‹‹በገነት አገልጋይ ከመሆን፤ በሲዖል መንገስ ይሻላል?››

ፈረንጆቹ ዜሮ ሰዓት ይሉታል፡፡ 1945 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ለጀርመኖች ‹‹ዜሮ ሰዓት›› ነበር፡፡ ከዚያ ነጥብ ጀምረው በአዲስ መንፈስ እና ጎዳና ጉዞአቸውን እንደ አዲስ ቀጠሉ፡፡ የዌመር ሪፐብሊክ የፈፀማቸውን ስህተቶች ላለመድገም በብርቱ ተጠነቀቁ፡፡ አዲስ ሀገር እና ህብረተሰብ ለመፍጠር ጉዞ ጀመሩ፡፡ በአጭር ጊዜ ከግባቸው ደረሱ፡፡

ሐምሌ 1/2010 ዓ.ም ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ‹‹ዜሮ ሰዓት›› ሊባል የሚችል ነው፡፡ በመጥፎ የጥርጣሬና እና የመዘራጠጥ ፖለቲካ ታስሮ የኖረውን ግንኙነት ቀይረው አዲስ የፍቅር እና የመከባበር መንፈስ ፈጥረው ጉዞ ጀመሩ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፤ አንዱ የአንደኛውን ቤት በእሳት ለመለኮስ አድፍጦ የሚያሴርበት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ይህን ታሪክ በፍቅር በመቀየር ያለ አንዳች የፈረንጅ ሽማግሌ ሰላም አወረዱ፡፡ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ሰላም በመውረዱ ፍጹም ፈነደቁ፣ ተደሰቱ፣ በፍቅር እንባ ታጠቡ፡፡

 ‹‹አፍሪካ ራስን የማጥፋት ዓመል የተጠናወታት አህጉር ናት›› ይሏታል፡፡ አፍሪካ ድሃ አህጉር ነች፡፡ ግን የድህነት ዘበኛ የሆነውን ጦርነትን በቀላሉ ይቀበሉታል፡፡ ከአህጉሪቱ ህዝብ 45 በመቶ የሚሆነው በድህነት ይኖራል፡፡ የአፍሪካ ሐገራት ይህን አኃዝ በግማሽ ለመቀነስ፤ ለ15 ዓመታት 7 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህን ግብ ለማሳካት ከጦርነት መውጣት ያስፈልገናል፡፡ በኢኮኖሚው መስክ የምናገኘው ውጤትም በኢኮኖሚ አጥር ብቻ ተወስኖ የሚታይ ሳይሆን ከዛ ክበብ አልፎ የሚሄድ ፋይዳ ያለው ነው፡፡

አሁን ኢትዮጵያ በመጥፎ የጥርጣሬ እና የመዘራጠጥ ፖለቲካ የኖረውን የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ነባር ባህርይን የሚለውጥ አካሄድ ይዛለች፡፡ አንዱ የአንደኛውን ቤት በእሣት ለመለኮስ የማድፈጥ የቀውስ ፖለቲካ ባህልን የሚቀይር አቋም እና እርምጃ ወስዳለች፡፡ የሀገራት ትስስርም ከምንም በላይ የሚጸናው በኢኮኖሚ ትስስር እንጂ በክፍለ አህጉራዊ ድርጅቶች ብዛት እንዳልሆነ ተገንዝባ አዲስ ታሪክ እየሰራች ነው፡፡ አዲሱ አመራርም እውነተኛና ጠንካራ ክፍለ አህጉራዊ ግንኙነት የሚፈጠረው የኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጠናከር መሆኑን ተገንዝቧል፡፡

ኢትዮጵያ ከድህነት የምትወጣው እና አሁን የሚታየው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቀጣይነት የሚኖረው ውስጣዊ ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ዘላቂ ውስጣዊ ሰላም የሚረጋገጠውም በቀጠናው ሀገሮች ትብብር መሆኑ ግንዛቤ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሀገሮች መካከል የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር ከቀንዱ ሀገሮች ጋር ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ችግር የነበረው ከኤርትራ ጋር ነበር፡፡ አሀን ይህ ችግር ተወግዷል፡፡ ቀድመም ችግሩ ከህዝብ ጋር የተያያዘ አልነበረም፡፡ የጠ/ሚ አቢይ አህመድ ገብኝት፤ የኤርትራ ህዝብ ለኢትዮጵያ እና ለህዝቦችዋ ምን ያህል መልካም አመለካከት እንዳላቸው ከበቂ በላይ ያረጋጠ ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ መልካም አመለካከት መሬት ወርዶ ከእውነተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር ሲተሳሰር- ሁለቱንም ወገን ተጠቃሚ ሚያደርግ ግንኙነት ሲመሰረት ዘላቂነት ያለው ግንኙነት ይፈጠራል፡፡

