ኩሬን እናጎልብት፤ ውሃችንን እናቅብ

ከከፊል በላይ የተጓዝነው የትራንስፎርሜሽንና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ዘመን በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ላይ የተመሠረተ የግብርና ልማት በማፋጠንና በተጨማሪም የተማሩ ወጣቶችን በማደራጀት በግብርና ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚያደርግ እንደሆነ ተመልክቷል። አገራዊ እና የተመረጡ የውጭ የግል ባለሃብቶች እንደየችሎታቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲሳተፉ በማድረግ በሰብል፣ በአበባ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት ሃብት ልማት ዘርፎች ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት የሚሰራበት ዘመን የሚሆን እንደሆነም በተመሳሳይ ተመልክቷል፡፡

በመሆኑም የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሩ ግብርና አሁንም ዋናው የግብርና ዕድገት መሠረት ሆኖ እንዲቀጥልና የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሩ ግብርና ፈጣን እድገት እንዲያረጋግጥ የማስፋት ስትራቴጂውን አሟልቶ መተግበር፣ የልማት ቀጠናዎችን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማት መከተል እና ሌሎች በግብርና ግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ችግሮችን መፍታት ትኩረት የሚሰጣቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

በተመሳሳይ የግል ባለሀብቱ በግብርና ልማት ላይ የሚኖረው ድርሻ ከፍ እንዲል በማድረግ ሀገሪቱ ለያዘችው ልማትና ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት እንዲያግዝ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑንም የቀጣዩን አመት በጀት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሰጡት ማብራሪያ አስምረውበታል፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በማጎልበት አስተማማኝ የግብርና ልማት ለማረጋገጥ እንዲቻል የግብርና ልማት ዕቅዶች በይዘትም በትግበራም ከአረንጓዴ ልማት ራዕይ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማስቻል ከዚሁ ጋር ሁሉም ክልሎች የመስኖ ልማትን ማስፋፋት ሌሎች የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቁመዋል፡፡  

የማህበረሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን በተመለከተ አሁንም ቀርነቱ እየሰፋ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡የአርሶ አደሩን ገቢ በፍጥነት ለማሳደግ አርሶ አደሩ የላቀ ዋጋ ወዳላቸው ምርቶች ማምረት እንዲሸጋገር ማድረግና የግብርና ግብይትን በተቀላጠፈ አካሄድ ተግባራዊ ማድረግ፣ በገጠር ፈጣን ዕድገት የሚፈጥረውን ዕድል በመጠቀም የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሌሎች ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸው መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡

በተጨማሪም ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካትና መሠረታዊ አቅጣጫዎቹን ለመተግበር አስፈላጊ የሆኑ ስርዓቶችን አሟልቶ ማስኬድ እና ደረቅና ከፊል ደረቅ በሆኑ አካባቢዎች የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የኑሮ ማሻሻያና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ የሚያረጋግጡ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል።

የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የግብርና ዘርፍ ዋና ዓላማ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ የግብርና ልማትን መሠረት ያደረገ በዘርፉ ፈጣንና ዘላቂነት ያለው ዕድገት በማምጣት የህዝቡን ተጠቃሚነት በየደረጃው ማረጋገጥና በአጠቃላይ ኢኮኖሚውና በዘርፉ ደረጃ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻል መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ማሳደግና ለማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት ያለውን ወሳኝ ሚና መጫወት የሚያስችል የማምረት አቅም መገንባትን የተመለከተውም በዋነኛ አላማነት ተመልክቷል።ስለሆነም የያንዳንዷ መኸር ስራ እኒህን አላማዎች ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል።

በግብርናው ሴክተር የሚታዩትን ውስንነቶች ከመፍታት አኳያ በግብርናው ሴክተር ያለውን የሰው ኃይል በአመለካከትና በክህሎት የማብቃት ተከታታይ ሥራ በመስራት የሰው ኃይሉን ምርታማነት የማሳደግ፣ እነዚህን የልማት አቅሞች ከተግባር ጋር በማስተሳሰር የማብቃት፣ አደረጃጀቶቹን የማጠናከርና የልማት አቅሞቹን የማነቃነቅ እና ውጤታማ ተሞክሮዎችን እየቀመሩ የማስፋት ሥራ ማከናወን መኸሩን ውጤታማ ያደርገናል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም ተፋሰስን መሠረት ያደረገ የግብርና ልማት ሥራ መስራት ለዚህ መኸርም ሆነ ዘላቂነት ላለው ልማት ወሳኝ ነው።ሰፋፊና አነስተኛ የመስኖ አውታሮች ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው፣ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ የግብዓትና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት እየተሻሻለ እና ለእንስሳትና ለሰው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንና ተደራሽነት እየጨመረ መምጣቱን ታሳቢ ያደረገ  የአኗኗር፣ የአመራረትና የአረባብ ዘይቤንም ጭምር መቀየር ያስፈልጋል፡፡

