የኢትዮጵያ መደመር በዓለም ሚዲያዎች ዕይታ

ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን የሰላም ጉዞ ተከትሎ የዓለምን ሚዲዎች ዕይታ መሳብ ችላለች፡፡ በሀገርም ውስጥ ሆነ ከሀገር ውጭ ኢትዮጱያ ስለሰላም ያላትን ቁርጠኛ አቋሟን ማንፀባረቋ የዓለምን ህዝብና ሚዲያዎችን በአግራሞት ሲዘግቡት ሰንብተዋል፡፡ ከነበረችበት የእርስ በርስ ግጭትና አለመግባባት ሰላምን በመምረጥ ለህዝቦቿና ለቀጣናው መልካም የሚባል የፍቅርና የሰላም ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡ ባሳለፈናቸው የፖለቲካ አለመግባባት ባስከሰቱት ቀውስ ምክንያት ቀላል የማይባል የሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጎዳትና  የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡  በተጨማሪም  የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ንብረታቸው በመውደሙ ምክንያት በሥራ ተቀጣሪ የነበሩ ሥራ አልባ ሆነዋል ፡፡ እናተርፋለን ሲሉ ከስረዋል፣ ንብረታቸውንም መሰብሰብ ሳይችሉ የእሳት ራት ሁኖ ቀርቷል፡፡

ባለሀብቶች ኢንቨስት ለማድረግ ሰላሟ የተጠበቀና መሥራት የሚችል የሰው ኃይል ይፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያው አላማቸው ትርፋማ መሆን ስለሆነ፡፡ ነገር ግን ይህ ባለመሆኑ ባሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ በደረሰው ቀውስ ብዙ ባለሀብቶች ሲከስሩ ገሚሶች ደግሞ ያተረፉትን ትርፍ ይዘው ወደ እናት ሀገራቸው ተመለሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ ሰውችን ያለ ሥራ እንዲቀሩ አድርጓል፣ ለተከሰተውን ግጭት “በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” ሁኖ አልፏል፡፡

ነገር ግን ከዚህ አስከፊ ግጭት ለመውጣት በታለመ መልኩ የተደረገውን ሪፎርም ተከትሎ ጥሩ ሊባል በሚችል ሁኔታ የውስጥ ችግሮቿን ከመፍታት አልፋ ከጎረቤት ሀገሮች ጋርም ጥሩ የሆነ መግባባት እየፈጠረች ትገኛለች፡፡ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም እንዲሰፍን ቀላል የማይባል አስተዋፅዖ እያደረገች ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ያዩ የተለያዩ ሚዲያዎች ስለመጣው አንፃራዊ የሆነ ሰላም እና ስለኢኮኖሚው መረጋጋት ብዙ ሲሉ ተሰምተዋል፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ለውጭ ባለሀብቶ ምቹ እንደሆነችም ገልጸዋል፤ ይህን የተመለከቱ የሀገርና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጭምር ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያካሄደችው እርቅና ሰላም ከአፍሪካም አልፎ ለዓለም ሀገሮች ምሳሌ ለመሆን የሚያስችላት ነው፡፡ ይህን ለውጥ በማድነቅም እየታየ ያለውን ሰላም ለማስቀጠል ከሀገሪቱ ጎን እንደሚቆም በአደባባይ መስክረዋል፡፡ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ የፍቅርና የሰላምን ለውጥ የፊት ገፅ በማድረግ ሰለ ኢትዮጵያ አዎንታዊ መረጃዎችን ዘግበዋል፡፡

የሀገሪቱን መረጋጋት ተከትሎ፤ብዙ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ይህም የሚያመለክተው ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ያላትን ተሰሚነትና ተቀባይነት የሚያመላክት ነው፡፡ ስለሆነም ሰላም መስፈኑ ለሀገር ዕድገት ወደር የሌለው ሚና ይጫዎታል፡፡ ሀገራችን ሰላም ሆና የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ ከቻለች የሥራ አጥ ቁጥር ይቀንሳል፣ሀገርም ግብር ከፏይዋ ሰለሚበዛ ጥሩ የሆነ የገቢ ምንጭ ለማመንጨት ያስችላታል፡፡

