለፉት 100 አመታት ጥላቻ ቀልዶብናል፤ ግለኝነት፣ ለእኔ ብቻ ማለትና ሆዳምነት ሸብቦናል፤ ይህን አሸንፈን እንድንሻገር የሚያደርገን ይቅርታና ፍቅር ነውም ሲሉ በተደጋጋሚ እና በተገኙበት መድረክ ሁሉ እንደገለጹ ነው።  

 

በቀል የደካሞች ነው ያሉት ኢትዮጵያውያን ግን ደካሞች አይደለንምና በፍቅር እናሸንፋለን ሲሉ በተደጋጋሚ እየተደመጡ የሚገኙት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ግለሰቦችን ከህዝብ ለይተን እንመልከት፤ እሾህን ከፅጌረዳው እንነጥል፤ አይጥ በበላ ዳዋ አይመታ፤ በአንድ ጠማማ ዛፍ የተነሳ ደኑ አይለቅ ሲሉ መናገራቸውም ይታወሳል።

ሀገራችንን ከወደድን ግዴታችንን እንወጣ፤ መብታችንንም እንጠይቅ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁላችንን እናስፈልጋታለን ማለታቸውም በተመሳሳይ።

 

በጥቅሉ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በቅጡ የሚከታተል ማንም ሰው መልካም አጋጣሚዎች መፈጠራቸውን እና ሃገራችን በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን በቀላሉ ይረዳል፡፡ ያም ሆኖ ግን ለውጡን መቀልበስን ታሳቢ ያደረገ መፍጨርጨር እዚህም እዚያም እየታየ ሲሆን፤ይህን በአገባቡ እና በምክንያት መመከት የሚቻልባቸው በርካታ አማራጮች ቢኖሩም በአንድ ጠማማ ዛፍ የተነሳ ደኑን የመጨረስ ያልተገባ አዝማሚያም እየተስተዋለ ነው።ከላይ በተመለከተው አግባብ ግለሰቦችን እና ህዝብን ያለየ የለውጥ ድጋፍ መልሶ መቀልበስ መሆኑን እዚህ ጋር ማሰብ ተገቢ ይሆናል።

 

እነዚህ መልካም አጋጣሚዎች አስተማማኝ እንዲሆኑ ከውጤት በፊት ሒደቱን በመግራት በተፈጠሩት መልካም አጋጣሚዎች ምን መደረግ እንዳለበት ጠንቅቆ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ አገር የለውጥ ባህር ውስጥ ስትገባ ዓላማው መታወቅ አለበት፡፡ እንደ አገር ከየት ወዴት መሸጋገር እንደሚያስፈልግ፣ በየመንገዱ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ተግዳሮችችና ተስፋዎች፣ በተጨማሪም ዓላማን ለማሳካት ሲባል ሊኖሩ ስለሚችሉ የተለያዩ አማራጮች ማሰብም  የግድ ይሆናል፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአገር ህልውናን ማስቀደም የዓላማ መነሻ መሆን አለበት፡፡ ከኢትዮጵያ በፊት ምንም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የለም።

 

በእርግጥ የህዝብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ የተጀመረው ፈጣን ለውጥ ተጨባጭ ስኬቶችን ማስመዝገብ በመቻሉ አሁን ላይ ለውጡን ማንም ሊያቆመው በማይችለው ደረጃ ላይ ደርሷል። ባለፉት ጥቂት ወራት መንግስት አገራዊና ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ እየወሰዳቸው ባሉ እርምጃዎች ፈጣንና ተጨባጭ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ናቸው። ይሁንና እየመጡ ያሉ ፈጣን ለውጦች ከስጋት ላይ የጣሏቸው አንዳንድ አካላት የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ በርካታ እንቅፋቶችን እያስቀመጡልን የህዝብና መንግስትን የለውጥ አቅጣጫ ለማስቀየር ሳይታክቱ በመስራት ላይ ናቸው።

 

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ባካሄደው ጥልቅ ግምገማ በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችና ችግሩ ለፈጠረው አገራዊ ቀውስ የድርጅቱ የበላይ አመራሮች ሃላፊነቱን ወስደው፣ ህዝብንም በይፋ ይቅርታ ጠይቀው፣ የተሳሳቱ አካሄዶችን ለማስተካከል መወሰናቸው ይታወሳል። ይህን ውሳኔ ተከትሎ መንግስትና ድርጅት በአገራችን የሚስተዋሉ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ በርካታ እርምጃዎችን በቅደም ተከተል በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

