አንድ ሰው አስቦ አንድ በሬ ስቦ!

ከሦስት አመታት በፊት በሀገሪቱ ሕገ-መንግስት የሰፈረውን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲሁም አመራሩ የፈጠራቸውን የተለያዩ ችግሮች ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የሕዝብ ተቃውሞ ተቀስቅሶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡  ኢህአዴግ የተረከበውን ሀገራዊ ኃላፊነትና አደራ ለመወጣትም ለ17 ቀናት ቁጭ ብሎ በመምከር የነበሩበትን ስህተቶች አምኖ ሕዝቡን ይቅርታ በመጠየቅ ሥር-ነቀል ለውጥ እንደሚያደርግ በገባው ቃል መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጥ የሕዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጠና ምላሽ እየሰጠ በለውጥ ጎዳና ላይ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሀገሪቱ መሪ ሆነው ከተሰየሙበት ቀን ጀምሮ ያስተላለፏቸውን መልዕክቶችና የሠሯቸውን አበይት ሥራዎች አስመልክቶ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ሀገር ያሉ ሚዲያዎች ብዙ ብለዋል፡፡ በዚህ ሦስት ወር የስልጣን ጊዜያቸው ይሆናሉ ተብለው የማይታሰቡ በርካታ ጉዳዮችን ፈጽመዋል፡፡ በዋናነትም የራሳቸውን ካቢኔ በማቋቋምና በከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት የአመራር ቦታላይ በማስቀመጥ ለውጡ እስከ ታችኛው መዋቅር ወርዶ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ሠርተዋል ፡፡

እነዚህ የመንግሥት ተቋማት ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ለውጡን ማዕከል በማድረግ እቅዶቻቸውን ማቀድ እንዳለባቸውና በምክር ቤቱ በተቋቋመው ኮሚቴ በማስገምገም ቆጥረው የተረከቡትን ሥራ በበጀት አመቱ ፍጻሜ ቆጥረው እንዲያስረክቡ የሚያደርግ አሰራራር ተፈጥሯል፡፡ እቅዶቹ እንደከዚህ ቀደሙ ለይስሙላህ ተብለው የሚዘጋጁ ሳይሆን በትክክል መሬት ላይ ማረፍ የሚችሉ መሆናቸውን መተማመን የመጀመሪያው ተግባር እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥም በየወቅቱ ብርቱ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካስቀመጧቸው አዳዲስ አሠራሮች አንዱ ነው፡፡

የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለማረጋገጥም በዋናነት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግና  እያንዳንዱ ዜጋ የተለያዩ ፍላጎቶችን ከማስቀደሙ በፊት ሰፊውን መሬታችንን በማረስ በይበልጥም መስኖን በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ እራስን በምግብ ከመቻል በዘለለ የግብርናው ዘርፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተመክሮበታል፡፡

ለውጡ አብዛኛዎቹን የሀገሪቱን ዜጎች ያነቃቃና ያስደሰተ ሆኖ የሚቀጥለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየፈጸሙ እንዳሉት ዘርፈ ብዙ ተግባር በተዋረድ ያሉ የመንግሥት ተቋማትም በዚያው ልክ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ነው፡፡ የክልል ምክርቤቶች ሰሞኑን ባካሄዷቸው ስብሰባዎች የመንግሥትን አፈጻጸም ጠንካራና ደካማ ጎኖች ለይተዋል፡፡ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል እንዲያመቻቸውም ከአዳዲስ አስተሳብ ጋር መጓዝ የሚችሉ አዳዲስ አመራሮችን በመሾም ወደሥራ ገብተዋል፡፡

