ሰላምን እንደገና…

 በዚህች ጠባብና ነገሮች በሰከንዶች ሽርፍራፊና በአጭር ጊዜ በሚቀያየሩባት ዓለም ውስጥ ለሚኖር ፍጡር ይቺ ምድር ምን ያህል እንደ ጠበበች ለመረዳትና አንድ መንደር ለመሆን እያኮበኮበች መሆኑን ለመገንዘብ  ነጋሪ አያሻም :: ወደ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) እያመራች ባለችው በዚች ጠባብ ዓለም ውስጥ ለሚኖር ሰው ከቤቱ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ፣ ዘርቶ መልቀም፣ወልዶ መሳም፣ ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው በየአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ሲኖር ነው::

ከብዙ ሰዎች አፍ  ላይ የማይጠፋ ቃል አለ “ዋናው ነገር ጤና” የሚል እውነት ነው ለሰው ልጅ ዋና ተብለው ከሚጠቀሱ ነገሮች አንዱ ጤና ነው:: ካለ ጤና የሚያልፍ እያንዳንዱ የሰከንድ ሽርፍራፊ መራር ነው :: ሰው ከጤናው ሲጣላ የማይሆነው ይሆናል ፣ ጠንካራ ሠራተኛ ለፍቶ አዳሪው እንኳን ከሰው እጅ ይወድቃል ሰው ጤና ሲያጣ መኖር የሚባለው ነገር በራሱ ከጣእም ይጣላል::

ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን ቅሉ እስካሁን ስለጤና ያወራነው በሙሉ ልክ ሊሆን የሚችለው በአካባቢው ላይ የሚነፍሰው ንፋስ ሰላማዊ ሲሆን ብቻ ነው:: ሰው ጤነኝነቱ በምንም ደረጃ ቢለካ የቱንም ያህል  ጤነኝነት ቢሰማው እራሱ ሁሉም ነገር ሰላም ካልሆነ ጤና ቀልድ ይሆናል :: ጤነኛው ታማሚ ይሆናል እዚም እዛም ፍርሃትና ሰቀቀን ብቻ ይሆናል ሰው ሁሉ የሚያስበው ነገር “ደሞ ነጋ ምን ያሰማኝ ይሆን” ብሎ ነው ::

“ሰላም ማለት ሲይዙት የሚቀል ግን ሲታጣ ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ነው”:: እውነት ነው በአካባቢያችን ሰላም ሲደፈርስ የሚጎድል ብዙ ነገር አለ:: ከተወሰኑ ወራት በፊት ሀገሪቷ በሰላም ማጣት ደዌ ተመትታ ነበር:: ህመም ደግሞ የቱንም ያህል ትንሽ ቢሆን መድሃኒት ያውም ትክክለኛ የሆነ መድሃኒት ካልተገኘ በሽታው ሥር ከሰደደ ውስጥ ውስጣችንን መጉዳቱ አይቀርም :: የግድ እየተጎዳንበት ያለው በሽታ ከሱ በላይ በሚያም መድሃኒትም ቢሆን የሆነ ቦታ ላይ ፈውስ ሊገኝለት ይገባል:: ፈውስ ካላገኘ ግን  “ቂም ይዞ ፀሎት ሳል ይዞ ስርቆት” የሚሉት ነገር ማለት ነው::

ከወራት  በፊት በነበሩት የሰላም ማጣት ችግሮች የተፈጠሩ  እያንዳንዱ ክስተቶች ለዚህ ምስክር ናቸው በአሁኑ ወቅት ግን በመላው ሀገሪቷ ያለ ሌላ ኃይል ጣልቃ ገብነት የተገኘው ሰላም እና መረጋጋት ያስከተላቸው ለውጦች  ይበል የሚያስብል ነው፡፡

 

 