 

በዚህም በርካታ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ ከእስር ተለቀዋል፣ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር መልካም ግንኙነትን መፍጠር ተጀምሯል፣ በትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩ ሃይሎችም ሰላማዊ የትግል መስመርን ተቀላቅለዋል፣ በውጭ አገር የነበሩ ሚዲያዎች በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ወደ አገር ቤት መመለስ ጀምረዋል፣ የዳያስፖራውም የፖለቲካ አተያይ መቀየር ጀምሯል፣ ከኤርትራ ጋር የነበረው ሞት አልባ ጦርነትም መቋጫ በማግኘት ላይ ነው። ይሁንና እየተካሄደ ያለው አገራዊ ለውጥ ቀድሞ ለፈጸሙት በደልና ጥፋት ተጠያቂነትን ያስከትልብናል ወይም ቀጣይ ህገ ወጥ የሆነውን የጥቅም ማጋበሻ መንገድ ይዘጋብናል የሚል ስጋት የፈጠረባቸው አካላት እንዳሉ መገንዘብ ተችሏል።

 

በመሆኑም እነዚህ ቡድኖች የህዝብን የለውጥ ፍላጎት ለማደናቀፍ እስከታችኛው እርከን በዘረጓቸው የጥፋት መረቦቻቸው በመጠቀም በረቀቀና ውስብስብ በሆነ መንገድ የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀየር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ለአብነት በቅርቡ እንኳን መንግስት እስካሁን ላካሄዳቸው ለውጦች ምስጋና ለማቅረብና በቀጣይም ድጋፉን ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ በመስቀል አደባባይ ባካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያዊ ስነ ምግባርነት በጎደለው መልኩ በህዝብ ላይ ቦምብ በመወርወር ለንጹሃን ዜጎቻችን ህይወት መጥፋትና አካል መጉደል ምክንያት ሆነዋል።

 

እነዚህ ሃይሎች በዚህ ብቻ ሳይታቀቡ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የህዝብን ትክክለኛ ጥያቄዎች ከለላ በማድረግ አብረው ለዘመናት የኖሩ ህዝቦችን እርስ በርሳቸው እንዲጋጩ በማድረግ ላይ ናቸው። በዚህም ሳቢያ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተከሰቱ ሁከቶች ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድልና ንብረት እንዲወድም እያደረጉ ናቸው።

 

ከዚህም ባሻገር እነዚህ ሃይሎች በህዝቡ ውስጥ ባደራጇቸው የጥቅም ተጋሪዎቻችው ሳቢያ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ቅሬታ እንዲያስነሳና የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀየር በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት እንዲደርስና የሃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ፣ የስልክ ኔትዎርክ እንዲጠፋ፣ መሰረታዊ የሸቀጦች አቅርቦት ላይ ጫና በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንዲሁም የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራዎች እንዲደናቀፉ በማድረግ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ እንዲማረርና የተጀመረው የለውጥ ፍላጎት አቅጣጫውን ስቶ እንዲንገራገጭ በመፈራገጥ ላይ ናቸው። በይቅርታና ፍቅር አገራዊ መግባባትን ለማጠናከር፤ የህዝቦችን አብሮነት ለማጎልበት መንግስት በርካታ ነገሮችን እያየ በለሆሳስ  ማለፍን መምረጡ በቂ ምክንያት ይሁን አይሁን ለጊዜው ብንተወውም  አንዳንድ  አካላት የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ግን ከህግ የወጡ ስለመሆናቸው እያስተዋልን ነው። 

 

ስለሆነም መንግስት በቀጣይ በእንዲህ ያሉ ኢ-ህገመንግስታዊ የሆኑ በተለይ ህዝቦችን የማሸበር፤ ለውጡን የማደናቀፍ  አካሄዶች  ላይ መደራደር የለበትም። በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት  እንዲሰፍን  መንግስት  እየወሰደ የለው  እርምጃ በአንዳንድ ሃይሎች  ዘንድ  በተሳሳተ መልኩ  በመተርጎም መንግስት አቅም እንደጎደለው ተደርጎ እየተወሰደ በወንጀል ላይ ሌላ ወንጀል በመስራት ላይ የሚገኙ  አካላትም  እየተስተዋሉ ናቸው። ይህ አይነት አካሄድ ሊታረምና ሊስተካከል ይገባል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ማሰር፣ ማባረርና መገደል ቀላል ናቸው፤ ነገር ግን አገራዊ መግባባትንና አገራዊ አንድነትን  አያመጡም።

