የኢኮኖሚ “ሳቦታጅ”…

በአገራችን ውስጥ አንዳንድ ሃይሎች የህዝብን የለውጥ ፍላጎት አቅጣጫ ለማስቀየር አስበውና አልመው የማያከናውኑት ነገር እንደሌለ ገሃድ እየሆነ ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው አርቴፊሻል የገበያ ስርዓት ለመፍጠር እያደረጉ ያሉት የኢኮኖሚ አሻጥር ይጠቀሳል።

በዚህም አንዳንዶች በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ሆን ተብሎ እጥረት እንዲፈጠር በማሰብ ሸቀጦችን ሲሰውሩ ይስተዋላል። ሌሎቹ ደግሞ አጋጣሚውን ተጠቅመው የማይገባ ትርፍ ለማጋበስ ሲሉ መሰረታዊ ሸቀጦችን በማከማቸት ገበያው ተፈጥሮዊ ሂደቱን እንዲያጣ እያደረጉ ነው።

የአገራችን ገበያ እውነታ ግን መንግስት መሰረታዊ የመገልገያ ሸቀጦች እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊውን ተግባር በማከናወን ላይ ስለሚገኝ እጥረት የሌለበት መሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚፈፅሙ ሃይሎች በኢኮኖሚ ሳቦታጅ የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት መግታት እንደማይችሉ የተገነዘቡ አይመስሉም። ተግባራቸው በአገርና በህዝብ ላይ የሚከናወን መሰሪ ሁኔታ ከመንግስትም ይሁን ከህብረተሰቡ እንደማይሰወር ማወቅ አለባቸው።

በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ክልሎች ከውጭ የመጡ ምርቶችን በመጋዘን አከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው። እርምጃ የመውሰድ ስራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል። ገበያውን ለማረጋጋት የጅምላ መሸጫ ሱቆች መሰረታዊ ሸቀጦችን በበቂ ሁኔታ እንዲቀርብ ጥረት እየተደረገ ነው።

ይህ ሁሉ የመንግስት ጥረት ህዝቡ በዋጋ ንረት እንዳይጎዳ ለማድረግ የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው። በሌለ የገበያ ክፍተትና እጥረት አገርንና ህብረተሰቡን ለመጉዳት የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ግባቸው ህዝቡን መጉዳት ነው። የገበያው ተዋናይ ህብረተሰቡም ጭምር በመሆኑ የችግሩ የመጀመሪያ ተጠቂ መሆኑ አያጠያይቅም። በመሆኑም አገርንና ህዝብን በሚጎዳ የኢኮኖሚ ሳቦታጅ አርቴፊሻል የገበያ እጥረት እንዳይፈጠር የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባዋል።

ያም ሆኖ ህብረሰቡ በአገርና በህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ይህን እኩይ ሴራ በማጋለጥ መብቱን ማስጠበቅና የድርጊቱን ፈጻሚዎች መታገል አለበት። ለዚህም ተገቢውን መረጃ ለሚመለከተው አካል በመስጠትም የኢኮኖሚ “ሳቦታጅ” ፈፃሚዎቹን ድርጊት መቆጣጠር ይኖርበታል።

እጥረት ሳይኖር እጥረት እንዳለ የሚያስመስሉና መሰረታዊ ሸቀጦችን በማከማቸት አላስፈላጊ ትርፍ ለማጋበስ የሚሹ አካላትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ አገርንና ህዝብን መጠበቅ ነው።

መንግስት የሸቀጦች እጥረት በገበያው ላይ አንዳይፈጠሩ የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ተከታታይ የሆኑ ልማታዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። በዚህም ህብረተሰቡ እንዳይጎዳ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲሁም መሰረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን ራሱ በማስገባትና በሸማቾች ማህበራት አማካኝነት እያከፋፈለ ይገኛለ።

የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለምርት መጠኑ ማደግ መንግስት ከፍተኛ ተግባራት ሲፈጽምም መጥቷል። በዘላቂ መፍትሔነትም አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርን፣ ማዳበሪያንና ሌሎች አቅርቦቶችን በበቂ ሁኔታ አግኝቶ ወደ ምርት ተግባር እንዲገባ እያደረገ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ ልዩ ልዩ የቴክኒክ ድጋፎችን የመስጠት ስራዎችን በመከወን ውጤታማ ተግባራትን በመፈፀሙ የዋጋ ንረቱ ይበልጥ እንዳይንር በመቆጣጠር ላይ ይገኛል። ውጤትም እያገኘ ነው።

ህብረተሰቡ መንግስት እየተከተለ ባለው የግብርና ልማት ስትራቴጂ ትርፍ አምራች ዜጋዎችን መፈጠራቸውን በማወቅ እጥረት እንደማይኖር ማወቅ አለበት። እነዚህ አባቢዎች ለአገራችን የሚሆኑ መሰረታዊ የምግብ አቅርቦቶችን አየሸፈኑ ነው። አቅርቦቶቹ እጥረት የሚስተዋልባቸው ናቸው።

መንግስት በአሁኑ ሰዓት ከውጭ የሚገባውን ነዳጅ በየጊዜው ድጎማ በማድረግ በየወሩ ባለበት እንዲቀጥል በማድረግ ላይ ይገኛል። ይህም መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች የዋጋ ጭማሪ ሳያሳዩ ባሉበት እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ነው። እናም ህብረተሰቡ በሸቀጦች ላይ የሚደረጉ የኢኮኖሚ ሳቦታጆችን መከላከል ይኖርበታል።

የገበያ ሁኔታውን ለማረጋጋት በማሰብም መሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ከራሱ ካዝና በመደጎምም ይሁን ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ እያደረገ ነው። በዚህም ንረቱን በማስተካከል ላይ ይገኛል።

የገበያው ሁኔታ እየተረጋጋ ባለበት በዚህ ሰዓት በንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ የኢኮኖሚ ሳቦታጅ ለመፈፀም የሚሰሩ አካላት እየታዩ ነው። እነዚህ አካላት አርቴፊሻል ገበያ በመፍጠር ህብረተሰቡን እያማረሩና በመንግስት ላይ ያልሆነ ቅሬታ እንዲይዝ እያደረጉ ነው።

እነዚህ አካላት ዋጋን ከመቆለል ባሻገር ገበያው በእጥረት ድርቅ እንዲመታ መሰረታዊ ሸቀጦችን በመደበቅ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ይሻረካሉ። እየተመሳጠሩም ዋጋን በማናር በገበያው ውስጥ ክፍተት እንዲፈጠር እያደረጉ ናቸው።

አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎችም ሁኔታው ተመቸን በማለት ሸቀጦችን በመሰወርና ከገበያው ላይ እንደጠፋ በማስመሰል እጥረት አለ እያሉ ያለ አንዳች ምክንያት ህብረተሰቡን ሲበዘብዙት ይታያሉ።

እንዲሁም የኮንትሮባንድ አሰራርን በማጧጧፍ ህጋዊው ግብር ከፋይ ነጋዴ ተወዳድሮ ሸቀጡን እንዳይሸጥ እያደረጉት ነው። በተለይ በመሰረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ማከናወን ብቻ ሳይሆን ዋጋቸውም ንሮ ህብረተሰቡ ለምሬት አንዲጋለጥ እያደረጉት ይገኛሉ።

ያም ሆኖ ህብረተሰቡ በእነዚህ የኢኮኖሚ ሳቦታጅ ፈጻሚዊች ላይ ተገቢውን ክትትል ማድረግ አለበት። ከድርጊቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዩችን ሲመለከት አሊያም በግብይቱ ራሱ ተሳታፊ ሆኖ ያልተገባ ዋጋ ሲጠየቅ ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት ይኖርበታል። የኢኮኖሚ ሳቦታጅ ዞሮ…ዞሮ የሚጎዳው ራሱን በመሆኑ እጥረት በሌለበት ሁኔታ ገበያው ውስጥ እጥረት የሚፈጥሩ አካላትን በቁርጠኝነት በመታገል መብቱንና ጥቅሙን ማስከበር ይጠበቅበታል።