የአዲሱ ለውጥ አካል አለመሆን መብት ቢሆንም የሌሎችን ለውጥ ለማዳፈን ህገወጥ መንገድን መከተል ወንጀል ነው!!

የህዝብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ የተጀመረው ፈጣን ለውጥ ተጨባጭ ስኬቶችን ማስመዝገብ በመቻሉ አሁን ላይ ለውጡን ማንም ሊያቆመው በማይችለው ደረጃ ላይ ደርሷል። ባለፉት ጥቂት ወራት መንግስት አገራዊና ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ እየወሰዳቸው ባሉ እርምጃዎች ፈጣንና ተጨባጭ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ናቸው። ይሁንና እየመጡ ያሉ ፈጣን ለውጦች ከስጋት ላይ የጣሏቸው አንዳንድ አካላት የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ በርካታ እንቅፋቶችን እያስቀመጡልን የህዝብና መንግስትን የለውጥ አቅጣጫ ለማስቀየር ሳይታክቱ በመስራት ላይ ናቸው።

 

እነዚህ ቡድኖች የህዝብን የለውጥ ፍላጎት ለማደናቀፍ እስከታችኛው እርከን በዘረጓቸው የጥፋት መረቦቻቸው በመጠቀም በረቀቀና ውስብስብ በሆነ መንገድ የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀየር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ለአብነት እነዚህ ሃይሎች በህዝቡ ውስጥ ባደራጇቸው የጥቅም ተጋሪዎቻችው ሳቢያ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ ቅሬታ እንዲያስነሳና የለውጥ ሂደቱን አቅጣጫ ለማስቀየር በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት እንዲደርስና የሃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ፣ የስልክ ኔትዎርክ እንዲጠፋ፣ መሰረታዊ የሸቀጦች አቅርቦት ላይ ጫና በመፍጠር የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንዲሁም የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ስራዎች እንዲደናቀፉ በማድረግ ህብረተሰቡ በመንግስት ላይ እንዲማረርና የተጀመረው የለውጥ ፍላጎት አቅጣጫውን ስቶ እንዲንገራገጭ በመፈራገጥ ላይ ናቸው።

 

ይህን ጉዳይ በጥልቀት የሚመረምርና የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ መንግስት አቋቁሞ እየሰራ በመሆኑ ማንኛውንም ዜጋ ለኮሚቴው ተገቢውን መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪውን አቅርቧልና ስለህዝብ ተሳትፎ ይህ ተረክ የኢኮኖሚውን አሻጥር የተመለከተ መረጃ ይሰጣል።

 

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በዘርፈ ብዙ የለውጥ ሂደት ውስጥ ናት። ለውጡ የሚበዛውን ህዝብ ያስደሰተ ቢሆንም ጥቂቶችን በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከቷል። ሁኔታው በተስፋ መቁረጥ ብቻ የሚገታ ሳይሆን በተለያየ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች የሚገለፅ ሆኗል። በሰላም ተከባብረው የሚኖሩ ህዝቦችን እርስ በእርስ ማጋጨት አንዱ የፖለቲካው አሻጥር መገለጫ ሲሆን ይህም ችግር እየተከሰተ ያለው የራሱን የመንግስት መዋቅር ጭምር በመጠቀም ነው።

 

ይህንን ችግር በሚገባ የተረዳው  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር የራሱን የውስጥ ጥናት በማካሄድ በመዋቅሩ ውስጥ ተሰግስገው ያሉ አደገኛ ኃይሎችን አንድ በአንድ በመመንጠር ከሁለት ሺህ ያላነሱ ሰዎችን አባሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በቅርቡ በደቡብ ክልል በነበራቸው ቆይታም በህዝቦች መካከል ጥላቻን እየዘሩ የራሳቸውን እኩይ አላማ የሚያስፈፅሙ ኃይሎች መኖራቸውን በመረዳታቸው እነዚህ ኃይሎች በአፋጣኝ በራሳቸው ፈቃድ ከኃላፊነት እንዲነሱ ማሳሳቢያ የሰጡበት ሁኔታ ይታወሳል። ይህንንም የእሳቸውን ጥብቅ ማሳሰቢያ ተከትሎ በወላይታ ዞን አመራሮች በኩል የታዩ ጅምሮች ቢኖሩም አሁንም ገና ብዙ ይቀራል። ይህ ሁኔታ የደኢህዴን ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በራሳቸው ጥያቄ ከኃላፊነት እንዲነሱ ገፊ ምክንያት ሆኗል።

 

