ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህሊና እርካታ እንጂ…

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰው ልጅ ምንም አይነት ክፍያ የማያገኝበት ይበጃል፣ ይሆናል፣ ያስደስታልና የህሊና እርካታ ያስገኛል ብሎ ያለምንም ቀስቃሽና ጎትጓች በእራሱ ተነሳሽነት እሚፈፅመው  ተግባር ነው፡፡ ይህ ተግባር ማንኛውንም ዜጋ የሚያሳትፍ ቢሆንም በዋናነት ግን ወጣቶችን በስፋት የሚመለከት ተግባር ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ማህበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ ማስቻሉ ደግሞ ሌላኛው ተግባር ነው፡፡ መንግሥታትን ከከፍተኛ የገንዘብ ወጭ በማዳን የአገራትን ኢኮኖሚ ማጎልበትም ከሚሰጠው ፋይዳ ጋር ይደመራል፡፡ በዚህ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ በበርካታ ሚሊዮን ብር ሊሰራ የማይችል ተግባር በየዓመቱ ሲከናወን ይስተዋላል፡፡

ከፌዴራሊዝም ስርዓት ጋር በተያያዘም ሀሳቦችን ከወዲያ ወዲህ በማንሸራሸርና ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠር የሰላም እሴቶችን ያዳብራል፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራ በእርስ በእርስ ትስስር አንድነት እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሚሰጠው ማህበራዊ መስተጋብር የጎላ ነው፡፡ ምሁራን እንደሚናገሩት አሁን በአገራችን እየተፈጠረ ላለው የኢትዮጵያዊነት ስሜት አስተሳሰብም በዚህ ዓይነቱ መንገድ ከመጣ ከበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ከግንዛቤ በማስገባት በተለይ የዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን፣ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ተማሪዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በዚህ መልካም ተግባር እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ እውነታ ነው፡፡ ከዚህ ጥሪ ጋር አያይዘውም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስካሁን ድረስ የሚከናወነው ወጣቶቹ በሚኖርበት አካባቢ የተወሰነ ነው፡፡ ይህ ግን በአንክሮ ተይዞ ወጣቶቹ ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች በመዘዋወር እግረ መንገዳቸውን አንድነታቸውንና የባህል ዕሴቶቻቸውን የሚያጋሩበትና የሚያጎለብቱበት ስለሆነ በዚህ ሁኔታ ቢሳተፉ መልካም ነው በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ በአፅንዖት ታይቶ ቢሰራበት ከዚህ መልካም ተግበር ጎን ለጎን ቋንቋ፣ ባህል፣ የአሰራር ዘይቤ እንዲሁም የተለያዩ የባህል እሴቶችንና አንድነትን የሚያጠናከር አንዱ መንገድ ስለሆነ ሁሉንም የሚያስማማ ጉዳይ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ይህ እሳቤ ዕውን እንዲሆን ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራን በባለቤትነት የሚመራው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በትኩት ሊሰራበት ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ወጣት የዩኒቨርሲቲ፣ የከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ያሳተፈ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ እንደተጀመረ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር በህግና ደንብ የሚመራ አይደለም፡፡ ምክንያቱም “በጎ ፈቃድ” የሚለው ቃል ትርጉሙ እንደሚያመለክተው የሰው ልጆች  ማንም ሳያስገድዳቸውና ሳያነሳሳቸው በራሳቸው ህሊና ቀስቃሽነት ከውስጣቸው በሚመነጭ መልካም ስሜት ተነሳስተው ለማህበረሱቡ የሚጠቅሙ አገልግሎቶችን የሚሰሩበት ተግባር፣ እንዲሁም በጊዜና በሁኔታዎች የማይገደብ አገልግሎት መሆኑ ከሌሎች አገልግሎቶች በዓይቱ ልዩ ያደርገዋል፡፡

