ከአጥፊ ድግስ የታደገን “መደመር”

ሀይማኖታዊ እምነትን አስመልክቶ ለሚከሰቱ ችግሮች በአግባቡ መፍትሄ ካልተገኘላቸው ሂደቱን ለመቆጣጠር ወደማያስችል ሁኔታ ስለሚወስድ አዲሱ  ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ  የእርቅና የመደመር ስራ ከመጀመራቸውም በላይ ሀገር ወዳዶችና ለሕዝብ ቀናዒ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ኃይላት ሁሉ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ማሳሰባቸውም ይታወቃል።   

 

የአንድ ሀገር ሕዝብ የፖለቲካ ነፃነቱ ተከብሯል ተብሎ በሚነገርበት ጊዜ የሚሰጠው ግንዛቤ በሀገሪቱ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ በርካታው ሕዝብ የነፃነቱ ተጠቃሚ መሆን ችሏል ሲባል ብቻ ነው። እንደ ኢትዮጵያ በመሰሉ በርካታ እምነቶች በሚመለኩበትና ሕብረተሰቡ የመድበላዊነት ጠባይ በሚያንፀባርቅበት ሁኔታ የሃይማኖት ጥያቄ በጥንቃቄና አርቆ አስተዋይነት በተሞላበት መልክ ካልተያዘ በሕዝብ አንድነትና በሀገራዊ ሉዓላዊነት ላይ የሚያስከትለው አደጋ በጣም ከፍተኛ  ነው።

 

የፖለቲካ ነፃነት አይነተኛ ጠባይ ያለው በእያንዳንዱ ግለሰብ መብት ላይ የሚመረኮዝና የሚያነጣጥር፤ በግልም ሆነ በወል በመደራጀት የራስን አመለካከትና ፍላጎት ወደ ፖለቲካው መድረክና በሀሳብ ግንባታና የውሳኔ ሂደት በማቅረብ በውይይቱ ተካፋይ ለመሆን የሚያስችል መብት ነው።  ይህ የፖለቲካ ነፃነት በነፃ የመደራጀትና ከመንግሥትም ሆነ ከተለየ ቡድን ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመንቀሳቀስን መብት የሚያጠቃልል ነው።

 

ሰብዓዊ መብት ከሥረ መሰረቱ የግለሰብ መብት ሲሆን ሰው ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ የተቀዳጀው ነው።  ሰብዓዊ መብት የግል ነው ሲባል የሚሰጠው ግንዛቤ ይህ መብት የወል ጥገኛ እንዳልሆነ የሚያመላክት ነው። እንዲያውም የወል መብት ምንጩ ከግለሰብ መብት የሚፀነስ ነው። የእምነትና የሃሳብ ነፃነት መብትም መሠረታዊ ተብለው ከሚቆጠሩት ሰብዓዊ መብቶች ውስጥ በመሆናቸው ይህንን መብት ተግባራዊ በማድረግ የእምነቱ ተከታዮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መድረኩን ማመቻቸት በሥልጣን ላይ ከተቆናጠጠ ቡድን ምንጊዜም ቢሆን መጠየቅ የሚገባቸው እሴቶች ናቸው።

 

የፖለቲካ ነፃነት መረጋገጥ የሕሊና፤ የሃሳብ፤ የእምነትና የአስተሳሰብ ነፃነት መብት እንዲከበር መጠየቅን የሚያጠቃልል ነውና ማንኛውም ግለሰብ ወይም ዜጋ አንድን እምነት (ርዕዮተ-ዓለምን ያካትታል) በራሱ ግላዊ ምርጫ በነፃነት ለመቀበልና ለማምለከ፤ ለራስ መገለጫ አድርጎም ለመጠቀም፤ ካልተሰማማው ለመቀየር፤ በግልም ሆነ በጋራ ሲፈልግ ብቻውን በልቦናው የማመን ወይንም ከሌሎች ጋር በማህበረሰብ በአደባባይ ወይንም በፀሎት ሥርዓት ቦታ ተካፋይ በመሆን፤ በማዘውተር፤ በመማርና በማስተማር መተግበርን ሁሉ ይህ መብት የሚያጠቃልል ነው።

 