እነዚህ የአዲሱ ለውጥ አካል መሆን የማይፈልጉ ኃይሎች ከፖለቲካው ባሻገር በኢኮኖሚውም ዘርፍ እየፈጠሩት ያለው አሻጥር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ዛሬ ከምንጊዜውም በላይ መሰረታዊ የሚባሉት የውሃና የኤሌክትሪከ መቆራረጥ እንደዚሁም የትራንስፖርት ችግሮች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ የመባባስ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል። ችግሮቹ ሰው ሰራሽ መሆናቸው ፈጠው የሚታዩበት ደረጃ ደርሰዋል።

አዲሱ መንግስት የተንጠለጠለው በቀደመው አመራር መዋቅር ውስጥ በመሆኑ በዚህ አይነት ሥር ነቀል ለውጥ ውስጥ ይሄ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ መንግስት ሊደርስ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክስረት ታሳቢ በማድረግ በአፋጣኝ መዋቅራዊ ፅዳት ሊያካሂድ ይገባል። የአዲሱ ለውጥ አካል አለመሆን መብት ቢሆንም የሌሎችን ለውጥ ለማዳፈን ህገወጥ መንገድን መከተል ወንጀል ነው። ይህም በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች በአፋጣኝ መፍትሄ ሊያገኙ ይገባል። አሁን እየተካሄደ ያለው የለውጥ ባቡር በኢኮኖሚያዊ አሻጥር ይቆማል የሚል አስተሳሰብ ያላቸው አካላት ካሉም በእጅጉ የተሳሳቱ መሆኑን በሚገባ ሊረዱት ይገባል። ሁላችንም ኢኮኖሚያችን እንዲያድግ ከፈለግን ኢኮኖሚው በጤናማ ሁኔታ እንዳያድግ  የሚያደርጉ አሻጥረኞችን ልንታገል ይገባል። አንዳንድ ሃይሎች የህዝብን የለውጥ ፍላጎት አቅጣጫ ለማስቀየር  አስበውና አልመው  አርቲፊሻል የገበያ ስርዓት ለመፍጠር ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በተለይ በመሰረታዊ የፍታ ዕቃዎች ላይ ሆን ተብሎ እጥረት ለመፍጠር ሸቀጦችን በመሰወር ህዝብ በመንግስት ላይ ቅሬታ እንዲፈጥር ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

 

አንዳንድ ሃይሎች ደግሞ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው የማይገባ ትርፍ ለማጋበስ ሲሉ መሰረታዊ ሸቀጦችን በማከማቸት  ገበያው ተፈጥሮዊ ሂደቱ እንዲያጣ በማድረግ ላይ ናቸው። ህብረተሰቡ ይህን ሁኔታ ተገንዝቦ መብቱን ማስጠበቅ፣ ህገወጦችን መታገል ይኖርበታል። እንዲሁም ተገቢውን መረጃ ለሚመለከተው አካል  መስጠት ማጋለጥ ይኖርበታል። መንግስት መሰረታዊ የመገልገያ ሸቀጦች እጥረት እንዳይከሰተ ተገቢውን ስራ የሰራ በመሆኑ እጥረት የሌለ መሆኑን ስለትግል ተሳትፎው ህዝቡ ያለአንዳች ጥርጣሬ ሊገነዘብ ይገባል።

 

ሠራተኛውም ካፒታሉም መሬቱም ድርጅቱም በምርታማነታቸው ልክ የሚገባቸውን ካላገኙ ግን የሚገኘው ተጨማሪ ገቢ ከዕድገት የመጣ ሳይሆን አንዱ ሌላውን እየበዘበዘው ነው፡፡ በአንድ ነጥብ ሁለት ሚልዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ላይ ያለን፣ ከመቶ ሚልዮን በላይ የሆነ ሕዝብ በዝብዛ በፍጥነት ባደገች የአምስት መቶ ካሬ ኪሎ ሜትር የአዲስ አበባ ምድር ላይ የምንገኝ ጥቂት ሰዎች የራሳችንን ማደግ የአገሪቱ ዕድገት አድርገን እንቆጥራለን፡፡

 

በአዲስ አበባዋም ቢሆን ከጥቂት ተጠቃሚዎች በስተቀር ቤተሰቦች በሸቀጦች ዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ተማረዋል፤ ድርጅቶች በካፒታልና በጥሬ ዕቃ ዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ተማረዋል፤ ሠራተኞች በደሞዝ አወሳሰን ሥርዓት ተማረዋል፡፡ ከግብዓተ ምርቶች ውስጥ የመሬት አገልግሎት ዋጋ ኪራይ ያለቅጥ ወደ ላይ ተምዘግዝጓል።  