ዛሬ እኛ እንደ ህዳሴው ግድብ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምረናል፡፡ ወገብ የሚፈትሽ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነድፈናል፡፡ ኢኮኖሚያችን ሊያድግ በሚችለው የተፈጥሮ ገደቡ ልክ እንዲያድግ ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል፡፡ ይህ ሥራ እንደ ጀርመኖች ባለ ከፍ ያለ የአርበኝነት ስሜት ታጥቆ በመነሳት፤ ያለውን ውስን ሀብት ሳያባክኑ በመጠቀም፤ ቁጠባን በማጠናከር፤ በዙሪያችን በሚነሱ ጊዜያዊ ጫጫታዎች ከሥራ ሳንናጠብ፤ ኃይላችንን በግጭት እና በእሣት ማጥፋት ግርግር ሳናባክን ተጠንቅቀን በመጓዝ፤ እንደ ልጅ ሣይሆን እንደ አዋቂ እያሰብን፤ የምንደርስበትን ግብ አውቀን፤ በፍቅር፣ በይቅርታ እና ይቻላል መንፈስ ጠንክረን መጓዝን ይጠይቀናል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ቀበቶን ማጥበቅ በሚጠይቀው በዚህ ዘመን፤ በምን መልክ እንደሚጓዝና ለመጭው ተከታታይ ትውልድ የመንፈስ ኃይል እየሆነ ለታላቅ ሥራ መሰለፍን እና ለድል መብቃትን እንዲያውቅበት የሚያደርግ፤ ትልቅ ሀገራዊ ቅርስ የሚሆን የቤት ሥራ ከፊቱ ተቀምጧል፡፡ ህዝቡ በድንገት ግለት ቱግ ብሎ በሚከስም ድንገተኛ የስሜት ኃይል የሚገፋ ሳይሆን፤ በሰከነና ሩቅ አላሚ በሆነ አስተዋይ የዕውቀት እና የፍቅር መንፈስ የሚመራ መሆኑን ማሳየት ከቻለ፤ ይህ እንደ ሀገር ትቶልን የሚሄደው መንፈሳዊ ቅርስ ቀላል አይደለም፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረውን የሥራ መንፈስ፣ ትጋት፣ ጽናት፣ ፈጣሪነት እና ሩቅ አሣቢነት ስንመለከት፤ ይህ ኃይል እንኳን ለኢትዮጵያ፤ ለአፍሪካ ብልጽግና ሊፈጥር የሚችል ኃይል ሆኖ ይታያል፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የሆነ ታሪካዊ ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡ አባቶቻችን ከኢምፔሪያሊዝምና ከፋሺዝም ኃይል ጋር የመጋፈጥና ነጻነትን የማስከበር ታላቅ ኃላፊነት ተጣለባቸው፡፡ በታላቅ ፅናትና ፈተናውን አልፈው ኃላፊነታቸውን ተወጡ፡፡ መላው ዓለም በፈተናው እየወደቀ ለቅኝ ተገዢነትና ለባርነት ሲዳረግ፤ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ትውልድ ተሻጋሪ የሆነና ቅስም ሰባሪ የግፍ ፅዋ ለመጨለጥ ሲገደዱ፤ አባቶቻችን በፅኑ ተጋድሎ ከዚያ መከራ ጠብቀው፤ ሰብአዊ ክብርን ያህል ትልቅ ሀብትን ሰጥተውን አለፉ፡፡ ይህ የሰብአዊ ክብር ስሜት ድህነትን በመጠየፍ፣ ተረጅነትን በመጥላት እና ለስራ በመትጋት በእኛ ትውልድ መጎልበትና መፋፋት አለበት፡፡ ዛሬ ሌሎች በመረጡልን ሳይሆን እኛው በተለምነው መንገድ የመጓዝ መንፈሳዊ ኃይል ያገኘነው በነፃነት ስለኖርን ነው፡፡