ማንኛውንም እምነት በሰላማዊ መንገድ ምንም አይነት የኃይልና የተፅዕኖ እርምጃ ሳይወስድ ለማስፋፋት፤ በእምነቱ መሰረትም እሴቶቼ የሚላቸውን መንከባከብና ተግባራዊ ማድረግ፤ ነፃነቱ መጠበቅና ዋስትና ማግኘት የሚኖርበትም በዚሁ ምክንያት ነው። ለዚህም ነው አማኝ የመረጠውን እምነቱን እንዳያመልክ ሊታገድ ወይም በሥልጣን ባለ አገዛዝ አማካኝነት በሌላ እንዲተካበት ማድረግ ሰብዓዊንና ዴሞክራሲያዊ መብትን መጣስ ነው የሚባለው።

 

በሃገራችን ጥንታዊና ዋነኛ በሆኑቱ የሙስሊም እና ክርስትና እምነቶች ዘንድ የእርስ በእርስ መከባበሩና መቻቻሉ ከላይ በተመለከተው አግባብ ልኩን ይዞ መጓዙ እንደተጠበቀ ሆኖ በህገ መንግስቱም ከተመለከተው ድንጋጌ ውጪ ሃይማኖቶቹ በየገዛ ቤታቸው ለሁለት ተከፍለው ጥቂት ለማይባሉ አመታት ሲታመሱ መኖራቸው ይታወሳል።

 

በዚሁ መሰረት እና ከላይ ስለተመለከቱት አደገኛ ውጤቶች  ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በ8/10/2010 የኢድ አልፊጥር በአልን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ የህዝበ ሙስሊሙን ያልተመለሱ ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን በመግለፅ ጥሪ ያደረጉ ሲሆን፤ በሙስሊሞች መካከል ልዩነት አስመልክቶ የመደመር አስተሳሰብ ይዞ ለመጣው አዲሱ የለውጥ አመራር ጥሪ የቀረበው መልስም ፈጣንና የሃይማኖቱን አስተምህሮም የተከተለና አርአያነት ያለው ነው።

 

ለቀረበው ጥሪ ህዝበ ሙስሊሙ የጣለብንን መፍትሄ የማፈላለግ ሃላፊነታችንን ለመወጣት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማዕከል ያደረገ፣አካታች የመፍትሄ አቅጣጫ እንከተላለን ሲል ፈጣን ምላሽ የሰጠው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ፤ ለዚህም ዑለሞችን ፣ምሁራንን፣የሀገር ሽማግሌዎችን፣ወጣቶችና ሴቶችን እንዲሳተፋ እናደርጋለን። እንዲሁም የህዝበ ሙስሊሙን ጥቅም የሚያስጠብቅና የተሻለ መፍትሄዎች ያላቸው ግለሰቦች፣ ተቋማትና ምሁራን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱና አብረውን እንዲሰሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ።ሲል በምላሹ ገልጾ የነበረ መሆኑም የታወሳል።

 

በተለይ ኮሚቴው “የምንፈልገው መፍትሄ አሳታፊ ፣ ዘላቂና ሁለንተናዊ የህዝበ ሙስሊሙ መብት የሚከበርበት መሆን ስላለበት ህዝባችን ይህንን ተገንዝቦ በአንድነት መንፈስና በትዕግስት ከጎናችን በመቆም በላቀ ትብብር አብረን እንድንዘልቅ አደራችን የጠበቀ ነው።”ሲል ያስተላለፈው መልእክት የመንግስትንም ሆነ የየትኛውንም እምነት ተከታይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ቀልብ የገዛና መልእክት ነው። 

በርካታ የሃይማኖቶች ተከታዮች በመከባበርና በመቻቻል የሚኖሩባት አገር ናት ኢትዮጵያ ፡፡

 

ይሁን እንጂ የሃይማኖት እኩልነት እውቅና አግኝቶ በተግባር መተርጎም ከተጀመረ ያስቆጠረው አጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ለዚህ መሰረታዊ መብት መከበር ወሳኝ የታሪክ ጊዜያት ነበሩ፡፡  ሁሉም ሰው ያመነበትን እምነት የመከተልና የማራመድ እንዲሁም ሥርዓተ አምልኮን የመፈፀም ነፃነት ተጎናፅፏል፡፡ ይህም በህገ-መንግስቱ ተረጋግጧል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሃይማኖት ነፃነት እውቅና አግኝቶ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የተገኘውን የእምነት ነፃነት በመጠቀምም እያንዳንዱ ቤተ-እምነት የየራሱን የልማት ተግባራት እያከናወነ ነው፡፡  

