በጋውንም ማረስ ይኖርብናል

ኢትዮጵያውያን ከሶስቱ የክረምት ወራት ዋነኛው የሆነውን ሃምሌን ተቀበለናል። ሃምሌ ደመናው ወፍራም ግራጫ ስለሆነ፣ ዝናቡም ከባድ ስለሆነ ጨለማው ወር ይባላል፤ የሃምሌ ጨለማ። እርግጥ ሃምሌ ጨለማ አይደለም፤ ኢትዮጵያውያንን የሚመግበው የግብርና ምርት አብዛኛው በዚህ ወር ከሚከናወን እርሻ የሚገኝ ነው። እናም ሃምሌን በጨለማ መመሰል ይከብዳል። ሃምሌ የጠራ ሰማይ ኖሮ በጸሃይ ከሚደምቅ፣ ሲጨልም ነው ብርሃን የሚኖረን። ያም ሆነ ይህ፣ አሁን ዋነኛው የመኸር እርሻ የሚከናወንበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

የግብርናና የእንስሳ ሃብት ልማት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በያዝነው መኸር ከ13 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ይታረሳል። በእርሻ ለሚሸፈነው መሬት 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ኩንታል ምርጥ ዘር ቀርቧል። 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የዩሪያ እንዲሁም 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ቅይጥ ማዳበሪያ ቀርቧል። እስካሁን ባለው መረጃ ከ50 በመቶ በላይ መሬት ታርሷል። የግብርናና የእንስሳት ሃብት ልማት ሚኒስቴር የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት መኖሩን ቢናገርም፣ አንዳንድ አካባቢ ግብአቶቹ እንዳልደረሱ ከአርሶ አደሮች ቅሬታ ማወቅ ይቻላል። ግብአቶቹን የዘር ወቅት ካለፈ በኋላ ማቅረብ የሚያስገኘው ጥቅም ስለማይኖር ይህ ችግር ሊታሰብበት ይገባል።

በአጠቃላይ ከዘንድሮ የመኸር እርሻ 375 ሚሊየን ኩንታል የሰብል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። ባለፈው ዓመት መኸር 342 ሚሊየን ኩንታል ሰብል ለማምረት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የተሰበሰበው ግን ከ320 ሚሊየን ኩንታል እንደማይበልጥ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም ቢሆን ከ2008 ዓ/ም መኸር ከተሰበሰበው 292 ሚሊየን ኩንታል ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እድገት አሳይቷል። በማሳ ትንበያና በተጨባጭ በሚሰበሰበው የሰብል ምርት መሃከል ይህን ያህል በሚሊየን ኩንታሎች የሚለካ ሰፊ ልዩነት እንዲታይ በማድረግ ረገድ በምርት ስብሰባ ወቅት ያለ ብክነት ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል። አብዛኛው አርሶ አደር ባህላዊ የሰብል አሰባሰብ ስልትን ስለሚጠቀም፣ በሰብል ስብሰባ ስራ ብቻ እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ምርት የሚባክን መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በመሆኑም ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂንና የተሻሻለ ግብአትን ለመጠቀም የተሰጠው ትኩረት በምርት ስብሰባውም ላይ ሊኖር ይገባል። አለበለዚያ የማሳው ሰብል ሜዳ ላይ ነው የሚቀረው።

አርሶ አደሩ በአጠቃላይ በእርሻ ስራው ስኬታማ እንዲሆን የሞባይል የመረጃ አገልግሎት ስርአት ተዘርግቷል። ከ2006 ዓ/ም ጀምሮ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የ8026 የሞባይል የግብርና መረጃ አገልግሎት ስርአት ከሚቲዮሮጂ ጀምሮ የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አጠቃቀም፣ የምርት አሰባሰብን ወዘተ በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ለአርሶ አደሩ ሙያዊ መረጃ ይሰጣል። የመረጃ ስርአቱ በኦሮሚኛ፣ አማርኛ፣ ሲዳምኛ፣ ትግርኛ፣ ወላይትኛ ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣል። አገልግሎቱ በተሰጠባቸው ያለፉ አራት ዓመታት የተጠቃሚዎች ቁጥር እያደገ መጥቶ አሁን 30 ሚሊየን ገደማ ደርሷል። ይህ በአፍሪካ ቀዳሚው ነው። የመረጃ ስርአቱ የግብርናን ምርታማነት በማሳደግ በኩል  ጉልህ ድርሻ ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል። በመሆኑም ተደራሽነቱን አሁን ካለውም በላይ ለማሰፋት የአገልግሎት መስጫ ቋንቋዎችን መጨመር ያስፈልጋል።

የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ለኢትዮጵያ ከጎን የተወዘተ አይደለም። የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የሃገሪቱ ህዝብ በግብርና ስራ ነው የሚተዳደረው። ግብርናው አጠቃላይ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻም ከ36 በመቶ በላይ ነው። የሃገሪቱ የወጪ ንግድም በዚሁ ዘርፍ ላይ የተመሰረተ ነው። ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመም፣ አበባና የቁም ከብት  ከሃገሪቱ የወጪ ንግድ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉን ይሸፍናሉ።

በመሆኑም፣ የሃገሪቱን ህዝብ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የግብርናን ምርታማነት ማሳደግ አማራጭ የለውም። ግብርናው ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች – አገልግሎትና ኢንደስትሪ መፈጠርና እድገት መሰረት ነው። ከሃገሪቱ ህዝብ 80 በመቶ ያህል የሚሆነውን አርሶ አደር ገቢ ማሳደግ በሃገሪቱ ትልቅ የገበያ አቅም ይፈጥራል። ይህ የገበያ አቅም ንግድን ጨምሮ የአገልግሎትና አምራች ዘርፎች ትርፋማነት እንዲያድግ ያደርጋል። ይህ ትርፍ የኢንቨስትመንት አቅም ይፈጥራል። በአጠቃላይ ግብርና የሃገሪቱ የካፒታል ክምችት ፈጣሪም ነው።

ይሁን እንጂ የግብርናው ዘርፍ አሁንም በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳ ላይ የተመሰረተና ዝናብ ላይ የተንጠለጠለ ነው። ይህን ሁኔታ ለመቀየር የመስኖ እርሻንና ዘመናዊ የእርሻ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን፣ ሜካናይዜሽንን ማስፋፋት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም። እርግጥ በዚህ ረገድ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ይታወቃል።

የመስኖ ልማትን በተመለከተ፣ ዘንድሮ በአነስተኛ ማሳ ከ7 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮችን በመስኖ ልማት ፕሮግራም የማሳተፍ ስራ ተከናውኗል።  በዚህ የመስኖ ልማት ፕሮግራም ከ3 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለምቷል። ከዘንድሮ የመስኖ ልማት 450 ሚሊየን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል የሚል እቅድ ተይዞ ነበር። እስካሁን ምን ያህል ምርት እንደተሰበሰበ የሚያመለክት መረጃ ይፋ አልሆነም።  