ከብዙ በትንሹ ዋም፣ፐሬንሳ ላቲና፣አልዋስት.ኔት እና ሮይተርስ የተባሉ ድረ ገፆች  ባሳለፍነው ሳምንት ስለ ኢትዮጵያ ብዙ ብለዋል፤የሻርጃ ንግድ ምክር ቤት ልዑካን አዲስ አበባ በገቡበት ጊዜ ዋም የተባለው ሚዲያ እንዲህ ሲል ነበር ስለ ኢትዮጵያ ያስነበበው፤በአረብ ኢምሬትና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ ፣ኢንቨስትመንት እና የማህበራዊ ግንኙነቶች በስፋት አጠናክሮ  መሥራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ በአዲስ አበባ መምከራቸውን ጠቁሟል፡፡ እንዲሁም በተካሄደው ውይይት ላይ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬት የሻርጃ ኮሙኒቲ መካከል ሰፊ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር በሚካሄድበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገው ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ሲል አስነብቧል፡፡

ሐምሌ 4/2010 ዓ.ም የዓለም ሜትሮሎጅ ድርጅት የአፍሪካ አቻ ተቋማትን ለማዘመን  ይረዳው ዘንድ ጽ/ቤቱን በአዲስ አበባ ሊከፍት መሆኑን ተከትሎ ፐሬንሳ ላቲና የተባለው ድረ ገፅ ድርጅቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ጠቁሞ  የአህጉሪቱን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱን በአ∙አ ለመክፈት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ይህም የሀገሮችን የሜትሮሎጅ አገልግሎት፣ ቴክኖሎጂና ክህሎት የማሳደግ ሚና ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም አየር ሁኔታ ላይ ወቅታዊ መረጃዎችን በፍጥነት የማድረስ እና የአገልግሎት ተደራሽነትን ከፍ የማድረግ ጠቀሜታዎች እንደሚኖረው ተገልጧል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በአግባቡ መደገፍ የሚችል አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ የስምምነቱ አካል መሆኑንም አስነብቧል፡፡

የጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይንና የፕሬዚዳንት አብድልፈታ አልሲሲን ግንኙነት አስመለክቶ የአረብ ድረ ገጽ አልዋስት.ኔት እንዳለው የኢትዮጵያና የግብጽ ግንኙነት ታይቶ ወደ ማይታወቅ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር እና በአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካይ አቡበከር ሂፍኒ መግለፃቸውን አስታውቋል፡፡ አምባሳደሩ ጨምረውም እንዳሉት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መግባባትን እና የጋራ ጥቅምን መሠረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ የህዳሴውን ግድብ ጉዳይ በተመለከተ፣በህዳሴው ግድብ ውይይት ተስፋ ሰጭ እና አዎንታዊ ነገሮች እየታዩ መሆናቸውን ጠቁመው በሦስት ሀገራት መሪዎች መካከል ከመተማመን ደረጃ ላይ መደረሱን ለአንባቢዎቹ ይፋ አድርጓል፡፡

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ ኤርትራን መጎብኘታቸውን ተከትሎ ሮይተርስ እንዳስታወቀው ዶላር መር የሆነው የኢትዮጵያ ቦንድ ሽያጭ በእጅጉ መጨመሩን የሚያወሳ ዘገባ አውጥቷል፡፡ ይህ የቦንድ ጭማሪ ካለፉት 10 ሳምንታት ውስጥ ከታዩት የቦንድ ሽያጭ ዋጋ በእጅጉ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጿል፡፡ ቶምሰን ፋውንዴሸን የቦንድ ግብይት ገበያ  ተንተርሶ ይፋ ባደረገው መረጃ የኢትዮጵያ የቦንድ ሽያጭ ዋጋ በ$0.583 ሳንቲም ጭማሬ ማሳየቱን እና ይህም ካለፈው ረቡዕ ወዲህ አንድ የኢትዮጵያ የዶላር ቦንድ ሽያጭ ሦስት ዶላር ጭማሪ እንዳሳየ በፊት ገፁ አስታውቋል፡፡

ጂብራን ቁረይሺ የተባሉ የኬንያ የስታንቢክ ባንክ እና የምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ለሮይተርስ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቦንድ ሽያጭ ዕድገት ያሳየው በሀገሪቱ እየተወሰደ ያለው ፖለቲዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን ተከትሎ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያ ቦንድ ፍላጎትና መተማመን ስላሳደሩ ነው ብለዋል፡፡