ታዲያ ኢትዮጵያውያን የሀገሪቱን ሉአላዊነት ማስከበር ቢችሉም፤ በሀገሪቱ ውስጥ የቡድን እና የግለሰብ ነፃነትን እኩልነትን ማስፈን ተስኗቸው ቆይቷል፡፡ የእኛ ትውልድ ኃላፊነት፤ ነፃነትን፣ እኩልነትን እና ወንድማማችነትን በማስፈን የህዝባችንን ፖለቲካዊ አንድነት ማረጋገጥ ነው፡፡ የዛሬ ሃያ ዓመት የፀደቀው ህገ መንግስት፤ እንዲሁም ህገ መንግስቱ መሠረት ሆኗቸው የተፈጠሩት የዲሞክራሲ ተቋማት ሁሉ፤ የተዛባውን ነገር በመቀየር በሀገራችን እኩልነትን፣ ነፃነትን እና በተለያዩ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል የወንድማማችነት መንፈስን ለማስፈን የተደረገው ጥረት ውጤቶች ናቸው፡፡

ዛሬ ዓለም ለማወቅ የሚጓጓው ‹‹ትናንት ኢትዮጵያውያን ምን ወይም የት ነበሩ?›› የሚለውን አይደለም፡፡ በፍጹም! ይልቅ አብዝቶ የሚጓጓው ‹‹የቅርብ ትናንት ታሪካቸውን በመቀየር ምን ዓይነት ህዝብ ሆነው ይወጡ ይሆን?›› የሚለውን ማወቅ ነው፡፡ እኛንም የሚጓጓን ይኸው ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በጦርነትና በድህነት ከተጎሳቆለው የትናንት መንደራቸው ወጥተው ወደ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ብልፅግና አምባ ለመውጣት ምን ዓይነት ጉዞ ያደርጉ ይሆን ? ብለው በልዩ ትኩረት እየተመለከቱን ነው፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ነባር ፖለቲካዊ አደረጃጀቱን መሠረታዊ በሆነ መንገድ ቀይሮ አዲስ ህብረተሰብ ፈጥሯል፡፡ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የወትሮውን አይደለንም፡፡ ታዲያ ይህ ለውጥ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ነቅተን መጠበቅ አለብን፡፡ የአሁኑ ትውልድ በብዙ መስክ ከባድ ኃላፊነት መሸከሙን መረዳት አለበት፡፡ ይህን መረዳት ኃላፊነታችንን ለመወጣት ያግዘናል፡፡ የሌሎች ሀገራት ልምድን በመቃኘት ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚረዳ ዝጉጁነት መፍጠር አለብን፡፡ በደመ ነፍስ ወይም በተናጠል የክስተቶች ውሳኔ መንቀሳቀስ ሳይሆን የታሪክ ኃላፊነቱን የተረዳ ህዝብ Conscious agent of history መሆን አለብን፡፡ እንዲህ ከሆንን ከመንገድ ሊያወጡ የሚጎትቱንን የውጭና የውስጥ ኃይሎች ፈተና ማለፍ እንችላለን፡፡ ከስትራተጂክ ጥቅሞቻችን ጋር ሳንጣላ እንጓዛለን፡፡ 

አሁን የምንገኝበት ታሪካዊ ወቅት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መዓት ወጥተው በጦርነቱ ዘመን ከሸሹበት አካባቢ ሲመለሱ ቤታቸው ፈርሶ፤ ጎዳናው በታንክና በቦንብ ታርሶ፤ የጥይት ቅምቡላ በየቦታው ወድቆ፤ አገር ምድሩ ሁሉ በፍርስራሽ ተመልቶ፤ ነገንም ሆነ ዛሬን ወይም ትናንትን ማየት እየሰጉ አንገታቸውን ደፍተው ከጎዳና ዳር የተቀመጡበት ተስፋ ማጣት እንደ መርግ የተጫነው ጊዜ ውስጥ አይደለንም፡፡ በፍጹም፡፡ ያን ዘመን ተሻግረን መጥተናል፡፡ ግን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የፈረሰች ጀርመንን ከተረከበው ትውልድ የከበደ ኃላፊነት ተሸክመናል፡፡ አሁን የምንገኝበት ጊዜ ከዚህ ትውልድ የሚፈልገው አስተሳሰብና ባህርይ ምን ዓይነት እንደሆነ ለመረዳት ስንሞክር ከጀርመን ህዝብ ታሪክና ትጋት ትምህርት የሚሆኑ ነገሮችን እናገኛለን፡፡

