“ከአንድ ብርቱ…”

ባለፉት ጊዜያት በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴዎች በሀገርና በህዝቡ ላይ ሲያደርሱት የነበረውን አደጋ ግልፅ ነው። አደጋው የሰዎች ህይወትን ቀጥፏል። አካል አጉድሏል። ንብረት አውድሟል። ይህ አደጋ በመንግስትና በህብረተሰቡ የላቀ ርብርብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊወገድ ችሏል።

በአሁኑ ወቅትም ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው። የግጭት አደጋዎችን አሁንም በዘላቂነት ለመከላከል መንግስትን ጨምሮ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎችን ርብርብን ማድረግ ይኖርባቸዋል። የሰላምን ምንነት የሀገራችን ህዝብ በሚገባ ይገነዘባል።

የሰላም መታጣት ምን ያህል አስከፊ፣ ምን ያህል የሰው ህይወት ቀጣፊ፣ ምን ያህል ንብረት አውዳሚና ትውልድን አሸማቃቂ መሆኑን ለዚህ ህዝብ መንገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ይሆንብኛል። እናም ዛሬ ላይ በሀገራችን ውስጥ አልፎ…አልፎ በሚፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ  ሰላም ሲታወክ ህዝቡ በግንባር ቀደምትነት የሰላሙ ባለቤት ሆኖ ቢቆም እምብዛም የሚደንቅ አይሆንም።

ርግጥ የሀገራችን ህዝብ ሰላም ወዳድ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ ላይ የሰላም መታጣት በሃሳቡም እንኳን ቢሆን እንዲመጣበት መሻት የለበትም። ትናንት ያለፈበት አስከፊ መንገድ ዛሬ ያገኘውን አስተማማኝ ሰላም ገለል አድርጎ ቦታውን እንዲረከበው ቅንጣት ያህል ፍላጎት ያለው አይመስለኝም። የኋሊት የሚሸሸውና ዳግም እንዳይመጣም ዶሴውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዘጋው ለሶስት ዓመታት በስጋት ቆፈን ውስጥ እንዲያልፍ ያደረገው አባጣና ጎርባጣ መንገድ ተመልሶ እንዳይመጣ ለሰላሙ ፀር የሆኑ ሃይሎችን በማውገዝ፣ በማጋለጥና ተገቢውን ትምህርት እንዲወስዱ በማድረግ በባለቤትነት መንፈስ ጠንክሮ ሊንቀሳቀስ ይገባል።

የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ የኢትዮጵያዊነት አንድነቱ ማጠንጠኛ መሆኑን ከመገንዘብ ባሻገር፣ ነፃነትንና ዴሞክራሲን ለማምጣት ያደረገው ትግል ውጤቱም ስለሆነ ጭምር ነው። ሰላም መሆናችን ሁለንተናዊ መሰረትን በመጣል በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ስለሚያደርገውም ጭምር ነው። በተደጋጋሚ ‘ያለ ሰላም ልማት የለም’ የሚባለውም ለዚሁ ይመስለኛል። ሰላሙን የሚጠብቅ ማህበረሰብ በባለሃብቶች አመኔታን በማግኘት ኢንቨስትመንት በሀገሩ እንዲስፋፋ ያደርጋል። ከዚህ ኢንቨስትመንትም ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። እናም ህብረተሰቡ ትናንት አጥቶት የነበረውን ሰላም ዛሬ በአንፃራዊነት አግኝቶታል። ይህ አንፃራዊ ሰላም እንዳይስተጓጎልና ይበልጥ ሰላማችን እንዲያድግ የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል።

እንደሚታወቀው በመንግስት በኩል በጌዴኦና በጉጂ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው አካል ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም የዕለት ምግቦችና ቁሳቁሶች በመንግስት በኩል እየቀረቡ ነው። ወጣቶች፣ ተማሪዎች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እያደረጉ ያሉት ድጋፍም ከፍተኛ ነው። ይሀም መንግስት ራሱም ይሁን ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የተፈጠረውን ችግር በቁጥጥር ስር ለማዋል ያደረጋቸው ጥረቶች ወሳኝ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። 

በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አዋሳኝ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት በህዝቦቹ ባህላዊ የችግር አፈታት ደንብ መሰረት ተፈትቷል። ሁለቱም ህዝቦች ሰላም ፈላጊ በመሆናቸው፤ ወደየተፈናቀሉበት ቦታዎች ተመልሰው ሰላማዊ ህይወታቸውን እንዲመሩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፤ የጌዴኦና የጉጂ አባ ገዳዎች። ይህን መሰሉን የህዝቦች የሰላም መፍቻ መንገድ በመከተል መንግስት ትክክለኛ ተግባር ፈፅሟል። መንገዱ ምናልባት በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ችግሮች ከተፈጠሩ ህዝቡን ባማከለ መልኩ ለመፍታት ተሞክሮ ሊሆን የሚችል ይመስለኛል።  

ርግጥ ኢትዮጵያዊያን ኩሩ የሆኑ ባህል ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ችግሮቻቸውን የሚፈቱባቸው ለዘመናት ሲከተሏቸው የመጡት ባህላዊ መንገዶች አሏቸው። አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና በማህበረሰቡ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው ታላላቅ ሰዎች የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። በጌዴኦና በጉጂ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት የተፈታበት መንገድ ይህን እውነታ የሚያመላክት ነው።

ርግጥ በዘመናት አብሮነት ቆይታው ተቻችለው የኖሩ ህዝቦች በምንም ዓይነት ሁኔታ አብሮነታቸው ሊፈታ አይችልም። የዛሬን ሳይሆን የትናንትንና የነገን ህይወታቸውን ይመለከታሉ። እናም ጊዜያዊ ችግር አብሮነትን የማያበላሽ በመሆኑ ለዘላቂ ህይወት በጋራ ተሳስቦ መኖር ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ በህዝቦች መካከል መለያየት የለም። ሊኖርም አይችልም። የተፋለሱና ትክክል ያልሆኑ አስተሳሰቦች ካሉም በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ባህላዊ እሴቶች መሰረት ሊፈቱ የሚችሉ መሆናቸውን በጌዴኦና በጉጂ ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባት የዚህ አባባል ተደማሪ እውነታ ነው።

በየትኛውም ህብረተሰብ ውስጥ በአንዳንድ አጎራባች ህዝቦች መካከል ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ይህ ሃቅ የእኛን ሀገር ጨምሮ በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሊፈጠር የሚችል ነው። እናም ዋናው ጉዳይ ‘ግጭት ለምን ተፈጠረ?’ ሳይሆን የተፈጠረውን ግጭት እንዴት በባህላዊ አሊያም በዘመናዊ የግጭት አፈታት ደንብ መሰረት መፍታት እንደሚቻል ከመገንዘቡ ላይ ነው።

ርግጥ አንዳንዶቹ ግጭቶች ረዥም ዕድሜን ያስቆጠሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ ከልምድ ጉድለት፣ ከመልካም አስተዳደር እጦትና ይህንን ተንተርሰው የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚከጅሉ ጥቂት ሃይሎች የሚያባብሷቸው ወይም የሚቀሰቅሷቸው ናቸው።

እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች በአራት ወራት ውስጥ የተገኘው ለውጥ ጥቅማችንን ነክቶብናል ብለው የሚያስቡና ምንም ዓይነት ተንኮል ከመፈፀም ወደ ኋላ የሚሉ አይደሉም። ስለሆነም ለእነዚህ ሃይሎች የማይሆን ቦታ ባለመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ሰላምን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያዊ የመዳገፍና የመረዳዳት ባህላችን መጠናከር ሊላላ አይገባም። ከጌዴኦና ከጉጂ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎቻችንን በቋሚነት ለማደራጀት የሚደረገው ርብርብ የመንግስት ብቻ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ህብተረሰቡም በተለመደው የመደጋገፍ ባህሉ የበኩሉን እገዛ ማድረግ አለበት። “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ” እንደሚባለው፤ ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ተፈናቃዩቹ ወደ ነበሩበት ቀዬ ሲመለሱ በኢትዮጵያዊ የአንድነት መንፈስ ድጋፉን ማጠናከር ይኖርበታል። ይህ ሲሆንም ኢትዮጵያዊነታችን ይጠናከራል፤ አንድነታችንም ይጎለብታል።