ትሩፋቶቹን ለማጎልበት…

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በ100 ቀናት ውስጥ የሰሩት ተግባሮች ለአገራችን ያላቸውን ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ለህዝባችንም ያስገኟቸውን ትሩፋቶች  የትየለሌ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባሮች በአገራችን ህዝብ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ በሚችሉ የፌዴራል ተቋማት ላይም ለውጥ እያመጡ ነው። ይህም ተቋማቱ ከሚሰሩበት የዘልማዳዊ አሰራር ተላቅቀው ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተግባራቸውን እንዲከውኑ አስችሏቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለየተቋሞቹ አመራሮች መመሪያና አቅጣጫ ከመስጠት ባለፈ፣ ተጨባጭ የሪፎርም ስራዎች እንዲከናወኑ አድርገዋል። በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገኟቸው የ100 ቀናት ትሩፋቶች ጎልብተው እንዲቀጥሉ የመንግስትን ስራ የሚያስፈፅሙ ተቋማት አሰራራቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል።

ዶክተር አብይ በእነዚህ ቀናት የፈፀሟቸው የእርቅና የአንድነት ተግባሮች እጅግ የገዘፉ ናቸው። በተለይ ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር አኳያ የፈፀሟቸው ጉዳዩች ሀገራችንን ከነበረችበት የሁከትና የትርምስ መንገድ አላቆ ወደ ሰላም አውድ የመለሳት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ህዝቡ ያለበትን ችግር በቅርበት አድምጠዋል። ህዝባዊ ውይይቶችን በማካሄድ በሀገር ውስጥ ብሔራዊ መግባባትንና የአንድነት መንፈስን ፈጥረዋል።

በወቅቱም ህዝቡ ያለበትን ችግር በግልፅ አስታውቋቸዋል። እርሳቸውም በመንግሥት በኩል አቅም በፈቀደ መጠን የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኝነቱ መኖሩን ገልፀው ችግሩን ለመፍታት እየጣሩ ነው፤ ተጨባጭ ውጤትም እየመጣ ነው። እነዚህ የዶክተር አብይ የአገር ውስጥ መድረኮች አገራዊ ፍቅርን፣ አንድነትንና የጋራ መግባባትን ማምጣት የፈጠሩ ነበሩ።

በእነዚህ ቀናት በአገር ቤትና በውጭ ታስረው የነበሩ ዜጎች በይቅርታና በምህረት እንዲፈቱ ማድረግ ችለዋል። በውጭ በትጥቅ ትግል ጭምር ሲነቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ አድርገዋል። በውጭ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃንም ወደ አገር ቤት ገብተው ለዴሞክራሲው መስፋት የበኩላቸውን እንዲወጡ እያደረጉ ነው።

በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ የጥላቻና የቂም በቀል ፖለቲካ እንዲያከትም፣ የይቅር ባይነትና የፍቅር መንፈስ እንዲሁም የመደመር አስተሳሰብ እንዲጎለብት ብሎም የተለየ ሃሳብ መያዝ ሃጢያት ወይም ግፍ አለመሆኑን በአዲስ የለውጥ መስመር አስተምረዋል።

በእነዚህ ቀናቶች ውስጥ ቀደም ሲል በህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩት ግንቦት ሰባት፣ ኦነግና ኦብነግ ከአሸባሪነት ርዝር ውስጥ እንዲሰረዙ አድርገዋል። በዚህ ድርጊታቸውም የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሁሉም ለአገሩ የቻለውን ያህል አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ሰርተዋል።

በውጭውም ግንኙነት የዲፕሎማሲ ድሎችን አጎናፅፈውናል። ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና አገራዊ ህልውናችንን አረጋግጠዋል። ከማንኛውም አገር ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመሰረታዊ አገራዊ ጥቅማችን ደህንነት ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም የልማትና የዴሞክራሲ ሂደቱ ስር እየሰደደና የአገራችን ዕድገት እየተፋጠነ በሄደ ቁጥር ለአደጋ ተጋላጭነታችን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ አድርገዋል።

በቂ ጥናት በማካሄድ አደጋዎችን የሚቀንሱ፣ ግጭቶች ሲፈጠሩ በውይይት የሚፈቱ፣ በዚህ ሂደት ሊፈቱ ያልቻሉትንም በአካል ተገኝተው የማረጋጋት ስራዎችን ሰርተዋል። ይህም ሰላምንና ዴሞክራሲን በአገር ደረጃ በማምጣት ተሰሚነታችን እንዲጨምር አድርጓል።