በአጠቃላይ ከ2008 በጀት ዓመት በስተቀር የግብርናው ዘርፍ በአማካይ 8 በመቶ ገደማ እድገት ማሳየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በ2008 በጀት ዓመት የግብርናው ዘርፍ የ2 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ነበር ያስመዘገበው። ይህ የሆነው በ2007 ዓ/ም ሃገሪቱ 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ህዝብ ለምግብ እጥረት ባጋለጠው ኤል ኒኖ የተሰኘው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተከሰተ ድርቅ በመመታቷ ነበር። በ2008 በጀት ዓመት ወደ 2 ነጥብ 3 በመቶ አሽቆልቁሎ የነበረው የግብርናው ዘርፍ እድገት፣ በ2009 በጀት ዓመት የ6 ነጥብ 7 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። ሰኔ 30 በተጠናቀቀው የ2010 በጀት ዓመት የግብርና ዘርፍ በምን ያህል እንዳደገ አጠቃላይ መረጃ ይፋ ባየሆንም 8 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የሃገሪቱ የግብርና ዘርፍ እድገት ጥሩ ሊባል የሚችል ቢሆንም፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው አሁንም እጅግ ብዙ ይቀረዋል። ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ የተመሰረተው ኢትዮጵያ እንኳን ለወጪ ንግድ የምታቀርበው የሰብል ምርት ሊኖራት የሃገር ውስጥ ፍጆታዋንም በወጉ መሸፈን አልቻለችም። ኢትዮጵያ ስንዴ አምራች ሃገር ነች። ይሁን እንጂ ፍላጎቷን በራስዋ መሸፈን ስለማትችል ስንዴ ሸማች ለመሆን ተገዳለች። የዓለም አቀፍ ገበያ የስንዴ ዋጋ ዝቅተኛ ገቢ ካለው ህብረተሰብ የመግዛት አቅም በላይ ስለሆነ ከውጭ የተገዛው የስንዴ ምርት ህዝብ ጋር የሚቀረበው በመንግስት ድጎማ ነው። ለሌላ የልማትና የአገልግሎት ተግባር ሊውል የሚችል ባጀት ለስንዴ ድጎማ እየዋለ መሆኑን ልብ ይሏል።   

ኢትዮጵያ ስንዴ ሸማች መሆኗ ያስከተለው ችግር ይህ ብቻ አይደለም። ከውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከግዢ እስከ ስርጭት ባለው ሎጂስቲክስ ደካማ መሆን የተነሳ ለአጭር ጊዜም ቢሆን እጥረት የሚያጋጥምበት ሁኔታ የተለመደ ነው። ለምሳሌ በያዝነው ዓመት ይህ ችግር ተፈጥሯል። ችግሩ አሁንም ሙሉ በሙሉ አልተፈታም። ከስንዴ ግዢና ስርጭት ጋር በተያያዘ ባለው የሎጂስቲክስ ችግር ሳቢያ በመንግስት ድጎማ የሚቀርብ ስንዴ እጥረት በማጋጠሙ የዳቦ እጥረት ተፈጥሯል። አንዳንድ ዳቦ ጋጋሪዎች ስራ ለማቆም የተገደዱበት ሁኔታ ነበር። የተወሰኑት ደግሞ ከድጎማ ውጭ ስንዴ በመግዛት በመንግስት ከተተመነው በላይ በሆነ ዋጋ ዳቦ ሲያቀርቡ ተስተውሏል። ለምሳሌ 1 ብር ከ30 ሳንቲም እንዲሸጥ የተተመነው 120 ግራም ዳቦ በአሁኑ ጊዜ በሁለት ብር እየተሸጠ ነው። ይህ ሁኔታ ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ላይ ጫና እያሳደረ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል።

ይህን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችለው የሃገሪቱን የሰብል እርሻ ምርታማነት ማሳደግ ብቻ ነው። የግብርናና እንሳት ሃብት ልማት መኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው አሁን ያለው በሄክታር አማካይ የሰብል ምርት ከ25 እስከ 27 ኩንታል ይደርሳል። ሃገሪቱ የስንዴ ፍላጎቷን ሙሉ በሙሉ በራስዋ አቅም እንድትሸፍን ይህ የሰብል ምርታማነት በሄክታር ወደ 34 ኩንታል ማደግ ይኖርበታል።

በአጠቃላይ፤ የሃገሪቱ ህዝብ ኑሩ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትና ሃገራዊ የካፒታል ክምችት ፈጠራ የተመሰረተበት የግብርናው ዘርፍ እድገት አሁንም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ያለግብርና ዘርፍ እድገት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሞተር አልባ መኪና ነው። ኢኮኖሚው ሞተር እንዲኖረው ሃምሌን ብቻ ሳይሆን በጋውንም ማረስ ይኖርብናል፤ በመስኖ። ከበሬ ጫንቃ መላቀቅ የኖርብናል፤ በሜካናይዜሽን።