 

የየቤተ እምነቱ ምዕመናንም ሥርዓተ አምልኳቸውን ከመፈፀም ባሻገር በተለያዩ ቦታዎች የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች ተቋማት እንዲስፋፉና እንዲጠናከሩ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ይህንኑ የሃይማኖት ነፃነት በመጠቀም ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት፣ ኮሌጆችን ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የካህናት ማሰልጠኛዎችን ወደ ኮሌጅ በማሳደግ የተማረ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑም ይታወቃል፡፡

 

የተገኘው የሃይማኖት ነፃነት በአገሪቱ በሚታየው የሃይማኖት መቻቻል ይገለፃል፡፡ ለሰላምና ለልማት መጠናከር እንዲሁም ሰላም፣ ፍቅር፣ ዕድገትና ልማት እንዲኖር የሁሉም የሃይማኖት አባቶች ቀዳሚ ሃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም በጥቃቅንና ከየቤተ እምነቱ አስተምህሮ ውጭ በሆኑ ግለሰባዊ ምክንያቶች መናቆሩ ደግሞ በብዙዎቹ ቤት ተስተውሏል። ስለሆነም አዲሱ የለውጥ አመራር በመደመር ስሌት ህገ መንግስታዊ ስርአቱን ተከትሎ የሙስሊሙን ጉዳይ  ከተደገሰለት አጥፊ እቅድ አስቀድሞ ቋጭቷል።

 

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን እና የኢትዮጵያ ሙስሊም የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴን በተናጠልና በጋራ  ካወያዩ በኋላ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴው ሰላማዊ በሆኑ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ተስማምተዋል።ሁለቱ ወገኖች ችግሮችን በእስልምና አስተምህሮት መሰረት በጋራ ለመፍታትም ተስማምተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱ ወገኖች በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በዘላቂነትና ሰላማዊ መፍትሄ ያገኝ ዘንድ ከሁለቱም ወገኖች የተወጣጡ ወኪሎችን ያካተተ መፍትሄ አፈላላጊ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

 

አዲስ የተቋቋመው ኮሚቴ ዘጠኝ አባላት ያሉት ሲሆን ሁለቱ ወገኖች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር አብይ አህመድ በጋራ ከተወያዩ በኃላ መሆኑም ተገልጿል። የኮሚቴዎቹ አባላት ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ፣ ከመጅሊስ፣ ከምሁራን እና ሽማግሌዎች የተውጣጡ ናቸው። የኮሚቴ አባላቱም  ማንም ሰው እስከተደማመጠ እና እስከ ተቀራረበ ድረስ የማይፈታው ችግር የለም ካሉ በኋላ ይህ ጅምር ፍሬ አፍርቶ ህዝበ ሙስሊሙ የሚደሰትበት ውጤት እንደሚያመጣ እምነታችን ነው ማለታቸውም ተመልክቷል።

 

በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የለውጥ እና የመደመር ሂደት ውስጥ ደማቅ አሻራ ያለውን የሙስሊሙን ማህበረሰብ የሚወክሉት ሁለቱ ወገኖቻችን ከሚያራርቋቸው ነገሮች ይልቅ የሚያቀራርቧቸውን የጋራ ግቦች በመመልከት አብሮነታቸውን እስካላጸኑ ድረስ የሙስሊሙ ወገንም ሆነ የሀገሪቱ ሰላም በፍጹም ሙሉ ሊሆን አይችልም ብለዋል የኮሚቴ አባላቱ፡፡ ሙስሊሙን ማህበረሰብ አገለግላለው የሚል መሪም አርአያ መሆን እንዳለበት እና ይቅር መባባል የሀይማኖቱም መሰረት እንደሆነ በመጥቀስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ቢጠነክር አንድ ቢሆን ለሀገርም ጥቅም እንደሆነ ተጠቁሟል።

