ካለያየን ይልቅ ያገናኘን ፍቅር ልቋል!

ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990 ዓ.ም በወረሃ ግንቦት ወደ ጦርነት መግባታቸውን ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው፣ ማህበራዊ ትስስራቸውና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ለሁለት አስርት ዓመታት ተቋርጦ ቆይቷል። በዚህም “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” እንዲል የሀገሬ ሰው በባህል፣ በቋንቋና በሐይማኖት ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው  ህዝቦች ተራርቀው እንደተነፋፈቁ ድፍን 20 ዓመታት አለፉ።

በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል መለያየቱ ያስከፈለው ዋጋ በእጅጉ ልብን የሚያደማና አጥንት ዘልቆ የሚሰማ ህመም አለው። ነገር ግን ከዚህ ህመም በላይ ነጥሮ የታየ አንድ ታላቅ ነገር አለ። እርሱም ፍቅር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የፍቅርን ሀያልነት ሲገልጹ “ቦምብ እና ሚሳኤል የሰውን አካል ይጎዱና ለጊዜው ያስከነዱ ይሆናል የሰውን ልብ ግን ሊማርኩ አይችሉም። የሰውን ልብ መማረክ የሚችለው ምንም ወጪ የማይጠይቀው በተፈጥሮ የተቸረን በልባችን ያለው ፍቅር ብቻ ነው” ብለዋል።

የቱንም ያህል አስቸጋሪ  የሆነ አካል በፍቅር እንደሚሸነፍ ለማናችንም እሙን ነው። ሩቅ ሳንሄድ በቀላሉ እያንዳንዳችን በዕዝነ ህሊናችን የሕይወት ጓዳ ጎድጓዳችንን እንፈትሽ። ትናንሽ የቤተሰብ ግጭቶች ሲገጥሙን እንኳ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብለን በፍቅር አሸንፈናል ብዬ አምናለሁ። በተቃራኒው ደግሞ ፍቅርን ትተን ወደ ክፋ የቤተሰብ ፀብ ውስጥ ገብተን ሰላም አጥተን የተራራቅን ለመኖራችን ጥርጥር የለኝም።

ላለፉት 20 ዓመታትም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ይሄው ነው። በደምና በስጋ የተዋሃዱ የማይለያዩ ህዝቦች ተለያይተዋል። አንድ ማህፀን የተጋሩ እህትና ወድማማች ተራርቀዋል፣ እናት ከልጇ ልጅም ከእናቱ ተነጥሏል፣ ባል ከሚስቱ የቃልኪዳን ቀለበታቸውን እንዳጠለቁ ሁለት አካል ሆነዋል፣ ከዚህም በላይ ከሁለቱም ሀገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህይወት መስዋዕትነትን በውድ ልጆቻቸው ከፍለዋል።

ይህ ከሆነ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በወሰዱት ተነሳሽነት ለኤርትራ የሰላም ጥሪን አቀረቡ። ይህንን ጥሪም ተከትለው የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፍወርቂ ለሰላም ተባባሪነታቸውን በመግለፅ አንድ እርምጃ ወሰዱ። ከዚህ በኋላ ለሃያ ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በብርሃን ፍጥነት ሊባል በሚያስችል ሁኔታ ምላሽ በማግኘቱ እነሆ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ያለፈ ታሪክን ረስተው አዲስ ታሪክ ሊሰሩ ፊት ለፊት ተገናኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሞት አልባው ጦርነትን በፍቅርና በይቅርታ  ለማከም ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም አስመራ ገቡ። አስመራ ሲደርሱ የተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ሁለቱን ሀገራት ከለያያቸው ሀዘን በላይ ዳግም ያገናኛቸው ፍቅር በእጅጉ ልቆ ታይቷል። የአስመራ ህዝብም ደስታውን ለመግለፅ የሁለቱን ሀገራት ባንዲራ፣ የዘንባባ ዝንጣፊና አምባሻ በመያዝ የአስመራን ጎዳና በእልልታና በሆታ  አደመቃት። ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይም የተደረገላቸውን ደማቅ አቀባበል ሲገልፁ “የአስመራ ሕዝብ ፍቅር መሆኑን በመፅሐፍ፣ በፊልምና በዘፈን እንደሰማነው ብቻ ሳይሆን በተግባርም ፍቅርን ሰጥቶናል” ብለዋል።  

የኤርትራ ህዝብ ለሰላም ለፍቅርና ለአንድነት ትልቅ ዋጋ መስጠቱን ለጠቅላይ ሚንስትሩ ባደረገው ደማቅ አቀባበል ተረጋግጧል። የእነዚህ ሁለት ሀገራት ህዝቦች ፍፁም መለያየት የማይገባቸው ነገር ግን የተለያዩ ህዝቦች ነበሩ። ዛሬ አዲስ ታሪክ ለመስራት የአንድነት ጉዟቸውን አንድ ብለው ጀምረዋል። ከዚህም በላይ የሚከልሉት ድንበር እንደማይኖር መሪዎቹ ገልፀዋል። በዚህም በርካታ የዓለም ሀገራት ሁለቱ ሀገራት የራሳቸውን ችግር በራስ መፍታት መቻላቸውን አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ እያበረከተች ያለችው የሠላም አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በኢኮኖሚያዊ ግንኙነትም ቢሆን በተለይም ከኤርትራ ጋር የአሰብ ወደብን ስትጠቀም ኤርትራም ከኢትዮጵያ መልማት ጋር ተጠቃሚ ትሆናለች። ሸቀጦችንም ከኢትዮጵያ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ትችላለች። ከሁሉም በላይ ግን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በዋጋ ሊተመን የማይችል ትልቅ ጥቅም ነው።