ቶማስ ማን የተባለ የልቦለድ ደራሲ ‹‹ቡደንብሩክ›› ስለ ተባለ አንድ ባለፀጋ ቤተሰብ  አነሳስ እና ውድቀት የሚተርክ መፅሐፍ አለው፡፡ በዚህ መፅሐፍ እንደምናነበው ‹‹ቡደንብሩክ›› በሚል የሚጠራው ቤተሰብ የመጀመሪያ ትውልድ የቤተሰብ ንግድ አቋቋመ፡፡ ‹‹የቡደንብሩክ›› ሁለተኛው ትውልድ የቤተሰቡን ንግድ ወደ ላቀ ደረጃ አደረሰው፡፡ ሦስተኛው ትውልድ ግን የቤተሰቡን ሀብት እንዳሻው በትኖ ሲጨርሰው እናያለን- በትረካው፡፡ 

ታዲያ ይህን የቶማስ ማን ትረካ፤ ባለፉት 50 ዓመታት ለታየው ሦስት የጀርመን ትውልድ ምሳሌ አድርገው የሚያቀርቡ ፀሐፊዎች አሉ፡፡ በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ የነበሩት ጀርመናዊያን በአስደናቂ ቁርጠኝነት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የደቀቀች ሀገራቸውን ከትቢያ በማንሳት ዓለምን ያስደመመ የኢኮኖሚ ተአምር ፈጠሩ፡፡ ይህን ተአምር የፈጠረው የጀርመን ትውልድ፤ ቶማስ ማን ከገለፀው ‹‹የቡደንብሩክ›› ቤተሰብ የመጀመሪያ ትውልድ ጋር ይነፃፀራል፡፡ በጦርነት የወደመችን ሀገር የተረከቡት እኒያ ጀርመናውያን ቅንጦትን አልተመኙም፡፡ ድሎት አላማራቸውም፡፡ በጋራ የመኖሪያ ህንፃ በአንዲት ክፍል ውስጥ እየኖሩ፤ ጥቂት ድንች እና ጎመን በልተው እያደሩ ዓለምን ያስደመመ ኢኮኖሚያዊ ተአምር ፈጠሩ፡፡ ማርሻል ፕላን የተሰኘውን የድጋፍ ፕሮግራም ተጠቅመው በጦርነቱ የፈራረሱ ኢንዱስትሪዎቻቸውን ገነቡ፡፡ በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የሀገሪቱ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት በሦስት እጥፍ አደገ፡፡  ጀርመን አንድም ሥራ አጥ የማይገኝባት ሀገር ሆነች፡፡

ሁለተኛው ትውልድ፤ በ1970ዎቹ የመጣው ነው፡፡ ይህ ትውልድ፤ አባቶቹ የሰጡትን የኢኮኖሚ ቅርስ ተረክቦ ፈጣን ዕድገቱን አስቀጠለው፡፡ በ1995 ዓ.ም (እኤአ) እስከ ታየው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ድረስ የቀጠለውንና አንዳንድ የኢኮኖሚ ሊቃውንት Permanent boom ‹‹ያልተቋረጠ ቋሚ ትንግርታዊ ዕድገት›› ሲሉ የሚጠሩትን ተከታታይ ዕድገት ፈጠረ፡፡

እኒህ ጀርመናውያን ሀገራቸውን ከባዶ – ኦና አንስተው በሁሉም የኢንዱስትሪ ዘርፎች በዓለም ደረጃ የቴክኖሎጂ መሪ ለመሆን አበቋት፡፡ ሁለተኛው ትውልድ ጀርመንን የዓለም ትልቋ ነጋዴ አገር አደረጋት፡፡ የሀገሪቱ ገንዘብ በዓለም ጠንካራው ከረንሲ ሆነ፡፡ ጀርመን ሁሉን የምታስቀና ባለፀጋ ሀገር ሆነች፡፡ ይህን ተአምር የፈጠረው የጀርመን ትውልድ፤ ቶማስ ማን ከገለፀው የ‹‹ቡደንብሩክ›› ቤተሰብ ሁለተኛ ትውልድ ጋር የሚነፃፀር ነው፡፡

አሁን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የነበረው የጀርመን ትውልድ እያረጀ ነው፡፡ የመጪው ጊዜ ሁኔታ በሦስተኛው ትውልድ ሥራ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ሦስተኛው የጀርመን ትውልድ፤ ቶማስ ማን ከገለፀው የ‹‹ቡደንብሩክ›› ሦስተኛ ትውልድ ቤተሰብ ጋር የሚነፃፀር መሆን- አለመሆኑ ገና አልታወቀም፡፡ ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን ሀብት ዝም ብሎ ያባክናል ወይስ ዳግም የተዋሀደችውን ጀርመን ጠንካራና የበለጸገች ሀገር ለማድረግ ይጠቀምበታል? ይህ ወደ ፊት የሚታይ ነው፡፡ ግን አንዳንዶች በሦስተኛው የጀርመን ትውልድ ላይ ስጋትና ጥርጣሬ አላቸው፡፡

