ሌላው የዘጠና ቀናት ትሩፋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ ቦታዎች ባደረጓቸው ንግግሮች ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚያስብል ደረጃ ድጋፍ ስላስገኘላቸው ጉዳይ ባለፈው ሣምንት ጽሁፌ አነሳስቼ ቀጣዩን በሌላ ጊዜ ይዤ እንደምመለስ በቀጠሮ መለያየቴን በቅድሚያ ማስታወስ እፈልጋለሁ።

 

ከአገር ቤት ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያንም "አይዞን፤ ከጎንህ ነን – በርታ" በማለት ድጋፋቸውን ገልፀዋል። ይህንንም በሠላማዊ ሠልፍ ጭምር አረጋግጠዋል። እያረጋገጡም ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በአካል ተገኝተው በችግሮቻቸውና በመፍትሄ ሃሳቦቻቸው ዙሪያ በግልጽ መክረዋል።   

 

ሕዝቡም ለዓመታት ያለመፍትሄ አብሮት የኖሩትን ችግሮች አነሳስቶ ድምጹን አሰምቷል። እዚህ ላይ ከኢትዮጵያ በላይ አንዳች የሚያስቀድመው ቁም ነገር እንደሌለው በድጋሚ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጦላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በፊናቸው ይህን ታላቅ ሕዝብ ይዞ የማይገፋ ተራራ እንደሌለ በመግለጽ ወገኝተኛነታቸውን አሳይተዋል። የጋራ መግባባት ላይም ደርሰዋል።  

 

ትልቅ ሥራ ሊከውን የሚችል የሰው ኃይል ባክኗል። መልካም አጋጣሚዎች እንዲሁ እንደዋዛ አልፈዋል። አሁን ከዚያ ኋላ ቀር አስተሳሰብ መላቀቅ፤ በተጀመረው የለውጥ ጎዳና ላይ የራስን ድርሻ ማበርከት የግድ ይላል። የዓመታት ችግሮች የሚቀረፉትና ወደተሻለ ደረጃ መሸጋገር የሚቻለው የለውጥ ኃይል ሆኖ መደመር ሲቻል፤ በጋራ ተረባርቦ በአንድነት ሲቆም ብቻ ነው፡፡ ምርጫችንም ይህና ይህ ብቻ ነው።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘጠና ቀናት የኃላፊነት ቆይታቸው በእሥር ላይ የነበሩ የፖለቲካ መሪዎች እና ጋዜጠኞች ነጻ እንዲወጡ አድርገዋል። በፖለቲካ አስተሳሰብ መለያየት ጦር ሰብቀው የቆዩ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ወደ አገራቸው ገብተው ሠላማዊ ትግል እንዲያካሂዱ ጥሪ አቅርበዋል። ሁሉም ጥሪውን በአዎንታ ተቀብለዋል። መቀመጫቸውን ባህር ማዶ ያደረጉ ኢትዮጵያዊ የሚዲያ ተቋማትም አገር ውስጥ ገብተው በነጻነት እንዲሰሩ ጋብዘዋል። ይህም ሁኔታ በሁሉም ዘንድ ይሁንታን አግኝቷል። አያሰሩም የተባሉ አዋጆችም ማሻሻያ እንዲደረግባቸው እየተመከረባቸው ይገኛል።

ዶክተር አብይ አህመድ በዘጠና ቀናት የጠቅላይ ሚኒስትርነት የኃላፊነት ጊዜያቸው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው ከሕዝብ ጋር መምከራቸውንና ይህ ሁኔታም በአገር ውስጥ ብቻ ተወስኖ አለመቅረቱን በመጀመሪያ ክፍል ጽሁፌ ጠቃቅሻለሁ። በጂቡቲ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በሣውዲ ዐረቢያ፣ በኤምሬትስ፣ በኡጋንዳ፣ በግብጽና በሶማሊያ የሥራ ጉብኝቶች ማድረጋቸውን አነሳስቼያለሁ። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መብቶቻቸው እንዲከበሩ፤ ለረዥም ዓመታት በእሥር ሲማቅቁ የኖሩ ዜጎችም ከእሥር ተፈተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የተደረገው በእነዚህ ዘጠና ቀናት ውስጥ ነው።

በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ጉብኝቶቹ ለኢትዮጵያ ታላቅ ጠቀሜታን ማስገኘታቸውን ዘርዝሬያለሁ። ይህ ሁኔታ ሲጠቃለል ኢትዮጵያ እጅና እግሯን ጠፍረው ከያዟት ችግሮቿ ተላቃ በጋራ ጥቅም ላይ ወደተመሠረተ ብልጽግና ለመሸጋገር ጽኑ አቋም እንዳላት ለዓለም ያሳየችበት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

