ጥሰቶቹን ለመከላከል…

አንዳንድ አካሎች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት ለምን እንደሚቃወሙ ግልጽ ነው። ይኸውም መቃወም የጀመሩት አንዱ ምክንያት ቀደም ሲል በፈጸሙት አሰቃቂ ድርጊት ተጠያቂ ላለመሆን ወይም ለውጡ ጥቅማቸውን ስለሚነካባቸው እንደሆነ ይታወቃል። ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉት ማረሚያ ቤቶች በዜጎች ላይ የተፈጸመው የአካል መቆረጥ፣ የዘር ፍሬ መበላሸት፣ የአይን መፍሰስ፣ ግርፋት፣ ጭለማ ቤት ማቆየት የመሳሰሉ ህገ መንግስቱን የሚጥሱ ተግባራት የዚህ እውነታ ሁነኛ አስረጅ ነው።

እርግጥ እነዚህ ጉዳዩች ነገ እንዳይፈጸሙ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረውና እንዲያወግዛቸው ለማድረግ ጭምር ሚዲያው ተገቢ መረጃ ለህዝብ ማድረስ ይኖርበታል። ወደፊትም ቢሆን መገናኛ ብዙሃን የአገሪቱን ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲሁም የፕሬስ ህጉን መሰረት በማድረግ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ መስራት አለባቸው። ይህ ተግባራቸውም እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ ተቋም ለአገራቸው ማበርከት ያለባቸውን ማሀበራዊ ሃላፊነት እንዲወጡ የሚያስችላቸው ነው።

ነገር ግን ህገ መንግስቱን በመጣስ በዜጎች ላይ የሚፈፀሙ አካልንና የአዕምሮን የሚጎዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መከላከል የህዝቡና የሁሉም ተቋማት ኃላፊነት በመሆኑ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል።

ህገ መንግስቱ ለዜጎች የአመለካከትና ሃሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነት እንዲሁም አቤቱታን መብቶችን አጎናጽፏል። እነዚህ መብቶች አገራችን ውስጥ ጥበቃ ሊደረግባቸው የሚገቡ ብቻ ሳይሆኑ፣ በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ በተጨባጭ ገቢራዊ እየሆኑ ማምጣት የሚችሉም ናቸው። ባለፉት ጊዜያት በተገቢው መንገድ ገቢራዊ ሆነዋል ለማለት አያስደፍርም።

በተለያዩ ወቅቶች በተደጋጋሚ ይካሄዱ የነበሩት የመብት ጥሰቶች (በተለይም በማረሚያ ቤቶች) ዜጎች ህግን ቢጥሱም እንኳን በአስፈጻሚዎች የተለያዩ በደሎች ሲፈፀምባቸው እንደነበር ግልፅ ነው። በእነዚያ ጊዜያት በአገራችን ውስጥ የሚታየው ተደራጅቶ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትም ቢሆን እምብዛም አልነበረም። ወይም በቀጥታም የሁን በተዘዋዋሪ የመንግስት ፈቃድ ይከለከል ነበር። ይህም የፖለቲካ ሂደቱ አዲስ መንገድን ተከትሎ እንዳይራመድ ያደረገው ነው።

እንዲህ ዓይነቶቹ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ማናቸውም የቡድንና የግለሰብ ፖለቲካዊ መብቶች እንደ አሁን በሚገባ አልተረጋገጡም። ምስጋና የዛሬውን ለውጥ ላማምጣት ለዚህ ላበቁን ለእነ ‘ኦቦ ለማ ቲም’ ይግባውና ዛሬ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በነፃነት እየተከበሩ ናቸው።

አሁን በምንገኝበት የለውጥ ሂደት ውስጥ ማናቸውንም ዓይነት ሃሳቦች የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠውን የሰብዓዊ መብቶቹን በህገ መንግስት መሰረት ማስከበር አለበት። አዲስ የኢትዮጵያዊነት ማንነት የመገንባት ጉዳይም ከእነዚህ መብቶች ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው። የሰው ልጅ ሰብዓዊነቱን የሚጋፉ ተግባሮች ሊፈፀሙበት አይገባም። ለህዝብ የሚገደብ መብትም መኖር አይኖርበትም። የኢትዮጵያ ህዝቦች በግልም ይሁን በቡድን ሰብዓዊ በምታቸውን የማስከበር ነፃነት አላቸው።