የመሬት ዋጋ በካሬ ሜትር ከመቶ ሺሕ በላይ ሆኖ የአንዳንድ ሰዎች ወርሐዊ ደሞዝ ከመቶ ሺሕ ብር በላይ ሆኖ የአንዳንድ ንግዶች ትርፍ መቶ ከመቶ ሆኖ እነኚህ ዋጋዎች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሁኔታ በሚያንጸባርቅ ትክክለኛ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ነው የተተመኑት ብሎ ማለት ይከብዳል ስለሆነም ምንጩ የለውጥ አደናቃፊዎች መሆኑን መገመት ይቻላል ማለት ነው።

 

ዋጋዎች ሲዛቡና ትክክለኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ ለረጅም ጊዜ ጸንተው መቆየት ይሳናቸዋል። በቀናትና በሰዓታት ውስጥ ያለምክንያት ይለዋወጣሉ። ሰዎች የሚሰማሩበትን ዘርፍ መምረጥ ያቅታቸዋል። ዋጋዎችም ትክክለኛውን የሀብት ድልድል ማድረግ ይሳናቸዋል። በዚህን ጊዜም የኢኮኖሚው እድገት ጠማማ ይሆናል። መመረት የሚገባው ሸቀጥ ሳይመረት መመረት የማይገባው ሸቀጥ ይመረታል። ዋጋዎች የሚወላገዱት በዋጋ አወሳሰን ሥርዓት አምራቹና ሸማቹ ተመጣጣኝ አቅም ሳይኖራቸው ሲቀር ነው፡፡ይህን አቅም የተዛባ የሚያደርጉትም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አሻጥረኞች በውጭ ከሚገኙ አኩራፊ ፖለቲከኞች ጋር በማበር ነው።  

 

የታዳጊ አገራት የድህነት ቀለበት ውስጥ መዘፈቅም በቅድሚያ መመረት የሚገባው

ሸቀጥ ሳይመረት መመረት የማይገባቸው ሸቀጦች መመረት ወይም ከውጭ አገር በውጭ ምንዛሪ እየተገዙ መግባት ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱም ያደጉት አገራት በሚያሳድሩባቸው በፍጥነት የማደግ ጫና በሚሰጧቸው እርዳታዎችና ብድሮች የነርሱን ሸቀጦች እንዲሸምቱ አድርገው ስለሚቀርጹዋቸው ነው፡፡ የሚያዘጋጁን አምራች አንድንሆን ሳይሆን ሸማች እንድንሆን ነው፡፡

 

በቂ ገቢ አግኝተው የፈረንጆቹን ሸቀጦች ሸማቾች የሚሆኑትም በአገር ውስጥ ለግብዓተምርቶቻቸውና ለምርቶቻቸው ትክክለኛውን ዋጋ የሚያገኙ ሳይሆኑ የፈረንጆቹን ቀራቅንቦ የሚነግዱ ሰዎችና በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ተግባር ላይና በግል ንግድ አገልግሎት አሰጣጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ የከተማ አገልግሎት ሰጪዎች ወይም የፈረንጆቹን ለታዳጊ አገራት ተብሎ የተነደፉ ፖሊሲዎችን የሚያራምዱ ለውጥ አደናቃፊዎች  ናቸው፡፡

 

በነዚህ አሻጥረኞች ምክንያት በጥቂት ሣምንታት ውስጥ የእንቁላል የወተት የቅቤ ዋጋዎች የእጥፍ ያህል ሲጨምሩ፣ ሸማቹ ምንም የማድረግ አቅም አጥቶ የተጠየቀውን ይከፍላል። ከየት ያመጣዋል? አይባልም። እርሱም ትክክለኛ ባልሆነ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓት ውስጥ ተሰማርቶ በሚያገኘው ገቢ የተጠየቀውን ከፍሎ መሸመት ችሏል።

በሌሎች አገራት የነጻ ያህል ርካሽ የሆኑት ምግብ ነክ ምርቶች እኛ አገር እንደዚህ የሚወደዱት ለምንድን ነው? በእንስሳት ሀብት ከዓለም ዐሥረኛና ከአፍሪካ አንደኛ ሆነን በግብርና የተሰማራው ሕዝባችን ሰማንያ በመቶ ሆኖ ከዓለም ቁጥር አንድ የገበሬ አገር ሆነን በእንስሳት ተዋጽኦ አመጋገብ ከአፍሪካ ግማሽ ደረጃ ላይ እንኳ ያልደረስነው ለምንድን ነው?። መልሱ ያው የአሻጥረኞች ሴራ ነውና ለተቋቋመው ኮሚቴ ከመጠቆም ባሻገር እምቢኝ በማለት ልንታገላቸው ይገባል።

