የመደመር እምቢተኞችና እኩይ ተግባራቸው

በኢትዮጵያ  ምድር የይቅርታ፣  የፍቅር፣ የመከባበር፣ የመግባባትና የአንድነት መንፈስ ከተፈጠረ  ከጥቂት ወራት ወዲህ በሀገሪቱ  አንጻራዊ ሰላም እየሰፈነ መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዴግን  መንበረ ስልጣን ከተረከቡ ወዲህ ድርጅቱ ንሰሀ በገባባቸው ስህተቶቹ ላይ ተመስርተው በርካታ ማስተካከያዎችን አድርገዋል። በዚህም አብዛኛው ዜጋ ወደር የለሽ የድጋፍ ሰልፎችን በማድረግ ደስታውን ሲገልጽ ከርሟል። ይሁንና ከስንዴ ውስጥ እንክርዳድ እንደ ማይጠፋ ሁሉ ይህን በኢትዮጵያ ምድር እየፈነጠቀ ያለውን የፍቅር ብርሃን  ለማጨለም የሚሯሯጡ ፀረ-ሰላም  ሀይሎች እንዳሉ ሥራቸው ይናገራል፡፡    

ፍቅር፣ መከባበርና መግባባት እያቀነቀንለት ላለው ብሔራዊ አንድነት መሠረት ናቸው፤ ምናልባትም ሰው በማሕበራዊ መስተጋብር ውስጥ ሊኖሩት ከሚገቡት እሴቶች እነዚህ ዋነኞቹ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍቅርና መደመር በሰው ልጆች ተግባብቶ መኖር ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ  እንዳለቸው አምነው ሕዝባቸውን ወደ አንድ ለማምጣት እንደዋና መሳሪያ ሲጠቀሙባቸው የታየው ፤ በእርግጥም ተሳክቶላቸው በአገሪቱ እየነፈሰ የነበረውን አውሎ ንፋስ በማቀዝቀዝ ጸጥ ወዳለ የሰላም ነፋስ እንዲለወጥ ማድረግ ችለዋል፡፡ ነገር ግን ‹‹የአህያ ሥጋ አልጋ ሲሉት አመድ›› እንዲሉ የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአኩልነትና የአንድነቱ ቋንቋ ያልተመቻቸው ጥቂት ግለኞች የተሰጣቸውን ክብር አመድ ላይ በመጣል ወራዳ ተግባራትን ሲፈጽሙ ይታያል፡፡

እነዚህ ሀይሎች ምንም እንኳን ቁጥራቸው ኢምንት ቢሆንም ኢትዮጵያ እያጣጠመች ያለችውን ይህን የሰላምና የፍቅር አየር ለመበከል ሥራዬ ብለው እያቀዱ  እንደሚንቀሳቀሱ ተመልክተናል፡፡ ሰላሙ እነሱንም የሚጠቅም ሆኖ ሳለ እንደዚህ አይነቱን እኩይ ተግባር እንዴት ይፈጽማሉ የምንል የዋሆች ካለን ነገሮችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ የምናይ ነን ማለት ነው፡፡  እነዚህ ሀይሎች በተደረገው ለውጥ ጥቅማቸው የተነካባቸውና ቀደም ሲል በፈጸሙት ምዝበራና ወንጀል  ተጠያቂ የመሆን ስጋት ያደረባቸው ናቸው፡፡ መገኛቸውም በየትኛውም ክልል ሆኖ  ከትንሿ ቀበሌ እስከ ታላላቅ ፌደራል ተቋማት ባሉት የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ተሰግስገው የሚገኙ ናቸው፡፡  የሀገሪቱ ሰላም ከተረጋገጠ በጥፋታችን እንጠየቃለን የሚል ፍርሀት ያለባቸው በመሆኑ መንግሥት ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ እነርሱ የማዞር ዕድል እንዳያገኝ ጧት ማታ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ አንዳዶቹም በነበራቸው ስልጣን የመጠቀም ዕድላቸው ሲያከትም ‹‹እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል›› የሚል እሳቤ በመያዝ ከብዙኃኑ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም ለውጡን ለማጨናገፍ እዚህም አዛም አሳት በመለኮስ ተግባር ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስልጣነ መንበሩን ከተረከቡ ወዲህ የታየውን ፍሬያማ ለውጥ ለመቀልበስ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞችና በክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ሙከራዎች እንደነበሩ ለመታዘብ ችለናል፡፡ እነዚህ ጸረ- ለውጥ ሀሎች ደከም ያለ ንቃተ ህሊና ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመመልመል፣ በማሰልጠን እና ዳጎስ ያለ ብር ሰጥቶ በማሰማራት የብሄርና የድንበር ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ለውጡ ውጤት እንደሌለው ለማስመሰል ሲሞከሩ ተመልክተናል፡፡ ስልታቸውን በመቀያየርም  በተለያዩ ግዜያት የተለያዩ ግጭቶች እንዲፈጠሩ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አይተናል፡፡  

ለአብነትም ቀደምሲል በምዕራብ ጉጂና በጌዲዮ አዋሳኝ አካባቢዎች ከዛም በደብረ ማርቆስ መሰንበቻውን ደግሞ በባሌ ጎባ ከተማ የነዚህ ጸረ-ለውጦች ሕቡዕ ሴራ ተንጸባርቋል፡፡ በጉጂና ጌዲዮ አካባቢ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መፈናቀልና በጎባ ከተማም ለ11 ሰዎች ሞትና ለበርካቶች መጎዳት ምክንያት መሆናቸውን የለውጡ ፍሬ የሆኑት ሚዲያዎቻችን አስደምጠውናል፡፡  

