ብርን በጆንያ ለማሸሽ መሞከር ውርደት እንጂ…

አንዲት አገር አድጋለች ማለት የምንችለው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ምህዳሮች ሁሉ በከፍተኛ ሁኔታ ማደግ ስትችል ነው። ለዛ ደግሞ አገራችን ተሳክቶላታል ማለት አንችልም። ምክንያቱም በአገራችን እሰካሁን ባሳለፍናቸው የመንግስት ስርአቶች ዜጎች በቂ በሆነ ኢኮኖሚ እየኖሩ ነው  ብለን መናገር አንችልም። ይህ የሆነበት ምክንያት ተመጣጣኝ የሆነ የኢኮኖሚ ሁኔታ ስላልነበረን ነው። አገራችን በአሁኑ ሰአት ኢኮኖሚዋን ለማሳደግና እድገቷን ለማስቀጠል ደፋ ቀና በማለት ላይ ትገኛለች። ይህን ደግሞ ማፋጠን የሁሉም ህብረተሰብ ግዴታ ነው።

ጠቅላ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ዕለት አንስቶ በአገራችን የሚነፍሰው ንፋስ የለውጥ፣ የይቅርታና የፍቅር ነው። ይህ ደግሞ በሁሉም ህዝብ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ  ተቀባይነትን አግኝቷል። ይህ በዚህ እንዳለ  ይህ በአገራችን  የተጀመረው መልካም የለውጥ ጅማሮ ያላስደሰታቸው አንዳንድ አካለት ለውጡን ለማደናቀፍ በመትጋት ላይ ይገኛሉ። በተለይ ደግሞ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተመለከተ እንዲያሽቆለቁል የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ለአብነት ያክል በህዝብና በመንግስት መካከል ቅሬታን ለመፍጠር አርቲፊሻል የገበያ ስርአትን ለመፍጠር ጥረት በማድረግ የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረጋቸው ይታወቃል። በተለይ ደግሞ በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይ ሆን ብለው እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ ሸቀጦችን በመሰወር ህዝብ በመንግስት ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት ለማድረግ ብዙ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አስተውለናል። ከዚህ የከፋው ነገር ግን የዶላር ምንዛሬ ዋጋ መናር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህብረተሰቡ በሰጡት መግለጫ በአገራችን የዶላር ክምችት በመፈጠሩና በጥቁር ገበያ ላይ ያለው የውጪ ምንዛሬ ዋጋ  በከፍተኛ ሁኔታ በመናሩ የተነሳ በብዙ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉን አስታውቀዋል።

የዶላር ምንዛሬ ዋጋ መጨመሩና መቀነሱ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው አንድምታ በመገንዘብ ህብረተሰቡ አሁን ላይ ዶላሩን በጥቁር ገበያ ከመመንዘርና ከመሸሸግ አውጥቶ ህጋዊ በሆነ መንገድ  በባንኮች በመመንዘር  አገሩን በመጥቀም ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ባይሆንኖሮ ግን በአገራችን የተጀመረውን ለውጥ ከማስቀጠል ይልቅ ማበላሸት ይሆናል፤ ምክነያቱም ይህ ራሱ አንዱ የለውጡ አካል ስለሆነ ነው የዛኔ ነው አገራችን አድጋለች ህዝቧንም በበቂ ኢኮኖሚ ማኖር ችላለች ማለት የምንችለው።

ለአብነት ያክል ነጋዴው በከፍተኛ  ምንዛሬ በዶላር ገዝቶ የሚመጣው ሸቀጥ በአገር ውስጥ ገበያ ሲሸጥ ዋጋው ላይ የሚፈጥረውን ጫና መገንዘብ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ በማደግ ላይ ባለች  አገር  ለሚኖሩ ህዝቦች መልካም አይሆንም የአገርንም ኢኮኖሚ መጉዳትም ነው። ሌላው ህብረተሰቡ ሊያስተውለው የሚገባው ነገር በአገራችን የታየውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጣር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሁሉም ህብረተሰብ ግዴታ በመሆኑ ይህ ተግባር ለመንግስት ብቻ የሚተው ጉዳይ ስላልሆነ ሁሉም ህብረተሰብ ችግሩን ለዘለቄታ ለመፍታት ዶላሮችን ህጋዊ በሆነ መንገድና መንግስት በሚያውቀው መንገድ ወደ ባንክ በመሄድ መመንዘርና የሚጠበቅበትን ሀላፊነት በመወጣት የአገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲረጋጋ ከማድረግ አኳያ ከመንግስት ጋር መስራት ይገባል።

አንዳንድ አካለት ይህን  ህጋዊ አካሄድ ከመደገፍ ይልቅ ለብዙ ዘመናት የሸሸጉትን የዶላር ክምችት በማሸሽ ላይ እንዳሉ ባሳለፍናቸው ሁለት ሳምንታት ውስጥ በህገወጥ መንገድ ከአገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የዶላሮች እንዳሉ እያስተዋልን ያለ ተግባር ነው። ይህ መቼም የሚደገፍ ተግባር አይደለም ልክ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንደተባለው የአገርን ንብረት በመዝረፍ ለማሸሽ መሞከር ከአንድ አገር ወዳድ የሚጠበቅ ተግባር አይደለም።

አሁን ላይ ለማስተዋል እንደቻልነው በዶላር ምንዛሬ ላይ በመጣው ለውጥ ሣቢያ ብዙዎች በህጋዊ መንገድ ወደ ባንክ በመሄድ እየመነዘሩ ይገኛሉ። ይህ መልካምና ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው። ለአገራችንም የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦም አለው።በተጨማሪም በአገራችን እያየን ያለነውን የኑሮ ውድነት ለመቆጣጠር መንግስት ከወሰደው እርምጃ ውስጥ ዶላርን በህጋዊ መንገድ በባንኮች መመንዘሩ አንዱ ነው።

በመጨረሻም አገራችን በኢኮኖሚ አድጋና በልፅጋ እንድትገኝ ሁላችንም የበኩላችንን መወጣት አለብን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ላይ በተለያዩ አገራት ያሉ ዲያስፖራዎች ለአገራቸው የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለባቸው በማለት በቀን አንድ ዶላር ለአገራቸው በማበርከት አገሪቱ የጀመረችውን የለውጥ ግስጋሴ ማስቀጠል ይገባቸዋል በማለት አሳስበዋል። ዲያስፖራውም ለዚህ መልካም ተግባር ኮሚቴዎችን በማዋቀር መልካም ምላሽን በመስጠት ላይ ይገኛል።