ወጣትነት የመጨረሻው የህይወት የጡዘት ነጥብ

አንዱ በልጅነትና በጉልምስና መካከል ያለ ጊዜ ይለዋል፤ ሌላው ሌላ፡፡ ብቻ የሚሰጠው ትርጓሜ እንደየተርጓሚው፣ እንደየ በያኒው ይለያያል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የመጨረሻው የህይወት የጡዘት ነጥብ ነው፡፡ በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራ ለሚቀጥለው የህይወት ምእራፍ ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣቶች በነፃ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በሰፊው ሲሳተፉ ይስተዋላሉ፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በተለይ የወጣቶች የበጎ አድራጎት ሥራዎች እድሜ ጠገብ በሚባል ደረጃ ላይ በመሆናቸውና በማህበረሰቡም እየተለመዱ በመምጣታቸው ዛሬ ስለ አስፈላጊነታቸው የምናወራበት ጊዜ ላይ አይደለንም፡፡  ይልቁንም አንዳችን ለሌላችን እዚህ ቦታ ከነዚህ ተግባራት ይልቅ አነኝህ ቢቀድሙ ወይም ስለአሰራራችን ቅደም ተከተል፣ ስለአተገባበራችን ሂደት እናወራለን እንጂ፡፡ እንደዚህ ሲባል በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የሚሰሩ የወጣቶች የበጎ አድራጎት ሥራዎች ውጤታማ ናቸው ለማለት ታስቦ አይደለም፡፡ ብዙ ውስንነት የሚታይባቸውና አዚም የተጫናቸው የሚመስሉ የበጎ አድራጎት ተግባራትም እዚህም እዛም መታየታቸው አልቀረም፡፡

የወጣቶች በጎ አድራጎት ሥራዎች እንደዬ አካባቢው ሁኔታ የተቃኙ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጋር በፍቅር በአበድንበት በዚህ ወቅት በክልሎች ወሰኖች ላይ የሚታዩ አንዳንድ ግጭቶችና አለመግባባቶች በወጣቶች ሊፈቱ የሚችሉና እንዳይከሰቱ ሆነው ሊመክኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ በተለይም ጊዜው ተማሪዎች ከየዩንቨርሲቲው ለእረፍት ወደየአካባቢያቸው የሚመለሱበት ወቅት በመሆኑ የጉራጌው ዘርማ፣ የኦሮሞው ቄሮ፣ የአማራው ፋኖ ወዘተ ተጨማሪ ጉልበት የሚያገኙበት ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ ይህን ኃይል በአግባቡ ተጠቅሞ ከብክነትና ከጥላቻ በራቀ መልኩ ነገሮችን ማስኬድ ከተቻለ ጥቅሙ የትዬለሌ ነው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንደተገለፀው በክልሎች መካከል የአስተዳደር ወሰን እንጂ ድንበር የለም፡፡ በነዚህ ወሰኖችም መካከል ቢሆንም ግን የሚንፀባረቁ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን አስቀድሞ ሊያመክኑ የሚችሉ ሥራዎች በወጣቶች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በነዚህ ሥራዎች በወጣቶች እየተካሄዱ ያሉ የእርስ በርስ ጉብኝትና የባህል ተውውቅ መካሄዱ ሊቀጥል የሚገባውና ግጭትን ሳይፈጠር ማምከኛ አይነተኛ ዘዴ ነው፡፡ ወጣቶችም ለሰላም ዘብ መቆማቸውን አሳይተዋል፡፡

በጎነት ለራስ ነው፤ በጎ ማድረግም እንዲሁ፡፡ ርካሽ የሚባል የበጎ አድራጎት ሥራ የለም፡፡ ሁሉም አቅሙ የቻለውን ካደረገ ለአድራጊው ከሚሰጠው የማገልገል ስሜት በተጨማሪ አገር ትጠቀማለች፡፡ ወጣቶች በተደራጀ መልኩና በተናጠል በልዩ ልዩ ሁነቶች ላይ ደማቸውን ሲለግሱ በሚዲያ መመልከት የተለመደ ተግባር ሆኗል፡፡ ይህ ደም ልገሳም የሰው ህይወትን ለማዳን የተደረገ በመሆኑ አኩሪና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው፡፡ ህይወት በወጣትነት እድሜ ውስጥ የገራናትን ያህል እንደምንጠቀምባት ወይም እንደምንጎዳባት ብዙዎችን የሚያስማማ ጉዳይ ነው፡፡ በወጣትነት ማገልገል ክብር እንደሆነ ተገርታ ያደገች ማንነት በመጭው ጊዜም በተመሳሳይ ሁኔታ አምናና ተጠምቃ ትኖራለች፡፡ ያደገች ሀገር ለመፍጠርም የሚረዳው የህው ስሜት ነው፡፡

ወጣቶች በተለያዩ አካባቢዎች አቅመ ደካሞችን በመደገፍ፣ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጽዳት፣ በትራፊክ ደህንነት እና በመሳሰሉት የነፃ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ወጣትነት የመጨረሻው የህይወት የጡዘት ነጥብ ነው፡፡ የተጠቀምንበትን ያህል ይጠቅመናል፡፡ ሀገርን ስናገለግልበት በተለያ ደግሞ ይህም በነፃ ሲሆን ደግሞ ከክብርም በላይ ነው፡፡