 

ትክክለኛ የገበያ ዋጋ የሚፈጠረውም በሚያወጣው ወጪ ወይም በሚከፍለው ክፍያ ልክ ከሸቀጡ የሚያገኘውን ጥቅም የላቀ ለማድረግ የሚመርጥ አዋቂ ሸማችና ማምረት በሚችለው አቅም ልክ ትርፉን የላቀ ለማድረግ በሚሠራ አዋቂ አምራች መኖር ነው።

በትናንሾቹ በምግብ ወጪዎቻችን እንኳ በሚከፍለው ልክ የሚያገኘውን ጥቅም የላቀ ለማድረግና ማምረት በሚችለው ልክ ትርፉን የላቀ ለማድረግ የሚጣጣር አዋቂ ሰው ሳይኖር ከተቀረው ዓለም እኩል የቴክኖሎጂ ምርቶችን ለመሸመትና አምርቶ ለመሸጥ የሚችል አዋቂ ሊሆን እንዴት እንደሚችል ማሰብ ይከብዳል። የእንቁላሉና የወተቱ የገበያ መር ኢኮኖሚ በአሻጥረኞች እየተጠለፈ ከፈረንጆች ጋር የአክስዮን ገበያ ውድድር ውስጥ እንዴት ነው የምንገባው?።ብሎም ማሰብ ለትግሉ ስኬት ጠቃሚ ይሆናል።

 

ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛሉ ተብለው ልዩ ድጋፍ የሚደረግላቸው በልዩ ልዩ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ድጋፉን በሚገባ ቢያገኙም ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚያቀርቡበት ሁኔታ መኖሩም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል።እነዚህ ባለሃብቶች“አምርተን ኤክስፖርት እናደርጋለን” በማለት ለኤክስፖርት ማበረታቻ የሚሰጠውን ማሽንን እና የግብዓት ምርቶችን የመሳሰሉ ከቀረጥ ነፃ ከማስገባት ጀምሮ ለተወሰኑ ዓመታት የግብር የእፎይታ ጊዜን የሚያገኙበት እድል ተፈጥሮላቸዋል። ሆኖም ነጋዴዎች እነዚህን ጥቅማ ጥቅሞች በሚገባ ካገኙ በኋላ ኤክስፖርት አድርገው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት ይልቅ፤ ምርቶቻቸውን በሀገር ውስጥ ገበያ መሸጣቸው ሁለት መሰረታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን የሚያስከትሉ ሆነው ተገኝተዋል።

የመጀመሪያው ለውጭ ገበያ በሚቀርቡት ምርቶች ሊገኝ ይችል የነበረውን የውጭ ምንዛሪ የሚያሳጣ መሆኑ ሲሆን በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በኤክስፖርት ማበረታቻ ስም ሰፊ ድጋፍ ካገኙ በኋላ ሀገር ውስጥ ሽያጭን ማከናወኑ ሌሎች በሀገር ውስጥ ገበያ ውስጥ ብቻ ተሰማርተው ከሚሰሩ ባለሀብቶች ጋር የሚኖረውን የገበያ ውድድር ያልተገባና በኢፍትሃዊነት የተሞላ አድርጎታል።  

 

ህጉም ሆነ ተቋማቱ ዛሬም አሉ። ሆኖም ችግሩን ከመሰረቱ ፈቶ በማስተካከሉ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ መንግስት የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን ከላይ በተመለከተው መልኩ አሳይቷል። ይህም በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ያለው የጥቅም ትስስር ቀስ በቀስ እየተበጣጠሰ እስኪሄድ የህዝቡም ተሳትፎ ሊታከልበት ይገባል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ለአዲስ ለውጥ የመነሳታቸውን ያህል ቀላል በማይባል መልኩ አዲሱን የለውጥ ሂደት ወደኋላ ለመመለስ የሚጥሩም መኖራቸው ግልፅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጀመሪያው የፓርላማ ሪፖርታቸው ኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች እየተካሄዱ መሆናቸውን በሪፖርታቸው ላይ በግልፅ አስቀምጠዋል። እነዚህ አሻጥሮች ከአገልግሎት እስከ ምርት ያለውን የኢኮኖሚውን ዘርፍ የሚያዳክሙት ይሆናል። በዚህ ረገድ የዶክተር አቢይ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ብዙ የመዋቅራዊ ፍተሻዎችን ማድረግ  ጀምሯልና ከላይ በተመለከተው ጥሪ አግባብ በህዝብ ተሳትፎ ከታጀበ አሻጥረኞቹ መውጫ የሚያጡበት ቀን ቅርብ ይሆናል።