የደፈረሰው ይጠራል

ለውጥ በባህሪው ደፍርሶ የሚጠራ ነው፡፡ ረጅም ጊዜ በመውሰድ በሂደት የሚደረጉ ዘገምተኛ ለውጦች በቀላሉ ሊሰምሩ ይችላሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደረጉ የአብዮት መልክ ያላቸው ለውጦች ግን ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል። የብዙኋኑን ይሁንታ ያገኙና እጅግ የተዋቡ ለውጦች ቢሆኑ እንኳን በለውጦቹ የሚጎዱ ሰዎች መኖራቸው አይቀሬ ነው። ቀደም ሲል ሲያገኙ የነበረው ያልተገባ ጥቅም የሚቋረጥባቸው እና ትናንት በፈፀሙት በደል ነገ በለውጡ ኃይል ተጠያቂ እንሆናለን ብለው የሚሰጉ ወገኖች እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም፡፡ ከቻሉ ለውጡን ለመቀልበስ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡ ካልቻሉ ደግሞ አገርን ብጥብጥና ትርምስ ውስጥ ለማስገባት ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው በመስራት ሥርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን በማድረግ ጊዜ ለመግዛት ይታትራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ወደፊት ከለውጡ ተጠቃሚ በሚሆኑ ብዙኋን ላይ ለተወሰኑ ጊዚያት ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል።

አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ይህ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ለኃይማኖት መሪዎች፣ ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለአባ ገዳዎች፣ ለታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም ለአርቲስቶች እና አትሌቶች ባደረጉት የእራት ግብዣ ላይ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ ከመሰብሰቡ አምስት ቀናት ቀደም ብሎ እርሳቸውንና አቶ ለማን ጨምሮ በሌሎች ሦስት ጓዶቻቸው ላይ የእሥር ማዘዣ ወጥቶ እንደነበር ተናግረዋል:: ይህም የለውጡን ሽታ በእንጭጩ ለመቅጨት የተደረገ ሙከራ ነው፡፡

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ላመጧቸው ለውጦች  ምሥጋና ለማቅረብ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመግደል ሙከራ ተደርጓል፡፡ በዚህም የሁለት ወንድሞቻችን ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

ሕዝቦች ለዘመናት ያዳበሩት ተቻችሎ የመኖር ነባር እሴት ሲረጭ በቆየ ጥላቻ ተበርዞ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ዘርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች ተቀስቅሰው የበርካቶች ህይወት ተቀጥፏል፡፡ አያሌዎችም ያፈሩት ሀብትና ንብረት የእሣት እራት ሆኖ ቀያቸውን ትተው ለመሰደድ ተገድለዋል፡፡

እነዚህ በለውጡ የተነሳ ጥቅማችን ተነክቷል ብለው የሚያስቡ ኃይሎች አሁንም በርካታዎችን በገንዘብ መልምለው አሰልጥነው በማሰማራት መሰል ጥፋቶችን በስፋት ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ተግባራቸው ዋነኛ መሣሪያ አድርገው በመጠቀም ላይ ያሉት ደግም ማህበራዊ ድህረ ገጾችን ነው፡፡ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሀሰተኛ የፌስ ቡክ አካውንቶችን በመክፈት የሀሰት ዜናን በመፈብረክ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያጋጠሙ ችግሮችን በማጋነን እና ሌላ ትርጉም በመስጠት ከሌሎች አገራት የተገኙ ምስሎችን ሳይቀር በፎቶ ሾፕ በማቀናበር ህዝብ በህዝብ ላይ እንዲነሳሳ ለማድረግ እየሰሩ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህልም በባሌ ጎባ የነበረውን ግጭት ለማባባስ ሴራሊዮን ውስጥ ከዓመታት በፊት የነበረን ግጭት የሚያሳይ አንድ ፎቶ በፎቶ ሾፕ በማቀናበር ይዘቱ ኢትዮጵያዊ እንዲመስል በማድረግ ህዝብን ለጦርነት የቀሰቀሱበት ሁኔታ ተጠቃሽ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና የተለያዩ ኃይማኖቶች መገኛ አገር ናት፡፡ ሕዝቦቿ ለዘመናት ተቻችለው፣ እርስ በርስ ተከባብረው፣ ተረዳድተውና ተሳስበው ያለው ለሌለው እያካፈለ ዘር፣ ቋንቋ፣ ኃይማኖት ሳይለዩ በጋራ ኖረዋል፤ ተዋልደዋል፤ በደም ተሳስረዋል፡፡ ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው ዘርን መሠረት ያደረገ ግጭት ለዘመናት ከቆየው ህዝብ ታላቅ እሴት ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ግጭቶቹ ሆን ተብሎ ታስቦባቸው አገሪቱ ወደ ብጥብጥና ትርምስ እንድታመራ ገንዘብ ፈሰስ ተደርጎ ለሆዳቸው ባደሩ ግለሰቦች የሚዘጋጁ ድራማዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ዜጋ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ በተለያየ መንገድ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ተረድቶ በመሰል ድራማዎች ላይ ባለማወቅ ተዋናይ ሆኖ በመሳተፍ የዓላማቸው ማስፈፀሚያ ከመሆን ሊቆጠብ ይገባል፡፡