 

ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ በርካታ ህዝብ፣ በርካታ ልዩነትና እጅግ ሰፊ አገር ናት፡፡ በመሆኑም ወደ አገራዊ መግባባት ሊያመጡን የሚችሉት መቻቻል፣ ይቅር ባይነት፣ ሆደ ሰፊነት ማለት እንጂ በአንድ ጠማማ ዛፍ ምክንያት አይነቱ አካሄድ እንዳልሆነም ጠንቅቀን ልንረዳ ይገባል።

 

መረበሽ አይገባም።ምክንያቱም እዚህም እዚያም የሚፈጠሩ ትናንሽ ግጭቶች ለአጠቃላይ ኢትዮጵያ አለመረጋጋት ማሳያ መሆን ስለማይችሉ።የፌዴራል ስርዓታችን  ትላልቅ ግጭቶችን ሊያስወግድ ይችል እንደሆን እንጂ በየሰፈሩ የሚከሰቱ ትንንሽ  ግጭቶችን አያጠፋም።  ነገም ከነገ ወዲያም እንዲህ ያሉ  ነገሮች መኖራቸው አይቀርም።

 

ስለሆነም ይህን ጉዳይ በጥልቀት የሚመረምርና የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ መንግስት አቋቁሞ እየሰራ በመሆኑ ማንኛውንም ዜጋ ለኮሚቴው ተገቢውን መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪውን ሲያቀርብ በቂ ምክንያት ስላለው መሆኑንም ልንገነዘብ ይገባል። መንግስት በሁሉም አካባቢ የፅጥታ ኃይል ሊያሰማራ አለመቻሉ አንደኛው ምክንያት ነው። ቢያሰማራም ያለ ህዝቡ ድጋፍ የፅጥታ ኃይሉ ስኬታማ አይሆንም፤ በመሆኑም  ህብረተሰቡ የአካባቢው የጸጥታ ባለቤት መሆኑን ጠንቅቆ ከተገነዘበ እዳው ሁሉ ገብስ ከመሆኑም በላይ ጠማማ የሆነውን ዛፍ ከደኑ ለይቶ ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል።   

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ  ኢትዮጵያን ካለችበት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ በሰከነ መንገድ ድጋፍ ሊያደርግላቸው የሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኃላፊነትም ከበድ ያለ ነው።ጠማማውን ከደኑ የመለየት ሃላፊነት። ይኼንን እንደ ተራራ የገዘፈ ኃላፊነት በቅን ልቦና፣ እንዲሁም በከፍተኛ ትጋት መወጣት አለመቻል ሰላምን ያደፈርሳል፡፡ ዴሞክራሲ እንዳይሰፍን መሰናክል ይሆናል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ተዓምር መጠበቅ ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡ ይኼንን የሽግግር ወቅት በብልኃት ለማለፍ የሚቻለው፣ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ሆነው ለመፍትሔ ሲረባረቡ ነው፡፡  

 

በምክንያታዊነት የሚመራ ለውጥ ለስሜታዊነትና ለግብታዊነት ክፍተት አይሰጥም፡፡ ይልቁንም ሕዝብን ማዕከል በማድረግ ተሳትፎውን አካታች ይሆናል፡፡ የሕዝብ  ተሳትፎ ሲባል በቀጥታ በየተሰማራባቸው የሥራ መስኮች፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ ይወክሉታል ተብለው በሚታሰቡ አደረጃጀቶች ነው፡፡ መልካም አጋጣሚዎች የበለጠ እየጎመሩ የሚሄዱትም እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ ምን ማበርከት እንዳለበት መብቱንና ግዴታውን ሲረዳ ነው።ሰላምና ዴሞክራሲ የሚሰርፁት በዚህ መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሰላም አየር እየነፈሰባት መሆኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን ይህ የሰላም አየር አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ጠማማውን እና ደኑን የለየ የህዝብ ተሳትፎ ሲኖር ብቻ ነው።