ግብርናችን በቀጣይነት ያለማቋረጥ እያደገ በመምጣቱ ለአደጋ ተጋላጭነታችንና ድርቅን የመቋቋም አቅማችን እንደ ሀገር እየተገነባ የመጣበት እውነታ ከላይ በተመለከተው አግባብ ቢኖርም ከአካባቢ አካባቢ የተለያየ አፈፃፀም ያለና አሁንም ለአየር ንብረት መዛባት ተጋላጭነት ያላቸው አካባቢዎች ያሉን መሆኑን ታሳቢ ያደረገ እና ይልቁንም ጠንከር ያለ ድርቅ ቢከሰት አንኳን ችግሩን ተቋቁሞ የማለፍ አቅማችንን የሚጨምር ዝግጅትም ከወዲሁ ያስፈልጋል፡፡ የተሟላ አቅም መገንባት ገና የሚቀረን መሆኑም ግንዛቤ ተይዞ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ዕድገት እየተመዘገበ ባለበት ልክ የድርቅ መቋቋምና የአደጋ መከላከል አቅማችንን ማሳደግ እንደሚገባን ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ከውቅያኖሶች ሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የተከሰተው የኤሊኖ አየር መዛባት አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል ግምት የሚሰጠው ባለመሆኑ እንደዚህ አይነት ክስተትም ሆነ ተያያዥ ችግሮችን መቋቋም የምንችለው ለአየር ለውጥ የሚይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ መገንባት ስንችል ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም የተጀመረውን የተፈጥሮ ሀብትና የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከመስኖ ልማቱ ጋር አስተሳስሮ በላቀ ቁርጠኝነት በመፈጸም የግብርናን ምርትና ምርታማነት ዕድገት ማስቀጠል ወደ ኢንዱትራላይዜሽን የምናደርገውን ሽግግር በሚያቀላጥፍና አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የያዘችውን የህዳሴ ጉዞ በሚያሳካ መንገድ ለመፈጸም ያስችላል።

ስለሆነም አርሶ አደሮች በልማት ቡድን ተደራጅተው ለመኸር ሰብል እንክብካቤ ማድረግ ግድ ይላቸዋል፡፡ይኸውም በማሳ ላይ ያለውን  ሰብል የማረምና የመኮትኮት ስራን የሚያጠቃልል ነው፡፡የአረምና የኩትኳቶ ስራውን  ግንባር ቀደም አርሶ አደሮችና በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ ጭምር ማከናወን ደግሞ የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግና በዚህ መኸር ሁሉም ሊከተለው የሚገባ አቅጣጫ ነው፡፡የልማት ቡድኖችን በማጠናከር ከዘር ጀምሮ እስከ ምርት ስብሰባ ድረስ በጋራ መስራትም  ተገቢና ሊዘነጋ የማይገባው ነው፡፡

በልማት ቡድኖች አደረጃጀት የሚከናወኑ የልማት ስራዎች በተናጠል ከሚከናውኑት በበለጠ ጊዜና ጉልበት ይቆጥባልና፡፡የጋራ ስራው ከሰብል ልማት በተጨማሪም የችግኝ ተከላና እንክብካቤ የሚያካትት መሆንም አለበት፡፡ በቡድን ስራው ላይ ግንባር ቀደም አርሶአደሮች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበትን አሰራር መዘርጋት ለመኸሩ ውጤታማነት ጠቃሚ ነው፡፡

 

የክረምቱ ዝናብ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በመጠንና በስርጭት እየተጠናከረ እንደሚሔድ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሰጠውን መረጃም ማስታወስ ተገቢ ነው።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው አሁን እየታየ ያለው ዝናብ በአብዛኛው የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በስርጭት እየተጠናከረ ይሔዳል።ከዚሁ ጋር ተያይዞም በአገሪቱ ሰሜናዊ አጋማሽ ላይ የተሻለ የእርጥበት ሁኔታ ሊታይ እንደሚችል ይጠበቃል።አልፎ አልፎ በፀሐይ ታግዘው ከሚፈጠሩ ጠንካራ ደመናዎች ቅፅበታዊ ጎርፍና የወንዞች ሙላት ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሊኖር ይችላል ብሏል። በተጨማሪም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ የአገሪቱ ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች የዝናቡ አወጣጥ በመጠኑ ሊዘገይ እንደሚችል መተበዩን ነው የገለፀው ኤጀንሲው።

ስለሆነም ይህ የአየር ሁኔታ በመኸር ወቅት ለሚመረቱ ለመካከለኛና የረዥም ጊዜ ሰብሎች ዕድገት፣ ለቋሚ ሰብሎች የውሃ ፍላጎት፣ ለአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የመጠጥ ውሃና ለግጦሽ ሳር አቅርቦት አዎንታዊ ገጽታ እንዳለው ማጤንና በጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ።

ከዚም ባሻገር እንደትንበያው በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እርጥበቱ ከመጠን በላይ ሊሆን ስለሚችል በዚህ ምክንያት ውሃ ማሳ ላይ እንዳይተኛ ቦይ በማውጣትና በማንጠፍጠፍ የመከላከል ስራ ማከናወን ከመኸር ዝግጅቶቻችን ዋናው ሊሆን ይገባል።ከግብርና ባለሙያዎች በሚገኙ ምክረ ሐሳቦች በመደገፍ አረምን በወቅቱ በማረም፣ ፀረ-አረምና ፀረ- ተባይ ኬሚካሎችን በወቅቱ በመጠቀም ጥንቃቄ ማድረግም በተመሳሳይ። በትንበያው መሰረት በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩና የሚመለከታቸው አካላት በሰብሎችና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ ሊቦዝኑ አይገባም ። በአንፃሩ በቆላማ የአገሪቱ ቦታዎች የተገኘውን እርጥበት በአግባቡ በመጠቀምና የውሃ እቀባ፣ የኩሬ ማጎልበትና የዝናብ ውሃ መሰብሰብ ስራዎችን ማከናወን የመኸር ዝግጅቱ ቁልፍ ተግባራቶች ሊሆኑ ይገባል።