በየአካባቢያችን እንዲመለሱልን የምንፈልጋቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ካሉ በሠላማዊ መንገድ ብቻ በየደረጃው በመጠየቅ ምላሽ እንዲያገኙ ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡ ዛሬ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው በነጻነት አደባባይ ላይ ወጥተው ሠላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄያቸውን ማቅረብና ሀሳባቸውን መግለጽ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ወቅት የልማት ጥያቄዎች የለሙ አካባቢዎችን በማቃጠልና በማውደም መልስ ያገኛሉ ብሎ በማሰብ መንቀሳቀስ የአርቆ አሳቢውና ጨዋው ህዝባችን መገለጫ ባህሪ አይደለም፤ ይልቁንም አገርን የማተራመስ ተልዕኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ የለውጡ ጎታቾች ተግባር እንጂ፡፡

በለውጡ ያኮረፉ ኃይሎች የዘረኝነት መርዝ በመርጨት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት በሬ ወለደ እያሉ በማህበራዊ ድህረ ገጾች የሚያሰራጩትን መረጃ እንደወረደ ወስዶ በተነካው ተበደልኩ ስሜት በማራገብ ባለማወቅ የእነዚህ ወገኖች መጠቀሚያ እየሆነ ያለው የአገራችን ወጣት ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የተገኘውን መረጃ ሁሉ በቀጥታ ተቀብሎ ከማጋራት በፊት ቆም ብሎ የመረጃውን ትክክለኛነት ከተለያዩ ምንጮች ለማረጋገጥ መጣር ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ ከዘረኝነት በፀዳ መልኩ ምክንያታዊ በመሆን የኔ ወገን ተነካ ከሚል ስሜታዊነት ተላቆ ነገሮችን በሰከነ መንገድ አይቶ በመፈተሸ እውነታውን መረዳት ይኖርበታል፡፡ የተሳሳቱ ሰዎችን ተከትለን መሳሳት የለብንም፡፡ ዘርን እየጠቀሱ በሚሳደቡ ዘረኞች መረብ ውስጥ ወድቀን ለስድባቸው ስድብ ለመመለስ አፋችንን መክፈት ብዕራችንንም ማንሳት የለብንም፡፡

ለውጡ የታለመውን ግብ እንዲመታ እያንዳንዱ ግለሰብ ለውጡ ያልተዋጠላቸው ኃይሎች መጠቀሚያ ከመሆን ራሱን ማቀብ አለበት፡፡ የምንፈልገው ለውጥ እንዲመጣ እኛ ራሳችንም መለወጥ አለብን፡፡ ሰዎች ሳይቀየሩ የሚቀየር ሥርዓት ዕድሜ አይኖረውም።  ራስን የለውጡ አካል ከማድረግ ባለፈም ለውጡን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ኃይሎችን መታገል አለብን፤ ለውጥ ያለ ትግል እውን አይሆንምና። 

የደፈረሰው እየጠራ ለውጡ የሚያጋጥሙትን ወጀቦች ተቋቁሞ የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረሱ አይቀሬ ነው፡፡ በተለያዩ መስኮች እየተደረጉ ያሉት እንቅስቃሴዎች ይህን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ ከለውጡ ተጠቃሚ የሚሆነው ህዝብም ይህን ሁኔታ ተረድቶ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጎን መሆኑን ተጠባቂውን መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። የኋላ ኋላም  የደፈረሰው ይጠራል።