ሦስተኛው ትውልድ ከቀዳሚዎቹ ጀርመናውያን የተለየ ባህርይና አዝማሚያ እንዳለው ይነገራል፡፡ ሦስተኛው ትውልድ ‹‹እያወጣሁ እበትነዋለሁ›› ቢል እንኳን በቀላሉ የማያልቅ ሀብት በአያቶቹና አባቶቹ ተጠራቅሞለታል፡፡ ከፍተኛ የቁጠባ ባህል የነበራቸው አያት-አባቶቹ ድንች እና ሽንኩርት በልተው ያጠራቀሙት ሀብት አለ፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የጀርመኖች የቁጠባ ምጣኔ 11.1% ይደርስ ነበር፡፡ ይህ ከአሜሪካውያን የቁጠባ ምጣኔ ጋር በንፅፅር ሲታይ(4.2%)  ከፍተኛ ነው፡፡ እናም ከጃፓኖች (12.8%) በቀር ጀርመኖችን በቁጠባ  የሚልቅ አልነበረም፡፡ በዚህ መንገድ፤ ጀርመኖች ባለፉት 50 ዓመታት 3.3 ትሪሊየን ዶላር ለመቆጠብ ችለው ነበር፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ እንዳሻ በትኖ ለመጨረስ ጊዜ ቢወስድም፤ ዞሮ ዞሮ ያልቃል፡፡ ታዲያ አሁን የሚታየው አዝማሚያ አላምር ያላቸው ጀርመናውያን አስተያየት እየሰጡ ነው፡፡

ጀርመናውያን፤ በሣምንት 37.5 ሰዓት ብቻ መሥራታቸውን፤ ረጅም የእረፍት ጊዜ መውሰዳቸውን (በዓመት 24 ቀናት ሲሆን በዓለም ረጅም የእረፍት ጊዜ ነው)፤  ሥራ የሚጀምሩት በ25 እና ከዚያ በላይ በሆነ ዕድሜ መሆኑን፤ ጠቀም ያለ የጡረታ ክፍያ የሚከፈላቸው መሆኑን ወዘተ በማንሳት ኢኮኖሚውን ይጎዳል ብለው የሚጨነቁ አሉ፡፡ እንዲህ የተንበሸበሸ ትርፍ ጊዜ እና ገንዘብ ያላቸው ጀርመናውያን በዓመት ሁለት ጊዜ ሽርሽር ይወጣሉ – አንዱን በሀገር ቤት አንዱን በውጭ ሀገር፡፡

ታዲያ ይህ የሽርሽር መብዛት ያሳሰባቸው የዶች ባንክ ሊቀመንበር ፊልማር ኮፐር፤ ‹‹የጀርመን የድህነት መሥመር›› አሉ በቀልድ አዋዝተው ሲተቹ፤ ‹‹የጀርመን የድህነት መሥመርየተዘረጋው በማጆርካ እና በሲሸልስ ደሴቶች መካከል ነው፡፡››

ቻንስለር ሄልሙት ኮህል እንዲሁ በአንድ ንግግራቸው፤ ‹‹ብልፅግና በብድር አይገዛም›› ሲሉ ተችተዋል፡፡ ሆኖም ዜጎች ከሀብት ማባከን እንዲቆጠቡ ያስተላለፉት ማስጠንቀቂያ፤ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር፡፡ በዚህ ትችታቸውም የተነሳ ታይቶ የማይታወቅ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ፡፡

ፊልማር ኮፐር የተባሉ ሰው ደግሞ ‹‹ይሄ የተበላሸ ትውልድ ነው፡፡ ግን ትውልዱ የተበላሸው ከመንግስት በሚያገኘው ድጎማ ነው›› ብለው ነበር፡፡ የጀርመን የኢኮኖሚ ሚኒስትር ደግሞ፤ ‹‹መንግስት፤ በሰማይ የሚቀለብና በምድር የሚታለብ ላም አይደለም›› ሲሉ ድጎማን በመቃወም ተናግረው ነበር፡፡ ያን ተአምር የፈጠረው ትውልድ በልጆቹና ልጅ-ልጆቹ ደስተኛ አይደለም፡፡