ምንም እንኳን ባለፉት ጊዜያት የነበራቸው አሰራር ጥንካሬያቸው አጠያያቂ ቢሆንም አገራችን የምትከተለው ስርዓት የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ የተለያዩ መብት አስጠባቂ ተቋማትን አቋቁማለች። ከእነዚህ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት…ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው።

እነዚህ ተቋማት ከዛሬ ሶስት ወር በፊት ዜጎች የሚፈፀምባቸው የመብት ጥሰትን በተገቢው መንገድ የሚመለከቱ ባይሆኑም፤ አሁን ግን ግን የዜጎችን እንባ የሚያብሱበት ወቅት ነው። እነዚህ ተቋማት ህብረተሰቡ ማረሚያ ቤቶችን የመሰሉ መንግስታዊ ተቋማት አፈፃፀም ሳቢያ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጉዳዩችን ጥያቄ ሲቀርብላቸውና በራሳቸው ተነሳሽነትም የመመርመር ስራ ያከናውናሉ።

እንዲሁም ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ ሃሳቦችን በማቅረብም ተግባራዊነታቸውን ይከታተላሉ። በዚህ ተግራቸውም በስርዓቱ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ህገ መንግስታዊ ግዴታቸውን ይወጣሉ።

በቅርቡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም የመብቶች የጥሰት ጉዳዩችን አስመልክቶ መግለጫ መስጠቱ ተቋማቱ የዜጎችን መብቶች ከምንግዜውም በላይ እንዲጠበቁ በለውጡ ወቅት ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት አንድ ማሳያ ይመስለኛል። ይህም ለውጡን እንዲመጣ ያደረጉት ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በመሆናቸው ጥሰቶቹ በለውጡ ሂደት መገለጻቸውና እንዲታረሙ መደረጋቸው ትክክለኛ አሰራር ነው። ዜጎችም የደረሰባቸውን ግፍ መግለፃቸውህገ መንግስታዊ በምታቸው ከመሆኑም በላይ ወደፊትም እንዲህ ዓይነቱ ተግባር እንዳይፈፀም ትምህርት መስጠት የሚችል ነው።

እንግዲህ ይህን ሁኔታ ያስተዋሉ አንዳንድ ወገኖች ሲፈፅሙት የነበሩት የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂ እንደሚሆኑ የተገነዘቡ አሊያም ለውጡ ጥቅሜን ይነካብኛል ብለው በማሰብ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ሆኖም በህዝብ ጽኑ ፍላጎት የመጣውን ይህን ለውጥ መታገልና በእንቅፋትነት ማደናቀፍ የሚቻል አይደለም።

የለውጡ ባለቤት ህዝብ በመሆኑ ለውጥ መታገል ሀዝብን መታገልና ፍላጎቱንም መጻረር የሚቆጠር ነው። ይህ ደግሞ ፈፅሞ የማያስኬድ መሆኑን ባለፉት ሶስት ዓመታት በሚገባ ተገንዝበናል። በእነዚህ ዓመታት ማንም ይሁን ማን በህዝብ ፍላጎት ፊት የመቆም አቅም እንደሌለው ተገንዝበናል።

ዛሬ የህዝብ ሃይልና ፍላጎት በየትኛውም አገር ውስጥ ወሳኝና ገዥ እንደሆነ ያልተገነዘበ ዜጋ የለም። ህዝብ የፈለገውን ነገር በአገሩ ውስጥ ድረግ የሚያስችል አቅም ያለው መሆኑን ለውጡን ለማደናቀፍ ከሚሹት ጥቅማቸው የተካባቸው ጥቂት አካላት በስተቀር ሁሉም ኢትዮጰያዊ በሚገባ ያውቃል። ለህዝብ ፍላጎት የማይገዛ ማንኛውም አካል አወዳደቁ ምን ሊሆን እንደሚችል ያለፉት ዓመታት አስተምረውናል።

ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ለውጡን ለማደናቀፍ ላይ ታች የሚሉት ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት ከተግባራቸው አንዳችም ትርፍ እንደማያገኙ ማወቅ አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት ተግባራቸው ባዶ መሻት ነው። ከመንግስት ዕይታም ውጭ አይደለም።

እናም እጃቸውን ከለውጡ ላይ በማንሳት አርፈው መቀመጥ አለባቸው። ለእነርሱም ቢሆን የሚያዋጣቸው ከጫፍ እስከ ጫፍ ለውጡን ደግፎ ከሚንቀሳቀሰው ኢትዮጵያዊ ጋር መደመር ብቻ ነው። ያም ሆኖ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡም ይሁን መገናኛ ብዙሃን አገራዊ ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።