እነዚህ አካላት ገንዘብ በመስጠት በሚያሰማሯቸው  ጥቂት ግለሰቦች ከሚፈጥሩት ግጭት በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ሀሰተኛ የፌስ ቡክ አካውንቶችን በመክፈት  ከሌሎች ሀገራት ያገኟቸውን የዘረኝነት ማራገቢያ ምስሎችን በፎቶሾፕ በማቀናበርና የዛው ክስተት አካል አስመስሎ በማቅረብ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲነሳሳ ለማድረግ በስፋት እየሠሩ ናቸው፡፡ ለማሳያ ያህል ሰሞኑን በጎባ ከተማ የፈጠሩትን የብሔር ግጭት ለማባባስ ከአመታት በፊት በሴራሊዎን ሀገር የተፈጸመውን ግጭት በምን አይነት መንገድ አቀናብረው እንዳቀረቡት ማየት ችለናል፡፡

እነዚህ ከመሀል አስከ ዳር ባሉ የሀገሪቱ ክፍሎች እሳት እየለኮሱ ኢትዮጵያ ወደ ለየለት ትርምስ ውስጥ እንድትገባ የሚፈልጉ አካላት ለምን እርቅ፣ ፍቅርና ሰላም  ተሰበከ? ለምን ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ መሆን ጀመረ? ለምንስ በሕዝቦች መካካል ብሔራዊ መግባባት ተፈጠረ? በሚል የሀገሪቱን መጻኢ ዕድል ለማጨለም ቁጭ ብለው የሚዶልቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ግለኞች  ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ ያግበሰብሱ ከነበረው ጥቅም ሌላ በታማኝነት ሕዝብን በማገልገል የሚገኘውን ሁሉን አቀፍ ጥቅምና አገራዊ እድገት አያውቁትም፡፡ ግለኝነት ክፉ በሽታ ነው ፤ ሕዝብን እና አገርን ብቻ ሳይሆን ዘመድንም ያስረሳል፡፡ በጥቅም የታወሩ ዓይኖች ፍቅርና ሰላም ምናቸውም አይደል ፤ ሁልጊዜ ጭንቅላታቸው የሚያሰላስለው አብሮ ማደግን ሳይሆን ከሌሎች በልጦ መገኘትን በመሆኑ ባለገንዘብ ወይም ባለንብረት ለመሆን የሚያስችሏቸውን የሌብነት አማራጮች ከማስላት የዘለለ አገርን በማሳደግ ላይ ያለመ የአእምሮ ልህቀት አይኖራቸውም፡፡     

በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉት እነዚህ ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴዎች በሀገርና በሕዝቡ ላይ እያደረሱ ያሉት ጥፋት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ በየግዜው በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የሚጠፋው ክቡር የሰው ሕይወትና የሚወድመው ንብረት በሀገሪቱ እድገት ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ልብ ማለት ያስፈልጋል ፡፡ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ጥቅም ላይ የሚውለው ግዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ በሌሎች ልማቶች ላይ ቢውል ለሕዝባችን እና ለሀገራችን ምን ያህል ጥቅም ሊሰጥ እንደሚችል ሲታሰብ የነዚህን አካላት አፍራሽ እንቅስቃሴ በጽኑ መታገል እንደሚያስፈልግ እንገነዘባለን፡፡           

እነዚህ አካላት ስልታቸው እየተለዋወጠ ጉዳታቸውም እየከፋ መጥቷል፡፡  ከሰሞኑም እንደ ሰኔ አስራ ስድስቱ የቦንብ ጥቃት ሁሉ  በሥመ ጥሩ የሀገር ባለውለታና በልማት አርበኛው  በታላቁ የሕዳሴው ግድብ ሥራ አስኪያጅ ላይ የግድያ ወንጀል ሲፈጸም አይተናል ፡፡ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል የጸረ- ሰላም እንቅስቃሴው መልኩን እየቀያየረ ስለመምጣቱ አመላካች ነው፡፡ ምንም እንኳን የተሳካላቸው ባይሆንም ይህ ሥልት ደግሞ ሀገር ከሚዘምርለት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጀርባ የቆሙትን የኢትዮጵያውያን የቁርጥ ቀን ልጅ በመግደል ሀገሪቱን ድብልቅልቅ ለማድረግ ያለመ ሴራ እንደሆ ይታወቃል። እነዚህ ግለሰቦች የጥቅም ጉዳይ ያሰከራቸው በመሆኑ ነገ ደግሞ ሀገሪቱን ወደ ለየለት ትርምስ ሊያስገባት ይችላል የሚሉትን ሌላ ሴራ ጎንጉነው እንደሚመጡ ሕዝቡም መንግሥትም አስቀድሞ ማወቅ ይኖርበታል፡፡

ስለዚህ መንግሥት እነዚህን እምቢተኞች ልይቶ በማውጣትና አደብ እንዲገዙ በማድረግ  የህብረተሰቡንም ሆነ የሀገሪቱን ሰላም በማረጋገጥ  እየተመዘገበ ያለውን ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡  ህብረተሰቡም ከመንግሥት ጎን  በመቆም ለውጡን ለመቀልበስ የሚሯሯጡትንና በገዛ ወገናቸው ላይ ይህን መሰል ጥቃት የሚሰነዝሩ አካላትን አጋልጦ በመስጠት የአካባቢውን  ሰላም ማስጠበቅ ይኖርበታል፡፡