ክልሎች የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ በሕዝቦች መካከል ፍቅር፣ አብሮነት፣ መከባበርና የጋራ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር እራሳቸውን ከለውጡ አቅጣጫ አንጻር መቃኘት ጀምረዋል፡፡ የዜጎች ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት መከበር እንዳለበትና ሕገ-መንግስቱም በአግባቡ መተግበር እንዳለበት መክረዋል፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ100 ቀናት ውስጥ ያከናወኗቸውን ዘርፈ ብዙ ስኬቶች ተመልክተን የመንግሥት ተቋማትስ ለውጡን እንዴት እያስኬዱት ነው ? በእሳቸው ፍጥነት ልክ እየተጓዙ ነው? በዚህ ሦስት ወር ውስጥ የትኞቹ የመንግሥት ተቋማት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ ለማስፈጸም በተነቃቃው የለውጥ ሂደት ውስጥ እያለፉ ናቸው? የሚል ጥያቄ ብናነሳ አብዛኞቹ ተቋማት በውስጥ እየሰሩ ያሉትን ሥራ ጠለቅ ብለን ባናውቅም ለውጡን እያፋፋሙ ስለሚገኙ ጥቂት ተቋማት ያየነውን እና የሰማነውን ወደ አንባቢያን በማድረስ እንዲበረታቱ ማድረጉ አገራዊ ግዴታን ከመወጣት አንጻር ግድ ይላል፡፡

ለውጡን ተቀብለው የነበረባቸውን ተለምዷዊና ወገንተኛ አሰራር በማስወገድ በአዲሱ ባቡር ላይ ከተሳፈሩት ተቋማት መካካል የመንግስት ሚዲያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከአሁን በፊት የሚዲያ ሰዎች በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 29 ንዑስ አንቀጽ 2 ማንኛውም ሰው በቃልም ይሁን በጽሑፍ ወይም በህትመት ማንኛውንም መረጃና  ሀሳብ የማሰራጨት መብት እንዳለው የሚደነግገውን ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሰርተው ነበር ማለት አንችልም፡፡ በተለይም የመንግስት ሚዲዎች ከሚከተሉት ልማታዊ ጋዜጠኝነት አንጻር  የመንግስትን ድክመቶችና የሚታዩ ብሉሹ አሰራሮችን እንዲታረሙ ከመጠቆም ይልቅ የመንግሥትን የልማት ስኬቶች ብቻ በማውራት የተጠመዱ ነበሩ፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚዲያ በአንድ ሀገር ውድቀት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚፈጥርና በዕድገትም ላይ ምን ያህል አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት አበክረው ተናግረዋል፡፡ ሚዲያ ገለልተኛ ሆኖ በመንግስትና በሕዝብ መካከል ያሉ ክፍተቶች እንዲሞሉ አቅጣጫዎችን የሚያሳይ፣ የሚያሳውቅ፣ የሚያስተምር፣ የሚጠቁምና መፍትሄ የሚያፈላልግ መሆን እንደሚገባው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተገለጸ በኋላ ሚዲያዎቻችን ከተለመደው ወጣባለ መልክ የመንግስትን ጉዳይ ደፍሮ የመተቸት አቅም አግኝተው ብቅ ብለዋል፡፡ በዚህም ከምንግዜውም በላይ ተደማጭነትን እና ተአማኒነትን እያገኙ መጥተዋል፡፡ ሚዲያዎች የጠቅላይ ሚኒስተሩን ሀሳብ በማስተጋበትና እራሳቸውም የለውጡ ፋና ወጊ በመሆን  በተጀመረው የለውጥ ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን  ድርሻ እየተወጡ ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሆነዋል፡፡ በዚህም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወራት በፊት  ከመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት መከላከያ ሰራዊት ከየትኛውም የሀገሪቱ ፖለቲካ አካል ገለልተኛ መሆን እንደሚገባውና ተልዕኮው በሀገር ደህንነት ላይ ያነጣጠረ መሆን እንደሚገባው እንዲሁም መከላከያ ከመጣው ጋር የሚመጣና ከሄደው ጋር የሚሄድ ሳይሆን ሕገ-መንግስታዊ ግዴታውን በማክበር ተልዕኮውን የሚፈጽም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴሩ ኢታማጆር ሹም ጀነራል ሰአረ መኮንን ሰሞኑን ለሰራዊቱ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ብሔርተኝነትና ዘረኝነትን ማንሳት እንደማያስፈልግና ለሕ-መንግሥቱ ተገዢ መሆን እንደሚገባ በመግለጽ የጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይን ሀሳብ አጠናክረዋል፡፡ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ሉዓላዊነትና  የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠሩና የተጀመረውም ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ እንዳለ ለመታዘብ ችለናል፡፡

