የኢትዮ- ኤርትራ የአንድነት ምሰሶዎች

ጊዜው ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ሁለት ወንድማማቾች የደም አፋሳሽ መሣሪያቸውን መዝዘው እጃቸው ከምላጩ የማይፋታበት ወንድም በወንድሙ ላይ የጥይት ባሩድና የመትረየስ አረር ያርከፈከፈበት ያ የሰቀቀን ወቅት፤ ወደኋላ መለስ ተብሎ ሲታወስ በዶክተር አብይ የለውጥና የሰላም አራማጅነት በኢሳያስ አፈወርቂ እርቅ ተቀባይነት ታሪክ ሆኖ ሊወሳ እጁን ሰጥቷል፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ20 ዓመታት ያህል በሞት አልባ ጦርነት ውስጥ ቆይተው በተደረገው የጥላቻን ግንብ የማፍረስና የሰላም ድልድይ የመገንባት ሂደት ጥቁሩ መጋረጃ ተቀዶ ዳግም ላይመለሱ ተደምረዋል፡፡

በቅርቡ ወደ መንበረ ስልጣናቸው በመጡት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ባደረጉት  የሰላም ጥሪ አማካኝነት እንኳን በሁለትዮሽ ውይይት ይቅርና በሌሎች ፈርጣማ የማግባባት ባህልና ተሰጥዖ ባላቸው ሀገራት ጣልቃ ገብነትም የማይሞከር የሚመስለው እርቀ ሰላም ተፈፀመ፡፡ የሰላም ጥሪውንም አቶ ኢሳያስ አፈቀርቂ በአዎንታ ተቀብለው የልዑካን ቡድናቸውን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ለሰላሙ ጥሪ አንድ እርምጃ ወደፊት በመራመድ አዎንታዊ አቀባበላቸውን አስመለከቱ፡፡ ከዚህ ቀጥለውም የአ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አስመራ በመሄድ የሁለቱን አገራት የሰላም ጎህ ቀደዱ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስመራ መገኘትን አስከትለው በርካታ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እጅግ ፈጣንና የማይታመን ልዩ የአንድነት መድረክ ሲሉ አስደመጡ፡፡ በየ ድህረገፆቻቸው የፊት ገፅ ላይም በሰፊው አስነበቡ፡፡ ይህን በጉጉት ሲጠባበቁ የነበሩት መላ የአገረ ኤርትራ ፕሬዝዳንትና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በህዝብ ዝማሬ በመታጅብ አቀባበል አደረጉላቸው፡፡ 

መሪዎቹም የሁለትዮሽ ውይይት በማድረግ የሁለቱን አገራት አንድ ህዝቦች ዳግም አንድ መሆናቸውን አበሰሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሚሊኒየም አዳረሽ በኢትዮ- ኤርትራ የሰላም መድረክ ማበሰሪያ ላይ እንዲህ ሲሉ ተደመጡ፡፡ “ኢትዮጵያና ኤርትራ ሲነጣጠሉ ግንጥል ጌጦች፣ ሲደመሩ ያማሩ ፈርጦች ናቸው፡፡” በማለት የሁለቱን አገራት ውህደት ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ ተናገሩ፡፡ ሁልጊዜም ስለ አንድነትና አገራዊ ፍቅር ደጋግመው የሚያቀነቅኑት ኢትዮጵያዊነትና ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚያሳዩት የሰላምና የመተማመን መርህ ከልቡ ላዳመጣቸው ከምንም በላይ በእጅጉ አገራዊና አህጉራዊ የሰላምና የዲሞክራሲ ሐዋሪያ ቢባሉ የሚያንሳቸው እንጂ የሚበዛ አይመስለኝም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህም አሉ “ከጀብዳዊ ጭካኔ ይልቅ ጀብዳዊ ቅንነት፣ ከጠብ ይልቅ ፍቅር፣ ከቁርሾ ይልቅ ይቅርታ፣ ከመገፋፋት ይልቅ መሳሳብ መምረጥ ዘለቄታ ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ ለማምጣት ሁነኛ መሳሪያ ነው”፡፡ በማለት የሁለቱን ሀገራት የሰላም ብቸኛ አማራጭነት አመላከቱ፡፡ ከዚህ ጋር አያይዘውም የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ያጫወቷቸውን እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፤ “የሰላምና የነፃነት ዋጋ ከጤና ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ኢሳያስ እንደነገራቸው ጤና ሲገኝና በእጃችን ስንይዘው የረከሰ ስናጣው ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ ሰላምም እንዲሁ ሲኖር የረከሰ ሲጠፋ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ ሰላም የነፃነት፣ ነፃነት ደግሞ የብልፅግና እናት ነች፣ ከጤና ውጭ ሃብት ከንቱ ነው፣ ከሰላምና ከነፃነት ውጭ ብልፅግናም ህልም ብቻ ነው” በማለት አንድ የመሆንን፣ የሰላምንና የነፃነትን አስፈላጊነት አስገንዝበዋል፡፡

