ዛሬም ቀዳሚ ነው

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን…አሁን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየጎለበተ የመምጣቱ ሁኔታ እውነታ ነው። እዚህ ላይ "ጎልብቷል" ሲባል ግን አንዳች እንከን የለበትም ማለት አይደለም። ይህንን በተገቢው መንገድ መገንዘብ ይገባል። በዚህ ላይ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር ስኬት የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ ካልታከለበት በመንግሥት ጥረት ብቻ ተግባራዊ ይሆናል ማለት አዳጋች ይሆናል። በማንኛውም ጉዳይ ላይ የህዝብ ተሳትፎ ካልታከለበት ተፈፃሚ መሆን አይቻልም።  

 

በመሆኑም በመንግሥት በኩል መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ እየተሰሩ ያሉና በሂደት የሚከናወኑ በጎ ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው መላው ህዝብ ዛሬም እንደ ትናንቱ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።

 

በተለይም ቁልፍ የዴሞክራሲ ማስፈኛ ተቋማት በሚባሉት እንደ ፍትህ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋማት ዓይነቶችን በአግባቡ በመጠቀምና የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትሎ በማሳወቅ ለመልካም አስተዳደር እመርታ መትጋት ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ሥራ ይሆናል። መንግሥት ምንም እንኳን ይህንን የማስፈፀም ተልዕኮና ግዴታ አለበት።  በተለይ ህገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ብሎም ራሱም ለዴሞክራሲ ሥር መስደድ ካለው ቀናዒ ፍላጎት በመነሳት መልካም አስተዳደር ለማስፈን፣ ፍትህ ለመስጠት፣ የዜጎች አቤቱታ የሚደመጥበት ሥርዓት ለመገንባትና ተገቢው ምላሽ የሚገኝበት ተቋማት ማቋቋሙ በራሱ በጎ ርምጃ ነው።

 

ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እነዚህ አካላት እንዲቋቋሙ በአዋጅ ከማፅደቅ ጀምሮ ተግባራቸውንም የመልካም አስተዳደር እመርታን በሚያረጋግጥ አኳኋን እንዲፈፅሙ እስከ ማድረግ ድረስ አመቺ የሆኑ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።

 

እነዚህ ገለልተኛ አካላት ህዝቡ በህገ መንግሥቱ ላይ የተደነገጉትን መሠረታዊ መብቶች ተግባራዊ መሆናቸውን ያረጋግጥበታል። የመልካም አስተዳደር ሥራ ሂደት ነው። ምሉዕ ሊሆን በርካታ ጊዜያትን ይጠይቃል። እንዲህም ሆኖ ግን መልካም አስተተዳደር ትግበራ አፈጻፀም የአቅም ውስንነትን ተሻግሮ መሻሻል እየታየበት ነው። ይህ ሲባል ግን መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ ችግር የለበትም ማለት አይደለም። ሆኖም በአፋጣኝ ሊፈቱ የሚገቡ ችግሮች ጊዜ ሳይወስዱ መፍትሄ ሊያገኙ ግድ ይሆናል። ሌሎችም እንደየክብደታቸው እየታዩ በሂደት ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል።   

 

ክንዋኔዎች በአንክሮና በሰከነ አዕምሮ ከታዩ መንግሥት ለዴሞክራሲው ግንባታ እውን መሆንና ላሳየው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ምስጋና ይቸረዋል። በስሜት ብቻ እየተገፋፉ እየተከናወነ ያለውን ጥረት አለመቀበልና ማጣጣል በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት አይኖረውም። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ገንቢም ዴሞክራሲያዊም አይደለም። ይህ እሳቤ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ጠቃሚም አይሆንም።

  

እዚህ ላይ መልካም አስተዳደር የሚታሰበው ሥርዓቱ ተግባሩን ለማከናወን ካለው በጎ ምልከታ አኳያ መሆኑ እርግጥ ነው። ታዲያ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሥርዓትም መልካም አስተዳደርን በሂደት ለመፈፀም ቁርጠኝነት ያለው ብቻ ሳይሆን፤ አሁን…አሁን መልካምና የተመቻቸ ምህዳር ጭምር የነገሰበት ነው። ለምን ቢባል ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሥልጣን የህዝብና የህዝብ ብቻ መሆኑን በግልፅ በማስቀመጡ ጭምር ነው። ሥልጣን የተገልጋዩ ህዝብ መሆኑ ደግሞ ለመልካም አስተዳደር እመርታ የራሱ ጠቀሜታዎች አሉት። ይህን ጉዳይ መካድ ደግሞ አስቸጋሪ ነው።  

 

በግልጽ መጥቀስ እንደሚቻለው መልካም አስተዳደር የተግባር እንጂ የንድፈ ሐሳብ ጉዳይ አይደለም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው የመልካም አስተዳደር ተግባር ከዜጎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ፤ በአተገባበሩ ላይ የሥልጣኑ ባለቤት የሆነው ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆን አለበት። ህዝቡ በህገ መንግሥቱ የተጎናፀፈውን ሥልጣን በአግባቡ እንዲጠቀምበት ዕድል ይፈጥርለታልና ነው።

 

እነዚህ አካላት ለመልካም አስተዳደር አተገባበር ያላቸው የማይተካ ሚና ስለሚታወቅ እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲያዊ አገር በምክር ቤቶች የሚሾሙ ወይም ለምክር ቤቶቹ ተጠሪ ይሆናሉ። ሆኖም ግን የየራሳቸው ነፃነት ያላቸው አካላት መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም። እነዚህ አካላት ህዝቡና የህዝቡ ተወካዮች በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ መክረው ያፀደቋቸውን ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ህጎች በተሟላ ሁኔታ የሚያስፈፅሙ እንዲሁም ለሁሉም ዜጋ ያለ አድልኦ ፈጣን አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ማወቅ ተገቢ ይሆናል። እነዚህ አካላት ይህን በማድረጋቸው የህዝቡ ሉዓላዊነት መሣሪያዎች፣ አገልጋዮችና የመልካም አስተዳደር ፈፃሚዎች መሆናቸው አይቀሬ ይሆናል።

 

የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓቱ የተጠቃሚው መብትና ጥቅም እንዳይሸራረፍ እንዲሁም ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። ይህ ተግባርም መንግሥት በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን መተኪያ የሌለው ድርጊት መሆኑን ያምንበታል። በቁርጠኝነት ለመተግበርም በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ከዳኝነት ሥርዓቱ ጋር በተያያዘም ህዝቡ በተወካዮቹ አማካይነት ያፀደቀውን ህገ መንግሥትና ይወክሉኛል ባላቸው አካላት በኩል የሚወጡ ህጎችን በትክክል መተርጎሙ በዚህ መሠረት አቅም በፈቀደ መጠን ለባለ ጉዳዩ ፈጣንና ትክክለኛ ፍትህ ያለ አንዳች አድልኦ መስጠቱ ላይም በትኩረት ሊሰራበት ይገባል።