 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፍቅር እና ይቅርታን በሚሰብክ እና የሰላም ቤት ነው በሚባል የእምነት ተቋም ውስጥ ደግሞ ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ሰላም የግድ መኖር ያለበት ብቻ ሳይሆን ከሀይማኖታዊ ባህርይም በላይ የእምነት ተቋማት ተፈጥሮም ነው፡፡” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት የሁለቱ ወገኖች ለመነጋገርና ችግሮቻቸውንም በሰላም ለመፍታት መስማማት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን የሰላም ብስራት ነው ማለታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የወጡት መረጃዎች አመልክተዋል።

 

በኦርቶዶክስ ተዋህዶ በኩል ያለውም መከፋፈል በዚሁ አግባብ ወደ መደመር እየመጣ ለመሆኑ የሚያረጋግጡ መረጃዎች እያመለከቱ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ  ወቅታዊ ጉዳይ ያሳሰበው አዲሱ የመደመር አመራርና በበጎ ፈቃደኛነት የተቋቋመው የሁለተኛው ዙር የሰላምና አንድነት ኮሚቴ በሁለቱም ሲኖዶሶች መካከል ያለውን የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት በሰላም እንዲፈታ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።

 

አገራችን ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሁሉንም አካል የሚመለከት በመሆኑ ያለፈው የልዩነት፤ ጥላቻና መከራ ዘመን እንዲያበቃና በአንጻሩ ሰላም፤ፍቅርና አንድነት በሀገራችን ኢትዮጵያና በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዲሰፍን፤ ዕርቀ ሰላሙም የተሳካ እንዲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ በውጭ ከሚገኘው ሲኖዶስ ጋር ተደራዳሪ የሚሆን 3 ሊቃነ ጳጳሳትን ሰይሟል። ከተደገሰው ጥፋት ለማምለጥም በዶክተር አብይ ቀጣይ የአሜሪካ ጉዞ የሚደመሩ እንደሆነም አያጠያይቅም።

 

የእምነት ነፃነት መብት ተግባራዊ በሚሆነበት ወቅት ገደብ የሚበጅለት የሌላን ዜጋ መብት ያለማክበር ወይንም እምነቱን የተሳሳተ አድርጎ በመቁጠር ለመጋፋት የተንቀሳቀሰ እንደሆነ ግልፅ ነው። የሃይማኖት እምነት መከበርና ዋስትና ማግኘት የሚመሰረተው በተለይ ማንኛውም ግለሰብ ፈጣሪዬ ከሚለው ጋር በሃይማኖቱ መሠረት ግንኙነት ለማድረግ ባለው ፍላጎትና ይህም ስኬታማ ይሆን ዘንድ ባለው ችሎታ ላይ ነው። የሃይማኖት ነፃነት የሚረጋገጠው በተቋማቸው ነጻነትና በዚሁ ነፃነት ተመርኩዘው በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎቻቸው ነው።

 

በሃገራችን የሚገኙት እምነቶች በተለይም በርካታ ተከታዮች ያሏቸው የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖች መካከል በአርዓያነት ሊታይ የሚችል ድንቅ የሆነ የመቻቻል፤ የመከባበር፤ የመተጋገዝ ባሕልን ያሳዩ ለመሆናቸው እኛ ይህንን ታሪካቸውን የወረስነው የአሁኑ ትውልድ አባላት ብቻ ሳንሆን የዓለም አቀፍ ሰላም ወዳድ ኃይል ሁሉ የሚመስክሩልን ነው።እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ቀደም ብሎ እንደተጠቆመው ይህንን የመቻቻል እሴት መሠረቱን ሊያጠፋ የሚችል፤ በእምነቱ ተከታዮች መካከል ወደ የማያቋርጥ ብጥብጥ ሂደት ሊወስድ የሚችል እንቅስቃሴ  በመደመር ስሌት ጉዞውን አቁሟል።

 

ኢትዮጵያ ሃገራችን የተለያዩ ሃይማኖቶች የሚመለኩባትና መድበላዊ ጠባይ ያለው ሕብረተሰብ ያላት በመሆኗ የሁሉም ሃይማኖቶች እኩልነት ያለገደብ ማረጋገጥና ለሰላም መስፈን፤ ፖለቲካና ሃይማኖት በሚገባ ተለይተው የተግባር መድረኮቻቸውም በግልፅ ተወስኖ እንዲቀመጥ የመደመር ሃይል በቀጣይም ተግቶ ሊሰራ ይገባል ።