ሂደቱ የሁለቱንም አገራት ህዝቦች የፍቅር ውህደት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ በመሆኑ ሁለቱንም መሪዎች የዘመኑ የምሥራቅ አፍሪካ የሰላም ፈርጦች ለማለት ያስችላል፡፡ ከኢትዮ-ኤርትራ ህዝቦች ሰማይ የፍቅር ዝናብ ዘነበ፡፡ በመሆኑም ይህ ያልተጠበቀ ሁነት የጥላቻ ግንብ ፈርሶ የፍቅር ድልድይ ተገነባ እንዲባል አስቻለ፡፡ የኤርትራ ወደቦች ለኢትዮጵያ የወደብ አማራጮችን እንደሚያሳድግና ተወዳዳሪነትንም እንደሚፈጥርላት፤ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ለወደብ አገልግሎት ትከፍል እንደነበር ይታወሳል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የወሰደችው ስምምነት ከፍተኛ በሆነ መልኩ የውጭ ምንዛሬን ስለሚቀንስ ለሀገሪቱ ዕድገት አስተዋፅኦ አለው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የትራንስፖርት አገልግሎት የሁለቱ አገራት አየር መንገዶች በረራ እንደሚጀምሩና የኢትዮጵያ አየር መንገድም 20 በመቶ የሚሆነውን የኤርትራ አየር መንገድ ለመግዛት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ከዚህ የትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪም በሁለቱም አገራት በኩል የተዘጉ የየበስ ትራንስፖርት መንገዶች በቅርቡ እንደሚጀምሩ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ወደ ላቀ ምዕራፍ ለመሸጋገር ቆርጠው መነሳታቸውን የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡

የሁለቱን አገራት የሰላም ስምምነት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 465 መንገደኞችን በሐምሌ ወር መግቢያ ላይ ወደ ኤርትራ ታሪካዊ የሆነ በረራ አድርጓል፡፡  በዚህ ታሪካዊ በረራ ላይ የማይታመኑ ህልም መሳይ እውነቶችን ይዞ አውሮፕላኑ ኤርትራ አስመራ አየር መንገድ አረፈ፡፡ ከ20 ዓመት በፊት በሁለት ወንድማማቾች መካከል በነበረ ግጭት ወደ አገራቸው ሳይመለሱ የቀሩ 90 ያህል የአገረ ኤርትራ ህዝቦችን ያካተተ በረራ ነበር፡፡ እናም አስመራ በደረሱበት ወቅት በህይወት እንገናኛለን ብለው ያላሰቡት ሁነት ቤተሰቦቻቸው አበባ ይዘው አገኟቸው፡፡ ክስተቱ በደስታ ሲቃ ውስጥ ገብተው በእንባ እንዲራጩ አደረጋቸው፡፡ ባልና ሚስት፣ እናትና ልጅ ወዳጅ ዘመድ በዚህ ታሪካዊ ጉዞ በመሄድ ቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተው ደስታቸውን በእንባ ሲገልፁ ታይተዋል፡፡