  በሰላም ለመኖር እያንዳንዱ ሰው የራሱን አስተዋፅዖ  ሊያደርግ ይገባል  የሚባለው ለዛ ነው፡፡  የድህነትን እና ኋላቀርነትን ተራራ ሊናድ የሚችለው መጀመሪያ ለሰላምና መረጋጋት  የሰጠነው ቦታ እንደሚገባው ሲሆን ነው:: እናም  በሰላምና መረጋጋት ላልታጠረ ማህበረሰብ  ስላንድነት አና ሌሎች ተጓዳኝ ነገሮች ማውራት ከባድ ይሆናል ያም ልክ "ከፈረሱ ጋሪውን" ማስቀደም ማለት ነው ::

  ከምንምና ከማንም በፊት አንድ ማህበረሰብ  ስለ ሰላም ያለው አረዳድ  የተንሸዋረረ ሊሆን አይገባም::  ሁሉም ሰው ለሰላም መጠበቅ ዘብ ሊሆን ይገባል :: ሌላ ሰውን መጠበቅ አያስፈልገውም እናም ሁሉም ዜጋ ለገዛ ራሱ ሰላም ዘብ መቆም አለበት:: ሁላችንም ሰላምን የማስከበር አቅም በእጃችን ነው ያለው   ህብረተሰቡ ከተባበረ አሁን እየታየ ያለውን ለውጥ ተግዳሮቶችን በማስወገድ ማስቀጠል ይቻላል ::

    የ ሰላም ድምጽ ሲሰማ አይሆንም ተብሎ የሚታሰበው ሁሉ ይሆናል::  በኤርትራ ኢትዮጵያ መካከልም እየሆነ ያለው ነገር እንደዛው ነው::  በባህል፣ በቁዋንቃ፣ በእምነት፣ በደምና በደምና በአጥንት ዝምድናና ትስስር ባላቸው በኤርትራ ና ኢትዮጵያ  ጦርነት  ለሁለት አስርት ዓመታት የነጣጠሏቸውን ልጅንና እናት፣ ወንድምና እህት ሲገናኙ ማየት የሰላም ዋጋው ምን ያህል ትልቅና ጥልቅ ነገር  መሆኑን ያሳየናል::  በጦርነት ምክንያት ስንት ሰው ካለ  ቤተሰብ ሊቀር እንደሚችል ከዚህ በላይ ምንም እማኝ የማያሻው ነገር ነው::  ዛሬ ላይ እነዛ የጭንቅ ቀናት አልፈው ሀገራቱ ስለ ሰላም  ማቀንቀን ሲጅምሩ የነሱ እርቅ ማውረድ ለብዙ ምስኪን ሰዎች  ለዓይነ ስጋ መብቃት ምክንያት ሆኗል::

በአዲስ አበባ፣  በባህር ዳር፣ ከፋ  ፣ቻግኒ  እንዲሁም በአረብ ሀገሮችና በሰሜን አሜሪካ የተለያዩ አካባቢዎች  የነበረው  የድጋፍ ሰልፍ ህብረተሰቡ ለሰላም  እና  መረጋጋትን ምን ያህል  እንደተጠማ እንዲሁም የቱንም ያህል ዋጋ  ለመክፈል ቆራጥ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡   በተጨማሪም   ህዝብ ከሰላሙ የሚበልጥበት ምንም ነገር እንደሌለም ያሳየበት ሁኔታም ነበር፡፡

    ምንም እንኳን መገናኛ ብዙሃን ጠንካራና ደካማም ጎን ቢኖራቸውም በተመልካቾች ላይ ግን ቀጥተኛም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ተፅዕኖ ሊኖርው እንደሚችል ግን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  እነዚህ ተፅዕኖዎች ደግሞ በተቀባዩ የእድሜ ክልል እንደውም የትምህርት ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን መገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡት ነገር ያገሪቷን መልካም ስም የሚያጠለሽ አለመሆኑን ግን ማረጋገጥ የግድ ይላል፡፡