ኢትዮጵያና ኤርትራ የአንድ አካል የሰውነት ክፍሎችን ያህል መቀራረብ ያላቸው እንደመሆናቸው እነሆ በመደመር ዘመን ተደምረዋል። ይህን ተከትሎም የኤርትራው ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ በታሪክ ከ20 አመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ተማሩባትና ወደ ኖሩባት ሁለተኛዋ ሀገራቸው መዲና አዲስ አበባ ገብተዋል። ይህን ታሪካዊ ቀን አስመልክቶም የአዲስ አበባ ጎዳናዎች በተለይም ወደ ኤርፖርት የሚወስደው መንገድ በኤርትራና በኢትዮጵያ ባንዲራ አሸብርቆ ታይቷል።

የአዲስ አበባና አካባቢዋ ህዝቦች በነቂስ ወጥተው በዘፈንና አብይ… አብይ… ኢሳያስ… ኢሳያስ… በሚሉ ድምፆች ደስታቸውን ገልፀዋል። ከኤርፖርት እሰከ ቤተመንግስት ፍፁም ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በታየበት ስርዓት አክብሮታቸውን ይቅርባይነትንና ፍቅርን አሳይተዋል። ከዚህም በላይ በሀዋሳ ከተማና አካባቢዋ የተደረገው ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ አቀባበልና መስተንግዶ በእጅጉ አስደሳች ነበር።  

በአሁን ወቅት ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማህበራዊ ዘርፍ እንዲሁም የአካባቢን ሰላምና ፀጥታን በሚመለከት ጉዳይ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል። ይህም ሀገራቱን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።  ከፖሊቲካዊ ጥቅማቸው ባለፈም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በእጅጉ የተሳሰረና ላይበጠስ የተገመደ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ድንበር የማካለል ነገር ቀርቶ መጀመሪያ ቤተሰባዊ ፍቅርና አንድነት ይቅደም” መለታቸው ማሳያ ነው። ይህን ተከትሎም ሁለቱ ሀገራት ተደምረው በፍቅርና በአንድነት በጋራ ጉዞ ጀምረዋል።

በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ቀድሞ በነበረው ወቅት “ሁለቱ ሀገራት በተስማሙ ጊዜ ይስማማሉ። የህዝቦቹን ትስስር ግን የትኛውም ሀይል ሊበጥሰው አይችልም” ሲሉ ተደምጠዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የራሳቸውን ችግር ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሳቸው መፍታት ችለዋል። ይህንን ተከትሎም የሁለቱን ህዝቦች የጠነከረና የቆየ ወዳጅነት፣ አንድነት፣ ፍቅር፣ መተሳሰብ፣ መፈላለግና መነፋፈቅ የሀገራቱ መሪዎች ባደረጓቸው ጉብኝቶች ወቅት ከህዝቡ በተሰጠው ደማቅ አቀባበል ማየት ተችሏል። በርካታ የዓለም ሀገራትም ይህን እውነት የማይታመኔ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን የሆነን ትዕይንት በመከታተል አድንቀዋል።

አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል ለሁለት አስርት ዓመታት የቆየው የጥላቻ ግንብ ፈረሶ፤ ድንበር የሌለው የፍቅርና የአንድነት ድልይይ ተገንብቷል። ይህም በበርካታ የመገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ሆኖ ሰነባብቷል። ኢትዮጵያና አኤርትራ ከተስማሙባቸው ነጥቦች መካከል ጦርነት ማቆም አንዱ ነው። ይህ ትልቅ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደመሆኑ ከዚህም በላይ ደግሞ የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና ሰላማዊ ማድረግ ይጠበቃል።  

በአጠቃላይ የኢትዮጵያና የኤርትራን ህዝቦች ካለያያቸው ሀዘን በላይ ያገናኛቸው ፍቅርና አንድነት የቱን ያህል ጥልቀት እንዳለው ከሁለቱም ሀገራት ህዝቦች መዋደድ መገንዘብ ተችሏል። ይህን የጠለቀ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማስቀጠልም ሀገራቱ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ጀምረዋል። ከተጀመሩት ተግባራት መካከልም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም የሃገራቱ መሪዎች በተገኙበት በይፋ ተከፍቷል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም የኤምባሲውን ቁልፍ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስረክበዋቸዋል። በቀጣይ ደግሞ የሃገራቱ አምባሳደሮችን በመላክ በይፋ ስራ የሚጀምሩ ይሆናል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ 456 የህዝብ ለህዝብ ቡድንን አሳፍሮ አስመራ ገብቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን አስመራ ዓለማቀፍ ኤርፖርት ማረፉን ተከትሎ የተነፋፈቁና ይቺን ቀን በታላቅ ጉጉት የጠበቁ አይኖች በስጋ ተገናኝተዋል። የደስታ ዕንባንም ተራጭተዋል።