ከሁሉም…ከሁሉም በላይ ደግሞ ዶክተር አብይ በሣምንቱ መጨረሻ ላይ ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት "የክፍለ ዘመኑ ተጠቃሽ ታሪክ" ቢባል አይበዛበትም። ጉብኝቱ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የመተማመን መንፈስ የፈጠሩበት፤ ትብብሮችን በበለጠ ደረጃ ለማስቀጠል መሠረት የጣሉበት ሆኖ ተመዝግቧል።

የሁለቱም አገሮች ሕዝቦች የጦርነት ሥጋታቸውን የገፈፉበት፤ ለሁለት አሥርተ ዓመታት ጋርዷቸው የከረመውን የጨለማ ድንኳን ከላያቸው ጥለው የብርሃን ሻማ የለኮሱበት ሆኖም አልፏል። ህጻናትና ወጣቶች፣ እናቶችና አባቶች የአሥመራ ጎዳናን ሞልተው፣ የሁለቱን አገሮች ሠንደቅ ዓላማዎች እያውለበለቡና የዘንባባ ዝንጣፊዎችን ከፍ አድርገው ይዘው ፈንዲሻ ቆሎ እየበተኑ ሲጨፍሩ ለተመለከተ እንባ በጉንጮቹ ቢፈስ ምን ያስገርማል።      

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ካሁን በኋላ በአልባሌ የሚያጠፉት ጊዜ የላቸውም። ፈጥነው ወደ ሥራ መግባት ይኖርባቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሲናገሩ እንደተሰሙት በቅርቡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደአሥመራ በረራ ይጀምራል። የየብስ የትራንስፖርት አገልግሎትም ጥቅም ላይ ይውላል። በአዲስ አበባ እና በአሥመራ ከተሞች ተዘግተው ለዓመታት የቆዩ የሁለቱ አገሮች ኤምባሲዎች ይከፈታሉ። የወደብ አገልግሎቱም ሥራውን ይጀምራል። ኢትዮጵያዊያን በአሥመራ፤ ኤርትራዊያን በሸገር ዘና…ፈታ ይላሉ። ይህ ነው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት። መልካም…መልካሙ ያሰማን።

ኢትዮጵያ ለክፍለ አህጉሩ ሠላምና የምጣኔ ሀብት ትስስር መጎልበት ዛሬም የፀና አቋም እንዳላት ለዓለም በድጋሚ እያሳየች ትገኛለች። የዶክተር አብይ የአሥመራ ጉብኝት ለዚህ ጉዳይ ማሣያ መልካም አጋጣሚ ሆኗል።

ኢትዮጵያ የወደብ ልማትን ከጎረቤት አገራት ጋር በመሆን በትብብር ለማካሄድና ለማስተዳደር መስማማቷ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ትሩፋቶች መካከል ተጠቃሹ ነው።

ቀጠናውን በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ማስቻል የኢትዮጵያ  ቁርጠኛ አቋም ለዓለም ሕዝብ የተገለፀበት ነበር – ጉብኝቱ። ከአሥመራው ጉብኝት ቀደም ብሎ ከኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር የተደረገው ምክክር "በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተገኘ ድል" በሚል ሊወሰድ ይቻላል።

የኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ንግድ የሚስተናገድባት አገር ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር በባቡር መስመር የተሳሰረች ናት። ወደቧን በጋራ ለማልማት ከስምምነት ተደርሷል። በእርሻና በመንገድ ልማቶች ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶችን በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል – ሌላው የጉብኝቱ ትሩፋት ነው።

ኢትዮጵያ በፖርት ሱዳን ለብቻዋ የምትጠቀምበትን ወደብ በጋራ ለማልማትና ለማስተዳደር ከስምምነት ላይ ያደረሳት ጉብኝት የተደረገውም በዘጠና ቀናት ውስጥ ነው።

አዲስ አበባን ከካርቱም በባቡር መስመር ለማስተሳሰር ከስምምነት ተደርሷል። ለአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸው የታመነበት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጉብኝት ትሩፋት መሆኑን ልብ እንበል።   

በኬንያ ጉብኝት ያደረጉት ዶክተር አብይ በምጣኔ ሀብትና የፀጥታ ጉዳዮች፣ በላሙ ወደብ ልማትና ኬንያ በየዓመቱ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ባሰበችው 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ አተገባበር ዙሪያም መክረዋል። የኢትዮጵያና ኬንያ ሞያሌን የምሥራቅ አፍሪካ የቢዝነስና የንግድ ማዕከል እንድትሆን በጋራ ለማልማት ተስማምተዋል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ጆሞ ኬንያታ የጀመሯቸው የልማት ትብብርና የህብረት ራዕይን ለማሳካት የሁለቱ አገራት መሪዎች ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ በትረ ሥልጣኑ ከመጡ ዛሬ ዘጠና ቀናት ሞላቸው። በነዚህ ቀናት ከዶክተር አብይ ምን አገኘን፣ ምንስ አጣን?" – ልብ ያለው ልብ ይበል።