ዶክተር አብይ ኢትዮጵያ እንደ አገር ለመቀጠል የውስጥ ችግሯን መፍታት እንደሚኖርባት በማመን መፍትሔ የያዘን አቅጣጫ ተከትለዋል። ሁሉም ዜጋ እንደ ኢትዮጵያ አንድ ሆኖ ከተደመረ ተሰሚነታችን እንደሚጨምርም በተግባር አሳይተዋል።

ራሳችንንና የአካባቢያችንን ህዝቦች የጋራ ጥቅም ማዕከል በማድረግ ተደጋግፎ የማደግ አቅጣጫን መከተል አስፈላጊነቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ህዝቡ እንዲገባው ያደረጉ መሪ ናቸው። ለሶስት ዓመታት መመለስ ያልተቻለውን የሰላም አውድ ከሶስት ወራት እልፍ ባሉ ቀናት ብቻ ሰርተው ለህዝቡ ማሳየት ችለዋል። በዚህም የአገራችንን ገፅታ በመለወጥ ከሁከት ወደ ተሰሚነት አንድትሸጋገር አድርገዋታል። የመደመር አስተሳሰብ ከአገራችን አልፎ ቀጣናውንም እንዲያካልል በመጣር ለሰላምና ለጋራ እድገት ጥራል።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ወደ ውጭ አገር ባደረጓቸው ጉዞዎች አገራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ የሚያረጋግጡ ተግባራትን ፈፅመዋል። በጂቡቲ፣ በሱዳንና በኬንያ፣ በሶማሊያ፣ በኡጋንዳና በግብፅ ያደረጓቸው ጉብኝቶች ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚያስከብሩ ነበሩ።

ከአገራቱ ጋር በወደብ ማልማት፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ለአገራችን የሚበጀውን ነገር ፈፅመዋል። በተለይም ቀደም ሲል ከግብፅ ጋር የነበረውን የጭርጣሬ መንፈስ ወደ መተማመን እንዲቀየር አድርገዋል።

በሳዑዲ አረቢያና በተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ያደረጉት ጉብኝት ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ኢትዮጵያ ያላትን ጠንካራ ግንኙነት ያረጋገጠ ነው። የሁለትዮ ገንኙነትን ያጠነከረና አገራችን ከግንኙነቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማረጋገጥ የቻለ ነው።   

በኢትዮጰያ ታሪክ ሥልጣን በተረከቡባቸው 100 ቀናት ውስጥ ብቻ እርሳቸው ያመጡትን ለውጥ በመደገፍ ሚሊዮኖች ለድጋፍ የወጡላቸው የመጀመሪያው መሪ ይመስለኛል። ህዝቡ ላመጡት ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር ድጋፍ ሰጥቷል። እየሰጣቸውም ነው።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን “ሞት አልባ ጦርነት” በፍቅርና በሰላም መቀየር የቻሉ መሪ ናቸው። በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል የተጋረደውን ጥቁር መጋረጃ በመቅደድ ወደ አስመራ አምርተው የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ከ20 ዓመት በላይ ያላዩአትን አገራችንን እንዲጎበኙ በማድረግ የሰላም ስምምነቱ ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው አድርገዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የ100 ቀናቶች የፌዴራል መንግስት ስራ አስፈፃሚዎች ከነበሩበት አሰራር የተሻለ መንገድ እንዲከተሉ ያደረገ ነው። በእነዚሁ ቀናት ውስጥ ባደረጉት የስጣን ሽግሽግ ስራቸውን የሚያከናውኑ አካላት ተገቢውን ግንዛቤ እንዲያገኙ አቅጣጫና መመሪያ ሰጥተዋል። ተቋማቱ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን ተጠሪነታቸው ለህዝብ እንዲሆንም አድርገዋል።

የፀጥታና የደህንነት ዘርፉ ከለውጡ ጋር እንዲዘምንና ንድፈ ሃሳባዊ አሰራሮችን ተከትሎ ውጤት የሚያመጣበትን አቅጣጫ አሳይተዋል። ተቋማቱ በህገ መንግስቱ መሰረት ተግባራቸውን እንዲወጡ የሚያስችላቸውን አሰራርና አደረጃጀት በመፍጠር ላይም ይገኛሉ። የፌዴራል መንግስት ተቋማት ስራቸውን ዘመናዊና ሳይንሳዊ አድርገው ለሀብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት የሚሰጡበትንም መንገድ ቀይሰዋል። ስራቸውን ቆጥረው ተቀብለው ቆጥረው የሚያስረክቡበት አሰራርን አስፍነዋል። እነዚህ ሁሉ የ100 ቀናት ትሩፋቶች ናቸው። ትሩፋቶቹ እንዲጎለብቱም ተቋማቱ መጠንከር ይኖርባቸዋል።