በተደረገው ለውጥ መነቃቃት የታየባቸውና ሥራቸውን በአዲስ መንፈስ ለማከናወን  ጥርጊያዎችን ካመቻቹት የመንግሥት ተቋማት ወስጥ ከላይ ያሉትን ለአብነት ጠቀስን እንጂ እንደ ፍትህ ሚኒስቴርና ፌደራል ፖሊስ የመሳሰሉትም ሕገ-መንግሥታዊ ሂደትን ባልጠበቀ መንገድ ሲከናወኑ የነበሩ ድርጊቶችን በማረም በተለያየ የፖለቲካ ጉዳይ ታሥረው የነበሩ ዜጎች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲወጡ በማድረግ አዲሱን አስተታሰሰብ በመተግበር እምርታ ያሳዩ የመንግሥት ተቋማት ናቸው፡፡

ሰሞኑን ከ3000 በላይ የሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህራን በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳይና በትምህርት ጥራት ዙሪያ መክረዋል፡፡ በውይይቱም ከተነሱት ጉዳዮች የመማር ማስተማሩ ሂደት ከፖለቲካ ተጸዕኖ ነጻ እንዲሆንና ከዚህ በፊት ያለአግባብ ከሥራቸው የተባረሩ መምህራን ወደ ሥራቸው መመለስ እንደሚችሉ  ጠቅላይ ሚኒስተርሩ አብስረዋል፡፡ በዚህም  ትምህርት ሚኒስቴር ለውጡን ከመማር ማስተማር ሂደት አንጻር እየቃኘ ማስተካከያ በማድረግ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑኑ መገንዘብ ችለናል፡፡

በሀገሪቱ የተከሰተውን የዶላር ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕብረተሰቡ ያስተላለፉትን መልዕክት ተከትሎ መሰንበቻውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአማካይ በቀን ከ4 እስከ 6 ሚሊየን ዶላር እየመነዘረ መገኘቱም የለውጡ መነቃቃት የፈጠረው አንዱ የባንኮቹ ስኬት እንደሆነ እንረዳለን ፡፡

እንግዲህ ከላይ ለማየት እንደሞከርነው በለውጡ ሂደት ውስጥ እነዚህ ተቋማት እያበረከቱ ያለው አስተዋጽዖ ተጠቃሽ ቢሆንም ሌሎችም ሥራቸውን እንዲህ በይፋ ያላየንላቸውና ለውጡን ለመተግበር ተግተው የሚሠሩ እንዳሉ እንገምታለን፡፡ በአንጻሩ ደግሞ እራሳቸውን ከለውጡ ጋር ያላገናኙና ቀደምሲል ከነበረው ያረጀ አስተሳሰብ ጋር ተጣብቀው ባሉበት የቆሙ የመንግሥት ተቋማት እንዳሉ ሥራቸው ያሳብቃል፡፡ እናም እነዚህ የመንግሥት ተቋማት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ በመከተል ለውጡን ለማስቀጠል መነቃቃት ይኖርባቸዋላ፡፡ ‹‹ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ›› እንደሚባለው የተሰጣቸውን የስራ ድርሻ በአግባቡ በመወጣት እዚህም እዛም በማለት ያለ እረፍት እየሠሩ ያሉትን መሪ ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡         

የአገሩቱን ሁለንተናዊ ችግር በአንድ ሰው ጫንቃ ላይ ጭኖ ተመልካች መሆን  ‹‹አንድ ሰው አስቦ አንድ በሬ ስቦ ›› እንደሚባለው ሊዘለቅ የማይችል ጉዳይ በመሆኑ የክልልም ይሁን የፌደራል መንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ ዜጎች በተለይም ወጣቶች ከተኛንበት በመንቃት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሰምና ወርቅ ሆነን ለውጡን ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ተሸለ ደረጃ ማሸጋገር ይኖርብናል፡፡