ሦስተኛው የጀርመን ትውልድ፤ አንዲት ውሀ ጠብ እንዳትል ይጨነቁ የነበሩትን፤ ከነቤተሰባቸው በአንዲት ክፍል ተወስነው የኖሩትን፤ ገንዘብ ለማውጣት እጃቸው የሚንቀጠቀጠውን፤ የአባትና የአያቶቻቸውን አስተያየት እና የኑሮ ዘይቤ የሚነቅፉ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ሦስተኛው ትውልድ ‹‹አንድ ሰው ገንዘቡን ጥሩ ህይወት ለመምራት ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ እንጂ ገንዘብ ዝም ብሎ ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም›› የሚሉ ሆነዋል፡፡ አሳሳቢ የሆነውም ይህ አስተሳሰባቸው ነው፡፡ ከአባቶቻቸው እና ከአያቶቻቸው የወረሱት ባለብዙ ክፍል የተንጣለለ መኖሪያ ቤትና በባንክ የተቀመጠ ገንዘብ ያላቸው የሦስተኛው ትውልድ ጀርመናውያን ፈንደለላ የሚወዱ በመሆናቸው ይወቀሳሉ፡፡  

እርግጥ አሁን በጀርመን የሚታየው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የሚለወጥ መሆኑን የሚያምኑ፤ የሥራ ሰዓታቸው አነስተኛ መሆንም የማያስጨንቃቸውና አዲሱ ትውልድ የአያት – የአባቶቹን ጠንካራ የሥራና የቁጠባ ባህል ጨርሶ እንዳልተወ በመግለፅ ሥጋት የማይሰማቸው ወገኖች አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ሜይንሀርድ ሜይግል የተባሉ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ሜይግል፤ ‹‹ድሮም ጀርመኖች ለረጅም ሰዓት የሚሰሩ አይደሉም፡፡ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሰሩት ሥራ አንጀት አርስ ነው›› በማለት ይሞግታሉ፡፡

እንግዲህ ጀርመናውያን ያን የመከራ ጊዜ በፅናትና በንቃት፤ በትጋትና አስተዋይነት፤ በዕውቀትና በብልሀት ተራምደው አለፉት፡፡ ያን ክፉ ዘመን ተሻገሩት፡፡ በአውሮፓ ውስጥ ቀዳሚ የሆነ ኢኮኖሚ ያላት ሀገርም ፈጠሩ፡፡ በአጭር ጊዜ ከአሜሪካና ከቻይና የለጠቀ ሦስተኛ ግዙፍ የዓለም ኢኮኖሚ ገነቡ፡፡

ታዲያ አሁን አንዳንድ ጀርመናውያን ‹‹በዚህ ሀገር ጣሊያናዊነት እየተስፋፋ ነው›› ሲሉ የሚሰነዝሩት ትችትም አለ፡፡ ጣሊያኖች ፋሽን የተባለ የቤት ዕቃ ወይ መኪና ወዘተ ካልገዙ እንቅልፍ አይወስዳቸውም ይባላል፡፡ እና ይህም ያሳስባቸዋል፡፡ ለመሆኑ፤ አሁን እየተፈጠረ ያለው የሀገራችን መካከለኛ መደብ በዚህ ረገድ ያለው ባህርይ ምን ይመስላል? የአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ በመጀመሪያው የጀርመን ትውልድ ዘንድ የታየው ፅናት፣ ንቃት፣ ትጋት፣ አስተዋይነትና ዕውቀት ሊኖረው የሚገባ ትውልድ ነው፡፡

እንደ ሀገር ካሰብን፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ወገብን የሚፈትሽ ከባድ የልማት ሥራ ከፊታችን ተደቅኖብናል፡፡ ዓለም፤ እንደ ሀገር መፃኢ ጊዜያችንን እንዴት ቅርጽ እንደምናስይዘው ለማየት በአንክሮ ይከታተለናል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን ወደ ጥንቱ እንቅልፍና ቅዤታቸው፤ ሁከትና ጦርነታቸው ይመለሱ ይሆን?›› እያለ ይጠይቃል፡፡ ‹‹ወይስ ተስፋ ሰጪ አያያዛቸውን ውል አስይዘው አዲስ ታሪክ መስራት ይችሉ ይሆን?›› እያለ ይገምተናል፡፡ ይህን ታሪካዊ የትውልድ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በጆን ሚልተን ብዕር እንደ ተናገረው ሰይጣን ‹‹በገነት አገልጋይ ከመሆን፤ በሲዖል መንገስ ይሻላል›› ከሚል አስተሳሰብ እንውጣ፡፡