ይህንን ክስተት የተመለከቱ የዓለም መገናኛ ብዙሃን የካሜራ ራዳራቸውን ወደ ኢትዮ-ኤርትራ በማዞር ክስተቱን በግርምት ዘግበውታል፡፡ ይህ ክስተት ግን እጅግ የሚከብድ አባትን ከባለቤቱና ከልጆቹ የነጠለ፣ ልጅን ከእናት የነጠለ በአጠቃላይ የአንድን ሰው ልብ የከፈለ ድርጊት ሆኖ በታሪክ ዳግም ላይመለስ አልፏል፡፡ የሁለቱም አገራት ህዝቦች ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ እንዲሁም ከአስመራ አዲስ አበባ በሁሉም የትራንስፖርት ዓይነቶች በመጓጓዝ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ለመገናኘት ቋምጠዋል፡፡

ይህ በፍቅር ተርቦ የነበረው ህዝብ አሁን ላይ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማድረግ እንዳለባቸውም የአጋራቱ ህዝቦች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ግንኙነቱ እውን እንዲሆን በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ከነዚህ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ውስጥም አንዱ ስፖርዊ ውድድር ማካሄድ ስለሆነ በሚቀጥለው ነሀሴ ወር ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከኤርትራ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ስፖርታዊ ውድድር ጎን ለጎንም ተረስተው የነበሩ ባህሎችና የጋራ የሆኑ የሰላምና የአንድነት ዕሴቶችን ዳግም ማደስና በትውልድ ቅብብሎሽ ዘለቄታ እንዲኖራቸው ማድረግ  ነው፡፡

በዚህ የፍቅር ድልድይ ሁለቱ አገራት የጋራ ሃብት በሚባሉት ጉዳዮች ያለምንም ማመንታት በጋራ እንደሚጠቀሙ መስማማታቸውም ከሀገራዊ ጥቅም ባሻገርም በአገራቱ አዋሳኝ የሚኖሩ የአፋርና የትግራይ ህዝቦች ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ የአገራቱ ስምምነት ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና መረጋጋት ወሳኝ ሚና ከመጫወቱም ባሻገር ለአፍሪካ ብሎም ለአውሮፓ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ የአገራቱ የመደመር እሳቤ ዓለምን አጀብ አሰኝቷል፡፡ ይህም የበለጠ ቀጠናዊ ትስስሩን እንዲጠብቅ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

የሁለቱም አገራት ውህደት ያለምንም ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት እርስ በእረሳቸው መስማማታቸው ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ የሚያደርግና በዓለም አቀፍ ደረጃም ከአልጀዝራ እስከ ቢቢሲ፣ ከቢቢሲ እስከ ሲጂቲኤን፣ ከሲጅቲኤን እስከ ሲኤንኤን ወዘተ. የመሳሰሉ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች እየተቀባበሉ እንዲዘምሩለት ያሰገደደ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የታወቁ የፖለቲካ ምሁራን ከአፈሪካ ጀምሮ የመላ ዓለም ፖለቲከኞች የሁለቱን አገራት የመደመር ክስተት አግራሞተን በሚፈጥር መልኩ ትንታኔ ሰጥተውበታል፡፡ ትንተናቸውም አወንታዊ ነበር፡፡ አገራቱ የሁለት አገራት አንድ ህዝቦች የማይነጣጠሉ፣ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች እንደመሆናቸው መጠን የሚጠቀሙበትና ትርፍ የሚያገኙበት እንጂ አንዳችም ጉዳት እንደሌለው ሰፊ ትንታኔ ሲሰጡ ታይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ መጠቀሟ  በጅቡቲ በኩል የነበረውን የአንድ አይን እንቀስቃሴ ወደ ሁለት አይን የለወጠ በመሆኑ ተስፋ አሰንቋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የወጭና የገቢ ምርቷን እመታስገባውና እምትልከው በዚህ የጅቡቲ ወደብ አንድ ለእናቱ በተባለው መስመር ነበር፡፡