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር የሚሰማሩ ወጣቶች አገልግሎት የሚሰጡትን ማህበረሰብ ባህል፣ ወግና ሌሎች እሴቶችን ማክበር ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ሁኔታ ደግሞ ሁሉም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ወጣቶች ከፌደራል እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት በባለሙያዎች የታገዘ የግንዛቤ ፈጠራ መድረክ በማዘጋጅት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህ ጊዜም በማህበረሰቡ ዘንድ አሉታዊ ከሆኑ ድርጊቶች ታቅበው ቀና የሆነውን ተግባር ያከናውናሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ራሱን የቻለ መመሪያና መተዳደሪያ ደንብ ወጥቶለታል፡፡ ይህ ሲባል ግን የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን የሚገድብ አንዳቺም ነገር የለም ተብሏል፡፡ አገልግሎቱ እየተከናወነ ያለው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ጨምሮ የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ተማሪዎችን ወደ አገልግሎቱ በማሰማራት ነው፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በባህሪው ህዝብን ከህዝብ ጋር በጥብቅ የሚያቆራኝ እና የሚያስተሳስር ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም በመማር ማስተማር፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ከተማ ግብርና፣ በደም እጦት ለሚሞቱ ለሚሰቃዩና  ህፃናትና ወላድ እናቶችን ለመታደግ የደም ልገሳ ስለሚከናወንበት ነው፡፡ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንደሚባው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች የአቅመ ደካሞችን ቤት በመስራትና በመጠገን ለብርድ፣ ለዝናብ፣ ለአውሬ ለመሳሰሉት አደጋዎች እንዳይጋለጡ በማድረግ በስጋት ውስጥ ለሚኖሩት እፎይታን በመስጠት ድንቅ ተግባር ያከናውናሉ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ወጣቶቹ “አገሬ ለእኔ ምን ሰራችልኝ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን ሰራሁላት” የሚለውን መርህ መፈክር በማድረግ ለአገራቸው ያላቸውን አገራዊ ፍቅር ሲገልፁ ይስተዋላሉ፡፡ የዚህ የመልካም ተግባር ባለቤት የሆኑት ወጣቶች የሚያከናውኑት ማህበረሰብ ተኮር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው፡፡ ስለሆነም ለጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካሞችና ለአካል ጉዳተኞች አቅማቸው በፈቀደ መጠን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስልቶችን በመጠቀም እንደ ልብስ፣ ምግብና መሰል መሰረታዊ ፍላጎቶችን ከማሟላት ጀምሮ ሌሎች ድጋፎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በሌላ መልኩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከመስጠታቸው በተጨማሪ አሁን በአገራችን ላይ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ ወጣቱ ግንባር ቀደም ተዋናኝ በመሆን ሚናውን መጫወት ይኖርበታል፡፡ ከነዚህ ሚናዎች መካከል በዋናነት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተጓዳኝ በማህበራዊ ሚዲያ ድህረ ገፆች አማካኝነት ሰላም ጠፍቶ ግጭት፣ ልማት ጠፍቶ ጥፋት፣ እድገት ሳይሆን ውድቀት እንዲነግስ ለማድረግ ብሄርን ከብሄር፣ ሐይማኖትን ከሐይማኖት በማጋጨት ዕደገቱን ወደ ኋላ ለመቀልበስ የሚጥሩ ኃይሎችን ሀይ ልንላቸው ይገባል፡፡ ይህን ተግባር ማከናወን የሚቻለው ደገሞ እኩይ ተግባሩን ተቀብሎ ለማራገብ ከመሞከር ይልቅ ትክክለኛውን አገራዊ የፍቅር መስመር እንዲይዙ ሰህተታቸውን ነቅሶ በማውጣት ማረም ስንችል ነው፡፡ ስለሆነም ከግጭት፣ ከትርምስ ኪሳራ እንጂ ትርፍ አንደሌለው በአንክሮ መምከር አና ማስተካከል እንዲሁም በመረጃዎቹ ዙሪያ እውነተኛውን ነገር በማውጣት ማጋለጥ ከወጣቱ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